የመንግሥት ተቋማትን ልማዳዊ የግዥ ሥርዓት በኤሌክትሮኒክ የታገዘ ሥርዓት ለመዘርጋት የሚያስችል የስትራቴጂ ዕግድና መተግበሪያ ይፋ ሆነ፡፡
ሐሙስ፣ ኅዳር 6 ቀን 2011 ዓ.ም. በገንዘብ ሚኒስቴር በተካሄደ ዓውደ ጥናት የመንግሥት ግዥና ንብረት አስተዳደር ኤጀንሲ፣ ከኢንፎርሜሽንና ኢኖቬሽን ሚኒስቴር ጋር በመሆን የተዘጋጀውን የኤሌክትሮኒክ ግዥ ስትራቴጂ ከዕቅድ መተግበሪያ ሥርዓት ጋር አጣምረው ይፋ አድርገዋል፡፡
የዲጂታል ግዥ ሥርዓቱ በአገሪቱ ለዓመታት የቆየውን የግዥ ሥርዓት በማዘመን የተቀላጠፈና ግልጽ አሠራር እንዲኖር በማስቻል ትልቅ ሚና እንደሚኖረው የመንግሥት ግዥና ንብረት አስተዳደር ኤጀንሲ ዋና ዳይሬክተር ወ/ሮ ማርታ ሉጂ ገልጸዋል፡፡ ዕቅዱ ለአምስት ዓመት እንዲተገበር የተዘጋጀ ሲሆን እ.ኤ.አ. ከ2018 እስከ 2023 እንደሚቆይ አስታውቀዋል፡፡
ኃላፊዋ እንደገለጹት፣ የዲጂታል ግዥ በተወሰኑ የመንግሥት ተቋማት በኩል ከመጪው ወር ጀምሮ መተግበር ይጀምራል፡፡ አዲሱን ሥርዓት ለመተግበር የሚያስችል የመግባቢያ ሰነድም በኤጀንሲውና በኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር መካከል ተፈርሟል፡፡
የኤሌክትሮኒክ ግዥን መተግበር የሚያስችለው ሶፍትዌር በሚኒስቴሩ የተዘጋጀ ሲሆን፣ ለአገሪቱ ዘመናዊ የግዥ ሥርዓት ትልቅ ዕርምጃ እንደሚሆን ሚኒስትሩ ጌታሁን መኩሪያ (ዶ/ር) ገልጸዋል፡፡ ከ50 ዓመት በፊት ጀምሮ እየተተገበረ በሚገኘው የግዥ ሥርዓት መቀጠል ከአሁን በኋላ የትም እንደማያደርስ ሚኒስትሩ ገልጸዋል፡፡
የገንዘብ ሚኒስትር ዴኤታው ኢዮብ ተካልኝ በበኩላቸው፣ የስትራቴጂ ዕቅዱና መተግበሪያው ለአገሪቱ ከፍተኛ ስኬት ከመሆን አልፎ ‹‹ዓለም አቀፍ አገልግሎት መስጠት ወደምንችልበት ደረጃ የሚወስደን ነው፤›› በማለት አወድሰውታል፡፡
አዲሱ የዲጂታል የግዥ ሥርዓት በመንግሥት መሥሪያ ቤቶችን የግዥ ሒደት እንደሚያቀላጥፍ የሚጠበቅ ሲሆን፣ ለቁጥጥር እንዲመችና በመንግሥት ግዥ ሒደትም መንግሥታዊና የግሉ ዘርፍ ተዋናዮች ከሰው ንክኪ ውጭ በሆነ መንገድ በግልጽ እንዲወዳደሩ እንደሚያስችል ይጠበቃል፡፡