በቅርቡ የተቋቋመው የኢትዮጵያ አሠሪዎች ኮንፌዴሬሽን ከኢትዮጵያ ሠራተኞች ማኅበራት ኮንፌዴሬሽን ጋር በሚያገናኟቸው ጉዳዮች ላይ አብሮ ለመሥራት የመግባቢያ ሰነድ ፈረሙ፡፡
ሁለቱ ኮንፌዴሬሽኖች ኅዳር 7 ቀን 2011 ዓ.ም. በኃላፊዎቻቸው አማካይነት ፊርማቸውን አኑረዋል፡፡ የኢትዮጵያ አሠሪዎች ኮንፌዴሬሽን ፕሬዚዳንት አቶ ጌታሁን ሁሴን (ኢንጂነር) ‹‹የተረጋጋ የኢንዱስትሪ ሰላምን ለማስፈንና ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግ የአሠሪዎችና የሠራተኞች ማኅበራት ኮንፌዴሬሽኖች ስምምነት ማድረጋቸው ትልቅ አስተዋጽኦ ያበረክታል፤›› ብለዋል፡፡ የአሠሪዎች ኮንፌዴሬሽን ከተቋቋመ አጭር ጊዜ እንደሆነ ያስታወቁት ፕሬዚዳንቱ፣ የአሠሪውን መብትና ጥቅም ለማስከበር እየሠራ እንደሚገኝ በመግለጽ፣ ወደፊትም ከሠራተኛና ማኅበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር እንዲሁም ከሠራተኞች ማኅበራት ኮንፌዴሬሽንና ከአሠሪዎች ኮንፌዴሬሽን ጋር ጠንካራ ሥራ እንደሚሠራም ገልጸዋል፡፡
በኢትዮጵያ ሠራተኞች ማኅበር ኮንፌዴሬሽን ፕሬዚዳንት አቶ ካሳሁን ፎሎ ስምምነቱን ሲፈርሙ፣ ‹‹የአሠሪዎች ኮንፌዴሬሽን ከተቋቋመ አጭር ጊዜ ቢሆንም ተባብረን ካልሠራን አሸናፊ ልንሆን አንችልም በሚል መሪ ቃል በአገራችን ለመጀመርያ ጊዜ የኮንፌዴሬሽን ለኮንፌዴሬሽን ስምምነት መፈረማችን የኢንዱስትሪውን ሰላም ለማስፈን ትልቅ ሚና አለው፤›› ብለዋል፡፡ ሆኖም በውጭ ኩባንያዎች በኩል ሠራተኞች ላይ የሚደርስ የመብት ጥሰት ትልቅ ችግር ሆኖ ስለመቆየቱ፣ በተለይ በቻይና ኩባንያዎች ውስጥ ተቀጥረው የሚሠሩ ዜጎች ሕገ መንግሥታዊ የመደራጀት መብታቸው እንደማይከበርላቸውና የተደራጁትንም ቢሆን የሠራተኞች ማኅበር ኃላፊዎችን አሠሪዎቹ ከሥራ ማባረርን ጨምሮ የተለያዩ ጥቃቶችን በማድረስ ማኅበራቶች ህልውና እንዳይኖራቸው እያደረጉ እንሚገኙ ገልጸዋል፡፡