Thursday, May 23, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

የተመረጡ ፅሑፎች

የጉድ ቀን የማይመሽባት ኢትዮጵያ

ኢትዮጵያ በሙስና ተጨማልቃለች፣ የሚቦጠቡጧት ሌቦችም በዝተዋል መባሉ ትክክል ቢሆንም፣ በዚህ ሳቢያ የደረሰው የጉዳት ልክ መለካትና በተገቢው ደረጃ ማወቅ እንደሚቸግር ይታያል፡፡  ምክንያቱ ደግሞ መረጃና ማስረጃ ተከርቸም በሆነበትና አይነኬ ሆኖ በተኖረበት አገር ውስጥ ገደል አፋፍ ላይ ስለምትገኘው አገርና ሕዝቦቿ ትክክለኛ ጉዳት ለማመላከት ከባድ ይሆናል፡፡

ተሸፋፍኖ ከኖረው የውርደት ዶሴ ውስጥ ጥቂት ገጾችን መመልከት በመቻሉ ኢትዮጵያ ወዴት ስታመራ እንደነበር ለመታዘብ አብቅቶናል፡፡ የአገር ጉዳይና ጉዳቷ ቢያንስ ለጊዜው የሚቆረቁራቸው አካላት፣ ኢትዮጵያ ሲደርስባት የነበረውን ጉዳት ደፍረው ሲናገሩ ማስረጃ መዘውም ሲያስረዱ የችግሩን ጥልቀት ለመገንዘብ ዕድል አግኝተናል፡፡ የብረታ ብረትና ኢንጂነሪንግ ኮርፖሬሽን (ሜቴክ) ብቻ ስለመፈጸሙ የሰማነው ጉድ ሊታሰብ የማይችል ነበር፡፡ ሕገወጥነት ምን ያህል ነግሶብን እንደቆየን አሳይቶናል፡፡ በሜቴክና በሌሎች ተቋማት ሲፈጸም የቆየው ውንብድና በያዘው መንገድ ቢጓዝ ኑሮ፣ ኢትዮጵያ ከገደሉ በታች መከስከሷ እንደማይቀር መገመት አይቸግርም፡፡

ከምሥረታው ጀምሮ ይዞት የተነሳው ዓላማ ጥያቄ ሲያስነሳበት ቢቆይም፣ ለሚቀርቡበት ጥያቄዎች ሜቴክና አመራሮቹ ይሰጡ የነበረው ምላሽ ይጠጌ አይነኬ ዓይነት እንደነበር የሚያስረዳን፣ ሜቴክ ከተረከባቸው ሥራዎች ውስጥ አንድም እዚህ ግባ የሚባል ውጤት አለመገኘቱን ነው፡፡ ምናልባት አውቶቡስ መገጣጠም ከነመንቀራፈፉና ብዙ ወጪ ከማስወጣቱ ባሻገር ሊጠቀስለት የሚችለው ሥራው ሊሆን ይችላል፡፡ የጥራትና የብቃት ችግሮቹ አይጣል እንደሆኑ ግን ተገጣጥመው ሥራ ላይ የሚገኙት መኪኖች ዋቢ ናቸው፡፡ ብልሹ አሠራር አለባቸው የተባሉ ተቋማትን ማረቅ የነበረባቸው በሕግ ኃላፊነት የተጣለባቸው ተቋማትም ሆኑ የሥራ ኃላፊዎች ሜቴክን በመፍራት አለያም በግል ጥቅም በመደለል እንዳላዩ ሆነው ኖረዋል፡፡

በአንድ ወቅት ስለሜቴክ ጉዳይ የተጠየቁት የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ ሜቴክ በአንድ እጁ መሳሪያ የያዘ መሆኑን በመጥቅስ፣ በሜቴክ ጉዳይ ለተነሳው ጥያቄ የተድበሰበሰ ምላሽ መስጠታቸውን እናስታውሳለን፡፡ ከሰሞኑ በቀረበው ዘገባ የተመለከትናቸው የጉድ ተግባራት ይህች አገር በሕግና ሥርዓት የሚመራት አካል አልነበራትም ነበር ወይ? የሚለውን ጥያቄ ሁሉም ዜጋ ደጋግሞ እንዲጠይቅ አድርጓል፡፡ አገር ገደል አፋፍ ላይ ነበረች ለሚለውና ለዚህ አባባላቸው መረጃ የነበራቸው ወገኖች ሥጋታቸው ምን ያህል እውነትነት እንደነበረውም አሳይቷል፡፡ የተደረገው የመንግሥት አስተዳደር ለውጥ አገር ለማዳንና ከገደሉ አፋፍ ለማውጣት የተደረገ ትንቅንቅ ስለመሆኑ እንድንገነዘብ ያደርጋል፡፡

 ለማመን የከበደውን ሁሉ በአንድ ተቋም ብቻ ሲፈጸም ከቆየ፣ ከዳር ስንሰማቸው የቆዩ ሌሎችም ሙሰኛ ተቋማትና ኃላፊዎቻቸውም ጉድ ሊያሰኙን እንደሚችሉ አይጠረጠርም፡፡ ሜቴክ እንዳሻው ሲገዛና ሲሸጥ፣ እንዳሻው ሲመነዝርና ሲበትን በነበራቸው ስምንት ዓመታት ውስጥ ኢትዮጵያ ግን በውጭ ምንዛሪ እጥረት ስታክ ቆይታለች፡፡ አሁንም ከችጋሯ አልወጣችም፡፡ ሜቴክ ሲያንቀሳቅስ ከነበረው ገንዘብ ብዛት አንፃር የውጭ ምንዛሪ የሚገኘው ከድርጅቱ ተርፎ እንደው እንደ ፀበል እንዲዳረስ ይሰጥ ነበር እንጂ፣ ያውም በስንትና ስምት ወረፋና ጉቦ እንድንል ያደርጋል፡፡ ስለዚህ ለአገሪቱ የውጭ ምንዛሪ እጥረትና ብክነት እንደ ሜቴክ ያሉ ገንዘብ፣ ሥልጣንና ጠመንጃ የያዙ ተቋማት በዚህች አገር ነፃ የገበያ ውድድር ላይ ምን ያህል ተፅዕኖ እንደነበራቸውና እንዳላቸው እንድንረዳው ያደርጋል፡፡

እንደ ሜቴክ ሁሉ በየፓርቲው ጥላ ሥር የተሰገሰጉ ድርጅቶችም መታየት አለባቸው፡፡ አሠራራቸው፣ ወጪ ገቢያቸው፣ ማንነትና ምንነታቸው፣ በውጭ አገሮች ያንሰራፏቸው ቢሮችና የሚያንሳቅሱት ሀብትና ንብረት ተቆጥሮና ተዘርዝሮ ሊነገር ይገባል፡፡

የኮንትሮባንድ ዕቃ በወታደራዊ አጀብ ተሰልፎ መሐል መርካቶ ሲራገፍ ከነበረ፣  የአገር ሕግና የሕዝብ መብት ተጥሶ የገበያ ሕግም እጁን ለጉልበተኞች ሰጥቶ ነበር ማለት ነው፡፡ ይህም ነጋ ጠባ ለሸቀጦች ዋጋ መውጣትና መውረድ አንዱ ምክንያት የት ነበር ማለት ነው፡፡ እንዲህ ያለውን ነገር የተመለከተ ሌላው ነጋዴው በምን ሞራል ሕጋዊ ሥራ ይሠራል ተብሎ ይጠበቃል? ስለዚህ ሥነ ምግባር ያለው የንግድ ኅብረተሰብ ማብዛት አልቻልንም እየተባለና መፍትሔ ለማግኘት ሳይቻል የቀረበት ምክንያት እምነት የተጣባቸው የአገር ተቋማት ኮንትሮባንድ ንግድ ውስጥ በመግባታቸው ጭምር ነው ልንል የምንችልበት ደረጃ ላይ ያደርሰናል፡፡ የኮንትሮባንድ ንግድ ያውም በመንግሥት ተሽከርካሪና በሕዝብ ገንዘብ ደመወዝ በማካፈላቸው ተቀጣሪዎች ሲፈጸም ነበር፡፡ ከሕገወጥ ተግባራት የኢሰብዓዊ ድርጊቶች ምንጭም መሆናቸው የማይቀር በመሆኑ  ሰለባ ሊሆኑ እንደሚችሉም መገመት አያስቸግርም፡፡

ለማንኛውም በዚህን ያህል ደረጃ አገር ትመዘበራለች በገዛ ልጆችዋ ትበደላለች ተብሎ ባይታሰብም፣ ከሰሞኑ የተመለከትነው አፍ የሚያስጭን ‹‹ትዕይንት›› ግን ለቀደመው ጥቂት ብቻ ሳይሆን ከዚህም በኩል ላለው ትምህርት መሆን አለበት፡፡

ስለዚህ ከሰሞኑ በጨረፍታም ቢሆን የተመለከትነው ብክነት ፈጻሚዎች ተጠርጣሪዎች እየተያዙ ነው፡፡ በሕግም ፊት እየቀረቡ ነው፡፡ ይህ የሕግ የበላይነትን ለማረጋገጥ ዘገየ እየተባለ ለተወተወተ መንግሥት ቃል የገባውን ምላሽ የሰጠበት ነው፡፡

የሕግ የበላይነትን ከማስፈን ጎን ለጎን ለጥይትና ለክብሪት የሚዘረጉ እጆች እንዲሰበሰቡ እንዲሁም አሁንም ብዙ ወጪ የደረሰባቸውን የአገር ሀብቶች መልሶ ጥቅም ላይ ለማዋል የሚቻልበትን መንገድ ማመቻቸት ግድ ይላል፡፡

ስለዚህ አገር እንዲህ ያውን ጥፋት ደግማ እንዳታስተናግድ ሁሉም እኔን ያየህ ተቀጣ  መባል አለበት፡፡ ከዚህ በኋላ ጠመንጃና ንግድ መለየት አለባቸው፡፡ ሥልጣንና ቢዝነስ የተለያዩ መሆናቸውን ጠንቅቀው ማወቅ ያለባቸው የመንግሥት አመራሮች ታች ድረስ ሊኖሩን ይገባል፡፡ በነፃ ገበያ ሥርዓት ነፃ የሆነ ውድድር ያሻልና የተሻለ አገር ለመፍጠር ከተፈለገ በውድድር የሚያምን በሥራው የሚተማመን የንግድ ኅብረተሰብ መፍጠር ያስፈልጋል፡፡ በአቋራጭ በመበልፀግ ከዚህ በኋላ እንደማይሠራ ሊያረጋግጥ የሚችል ሥርት ሊኖረን ይገባል፡፡ አጥፊዎችን ለሕግ ማቅረብ ብቻ ሳይሆን ሕገወጥ ተግባራትን እንዳይደግሙ ለማድረግ ጨዋ አመራር ይጠይቃል፡፡ ከዚህም እንደተመለከትነው ለመነቋቆር ሳይሆን ስለአገር አስበው የሚናገሩ ጠንካራ ኢትዮጵያዊያን ማብዛትንም ይጠይቃል፡፡

ከአገሪቱ ከነበረችበት ጥልቅ ችግር አንፃር አሉ የተባሉ ችግሮችን ለማከም አሁንም ጊዜ መስጠትና በቂ መረጃ መሰብሰብን ይጠቀይቃልና ኅብረተሰቡም ይህንን መገንዘብ ይኖርበታል፡፡ በዚህ ፍጥነት ወይም በአቋራጭ ለመበልፀግ መሞከር ሥር እየሰደደ መሄድ አገር መጉዳት መሆኑን በማመን መሰብሰብ ያስፈልጋል፡፡ ለዚህም ጨዋና ለአገር የሚቆረቆር ዜጋ በሁሉም ማኅበረሰብ ለማፍራት እንዲችል ይህ መልካም አጋጣሚ ነው፡፡

ከሁሉም በላይ ግን አገርን ወደ ጥፋት ሊወስዱ የነበሩ አሠራሮችን እንዳይደገሙ ማድረግ ትልቅ የቤት ሥራ ነው፡፡ ከዚሁ ጎን ለጎንም አሁን በሕግ እጅ የሚገኙ ተጠርጣሪዎችን በአግባቡ በመያዝና ሕጋዊ ሒደቱም እንደቀድሞ ያለመሆን ሊያሳይ በሚችል መልኩ እንዲፈጸም ማድረግ ትልቅ ዋጋ አለው፡፡

Latest Posts

- Advertisement -

ወቅታዊ ፅሑፎች

ትኩስ ዜናዎች ለማግኘት