Monday, June 24, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ተሟገትአገሬ ለምን የምርኮ ሲሳይና የሰቆቃ ምድር ሆነች?

አገሬ ለምን የምርኮ ሲሳይና የሰቆቃ ምድር ሆነች?

ቀን:

በገነት ዓለሙ

ደርግ በገዛ ራሱ ዘመን ጭምር ስም የወጣለት የለየለት፣ የአፈናና የጭቆና አገዛዝ ነበር፡፡ ደብድብ፣ እርገጥና ግደል የሚል ስም የተሰጠው በዘመኑና ከውስጥ ከአገር ቤት ነው፡፡ የደርግ ዘመን የታጠቁ የቀበሌ ሹማምንትና ካድሬዎች አገርን ፍተሻ በፍተሻ ያደረጉበት፣ ንብረት የሚያወድሙበት፣ ገንዘብ የሚዘርፉበት፣ ያማራቸውን መኪናም ሆነ ቤት በፀረ አብዮት ስም የሚነጥቁበት፣ ያሻቸውን ከቤትም ከመንገድም ጎትተው የሚያስሩበት፣ የሚገርፉበት፣ የቀበሌና የከፍተኛ ጽሕፈት ቤቶች በያሉበት ወደ እስር ቤት ተለውጠው የማይታመኑ የሥቃይ ዓይነቶች ሁሉ የሚቀፈቀፉባቸው የሰው ልጅ ዕንባና ደም የረከሰባቸው ሥፍራዎች የሆኑበት ዘመንም ነበር፡፡

በደርግ ጊዜ የተገደለ፣ ለፍች የሚጠራበት፣ የተፈታ ለቀይ ሽብር የሚፈለግበት፣ ሰው ከቤቱ ወጥቶ በዚያው የሚቀርበት፣ ልጄ፣ ወንድሜ ወይም እህቴ ብሎ መፈለግ በራስ ላይ መፍረድ የሆነበት፣ በቀይ ሽብር የተመታ የቤተሰብ አባልን አንስቶ መቅበር፣ ድንኳን ጥሎ ማልቀስ የተከለከለበትና እናት ዕንባዋን ለመጠጣት የተገደደችበት ግፍና መከራ በኢትዮጵያ ምድር ተሾመና አገር አመሰ፡፡ የደርግ ዘመን የሚታወቀው ይህንን በመሰለ ኢትዮጵያ ገላ ላይ ጥሎ ባለፈው ጠባሳው ነው፡፡

ደርግ ከተወገደ ግንቦት ሲመጣ 28 ዓመት ይሞላዋል፡፡ ከአንድ መቶ ሚሊዮን ሕዝብ በላይ ከሆነው ከኢትዮጵያ ሕዝብ መካከል አብዛኛው ወጣት ነው፡፡ ደርግን ብዙም የማያውቅ፣ ታሪኩንም፣ ምግባሩንም ፖለቲካና ፕሮፓጋንዳ ያልበረዘውና ትምህርት ያላስረዳው ትውልድ ነው፡፡

ከሁሉም በላይ የሚገርመውና የሚያመው ደግሞ ደርግ ሠራው፣ አደረገው ብለን ከምናስተምረው የተለየ ያንን ታሪክ ያደረገ አዲስ ነገር ውስጥ አለመግባታችን፣ ስላለፈው ማውራትን አሳፋሪ አድርጎታል፡፡ በአጠቃላይ የተለያዩና የተወሳሰቡ ነገሮችና ስለደርግ ማውራትን፣ እሱን ታሪክ አድርጎ መማርን ትርጉም አልባ አድርጎታል፡፡

እንዲያም ሆኖ ግን ኢሕአዴግ ዛሬም ደርግን ማነፃፀሪያው፣ ማስፈራሪያውና መሳደቢያው አድርጎ ይጠቀምበታል፡፡ የመጀመርያው የአገሪቱ ፕሬዚዳንት ነጋሶ ጊዳዳ (ዶ/ር) ከ18 ዓመታት በፊት ‹‹በቃኝ›› (ከእንግዲህ በቃኸኝ!) ከማለታቸው በፊትና ወደዚያ መዳረሻ ላይ የቀድሞውን (የመጀመርያውን) ጠቅላይ ሚኒስትር፣ ‹‹አሁንስ መንግሥቱ ኃይለ ማርያምን መሰልከኝ፤›› ማለት ድረስ ተዳፍረው እንደነበር ሰምተናል፡፡ የድሮ ሥርዓት ናፋቂ ማለት መወንጀልም ‹‹መሳደብ››ም ነው፡፡

ኢሕአዴግ ራሱን ከአፄውና ከደርጉ መንግሥት ጋር እያነፃፀረ እበልጣቸዋለሁ ቢልም ተጠራቅመው፣ ታምቀውና አመርቅዘው ዓብይን የወለደውን ለውጡን ያመጡት የከፋ ገመናዎቹ ናቸው፡፡ ከዚህ ቀደም በአፍ ሹክሹክታ የጠገበው የሜቴክ ምዝበራ ብኩነትና ‹‹የሰብዕና ወንጀሎች›› መግለጫ ዝርዝር ዓቃቤ ሕግ ይፋ ሲያደርግ ደግሞ፣ በአዲሱ ትውልድ ውስጥ በራሱ የተነሳው ጥያቄ ስለደርግ ማውራትን መከልከል ያህል የሰፋና የከፋ ነው፡፡

ደርግን መታገልና መጣል ያስፈለገው ከጭቆናና ከአፈና ለመገላገል ነው፣ ነበር፡፡ የኢትዮጵያ ሽግግር ወቅት ቻርተር በመግቢያው የወታደራዊው አምባገነን መንግሥት ውድቀትና የጭቆናንና የአፈናን ዘመን ማክተምን ያመላክታል፣ የነፃነትንና የእኩልነት መብቶችን አዲስ ምዕራፍ ይከፍታል ሲልም ይህንኑ ማለቱ ነበር፡፡ ‹‹ኢትዮጵያን ለ17 ዓመታት ሲገዛ የቆየው የወታደራዊው አምባገነን መንግሥት መገርሰስ፣ የኢትዮጵያ ሕዝብ አገሩንና መንግሥቱን በዴሞክራሲያዊ መንገድ እንደ አዲስ ለመገንባት የሚችልበትን ዕድል የከፈተ ታሪካዊ ወቅት›› ነው፡፡ የዕድገት መሠረታዊ ሁኔታዎች የሆኑትን ሰላምና መረጋጋትን ለማስፈን፣ የጠላትነት ስሜቶችን ለማስወገድ፣ በግጭቶች ምክንያት የተፈጠረ መቆሳሰልን ለመሻር፣ ፍትሐዊ ሰላምን ለማምጣት፣ ‹‹ዴሞክራሲያዊ ሥርዓትን ማወጅ አማራጭ የሌለው ግዴታ›› ነው ተብሎ ታወጀ፡፡

ከሁሉም በላይ ደግሞ በደርግ ዘመን ስለተፈጸሙ ወንጀሎች የተባለውና የታወጀው፣ በሕግ የተደነገገው፣ ትናንት ያኔ ሳይሆን ዛሬ ላይ ሲያዩት የሚገርምና የሚደንቅ ነው፡፡ የዚህች አገር ፍዳና ግፍ፣ እንዲሁም ያመለጡ ዕድሎች ቆጠራ የሚያበቃው መቼ ነው የሚያሰኝ ነው፡፡ ኢሕአዴግ በአዋጅና በሕግ የተናገረውን ሁሉ ስለሚረሳ፣ የልዩ ዓቃቤ ሕግ ጽሕፈት ቤትን ባቋቋመበት አዋጅ ያለውን ለማስታወስ ትንሽ ሰፋ አድርጌ እጠቅሳለሁ፡፡    

የልዩ ዓቃቤ ሕግ ማቋቋሚያ የነሐሴ 1984 ዓ.ም. አዋጅ (አዋጅ ቁጥር 22/1984)፣ ‹‹የኢትዮጵያ ሕዝቦች ባለፉት 17 ዓመታት በአምባገነኑ ደርግ/ኢሠፓ መንግሥት ሰብዓዊና የፖለቲካ መብታቸውን ተገፈው››፣ በከፍተኛ ጭቆና ፋሽስታዊ ሥርዓት ቀንበር ሥር መቆርቆዛቸውንና መሰዋታቸውን፣ ‹‹በኢትዮጵያ ሕዝቦች ታሪክ ውስጥ ልዩ ቦታ የሚሰጣቸው እጅግ አስከፊና አሰቃቂ የወንጀል ድርጊቶች የደርግ/ኢሠፓ መንግሥት ባለሥልጣናት፣ የደኅንነትና የጦር ኃይሎች አባላት ተባባሪ ግለሰቦች በኢትዮጵያ ሕዝቦች ላይ መፈጸማቸውን››፣ ‹‹የአምባገነኑ ደርግ/ኢሠፓ መንግሥት ባለሥልጣናትና ተባባሪ ግለሰቦች በግፍ የሕዝቦችን ንብረት በመቀማት፣ በሕገወጥ መንገድ በመውረስ፣ በማጥፋት፣ እንዲሁም የሕዝብና የመንግሥት ንብረቶችን በመመዝበር የአገሪቱ ኢኮኖሚ እንዲቆረቁዝ ማድረጋቸውን››፣ ‹‹የኢትዮጵያ ሕዝቦች አብዮታዊ ዴሞክራሲያዊ ግንባር ታሪካዊ ትግሉ በመጠናቀቁ፣ አገሪቱን በተቆጣጠረበት ወቅትና ከዚያም በኋላ በቁጥጥር ሥር እንዲውሉ የተደረጉ ወንጀል ፈጽመዋል ተብለው የሚጠረጠሩ የኢሠፓ የበላይ ባለሥልጣናት፣ የደኅንነትና የጦር ኃይሎች አባላት፣ የመንግሥት ባለሥልጣናት፣ እንዲሁም በወንጀሉ አፈጻጸም በከተማ ነዋሪዎችና በገበሬ  ማኅበሮች ስምና በግለሰብ ደረጃ ተባባሪዎች የነበሩ ሁሉ ፍትሕ የተሞላበት ፍርዳቸውን እንዲቀበሉ ማድረግ አስፈላጊ መሆኑን››፣ ከሁሉም በላይ ደግሞ ‹‹የኢትዮጵያ ሕዝቦች በደርግ/ኢሠፓ መንግሥት አማካይነት የደረሰባቸውን አረመኔያዊ ወንጀሎች፣ የንብረትና የሀብት ምዝበራ ለመጪው ትውልድ በሀቀኛ መንገድ መዝግቦ ማቆየትና ዳግም የዚያ ዓይነት የመንግሥት ሥርዓት እንዳይደገም ማስገንዘብና ማስተማሩ ትክክለኛ ታሪካዊ ግዳጅ መሆኑን››፣ ገልጾና ዘርዝሮ በወንጀል የሚጠየቁ ሰዎች ሁሉ ጉዳያቸው በአስቸኳይ እየተጣራ ለፍርድ እንዲቀርቡ የሚያደርግ ልዩ የዓቃቤ ሕግ መሥሪያ ቤት አቋቁሜያለሁ ብሎ አወጀ፡፡

ለመጪው ትውልድ በሀቀኛ መንገድ መዝግቦ ማቆየትና ዳግም የዚያ ዓይነት የመንግሥት ሥርዓት እንዳይደገም የሚለው ‹‹ቁርጠኝነት›› ቀርቶ፣ ‹‹በአስቸኳይ እየተጣራ›› ለፍርድ የማቅረብ ነገር ራሱ በዚያው በሽግግር ዘመን የአገርና የመንግሥት መሪ የነበሩትን የፕሬዚዳንቱን መግለጫዎች፣ ንግግሮች፣ ቃለ መጠይቆች ሁሉ የሚያሸማቅቅ፣ የሚያሳፍር መልስ የሚሰጥበት ጥያቄ ነበር፡፡ በወቅቱ ፕሬዚዳንት የነበሩት መለስ ዜናዊ ከዚህ በኋላ እንደ ከዚህ ቀደሙ በዚህ ቀን ክስ ይመሠረታል ብዬ አልናገርም እስኪሉ ድረስ፣ በዚያው ደረጃ እንኳን ያሳፈረ ጉዳይ ነበር፡፡ ይህ ክስ ለመመሥረት፣ ክስ ከተመሠረተ በኋላ ጉዳዩን ለማጠናቀቅ የፈጀውን ጊዜ የሚመለከተው ብቻ ነው፡፡

የልዩ ዓቃቤ ሕግ ሥልጣን በሆነ ጉዳይ ክስ የመመሥረትና ‹‹ፍርዳቸውን እንዲቀበሉ›› ማድረግ ራሱ የወሰደውን ጊዜ ወስዶም ቢጠናቀቅም (ተጠናቀቀ ቢባልም)፣ ‹‹ዳግም የዚያን ዓይነት የመንግሥት ሥርዓት እንዳይደገም ማስገንዘብና ማስተማር››ን የሚያህል ‹‹ትክክለኛ ታሪካዊ ግዳጅ›› የተወጣ፣ የተዋጣለት በተለይም የዘር ማጥፋትን ሕግ አፍታትቶ የተረጎመና አደላድሎ ያስቀመጠ ‹ጁሪስ ፐሩደንስ› አልተረፈልንም፡፡ በዋነኞቹ ተከሻሶች (እነ መንግሥቱ ኃይለ ማርያም) ላይ በአማራጭ ዘር ማጥፋት፣ አለዚያም ሰው መግደል ተብሎ የቀረበው ክስ ዘር ማጥፋት ነው ተብሎ ቢፈረድም፣ በከፊል በተጠቀሰው ጉድለት ምክንያት ዛሬም የሚታወቀው በሕዝብና በተለምዶ ቋንቋ የ‹‹ቀይ ሽብር›› ጉዳይ ተብሎ ነው፡፡ እንዲያውም በወቅቱ ተይዘው በእስር ላይ የሚገኙ ሰዎችን አስመልክቶ ከነሐሴ 2 ቀን 1984 ዓ.ም. ጀምሮ ለስድስት ወራት የታገደው የፍትሐ ብሔር ሥነ ሥርዓት ሕግ ቁጥር 177 (የሀብየስ ኮርፐስ) መብት በዚያ ጦስ በዚያው ደብዛው ጠፍቷል፡፡ በብዙ የተያዙ ምክንያቶች በደርግ/ኢሠፓ መንግሥት ዘመን የተፈጸመው ወንጀልና ምዝበራ ‹‹ለመጪው ትውልድ በሀቀኛ መንገድ መዝግቦ ማቆየት››ም፣ ‹‹ዳግም የዚያን ዓይነት የመንግሥት ሥርዓት እንዳይደገም›› ማድረግም አልተቻለም፡፡  ይልቁንም ‹‹ትሻልን ትቼ ትብስን አገባሁ›› ማለት የተጀመረው ገና ከጠዋቱ ነበር፡፡ ይህ በገፍና በጅምላ የሆነው ኢሕአዴግ ወታደሩን ጉርስ ነፍጎ ሲበትን ነው፡፡ የሕዝብ ወገንተኛ ነኝ የሚለው ኢሕአዴግ ፀረ ሕዝብ ወታደራዊ ተቋምን ማፍረስና ወታደሩን እንዳለ መበተን ተምታትቶበት ‹‹መንጌ ማረኝ›› የሚያሰኘውን የግፍ ሥራ መቁጠር ቀጠለ፡፡

በመሠረቱ ፀረ ሕዝብ ወታደራዊ ተቋምን ማፍረስ ማለት የዕዝ መዋቅሩንና የአቀራረፅ ሥርዓቱን መናድና ለአዲስ ግንባታ ማዘጋጀት እንጂ፣ ኢሕአዴግ እንዳደረገው የሚላስ የሚቀመስ አሳጥቶ ማፍረስና መበተን አልነበረም፡፡ አያሌዎች በአንድ ጀንበር በየፈፋው፣ በየሜዳውና በየጎዳናው የሰው እጅ ተመልካች ተደረጉ፡፡ አዲስ አበባ በየግንቧ፣ በየመንገድ ዳሯና በየአውቶብስ መጠለያዋ የደከሙና የተጎሳቆሉ ቅጠልያ ለባሾችን ማስተናገድ ውስጥ ገባች፡፡ ጭቁኑን ወታደር ጥሎ ይጥላል የሚል እምነትም፣ ጥርጣሬም ያልነበረው ሌላው ሰውም፣ እንኳን የደርግን ሥርዓት ሊሸፍጥ ስለመጪ ዕድሉ አስፈሪ ሥጋትና ጥርጣሬ በጭራሽ ያልነበረው ወታደሩም፣ በኢሕአዴግ የገፍና የጅምላ የሰብዓዊ መብት ጥሰት ተገረፈ፡፡

ጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ በዚህ ሳምንት በአንፃራዊነት የዘረገፈው የሰብዓዊ መብት ጥሰትና የምዝበራ ዝርዝር ከሞላ ጎደል ሕዝብ በሹክሹክታ ሲከሰክሰው የነበረው ነው፡፡ በሕይወት መኖር የቻለ የአገር ውስጥና የውጭ የሰብዓዊ መብት ተሟጋች በየዓመቱና በየአጋጣሚ ሪፖርት ሲያደርጉት የኖሩት የመንግሥት የዘወትር ሥራ ነው፡፡ መንግሥት የድርጊቱን መፈጸም ከማመንና ከማስተባበል ይልቅ፣ የመብት ተሟጋቾችና የሪፖርት አድራጊዎችን ‹‹ክፋት›› እና ‹‹ማንነት›› በማጋለጥ ሲሸሸው የኖረው ገመናው ነው፡፡

ድብቅ እስር ቤቶችን አቋቁሞ እስከ ማስተዳደር፣ እስር ቤቶችንና ወህኒ ቤቶችን ከደኅንነት ጋር እስከ ማቆራኘት ድረስ ኢሕአዴግ ደርግን በልጦና አስንቆ እንዲሄድ ያደረገው የመንግሥት ሥራ ሁሉ፣ ተቃውሞንና የተለየ ሐሳብን የመተናነቅ ግዳጅ ሆኖ በመቋቋሙ ነው፡፡ አገር የምርኮ ሲሳይና የዝርፊያ ማዕድ የሆነችው፣ አድራጊ ፈጠሪነት ከምንጊዜውም በላይ ክብረ ወሰን የሰበረው እሳጣለሁ፣ እጠየቃለሁ ብሎ መሥጋት ከህሊና ውስጥ እንኳን ድራሹ የጠፋው ኢሕአዴግን ለዚህ ያበቃው የእኔ ብቻ ልክ የሥልጣን ዳፍንት ነው፡፡ ይህንን ደግሞ የገዛ ራሱ ይዞታና አካል አድርጎ ጠፍጥፎ የሠራው አደረጃጀታችን ዋልታና ማገር ሆኖ አገልግሎታል፡፡

የተጀመረው ለውጥ አገር ሥልጣን የያዘ ግለሰብ የምርኮ ሲሳይና የዝርፊያ ማዕድ የሆነችበትን፣ ዜጎች በግለሰብም በመንግሥት ባለሥልጣንም አድራጊ ፈጣሪነት ሥር የሚዋረዱበትን ግፍና በደል በራሱ በመንግሥት አፍ/አንደበት ያሰማን አዲስ ሁኔታ ሥር እንዲይዝና የአንድ ሰሞን ‹‹ወሬ›› ሆኖ እንዳይቀር፣ ሕዝብ ፍላጎቱንና ብሶቱን በይፋ ለመናገር፣ በደልን ለመጋተርና መብቱን ለማስከበር የማይፈራበት የነፃነት አየር ይፈጠር ዘንድ ዋናው ቁልፉና አዛላቂ መንገድ ደግሞ የዴሞክራሲን መሠረት በመጣል መጀመር አለበት፡፡ የዴሞክራሲ ሥርዓተ መንግሥት ህልውና የየትኛውም ፓርቲ ይዞታ ያልሆነ ዓምደ መንግሥት ማደራጀት ነው፡፡ የኢትዮጵያ ዴሞክራሲ ተስፋ ሲጀመር መውጫ የሌለው ቅርቃር ውስጥ የገባው የፓርቲው ደባልና ተቀፅላ ያልሆነ መከላከያ፣ ደኅንነት ፍርድ ቤት ባለመገንባቱ ነው፡፡ ከዚያ ባለመጀመሩ ነው፡፡ የዓብይ አህመድ መንግሥት የሚመራው ለውጥ ከዚህ ማዕዘን በመጀመሩና ይህንን መፈክርም በማንገቡ፣ ከወዲሁም ተስፋ ሰጪ ምልክቶች እየታዩ በመሆናቸው መበርታትና መገዛት ያለብን በዚሁ አቅጣጫ ነው፡፡

ወሬው ራሱ የሚደንቅና የሚያስደነግጥ ስሜት የፈጠረው የሜቴክ ምዝበራና ብኩንትና የደኅንነት፣ የፖሊስና የእስር ቤት የመንግሥት ባለሥልጣናት የአንቀጽ 28 (የሕገ መንግሥቱ) ወንጀሎች አደባባይ በይፋ የወጣበት ምክንያት ለውጡ ያመጣው ዴሞክራሲያዊ ሁኔታ ነው፡፡ በኢሕአዴጎች ውስጥ የተፈጠረውን ልዩነት ተከትሎ የመጣ የተለመደው ዓይነት የመጠቃቃት ሴራ ነው የሚል መኖሩን መጠርጠር ባይከፋም፣ ለእኔ ግን ይህ ግፍና ዝርፊያ ተወዝፎ ያደረ ዴሞክራሲያዊው ሁኔታ መተንፈስ ፈቅዶ አደባባይ ያወጣው ዜና ነው ባይ ነኝ፡፡ ማሳደግና ማጎልበት ያለብን ይህን ዴሞክራሲያዊ ሁኔታ ከማስፋትና ከማደላደል አኳያ ነው፡፡ ጥፋትን፣ በደልን ማጋለጥና መዋጋት ባህል እንዲሆን፣ ለእንደዚህ ዓይነት ግዳጅና መቆርቆር የሁሉም ሰውና የየትም ቦታ ባህርይ ይሆን ዘንድ የተቆረቆረን ሰው ላጥቃ የሚል ቢመጣ ከበላዩ ሌላ ጌታ የሌለበት ሕግ አለሁልህ እንዲለን፣ የሕጉ አለሁልህ ባይነት ቢፈዝና ቢጓደል ሥር የያዘ ዴሞክራሲ እየተከታተለ ለሕጉ ጥበቃ እንዲያደርግለት (በሰው ንቁ ዓይንና ጆሮ አማካይነት ጭምር)፣ መጀመርያ አሁን መከፋፈትና መፍታታት የጀመረው ዴሞክራሲዊ ሁኔታ ማገዝ አለብን፡፡   

ላለፉት 27 ዓመታት በባዶ ሜዳ ዋስትና ያለው ዴሞክራሲ ዘላቂ ሰላም እያልን አገራችንን የምርኮ ሲሳይና የዝርፊያ ማዕድ ያደረገ ምዝበራ፣ ብኩንነትና ጥፋት ዓይተናል፡፡ ከገሃነመ እሳት የመጣ የሚመስል የግፍ ዜና ሰምተናል፡፡ ይህንን የሰማነው እንደተለመደውና እንደለመደብን ከውጭ አገር አይደለም፡፡ በአገራችን አዲስ በተፈጠረው የፖለቲካ አየር ውስጥ ነው፡፡ ይህን ማስፋት አለብን፡፡ ኢሕአዴጎች እርስ በርሳቸው አይጥና ድመት፣ እሳትና ጭድ የነበሩ ቡድኖች ጭምር ፌዴራላዊ ዴሞክራሲያዊ አገር መገንባትን የጋራ ጉዳያችንና መገናኛችን ብለው የተሰባሰቡበት፣ ነፃ የብዙኃን ማኅበራትና ነፃ የሕዝብ ዴሞክራሲያዊ ተሳትፎዎች የሚፍለቀለቁበት ሻል ያለና የሰፋ መልካም የፖለቲካ አየር መፍጠር የመጀመርያው ጉዳይ ነው፡፡ የፖለቲካ ወገንተኝነት የሌላቸው የዴሞክራሲ ተቋማትንና አውታራትን የማሰናዳት ነገር መታስብም መጀመርም የሚቻለው በዚህ ነፃና የተፍታታ የፖለቲካ አየር ውስጥ ነው፡፡

ነፃ የፖለቲካ አየር የመፍጠር ሥራችን ደግሞ ለዴሞክራሲ ድል ግድና ቀዳሚ ከሆኑ መፍትሔዎች በስተቀር በሌሎች የወሰንና የባለቤትነት የክልል የሕገ መንግሥትና የፌዴራል አካባቢዎች አወቃቀር ክለሳ ጥያቄዎች መዋከብና መጨናገፍ የለባቸውም፡፡ እነዚህ ጉዳዮች አዘላለቃችን የሚወስኑ አደጋዎችን እስከምናመክን ድረስ በእንጥልጥል መቆየት ባልተወሰነ ቀጠሮ ማደር ያለባቸው ናቸው፡፡

ከዚህ ቀደም በ1983 ዓ.ም. መጨረሻ ጥቂት ብሔርተኛ የፖለቲካ ልሂቃን ራሳቸውን የአገሪቱ ፌዴራላዊነት መሐንዲስ አድርገው ከራሳቸው አልፈው በብሔርተኛነት ያልተሳሳቡትን ማኅበረሰቦች ሁሉ በአገረ ብሔርነት አስተጫጪና ደልዳይ እስከመሆን ድረስ፣ በአገሪቱ ሕዝቦች ዓብይ ጉዳይ ላይ ፍላጎታቸውን በእናውቅለታለንና በውክልና ዘዴ በመጫን የሠሩት ስህተት ሳያንስ፣ አሁንም ያለመታረም አዝማሚያ ብቅ ብቅ እያለ ነው፡፡ ዛሬም የፊተኞቹ ቢጤ ልሂቃን አሳታፊነትን የመልክ ማሳመሪያ አድርገው ከአዳራሽ አዳራሽ እየተሰበሰቡ የብሔረሰቦች መብቶች መረጋገጥና ራስን በራስ ማስተዳደር ከዚህ ቀደም ቢጤዎቻቸው ከፈጠሩት መዋቅር ሊነጠልና በሌላ ቅንብር ሊሟላ እንደማይችል፣ ነባሩ ድልድል ተፈጥሯዊ የሆነ ይመስል እሱን ለማስተካከል መሞከርን ብሔሮችን ከመደፍጠጥና እየገነቡ ከማፍረስ ጋር አንድ እያስመሰሉ (ችግሮቻችንን ሁሉ የአፈጻጸም ውጤት አድርገው እያቀለሉ) መፍትሔ ፍለጋውን እያልኮሰኮሱት ይገኛሉ፡፡ የእነሱ ፍላጎት ከአዳራሽ ወደ አዳራሽ ከተገላበጠና ተቆነጣጥሮ በውስን የመገናኛ ብዙኃን ቀዳዳ ሕዝብ ጫፍ ጫፉ ከደረሰው ወዲያ መነሻ ሐሳብ አሰባስቦ ለሚመለከተው አርቃቂ/ወሳኝ አካል የማቅረብ እሽቅድምድም የተያዘም ይመስላል፡፡ ክልል ሆኖ ጎጆ መውጣት የሚባል ግብግብም አዘላለቃችንን የሚወስኑ አደጋዎችን ሳናስወግድ በፊት መነሳት ያለበት ጥያቄ አይደለም፡፡

በእነዚህ አከራካሪና መሠረታዊ ጉዳዮች ላይ ልዩ ልዩ የፖለቲካ ወገኖችና ሊቃውንት በጠንካራ ጥናታዊ ዝግጅት አለን የሚሏቸውን አማራጮች በገንዘብ አቅም ሳይቀየዱ፣ ለኢትዮጵያ ሕዝብ የማቅረብ ዕድል ማግኘታቸው የእነሱ ብቻ ሳይሆን የኢትዮጵያ ሕዝብም መብት ነው፡፡ የቀረቡትም አማራጮች ውስጣዊ መቆራቆስን በማቃለል አዋጭነታቸው፣ እንዲሁም ለጠንካራ አገር ግንባታና ለቀጣናዊ መሰባሰብ በመስማማት ትባታቸው ተውጠንጥነውና የሚዛመዱት ተዛምደው፣ መላው የአገሪቱ ሕዝቦች ውጤቱን ሀብቴ ሊሉ በሚችልበት አኳኋን በቀጥተኛ ድምፅ ሊወስኑበት ይገባል፡፡ እናም ይኼንን ሒደት በርጋታ ይዞ በአሁኑ ሰዓት አስቸኳይ በሆነው ፓርቲያዊነት ባልሳባቸው አውታራት ላይ ዴሞክራሲን መሠረት የማስያዝና ለዴሞክራሲ መክሸፊያ የሆነውን ንቅዘትን የመመነጋገል ለውጥ ላይ ትኩረትን ማሰባሰብ ይመረጣል፡፡

በይርጋ የማይታገድ በምሕረትም፣ በይቅርታም የማይታለፍ ወንጀል እየፈጸሙ ሳይጠየቁ መቅረት የአገራችን ወግ ባህል መሆኑ ታሪክ እንዲሆን፣ እንዲሁም አገር የምርኮ ሲሳይና የዝርፊያ ማዕድ መሆኗ እንዲቋረጥ በለውጡ ግፋ ማለት አማራጭ የሌለው መንገድ ነው፡፡ 

ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊዋን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እንገልጻለን፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

አስጨናቂው የኑሮ ውድነት ወዴት እያመራ ነው?

ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ የኑሮ ውድነት እንደ አገር ከባድ ፈተና...

‹‹ወላድ ላማቸውን አርደው ከደኸዩት ወንድማማቾች›› ሁሉም ይማር

በንጉሥ ወዳጅነው   የዕለቱን ጽሑፍ በአንድ አንጋፋ አባት ወግ ልጀምር፡፡ ‹‹የአንድ...

የመጋቢቱ ለውጥና ፈተናዎቹ

በታደሰ ሻንቆ ሀ) ችኩሎችና ገታሮች፣ መፈናቀልና ሞትን ያነገሡበት ጊዜ እላይ ...

ጥራት ያለው አገልግሎት መስጠት የሚያስችል ሥርዓት ሳይዘረጉ አገልግሎት ለመስጠት መነሳት ስህተት ነው!

በተለያዩ የመንግሥትና የግል ተቋማት ውስጥ ተገልጋዮች በከፈሉት ልክ የሚፈልጉትን...