Tuesday, October 4, 2022
ሌሎች ዓምዶች
  - Advertisement -
  - Advertisement -

  ‹‹የኢትዮጵያ አየር መንገድ አሁን ያለበትን ጉዞ ባናጨናግፍ ጥሩ ነው›› አቶ ግርማ ዋቄ፣ የቀድሞ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ዋና ሥራ አስፈጻሚ

  አቶ ግርማ ዋቄ በወጣትነታቸው ኢትዮጵያ አየር መንገድ በመግባት፣ እዚያው ተምረውና አድገው በተለያዩ ኃላፊነት ቦታዎች ለ34 ዓመታት አገልግለዋል፡፡ በመካከል ቅሬታ አድሮባቸው ወደ መካከለኛው ምሥራቅ ሄደው የገልፍ አየር መንድንና ዲኤቾ ኤል ኩባንያን በኃላፊነት አገልግለዋል፡፡ እ.ኤ.አ. በ2004 የኢትዮጵያ መንግሥት ያቀረበላቸውን ጥሪ ተቀብለው አየር መንገዱን ለሰባት ዓመት በዋና ሥራ አስፈጻሚነት መርተዋል፡፡ አቶ ግርማ ያቀረቡት የሥራ መልቀቂያ ተቀባይነት አግኝቶ እ.ኤ.አ. በ2011 በጡረታ ተሰናብተዋል፡፡ ከኢትዮጵያ አየር መንገድ ከለቀቁ በኋላ የሩዋንዳ አየር መንድ የቦርድ ሊቀመንበር፣ የሩዋንዳ የትራንስፖርት ሚኒስትር የአቪዬሽን ጉዳዮች አማካሪ በመሆን አገልግልዋል፡፡ በአሁኑ ወቅት የቶጎ ፕሬዚዳንት ልዩ አማካሪ በመሆን በማገልገል ላይ ይገኛሉ፡፡ የ75 ዓመት የዕድሜ ባለፀጋ የሆኑት አቶ ግርማ ባለትዳርና የአምስት ልጆች አባት ሲሆኑ፣ ስምንት የልጅ ልጆች ዓይተዋል፡፡ በአጠቃይ በአቪዬሽን ኢንዱስትሪ ውስጥ የ50 ዓመታት ልምድ ያላቸው አቶ ግርማ፣ በኢትዮጵያ አየር መንገድ ስለነበራቸው ቆይታ፣ ስለአወጣጣቸውና አየር መንገዱ አሁን ስላለበት ሁኔታ ከቃለየሱስ በቀለ ጋር ያደረጉት ቆይታ እንዲህ ተጠናቅሯል፡፡

  ሪፖርተር፡- መጀመርያ ኢትዮጵያ አየር መንገድ መቼና እንዴት እንደገቡ፣ በአጠቃላይ በአየር መንገዱ የነበረዎትን ቆይታና እንዴት እያደጉ እንደሄዱ ቢገልጹልን?

  አቶ ግርማ፡- እኔ አየር መንገድ የገባሁት እንደ ቀልድ ነው፡፡ አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የሁለተኛ ዓመት ተማሪ ሆኜ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ፓይለቶች ለማሠልጠን ማስታወቂያ ያወጣል፡፡ እኔ ማስታወቂያውንም አላየሁም፡፡ ኳስ ሜዳ እየተጫወትን ጓደኞቼ ቦሌ እንሂድ ይሉኛል፡፡ ለምን ስላቸው አየር መንገድ ለሥልጠና ስለሚቀበል ቃለ መጠይቅ እናድርግ ይሉኛል፡፡ እኔ ዓላማውም አልነበረኝም፡፡ እሺ ብዬ ከጓደኞቼ ጋር አብሬ ሄድኩኝ፡፡ አየር መንገድ ስንደርስ ጠየቁን፣ ፎርም ሰጡን፣ ሞልተን ተፈተንን፡፡ ፈተናውን በጥሩ ውጤት አለፍኩኝ፡፡ ለፓይለት ሥልጠና ተቀብለናችኋል አሉን፡፡ ወደ ማሠልጠኛው ገባን፡፡ ትምህርቴን አቋርጨ ለምን እዚህ እገባለሁ ስል፣ በኋላ ከዩኒቨርሲቲ ተመርቀህ የምታገኘው ደመወዝ በፓይለትነት ከምታገኘው ያነሰ ነው፡፡ ደመወዙ ብዙ ነው፣ አገርም ታያለህ አሉኝ፡፡  

  ሪፖርተር፡- በስንት ዓመተ ምሕረት ነው?

  አቶ ግርማ፡- እ.ኤ.አ. በ1965 ነው፡፡ የጓደኞቼን ምክር ተቀብዬ ፓይለት ማሠልጠኛ ገባሁ፡፡ የጤና ምርመራ ጨርሰን 15 የምንሆን ተቀጠርን፡፡ የኢትዮጵያ አየር መንገድ በወጣትነቴ በዚህ ሁኔታ ነው የገባሁት፡፡ ይሁንና በፓይለትነት መቀጠል አልፈለግኩም፡፡ ጥሩ ፓይለት አልሆንም ነበር፡፡ ከዚያ ወጥቼ ወደ ሽያጭ ክፍል ገባሁ፡፡ ለብዙ ዓመታት ሽያጭ ክፍል ሠራሁኝ፡፡ እ.ኤ.አ. ከ1965 እስከ 198. የኢትዮጵያ አየር መንገድ ውስጥ ወደ 27 ዓመታት ገደማ አገልግያለሁ፡፡ በእነዚህ ዓመታት አየር መንገዱ ብዙ ቦታ አቀያይሮ አሠርቶኛል፡፡ በየገባሁበትም ቦታ የትምህርት ዕድል ሰጥቶኛል፡፡ በዚያን ጊዜ ብዙዎቹ አሜሪካውያን ነበሩ፡፡ ኢትዮጵያውያንም ነበሩ፡፡ ነገር ግን የትምህርት ዕድል ካገኙት ኢትዮጵያውያን ውስጥ አንዱ ነበርኩ፡፡ አሜሪካ፣ ጀርመን፣ አየርላንድ፣ እስራኤልና ቤልጂየም የተለያዩ ኮርሶች እንድወስድ አድርገዋል፡፡ የአውሮፓ ኅብረት በሚሰጠው የትምህርት ዕድል ለሰባት ወር ሠልጥኛለሁ፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ አዳዲስ ክፍሎች ሲከፈቱ በመሪነት ተሳትፌያለሁ፡፡ ስፔስ ኮንትሮል የሚባለውን ክፍል እኛ ነን ያቋቋምነው፡፡ በውጭም ጋና፣ ታንዛኒያና ምዕራብ አውሮፓ ጀርመን ኤርያ ማኔጀር ሆኜ ሠርቻለሁ፡፡ ከዚያ እ.ኤ.አ. በ1988 ተመለስኩ፡፡ ከ1988 እስከ 1993 በዋና ዳይሬክተርነት ሠርቻለሁ፡፡

  ሪፖርተር፡- የኢትዮጵያ አየር መንድን እንዴት ለቀው ሊሄዱ ቻሉ?

  አቶ ግርማ፡- ኢሕአዴግ አዲስ አበባ ከገባ በኋላ እ.ኤ.አ. በ1993 በአዲሱ መንግሥት አየር መንገዱ ይጠና ተባለ፡፡ ከእኛ አሠራር ጋር ይሄዳል? አይሄድም? የሚል ጥያቄ ተነሳ፡፡ አንድ ኮሚቴ ተቋቁሞ እንዲጠና ተደረገ፡፡ እኔ አስተዳደሩን ወክዬ እካፈል ነበር፡፡ በጥናቱ አካሄድ ላይ ከመንግሥት አካላት ጋር ሳንስማማ ቀረን፡፡ በወቅቱ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ቦርድ ሰብሳቢ የነበሩት አቶ ስዬ አብርሃ፣ አቶ ተከስተ የሚባሉ ሹም ጠቅላይ ሚኒስትር ቢሮ ነበሩ፣ ሌሎችም ሚኒስትሮች ይህን እንዲያጠኑ በመንግሥት የተመደቡ ነበሩ፡፡ ከእነሱ ጋር በአካሄድ ልንስማማ አልቻልንም፡፡ አካሄዳቸው ከአየር መንገድ አሠራር ጋር የሚሄድ መስሎ ስላልታየኝ ይኼ ነገር ልክ አይደለም ብዬ እከራከራቸው ስለነበር በእኔ ደስተኛ አልነበሩም፡፡ አርፈህ የምንልህን አድርግ ይሉኝ ጀመር፡፡ እኔም የማላምንበትን ነገር አላደርግም፡፡ እናንተ ይኼ ነገር የሚያዋጣ መስሎ ከታያችሁ ቀጥሉበት፣ እኔ እዚህ ሆኜ እንቅፋት አልሆንም፡፡ እኔ የማላምንበትን ነገር አልሠራምና ልቀቁኝ አልኳቸው፡፡ በወቅቱ ጠቅላይ ሚኒስትር የነበሩት አቶ ታምራት ላይኔ ዘንድ ተልኬ ሦስት ቀን ተሰጠኝ፡፡ የሚሰጠኝን ትዕዛዝ ተቀብዬ በስብሰባ ላይ እንድገኝ ነው፡፡ በሚደረገው ነገር ላይ እምነት ስላልነበረኝ በስብሰባው ላይ ለመገኘት ፈቃደኛ እንዳልሆንኩ አስታውቄ የሥራ መልቀቂያ አስገባሁኝ፡፡ ከሥራ ወጥቼ አምስት ወራት ያለ ሥራ አዲስ አበባ ተቀመጥኩ፡፡ በኋላ ገልፍ ኤር ሥራ አገኘሁና ወደ መካከለኛው ምሥራቅ አቀናሁ፡፡ ያደግኩበትንና 27 ዓመታት ያገለገልኩበትን አየር መንገድ ለቅቄ ለመሄድ ተገደድኩ፡፡ የሄድኩት ገንዘብ ፈልጌ አይደለም፡፡ የነበረው ሁኔታ የሚያሠራኝ ስለነበረ ነው፡፡ እኔ ከወጣሁ ከትንሽ ጊዜ በኋላ 35 የአየር መንገድ ማኔጅመንት አባላትን ከሥራ አስወጧቸው፡፡ ከዚያ በኋላ አንተ የምትናገረው እውነት ነበር፡፡ ተመለስና ሥራ የሚል ጥያቄ በተደጋጋሚ ቀርቦልኝ ነበር፡፡

  ሪፖርተር፡- ወደ አየር መንገድ እንዴት ተመልሰው መጡ?

  አቶ ግርማ፡- በስተመጨረሻ ዋና ሥራ አስፈጻሚ የነበረው አቶ ብሥራት ንጋቱ በሚለቅበት ጊዜ፣ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ቦርድ ሰብሳቢ የነበሩት አቶ ሥዩም መስፍን ተመልሼ እንድሠራ ጥያቄ አቀረቡልኝ፡፡ አዲስ አበባ መጥቼ ተነጋገርን፡፡ እኔ የመመለስ ዓላማ አልነበረኝም፡፡ ነገር ግን በውይይታችን ወቅት አየር መንገዱ አንዳንድ ዕገዛ ያስፈልገዋል፣ ተመልሰህ መጥተህ ብትሠራ ደስ ይለናል አሉኝ፡፡ 

  ሪፖርተር፡- አየር መንገዱ ጥሩ ሁኔታ ውስጥ አልነበረም?

  አቶ ግርማ፡- አየር መንገዱ መጥፎ ሁኔታ ውስጥ አልነበረም፡፡ እንደ አጋጣሚ ሆኖ አንዳንድ ጭቅጭቆች ነበሩ፡፡ በማኔጅመንትና በቦርድ መሀል የመተማመን ስሜት እየቀነሰ ስለሄደ ለውጥ በፈለጉበት ጊዜ ጠሩኝ፡፡ ጥሪውን ተቀብዬ መጣሁኝ፡፡ የምታገኘው ደመወዝ እንዴት ነው? እንዴት ነው የምንከፍልህ? ሲሉ ጠየቁኝ፡፡ እኔ የምመለሰው ለገንዘቡ አይደለም፡፡ የኢትዮጵያ አየር መንገድ የሚፈልገኝ ከሆነና የምረዳ ከሆነ እኔ አሁን ካለው ዋና ሥራ አስፈጻሚ የተለየ ደመወዝ አልፈልግም፣ በዚያው ደመወዝ እመጣለሁ፡፡ ነገር ግን የምፈልጋቸው ነገሮች አሉ አልኳቸው፡፡ ምንድነው የምትፈልገው ነገር ሲሉኝ እኔ የምመጣው ሥራ ለመሥራት ነው፡፡ ሥራ ለመሥራት የሚያስችለኝ ሁኔታ መኖር አለበት፡፡ አንደኛ ቦርድም ሆነ መንግሥት ዝም ብሎ በሥራ ውስጥ ጣልቃ ገብቶ ይህን አድርግ፣ እከሌን ሹም፣ እከሌን ሻር ይህን ጣቢያ ክፈት፣ ይህን አውሮፕላን ግዛ የሚል ነገር ውስጥ እንዳይገባ፡፡ ዝርዝር ሥራ ውስጥ አትገቡም፡፡ ይህ ድርጅት የመንግሥት ነው፡፡ የመንግሥት ድርጅት እንደ መሆኑ መጠን መንግሥት የሚፈልገውን መጠየቅ ይችላል፡፡ እኔ ግን እንደ መሥሪያ ቤቱ ኃላፊ ዓይቼ ይህን ነገር አሁን ማድረግ እችላለሁ ብዬ ካመንኩና የምችል ከሆነ ፕሮግራሜ ውስጥ አስገብቼ እንግራችኋለሁ፡፡ የማልችል ከሆነ የማልችልበትን ምክንያት አስረዳችኋለሁ እንጂ፣ በየጊዜው በሥራ ጣልቃ መግባት የለባችሁም፡፡ በዓመቱ መጀመርያ ላይ የዓመቱን  ዕቅድ እሰጣችኋለሁ፡፡ እዚያ ላይ በቦርድ ስብሰባ ላይ መጨመር መቀነስ ትችላላችሁ፡፡ ከዚያ በኋላ ግን የተስማማንበትን ዕቅድ ሥራ ላይ በማውልበት ጊዜ በየሦስት ወሩ ሪፖርት እሰጣችኋለሁ፡፡ በሪፖርቱ ላይ አስተያየታችሁን መጨመር ትችላላሁች፡፡ ነገር ግን በመካከል በየዕለቱ በምሠራው ሥራ ውስጥ መንግሥትም ሆነ ቦርዱ ጣልቃ ገብቶ  ሥራውን እመራለሁ ማለት አይችልም፡፡ በዚህ ከተስማማችሁ ነው የምመጣው አልኳቸው ተስማሙ፡፡ እኔም ሥራውን ተረክቤ ገባሁ፡፡ እ.ኤ.አ. በ2004 በዋና ሥራ አስፈጻሚነት ሥራውን ተረክቤ መሥራት ጀመርኩ፡፡ እኔ ከመምጣቴ በፊት ቦርዱ የአየር መንገዱን ስትራቴጂካዊ ዕቅድ እንዲያወጡ ኧርነስት ኤንድ ያንግና ኤችኤስቲኢ የሚባል ድርጅት ቀጥረው ነበር፡፡ ከእነዚህ ድርጅቶች ጋር አብረን የአምስት ዓመት መሪ ዕቅድ ሠራን፡፡ ከድርጅቶቹና ከአየር መንገዱ ባለሙያዎች ጋር ሆነን በአምስት ዓመት ውስጥ አየር መንገዱ ምን መሆን አለበት? የሚለውን አቅጣጫ ያስቀመጠ ዕቅድ ሠራን፡፡

  ሪፖርተር፡- በዋነኝነት ያከናወናችሁት ምን ነበር?

  አቶ ግርማ፡- እኔ ተመልሼ ስገባ አየር መንዱ በዓመት የሚያመላልሰው የመንገደኞች ቁጥር 1.2 ሚሊዮን ነበር፡፡ ባዘጋጀነው የአምስት ዓመት ዕቅድ እ.ኤ.አ. በ2010 ሦስት ሚሊዮን እንዲደርስ ነው፡፡ በወቅቱ የነበረው ገቢ 390 ሚሊዮን ዶላር ነበር፡፡ በ2010 ወደ 949 ሚሊዮን ዶላር ለማድረስ ነው ያቀድነው፡፡ ግዴለም ለቁጥርም ያመቻል አንድ ቢሊዮን ዶላር እናድርገው፣ ለጥሪም ይመቻል ብለን ተስማማን፡፡ የነበሩን አውሮፕላኖች 28 ነበሩ፡፡ 30 ለማድረስ አቅደን 31 ሚሊዮን ዶላር የነበረውን ትርፍ ወደ 75 ሚሊዮን ዶላር ለማሳደግ አቀድን፡፡ ሌሎችም ዝርዝር ዕቅዶች ይዘን ወደ ሥራ ገባን፡፡ በወቅቱ ዕቅዱን የተቹ አልጠፉም፡፡ ይህ ስህተት ነው፣ ሊተገበር የማይችል ነው የሚል አስተያየት ከየአቅጣጫው ተሰንዝሯል፡፡ አየር መንገዱ በ60 ዓመት ዕድሜው በዓመት 1.2 ሚሊዮን መንገደኞች ማጓጓዝ የቻለው፡፡ እንዴት ሆኖ በአምስት ዓመት ከእጥፍ በላይ ሊያድግ ይችላል ሲሉ በርካቶች ሞግተዋል፡፡ እኛ ግን በጥናት ተመሥርተን የሠራነው ዕቅድ ስለነበር ተማምነንበት ሥራ ላይ አዋልነው፡፡ እ.ኤ.አ. ለ2010 ያቀድነውን አብዛኛውን በ2009 አሟልተናል፡፡

  ሪፖርተር፡- ያሳካችሁዋቸው ዋና ዋና ዕቅዶች ምንድን ነበሩ?

  አቶ ግርማ፡- በዋነኛነት አቅማችንን ማሳደግ ነበረብን፡፡ አቅማችንን ለማሳደግ የትምህርት ክፍሉን ማጠናከር ነበረብን፡፡ የትምህርት ክፍሉን አጠናከርን፡፡ የሚጎሉን ተቋማት ነበሩ፡፡ አቶ ብሥራት በነበሩ ጊዜ ታቅዶ የነበረው የካርጎ ተርሚናል ነበር፡፡ በእውነቱ አቶ ብሥራት ብዙ ነገር ሠርቷል፡፡ የካርጎ ዘርፍን ለማስፋፋት በማቀድ መጀመርያ ታቅዶ ከነበረው ከፍ አድርገን ሠራን፡፡ አውሮፕላኖቻችን ዱባይና ኢንቴቤ ሄደው ያድራሉ፡፡ ብዙ የማይሠሩበት ጊዜ ነበር፡፡ አውሮፕላኖቻችን ቶሎ ቶሎ እንዲመላለሱ አደረግን፡፡ በሳምንት ሁለት ቀን፣ ሦስት ቀን የምንበርበትን በየቀኑ አደረግን፡፡ ያን በምናደርግበት ጊዜ በእርግጥ ወጪ ይጨምራል፡፡ ነገር ግን ገቢያችንም በጣም ጨመረ፡፡ ለመንገደኛው ምርጫ በመስጠታችን በርካታ ደንበኛ አገኘን፡፡

  ሪፖርተር፡- ያገኛችሁትን ውጤት በአኃዝ አስደግፈው ቢገልጹልን?

  አቶ ግርማ፡- የመንገደኞች ቀጥር ከ1.2 ሚሊዮን ወደ 3.2 ሚሊዮን ማሳደግ ችለናል፡፡ ዕቅዱ ሦስት ሚሊዮን ነበር፡፡ ዓመታዊ ገቢን ከ390 ሚሊዮን ዶላር ወደ 1.2 ቢሊዮን ዶላር አሳድገነዋል፡፡ ትርፉን ከ31 ሚሊዮን ወደ 75 ሚሊዮን ለማድረስ ነበር ያቀድነው፡፡ እ.ኤ.አ. በ2010 101 ሚሊዮን ዶላር ማትረፍ ችለናል፡፡ ዓለም አቀፍ የመዳረሻ ብዛት ከ47 ወደ 55 አድጓል፡፡ የአውሮፕላኖች ቁጥር ከ28 ወደ 33 አድጓል፡፡ የሠራተኛ ብዛት ከ4,600 ወደ 6,200 አድጓል፡፡ ዕድገታችን በጣም በጥሩ ሁኔታ ሄደ፡፡ የበረራ መስመሮቻችን ጨመሩ፣ የበረራ ምልልሳችን በጣም ጨመረ፣ የሠራተኛው ምርታማነት በከፍተኛ መጠን ጨመረ፡፡ ሠራተኛው አየር መንገዱ ድርጅቴ ነው የሚለውን እምነቱን ለማጠናከር በሥልጠና፣ ችግሮች ሲኖሩም በመነጋገር በዓመት ሁለት ጊዜ ከሠራተኛው ጋር ተሰብስበን በሠራተኛው የፈለገውን ጥያቄ እንዲያቀርብ ዕድል ፈጠርን፡፡ በማኔጅመንትና ሠራተኛው መካከል የነበረውን ግንኙነት አሻሻልነው፡፡  

  ሪፖርተር፡- በዚያን ወቅት የባለሙያዎች መልቀቅ ችግር ነበር፡፡ በተለይ ልምድ ያላቸው ፓይለቶች በብዛት እየለቀቁ ነበር፡፡ ችግሩን እንዴት ፈታችሁት?

  አቶ ግርማ፡- እውነት ነው ችግሩ ነበር፡፡ የሠራተኛውን ደመወዝ በቻልነው መጠን አሻሽለናል፡፡ በተለይ ፓይለቶች አካባቢ እስከ 400 ፐርሰንት የሚደርስ የደመወዝ ማስተካከያ አድርገናል፡፡ ያም ሆኖ በዓለም አቀፍ ገበያ የሚፈለገውን ያህል አንከፍልም ነበር፡፡ ነገር ግን ሠራተኛው ዕድገቱ እንደሚጠበቅለት፣ አየር መንገዱ የራሱ መሆኑን በማሰብ እንደ በፊቱ ብዙ አይሄድም ነበር፡፡ ፍልሰቱ ቀንሶ ነበር፡፡ ቀስ በቀስ ሲያዩት እዚሁ አገራች እየሠሩ እያደጉ ወደ ውጭ የሄዱት ያልደረሱበት መድረስ እንደሚቻል እየተረዱ ሄዱ፡፡ በአገራችን በቤታችን ሠርተን ከቤታችን ጋር ብናድግ ይሻላል የሚል ምርጫ ወስደው አብዛኞቹ ከአየር መንገዱ ጋር ቀጠሉ፡፡ በእርግጥ የደመወዝ ጭማሪ አድርገናል፡፡ ነገር ግን ጭማሪው ከውጭ የሚያስቀር አይደለም፡፡ ኑሯቸውን እንዲያሸንፉና ልጆቻቸውን ማስተማር ያስችላል እንጂ፣ ከውጭ አየር መንገዶች ጋር የሚወዳደር ደመወዝ አልነበረም፡፡ ነገር ግን ለአገርና ለአየር መንገዱ ካላቸው ፍቅር የተነሳ ግዴለም ይህን ያህል ከተከፈለን በአገራችን ብንሠራ በማለት የሚሄደው ፓይለት ቁጥር ቀነሰ፡፡

  ሪፖርተር፡- ስለራዕይ 2025 የዕድገት መርሐ ግብር ዝግጅትና እንዴት በጡረታ ለመገለል እንደወሰኑ ቢገልጹልን?

  አቶ ግርማ፡- እኔ አየር መንገዱን አምስት ዓመት ለማገልገል ነው ተስማምቼ የመጣሁት፡፡ አምስት ዓመት ከጨረስኩ በኋላ እ.ኤ.አ. 2009 አምስት ዓመቴን ጨረስኩ፡፡ ሌላ ሰው ይተካና እኔ ልልቀቅ ብዬ በአቶ ሥዩም መስፍን ለሚመራው ቦርድ አመለከትኩ፡፡ የለም ራይዕ 2010 ይለቅ፣ ጥሩ እየሄደ ስለሆነ በዚህ ወቅት ባትሄድ መልካም ነው ስላሉኝ ሁለት ዓመት ጨመርኩ፡፡ በዚህ ጊዜ ውስጥ ሊተኩኝ የሚችሉ ሰዎች አዘጋጀሁ፡፡ ራዕይ 2025 ከውጭ ዕርዳታ ሳንጠይቅ በራሳችን ሰዎች ኮሚቴ አቋቁመን እያጠናን፣ እየሠራን፣ መጨረሻ አዘጋጅተን ለመንግሥት ላክን፡፡ ለቦርድ አቅርበን ፀደቀ፡፡ ዕቅዱ ለሥራ ዝግጁ ከሆነ በኋላ እኔ የእኔ ድርሻ አልቋል፣ ራዕይ 2025 ተዘጋጅቷል፣ የተዘጋጀም ሰው አለ፣ እኔም ከእንግዲህ ወዲህ 67 ዓመት ሆኖኛል፣ ከአሁን በኋላ መቆየቴ ትክክል አይደለም፡፡ ከዚህ በኋላ በእኔ መቆየት ወጣቶቹ ሳያድጉ ከቀሩና ከለቀቁ አየር መንገዱ ይጎዳል፡፡ እኔ አሁን ከወጣሁ ግን አየር መንገዱ የሚጎዳው ነገር የለምና ልቀቁኝ ብዬ ራሴ ጠይቄ ነው የወጣሁት፡፡

  ሪፖርተር፡- በስፋት ሲወራ የምንሰማው ከሥራዎት የለቀቁት በመንግሥት ተገፍተው ወይም እርስዎን በተኩዎት በአቶ ተወልደ ገብረ ማርያም ተገፍተው እንደወጡ ነው፡፡ ጡረታ እንዲወጡ የተደረገብዎ ግፊት ነበር?

  አቶ ግርማ፡- እኔን ማንም አልገፋኝም፣ ሊፈገፋኝም አይችልም፡፡ ነገር ግን ቀደም ብዬ እንደገለጽኩት እኔ የመጣሁት አምስት ዓመት ለማገልገል ነበር፡፡ መስተካከል የነበረባቸውን ሁኔታዎች ከባልደረቦቼ ጋር ሁኜ አስተካክዬ ለሰባት ዓመታት ሠራሁ፡፡ በመካከል አሞኝ ስለነበር ቀዶ ሕክምና አደረግኩ፡፡ ቀዶ ጥገናውን አድርጌ ተመልሼ ሠራሁ፡፡ ከዚያ በኋላ የእኔ መቆየት የሚያስፈልግ መስሎ አልታየኝም፡፡ እንዲያውም አቶ ሥዩም ለምን ትለቃለህ? ትንሽ ቆይ ብለው ሊያግባቡኝ ብዙ ጥረዋል፡፡ እኔ ግን ከዚህ በኋላ ይበቃኛል በሚለው አቋሜ ፀናሁ፡፡ ሊተካኝ የሚችል ሰው አዘጋጅቻለሁ ስላቸው፣ ማነው የሚተካህ? ሰው ብለው ሲጠይቁኝ አቶ ተወልደ ነው ብዬ ያቀረብኩት እኔው ራሴ ነኝ፡፡

  ሪፖርተር፡- አቶ ተወልደን እንዴት ለቦታው ሊያጩ ቻሉ?

  አቶ ግርማ፡- ቀደም ሲል ተወልደ የአሜሪካ ኤሪያ ማኔጀር ነበር፡፡ ከዚያ ያስመጣሁት እኔ ነኝ፡፡ የማርኬቲንግ ክፍል ኃላፊ የነበረው አቶ መኮንን አበበ ጡረታ ሊወጣ ሲል ማነው ሊተካህ የሚችለው ብዬ ስጠይቀው፣ ተወልደ በሚገባ ሊተካው እንደሚችል አስረዳኝ፡፡ በእሱ ጥቆማ መሠረት ተወልደ ከአሜሪካ እንዲመጣና የመኮንንን ቦታ እንዲረከብ አደረግኩ፡፡ አቶ ተወልደ በቅርበት አብሮኝ ሲሠራ ሥራውን ጠንቅቆ የሚያውቅ፣ ጊዜውንና ዕውቀቱን የማይቆጥብና ታታሪ ሠራተኛ መሆኑን ለመገንዘብ ችያለሁ፡፡ አቶ ተወልደ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ውስጥ ያደገ በመሆኑና ድርጅቱን ከታች እስከ ላይ የሚያውቅ በመሆኑ፣ በተለያየ ቦታና ኃላፊነት አስቀምጨ፣ ፈትኜና ዓይቼው ስለነበር ለአየር መንገዱ ሥራ ጠንካራ ነው ብዬ አምኜ ለቦርዱ አቅርቤ አሳምኜ ነው እንዲተካኝ አድርጌ የለቀቅኩት እንጂ ተወልደ አልገፋኝም፣ ሊገፋኝም አይችልም፡፡ ቦርዱም አንፈልግህም አላለኝም፡፡ እኔ ፈልጌና ፈቅጄ ነው ቦርዱን ወትውቼና አሳምኜ የለቀቅኩት፡፡ የሌለ ኃጢያት በሌላ ሰው ላይ መለጠፍ አግባብ አይደለም፡፡ ይህንን የሚያስወሩ ሰዎች ምናልባት መረጃው ስሌላቸው ይሆናል እንጂ፣ በምንም ዓይነት እኔ ከአየር መንገዱ ተገፍቼ አልወጣሁም፡፡

  ሪፖርተር፡- በወቅቱ ለመልቀቅዎ ዋናው ምክንያት መንግሥት በሥራዎ ላይ ተፅዕኖ ያደርግብዎ ስለነበር እንደሆነ ይነገራል፡፡ አንዳንዶች ከቦርዱ ጋር አለመግባባት ተፈጥሮ እንደነበር የሚገልጹ አሉ፡፡ የእርስዎ ምላሽ ምንድነው?

  አቶ ግርማ፡- መንግሥትም ሆነ ቦርዱ ያሳደሩብኝ ተፅዕኖ አልነበረም፡፡ መንግሥት በሥራዬ ጣልቃ አልገባብኝም፡፡ ከቦርዱም ጋር መልካም የሥራ ግንኙነት ነበረኝ፡፡ እውነቱን መናገር አስፈላጊ ነው፡፡ አቶ ሥዩም ለአየር መንገዱ ዕድገት ከነበራቸው ምኞት ለማኔጅመንቱ አስፈላጊውን ሁሉ ድጋፍ አድርገዋል፡፡ በሥራችንም ጣልቃ አይገቡም ነበር፡፡ ቀደም ብዬ እንደገለጽኩት በሥራ ጣልቃ እንዳይገቡ ቃል አስገብቼ ነበር የመጣሁት፡፡ እስከ መጨረሻው ቃላቸውን አክብረው ነበር አብረውን የሠሩት፡፡ ችግር እንኳን ሲፈጠር ከጎናችን ነበር የሚቆሙት፡፡ እሳቸውም መንግሥትም ቃላቸውን አክብረዋል፡፡ ሊመሠገኑ ይገባል እንጂ እኔን የጎዳኝ ሰው የለም፡፡ እንድወጣም የገፋኝ ሰው የለም፡፡ አጉል አጉል ጥያቄ የሚጠይቁ አንዳንድ የመንግሥት ኃላፊዎች ነበሩ፡፡ እነሱን እኔ በይፋ አይሆንም፣ ይኼን አላደርግም እላቸው ነበር፡፡ ያው ለጊዜው ተቀይመው ዝም ይላሉ፡፡ እኔም ብዙ አልተጨነኩበትም፣ እነሱም የግል ጉዳይ አድርገው እኔን ለማጥቃት የተነሱበት ጊዜ አልነበረም፡፡

  ሪፖርተር፡- እርስዎ ከኢትዮጵያ አየር መንገድ ከለቀቁ በኋላ አየር መንገዱ እየተጓዘበት ያለበትን ሁኔታ እንዴት ያዩታል? ማኔጅመንቱ እያከናወነ ባለው ሥራ ደስተኛ ነዎት?

  አቶ ግርማ፡- አየር መንገዱ በጣም እያደገ ነው፡፡ በራዕይ 2025 ያስቀመጥናቸው ግቦች በሙሉ እያሟሉ ነው፡፡ እንዲያውም በ2025 እንደርስበታለን ያልነውን ቦታ አሁን እንደማየው በ2021 ወይም በ2022 ይደርሳሉ፡፡ በአየር መንገዱ ዕድገት በኩል ኢትዮጵያውያን በሙሉ ሊያምኑበት የሚገባ ሌሎች የአፍሪካ አገሮች የሚቀኑበት፣ በደንብ ግልጽ በሆነ ሁኔታ የአፍሪካ መሪ አየር መንገድ ሆኗል፡፡ ያሉት የበረራ መዳረሻዎች ማንም የአፍሪካ አየር መንገድ የለውም፡፡ እጅግ ዘመናዊ አውሮፕላኖች ባለቤት ሆኗል፡፡ የመንገደኞች ቁጥር አሥር ሚሊዮን ደርሷል፡፡ ለዚያውም በዚህ ከባድ በሆነ ኤርፖርት ነው ይህን ሁሉ መንገደኛ ማስተናገድ የቻለው፡፡ ስለዚህ እኔ በበኩሌ የአየር መንገዱ ዕድገት ደስ ይለኛል፡፡ እንዲያውም እኔ በጣም ፈጥኖ ስላደገ ትንሽ ያዝ ቢያደርጉት እያልኩ የማኔጅመንቱን አባላት እመክራለሁ፡፡ አንዳንድ ጊዜ ሲሮጡ እንቅፋት ቢመታ አወዳደቁ ጥሩ አይሆንምና ትንሽ ያዝ አድርጉት እያልኩ ከእነሱ ጋር እነጋገራለሁ፡፡ ነገር ግን ዕድገቱ ከጠበቅነው በላይ ጥሩ ሆኖ እያደገ ነው ያለው፡፡ የማኔጅመንቱ አባላትም ይህን አየር መንገድ መምራት መቻላቸውን አረጋግጠዋል፡፡

  ሪፖርተር፡- ከአየር መንገዱ ሠራተኞች የሚነሱ ቅሬታዎች አሉ፡፡ አንዳንድ የአየር መንገዱ ሠራተኞች አሁን በሥራ ላይ ያሉ፣ ሌሎችም እንዲሁ የለቀቁ ሠራተኞች የአስተዳደር በደል እንደሚፈጸም በመግለጽ በማኔጅመንቱ ላይ የሰላ ትችት ይሰነዝራሉ፡፡ ይህን ጉዳይ እንዴት ያዩታል?

  አቶ ግርማ፡- አንድ ሰው ወይም የማኔጅመንት ቡድን አንድን ቦታ ወይም ድርጅት ሲያስተዳደር ሁሉንም ሠራተኛ ሊያስደስት አይችልም፡፡ እኔ እንደማየው አየር መንገዱ  በጣም ብዙ ሰው መስዋዕትነት ከፍሎ ያሳደገው ነው፡፡ ዕድገቱ በጣም ጥሩ ነው፡፡ መሆን ያለበት ሠራተኛውና ማኔጅመንት መነጋገር አለባቸው፡፡ ከሠራተኛው የሚነሳ ጥያቄ ካለ ከማኔጅመንቱ ጋር ተነጋግሮ መፍታት ነው፡፡ ሁለት ቡድን ሳይሆኑ አንድ ቡድን ናቸው፡፡ ቅሬታ ያለው ሰው አየር መንገዱ ሕግ ያለው በመሆኑ በሕጉ መሠረት መብቱን መጠየቅ ይችላል፡፡ አየር መንገዱ ውስጥ መብቱን ማስከበር ካልቻለ ፍርድ ቤት ከሶ ማስፈረድ ይችላል፡፡ አንድን ድርጅት በማኅበራዊ ሚዲያ መምራት አይቻልም፡፡ ሕግን ተከትሎ ችግሮችን መፍታት ነው እንጂ አንዱ በሌላው ላይ ጦርነት መክፈቱ ለአየር መንገዱ አይጠቅምም፣ ለአገሪቱም አይጠቅምም፡፡ ይህንን ዛሬ የአፍሪካ አየር መንገዶች የሚቀኑበትና ዓለም በሙሉ የተቀበለውን አየር መንገድ ማበላሸትና ማጥፋት የትም አያደርሰንም፡፡ ችግር የለም አይደለም የምለው፡፡ ችግር ካለ በትክክለኛው መንገድ መፈታት አለበት፡፡ ይህ አየር መንገድ ቦርድ አለው፡፡ በውስጥ ሥርዓቱ ሊፈታ ካልቻለ ቦርዱ ጋ ማቅረብ ይቻላል፡፡ ቦርዱ ነገሩን ሊያየው ይችላል እንጂ ይኼ በፌስቡክ የሚደረገው ዘመቻ አግባብ አይደለም፡፡ የአየር መንገዱን ስም ጥላሸት ማልበሱ ጥቅም ያለው አይመስለኝም፡፡

  ሪፖርተር፡- የኢትዮጵያ መንግሥት በቅርቡ የኢትዮጵያ አየር መንገድን ጨምሮ ትልልቅ የመንግሥት የልማት ድርጅቶችን በከፊል ወደ ግል ለማዞር ዕቅድ እንዳለው አስታውቋል፡፡ ብዘዎች የኢትዮጵያ አየር መንገድ ትርፋማ ነው፣ ከአፍሪካ ቀዳሚ አየር መንገድ ለመሆን ችሏልና ካስመዘገባቸው ስኬቶች አንፃር ለምን ፕራይቬታይዝ ማድረግ አስፈለገ የሚል ጥያቄ ያነሳሉ፡፡ በዚህ ላይ የእርስዎ አቋም ምንድነው?

  አቶ ግርማ፡- መንግሥት አየር መንገድን በከፊልም ቢሆን ለምን ወደ ግል ማዞር እንደፈለገ የተሟላ መረጃ የለኝም፡፡ ለሌሎች የመንግሥት ፕሮጀክቶች ገንዘብ ለመሰብሰብ ከሆነ ሙሉ መብት አለው፡፡ ነገር ግን የአጭር ጊዜ ፍላጎት የረዥም ጊዜ ተስፋችንን እንደማያጨልም ተስፋ አደርጋለሁ፡፡ ሌሎች ተመሳሳይ ዕርምጃ ከወሰዱ እንደ ኬንያ ካሉ አገሮች ተሞክሮ ትምህርት መውሰድ ያስፈልጋል፡፡ ኬንያ ኤርዌይስ በከፊል ፕራይቬታይዝ መደረጉ ብዙም አልጠቀመውም፡፡ እንደሚታወቀው ኬንያ ኤርዌይስ አሁንም ኪሳራ ውስጥ ነው የሚገኘው፡፡ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ትርፋማ ነው፡፡ ከአየር መንገዱ ትርፍ የተወሰነውን መንግሥት ለሌሎች ፕሮጀክቶች መደገፊያ ሊጠቀምበት ይችላል፡፡ እኔ እስከማስታውሰው ድረስ ዓለም አቀፍ የገንዘብ ተቋማት የኢትዮጵያ አየር መንገድን ፕራይቬታይዝ አድርጉ ብለው አያውቁም፣ በንግድ መርሆች እስከተዳደረ ድረስ፡፡

  ሪፖርተር፡- ኢትዮጵያ ውስጥ በታሪክ እንዳየነው የመንግሥት ለውጥ ሲኖር የፖለቲካ ትኩሳቱ አየር መንገዱ ላይ በተወሰነ ደረጃ ይንፀባረቃል፡፡ የንጉሡ ሥርዓት ፈርሶ ደርግ ሲመጣ አየር መንገዱ ላይ መንገጫገጭ ተፈጥሮ ነበር፡፡ ደርግ ወድቆ ኢሕአዴግ ሲመጣ በመንግሥትና በአየር መገንገዱ ኃላፊዎች መካከል ግጭቶች ተፈጥሯል፡፡ እናንተም ተጋጭታችሁ ሄዳችኋል፡፡ አሁን የአገሪቱን ፖለቲካ ሁኔታ ስንመለከት በለውጥ ላይ ያለች አገር ናትና ከዚህ አንፃር ከመንግሥት በኩል ምን ጥንቃቄ ሊደረግ ይገባል? ለመንግሥት የሚያስተላልፉት መልዕክት ምንድነው?

  አቶ ግርማ፡- እኔ በአየር መንገድ ውስጥ ሆኜ ሦስቱንም ሥርዓት አሳልፌያለሁ፡፡ አየር መንገዱን ንጉሡ ካቋቋሙት በኋላ እያደገ መጣ፡፡ ደርግ በሚመጣበት ጊዜ አየር መንገዱን ይኼ የኢምፔሪያሊስት ዕቃ ነው፣ ንጉሡ የፈጠሩት ለራሳቸው ዝና ሲሉ ነው በማለት ፊት ለፊት መጥተው የደርግ አባሎች ነግረውናል፡፡ በወቅቱ ዋና ሥራ አስፈጻሚ የነበሩት ኮሌኔል ስምረት መድኃኔ አንስተው ከአየር ኃይል ጄኔራል አምጥተው ሾመዋል፡፡ የእኛ ሰው ነው ብለው ያመኑበትን ሾመዋል፡፡ የሰው ኃይል አስተዳደር ኃላፊ የነበሩትን አቶ እጅጉ ደምሴና የፐርሶኔልና የደንበኞች አገልግሎት ኃላፊዎችን አንስተዋቸዋል፡፡ የንጉሡ ደጋፊዎች ናቸው ብለው ያሰቧቸውን በሙሉ አስወግደዋል፡፡  አዲስ አበባ ውስጥ የኢትዮጵያ ሠራተኛ ማኅበር የተቃውሞ ወረቀት በሚበትንበት ጊዜ፣ አየር መንገድ ውስጥም የተወሰነ ወረቀት በመገኘቱ መጥተው የሠራተኛ ማኅበሩን ሊቀመንበር ጎትተን እንሄዳለን በሚሉበት ወቅት ሠራተኛው በመቃወሙ ስምንት ሰዎች ተገድለዋል፡፡ 1,000 ሠራተኞች ታስረው ነበር፡፡ ያን ክፉ ጊዜ አልፈነዋል፡፡ አንዳንዶቹ እኛ ኮሙዩኒስት ስለሆንን የሩሲያ አውሮፕላን ካልገዛችሁ የሚል አቋም ይዘው ነበር፡፡

  አየር መንገዱ ያንን ሁሉ ተቋቁሞ፣ ማኔጅመንትና ሠራተኛው አንድ ሆኖ መንግሥትን አሳምኖ የሩሲያ አውሮፕላን ሳይገዛ ቀረ፡፡ መንግሥትም አየር መንገዱ የኢምፔሪያሊስት ወይም ጃንሆይ ለግላቸው ያቋቋሙት ሳይሆን ለአገሪቱ እንዲጠቅም እንደሆነ በተረዱ ጊዜ፣ እስከ መጨረሻው የኢትዮጵያ አየር መንገድን ደግፈው ነው የቆዩት፡፡ የኢትዮጵያ አየር መንገድ እንደሚጠቅማቸው ተረድተው የሚያስፈልገውን ነገር ሁሉ ከልባቸው ሲያደርጉ ቆይተው ሄደዋል፡፡

  እነሱ ሄደው ኢሕአዴግ በሚመጣበት ወቅት የኢትዮጵያ አየር መንገድ የደርግ አሽከር ነበር፣ የደርግ መሣሪያ አመላላሽ ነበር በሚል አየር መንገዱን ለማፍረስ እልም ያለ ትግል ተጀምሮ ነበር፡፡ አየር መንገዱን እንደገና ለማዋቀር በሚል የኢሕአዴግ ሹመኞች የተሳሳተ መንገድ ተከትለው ከአየር መንገዱ ኃላፊዎችና ባለሙያዎች ጋር ትልቅ ተቃርኖ ውስጥ ገብተው ነበር፡፡ የመንግሥትን ዕቅድ አይደግፍም፣ ከዚያም አልፈው ከውጭ ኃይሎች ጋር ተመሳጥረዋል በሚል ሰበብ 35 የማኔጅመንት አባላትን አባረዋል፡፡ ነገር ግን በኋላ ከሠሩት ጥፋት ተምረው አየር መንገዱ ለአገር የሚያበረክተውን አስተዋጽኦ ተረድው ድርጅቱንና ማኔጅመንቱን ሲደግፉ ቆይተዋል፡፡ የደርግም የኢሕአዴግም መንግሥት ከስህተታቸው ታርመው አየር መንገዱን ወደ መደገፍ ገብተዋል፡፡ ደግነቱ እንደ ሌላው የአፍሪካ መንግሥት በጭፍን ጥላቻ እስከ መጨረሻው አልሄዱም ተመልሰዋል፡፡ የአየር መንገዱ ማኔጅመንትና ሠራተኞች በአንድነት እንደ አንድ ቡድን ተባብረው በመሥራታቸው እነዚያን ፈታኝ ወቅቶች ተቋቁመው አልፈዋል፡፡ የአሁኑ ለውጥ አየር መንገዱን በመቃረን የመጣ አይደለም፡፡ የአየር መንገዱን ጠቀሜታ የሚገነዘቡ ሰዎች ናቸውና ለአየር መንገዱ ያስባሉ የሚል እምነት አለኝ፡፡ ነገር ግን ረጋ ብለው ማየት አለባቸው የተወሰኑ ሰዎች በሚያሰሙት ጩኸትና በአንዳንድ ግለሰቦች አስተያየቶች መመራት የለባቸውም፡፡ ጥርጣሬ ካላቸው ደግሞ ይኼ ነገር እውነት ነው ወይ ብለው ቦርዱን መጠየቅ አለባቸው፡፡ ቦርዱ ጥያቄውን አጣርቶ ማቅረብ አለበት፡፡ አየር መንገዱ በጥሩ ሁኔታ እያደገ ነው፡፡ ስህተት አለ ከተባለ ማኔጅመንቱን ጠርቶ ይህን ይህን የሠራችሁትን እንወዳለን፣ ይኼን ይኼን ደግሞ የሕዝብ ቅሬታ የሚያስነሳ ስለሆነ አርሙ፣ ይህ እንዲቀጥል አንፈልግም ብሎ አየር መንገዱ ባለው መስመር ቢቀጥል የተሻለ ይሆናል እንጂ፣ መንግሥት በተቀየረ ቁጥር ማኔጅመንቱን መቀያየር ሌሎች የአፍሪካ አገሮች እንደሆኑት ሁሉ አየር መንገዱን ማፍረስ ነው የሚሆነው፡፡

  ጋናና ናይጄሪያ ከእኛ የበለጠ አየር መንገዶች ነበሯቸው፡፡ ዛሬ እነዚህ ታላላቅ አገሮች ብሔራዊ አየር መንገድ የላቸውም፣ ፈርሰዋል፡፡ ኬንያ ኤርዌይስ እ.ኤ.አ. በ2004  ከኢትዮጵያ አየር መንገድ በ30 በመቶ ይበልጥ ነበር፡፡ ዛሬ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ኬንያ ኤርዌይስን በእጥፍ ይበልጣል፡፡ እነ ሳውዝ አፍሪካ ኤርዌይስ ያኔ ሰማይ ላይ እንዳሉ ነበር የምናያቸው፡፡ ዛሬ እነሱ ናቸው ሰማይ ላይ እንዳለን የሚያዩን፡፡ የኢትዮጵያ አየር መንገድ አሁን ያለበትን የዕድገት ጉዞ ባናጨናግፍ ጥሩ ነው፡፡ መንግሥት ድርጅቱን በትክክለኛው መንገድ ቀርቦ ስህተት ካለ ስህተቱን እንዲያርም ማድረግ እንጂ፣ በአንዳንድ ሰዎች ቅሬታ ተመርቶ ዕርምጃ መውሰድ የለበትም፡፡ ቅሬታ ያለው ሰው ቅሬታውን ለመንግሥትም ሊያቀርብ ይችላል፡፡ ነገር ግን ቅሬታው ሳይጣራ ምንም ዓይነት ውሳኔ መወሰን የለበትም፡፡ አንዳንድ የሚቀርቡ ቅሬታዎችን እመለከታለሁ፡፡ አንዱ ያለው ማታ ሲዝናና በተናገረው ነገር ምክንያት ከአብራሪነት መሬት ላይ እንዲሠራ መደረጉን ነው፡፡ ማወቅ ያለብን ነገር ከደኅንነት አንፃር በመንግሥት ወይም በአየር መንገዱ የሚወሰዱ ዕርምጃዎች አሉ፡፡ የጀርመን ዊንግስ ፓይለት በፈጸመው ድርጊት የብዙ ሰው ሕይወት ቀጥፏል፡፡ የበረራ ደኅንነት ለማስጠበቅ በመንግሥትም የሚወሰዱ ዕርምጃዎች ይኖራሉ፡፡ ይህን መረዳት ያስፈልጋል፡፡

  ሌላው መታወቅ ያለበት ጉዳይ ፓይለትነት የገባ ሁሉ ፓይለት ይሆናል ማለት አይደለም፡፡ እኔ ለፓይለትነት ነበር የገባሁት፣ በፓይለትነት ግን አልቀጠልኩም፡፡ ለፓይለትነት ሥልጠና 20 ገብቶ ሰባት ጥሩ ፓይለት ቢወጣ መልካም ነበር፡፡ እንዲያውም አሁን አየር መንገዱ ብዙ ምሥለ በረራዎች ገዝቶ ደጋግሞ ስለሚያስተምር የሚወድቀው ሰው እያነሰ ሄዷል፡፡ አንድ ፓይለት ይህ ችግር አለብህና ምሥለ በረራ ብረር ሲባል አልበርም ብሎ ወደ ግብርና ገባ ሲባል ለእኔ ለመቀበል ትንሽ ይከብደኛል፡፡ አንዳንድ ሰው በትምህርት ጎበዝ ሆኖ ሳለ በረራ ላይሳካለት ይችላል፡፡ ነገሮችን በሰከነ መንገድ ማየት ተገቢ ይመስለኛል፡፡

  ሪፖርተር፡- በኢትዮጵያ አየር መንገድ ብቻ ሳይሆን በመካከለኛው ምሥራቅና በተለያዩ የአፍሪካ አገሮች ካለዎት ተሞክሮ በመነሳት፣ ለኢትዮጵያ አየር መንገድ ሠራተኞችና ማኔጅመንት የሚያስተላልፉት መልዕክት ምንድነው?

  አቶ ግርማ፡-  እኔ ያለኝ መልዕክት አንድ ነው፡፡ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ሠራተኛ እኛ እንደምናውቀው ሃይማኖቱም፣ ዘሩም አየር መንገዱ ነው፡፡ በብዙ ልፋትና ድካም የተገነባ አየር መንገድ በስሜት በቀላሉ መፍረስ የለበትም፡፡ እኔ እስከማውቀው ድረስ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ሠራተኛ በሃይማኖት አይጣላም፣ በዘር አይጣላም፣ ሁሉም አብሮ በልቶ፣ አብሮ ሠርቶ፣ አብሮ ተነጋግሮ የሚያልፍ ነው፡፡ ሠራተኛው ከብሔርተኝነት ስሜት ነፃ መሆን አለበት፡፡ ይህን ለማስከተል የሚፈልግ የማኔጅመንት አባል ሆነ ሠራተኛ ተው መባል አለበት፡፡ የእኔ ምክር ይኼ አየር መንገድ ሁላችንንም ያሳደገ፣ ሁላችንም ላለንበት ደረጃ ያደረሰን ነው፡፡ ዛሬ ያሉትም ለብዙ ቦታ ሊያደርስ የሚችል ድርጅት ነው፡፡ ለአገሪቱም ጥሩ ምልክት ነው፡፡ የአየር መንገዱ ማኔጅመንትና ሠራተኛ ይባል እንጂ አንድ ቡድን ነው፡፡ በዚያ በቡድን መንፈስ ያለፉት ትውልዶች እንዳቆዩት አሁን ያሉት ወጣቶች ይዘው ለሚቀጥለው ትውልድ ማሳለፍ አለባቸው፡፡ ይኼ አየር መንገድ ከ70 ዓመታት በላይ ብዙ መስዋዕትነት ተከፍሎ የተገነባ ነው፡፡ በጊዜያዊ ግጭት በአጭር ጊዜ ውስጥ ቢፈርስ ሐዘኑ ለሁላችንም የከፋ ይሆናልናል አደራ እላለሁኝ፡፡

  ተዛማጅ ፅሁፎች