‹‹አገር ተዘርፋ፣ ወገንም ተሰቃይቶ ከማለቁ በፊት ለውጥ እንዲመጣ ታግሎ አሁን ለደረስንበት የተስፋ ዘመን አድርሶናል፡፡ ስለዚህም መንግሥት የሕዝብን ጥያቄ መመለስ ውዴታው ብቻ ሳይሆን ግዴታውም ነው፡፡ ፍትሕ የተበደለን ሕዝብ የመካሻ አንዱ መንገድ ነውና፡፡››
ይኼንን ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) በወቅታዊ ጉዳዮች ላይ ሐሙስ ኅዳር 6 ቀን 2011 ዓ.ም. አመሻሽ ላይ ባሠራጩት ጋዜጣዊ መግለጫ ነው።
የጠቅላይ ሚኒስትሩ መግለጫ ሰሞኑን የፌዴራል ጠቅላይ ዓቃቤ ሕግና የፌዴራል ፖሊስ ከፍተኛ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች በዜጎች ላይ ፈጽመዋል በተባሉ የመንግሥት የፀጥታ መዋቅር አመራሮችን፣ እንዲሁም ግዙፍ የዝርፊያ ወንጀሎችን በመፈጸም ጉዳት አድርሰዋል ተብለው የተጠረጠሩ ከፍተኛ አመራሮችን በቁጥጥር ሥር ማዋል መጀመራቸውን ተከትሎ የወጣ ነው።
የፌዴራል ጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ አቶ ብርሀኑ ፀጋዬ ባለፈው ሳምንት በሰጡት መግለጫ፣ እየተከናወነ ያለውን የሕግ ማስከበር ሥራ አብራርተዋል።
በዚህም መሠረት በቁጥጥር ሥር እየዋሉ የሚገኙት ተጠርጣሪዎች በዜጎች ላይ ከፍተኛ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች የፈጸሙ የመንግሥት ፀጥታ መዋቅር አመራሮችና በአገሪቱ በተለያዩ አካባቢዎች የተከሰቱ ብጥብጦችን ያስተባበሩ፣ እንዲሁም የተሰጣቸውን የመንግሥት ኃላፊነት ወደ ጎን በመተው የሕዝብና የመንግሥት ሀብት የዘረፉ፣ ሀብት ያሸሹና ያባከኑ እንደሆነ ተገልጿል፡፡ ዓርብ ኅዳር 7 ቀን 2011 ዓ.ም. በተካሄደው የሕግ ማስከበር ተግባር በአጠቃላይ 126 ተጠርጣሪዎች በቁጥጥር ሥር ውለዋል፡፡ በቁጥጥር ሥር ከዋሉት ተጠርጣሪዎቹ መካከል 63 በሽብር ድርጊት፣ 27 በሙስና፣ 36 ደግሞ በሰብዓዊ መብት ጥሰቶች ናቸው።
በሰብዓዊ መብት ጥሰቶች የተጠረጠሩት ግለሰቦች ፈጽመዋቸዋል ከተባሉት መካከል ግለሰቦችን ከፖለቲካ ፓርቲ አባልነት ራሳቸውን እንዲያገሉ ማድረግና ማሰቃየት፣ በአምቡላንስ እያፈኑ ሰዎችን መሰወር፣ ሕገወጥ መሣሪያዎችን የራሴ ነው ብሎ እንዲፈርሙ ማድረግ፣ የብልት ቆዳዎችን በፒንሳ መሳብ፣ ጫካ ማሳደር፣ ከአውሬ ጋር ማሰር፣ አፍንጫ ውስጥ እስክርቢቶ መክተት፣ ግብረ ሰዶማዊ ጥቃት መፈጸም፣ ሴቶችን መድፈርና የመሳሰሉት ተጠቅሰዋል።
በከፍተኛ የዝርፊያ ወንጀል ተጠርጥረው የተያዙት የብረታ ብረትና ኢንጂነሪንግ ኮርፖሬሽን (ሜቴክ) አመራሮች ሲሆኑ፣ የተጠረጠሩትም የውጭ አገር ግዥዎችን ያለጨረታ በማከናወን በመንግሥት ላይ ከፍተኛ የኢኮኖሚ ጉዳት ማድረስ ይገኝበታል። ከመደበኛው ዋጋ እስከ 400 በመቶ ዋጋ እየተጨመረ ግዥ ይፈጸም እንደነበር፣ ግዥ አፈጻጸሙ ከኮርፖሬሽኑ የበላይ አመራሮች ጋር የጥቅም ትስስርና የሥጋ ዝምድና ባላቸው ደላሎች መሆኑን፣ እነዚህ በድለላ የተሰማሩ ሰዎች በአገር ውስጥ ካካበቱት ሀብት በላይ ወደ ውጭ ሀብት ማሸሻቸው ተገልጿል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ የተጀመረውን የፍትሕና የሕግ ማስከበር እንቅስቃሴ አስመልክቶ ባወጡት መግለጫ የሚከተለውን ብለዋል።
‹‹አገራችን የቤትና የእንጀራ ልጅ ሊኖራት አይገባም፡፡ ቢሊዮኖችን መዝብሮ በነፃነት የሚኖርና አንድ ብር አጥቶ ከቆሻሻ ገንዳ ውስጥ ምግብ የሚፈልግ ሁለት ዓይነት ዜጋ ሊኖራት አይገባም፡፡ የውጭ ጠላት እንኳን የማይፈጽማቸውን አሰቃቂ ሰይጣናዊ መከራዎች በሕግ ማስፈጸም ስም በዜጎች ላይ አድርሰው የሰላም እንቅልፍ ተኝተው የሚያድሩ ወንጀለኞችና የመከራ ዶፍ የወረደባቸው፣ አካልና ህሊናቸው የተጎዳ፣ ተሸማቀው የሚኖሩ ሁለት ዓይነት ዜጎች ሊኖሯት አይገባም፤›› ብለዋል፡፡
የተጀመረው ፍትሕ የማስፈንና ሕግ የማስከበር እንቅስቃሴ ዋና ዓላማም አጥፊዎችን መቅጣትና ድርጊቱን መኮነን ብቻ ሳይሆን፣ ዳግም እንዳይመጣ አስተሳስቡን ማረም ጭምር እንደሆነ አስረድተዋል፡፡
ወቅታዊ አገራዊ ጉዳይን በተመለከተ የኢሕአዴግ ምክር ቤት ጽሕፈት ቤት ባወጣው መግለጫ፣ የአገሪቱን ሕዝቦች ለቅሬታና ለምሬት የዳረጉ ጥፋቶች በኢሕአዴግ የአመራር ዘመን የተፈጸሙ መሆናቸውን አበክሮ እንደሚገነዘብ አትቷል።
በማከልም፣ ‹‹አሁን ከደረስንበት ለውጥ በመነሳት የሕዝባችን ቅሬታ በዚህ መልኩ ምላሽ ሳያገኝ እንዲቆይ ማድረግ የሚቻልበት አንዳችም መንገድ እንደሌለ የተረዳው ድርጅታችን፣ ለሕዝቡ በገባው ቃል መሠረት ሥር ነቀል የአመራርና የአሠራር ለውጥና ማሻሻያዎች አድርጓል። የለውጥ ጊዜው አጭር ቢሆንም፣ በስፋቱና በጥልቀቱ ግን በአገራችን ታሪክ ጉልህ ሥፍራ የሚሰጠው ነው። አሁንም የተጀመረውን አገራዊ ለውጥ ዘላቂነት ከማረጋገጥ ጎን ለውጡ ተቋማዊ እንዲሆን ማድረግ የቅድሚያ ትኩረት ተሰጥቶት በድርጅታችን እየተፈጸመ ያለ ተግባር ነው፤›› ሲል ገልጿል።
እየተከናወነ ከሚገኘው ፍትሕ የማስፈንና ሕግ የማስከበር እንቅስቃሴ ጎን ለጎን የዴሞክራሲ ተቋማትን ለማጠናከርና ሕጎችን ለማሻሻል ገለልተኛና ስመጥር ባለሙያዎችን የያዘ ብሔራዊ ምክር ቤት በጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ ሥር ተደራጅቶ በጥናት ላይ የተመሠረተ የሕግ ማሻሻያዎችን የማርቀቅ ሥራ በመከናወን ላይ መሆኑን፣ ጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ ብርሃኑ ተናግረዋል።
የፀረ ሽብርተኝነት አዋጁን የመከለስ፣ የሲቪክ ማኅበራት፣ የብሔራዊ ምርጫ ቦርድ፣ የሚዲያና የመሳሰሉት ሕጎች እንዲሻሻሉ ከሚደረጉት መካከል የሚገኙ መሆናቸውንም አስረድተዋል።
የሚኒስትሮች ምክር ቤት ሐሙስ ኅዳር 6 ቀን 2011 ዓ.ም. ባካሄደው ስብሰባው የብሔራዊ ዕርቀ ሰላም ኮሚሽን እንዲቋቋም በመወሰን የተረቀቀውን ማቋቋሚያ አዋጅ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የላከ መሆኑን፣ በተመሳሳይ የማንነትና የወሰን ጉዳዮች ኮሚሽን እንዲቋቋም በመወሰን የማቋቋሚያ ረቂቅ ሕጉን ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እንደላከ አስታውቋል፡፡
የብሔራዊ ዕርቀ ሰላም ኮሚሽን በኢትዮጵያ ለበርካታ ዓመታት በተለያዩ ማኅበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ግጭቶች ምክንያት በሕዝቡ ውስጥ የተደራረቡ የቁርሾ ስሜቶችን ለማከም፣ እውነትና ፍትሕ ላይ መሠረት ያደረገ ዕርቅ ለማውረድ ጉልህ አስተዋፅኦ እንደሚኖረው ተጠቁሟል፡፡
የማንነትና የወሰን ጉዳዮች ኮሚሽን ደግሞ በክልሎች የአስተዳደር ወሰንና በማንነት ጥያቄዎች ላይ በተደጋጋሚ የሚታዩ ችግሮችን አገር አቀፍ በሆነና በማያዳግም ሁኔታ መፍታት፣ ብሎም ከወሰን ጋር ተያይዞ የሚነሱ ውዝግቦች በብሔር ብሔረሰቦች መካከል የቅራኔ ምንጭ መሆናቸውን በመገንዘብ ለሚነሱ ግጭቶችና ላለመረጋጋት መንስዔ ለሚሆኑ ለችግሮቹ ገለልተኛ በሆነ፣ ሙያዊ ብቃት ባለውና ሰላማዊ በሆነ መንገድ መፍትሔ የሚያፈላልግ እንደሚሆን ተገልጿል።
ከላይ የተገለጹት ሰሞነኛ ሁነቶች በአጠቃላይ በዓለም አቀፍ ደረጃ፣ እንዲሁም በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የሰብዓዊ ኮሚሽን ዕውቅና ያገኘውንና ከፖለቲካ ቀውስ ወጥተው በፖለቲካ ሽግግር ውስጥ የሚገኙ መንግሥታት የሚተገብሩትን የሽግግር ወቅት ፍትሕ (Transitional Justice) ጽንሰ ሐሳብ መገለጫ ባህሪያት ባመዛኙ የሚወክሉ ናቸው ይገባል፡፡
የሽግግር ወቅት ፍትሕና የሰሞኑ ኢሕአዴግ መንግሥት ተግባራት
የሽግግር ወቅት ፍትሕ (Transitional Justice) በአስቸጋሪ የፖለቲካ ቀውስ ውስጥ ያለፉ ሕዝቦች በፖለቲካ ቀውሱ ምክንያት ከደረሰባቸው በደል እንዲያገግሙ፣ በሕዝቦች መካከል ሰላምና ዕርቅን ለማውረድ፣ እንዲሁም ኢሰብዓዊ ድርጊት የተፈጸመባቸው ፍትሕ እንዲያገኙ በማድረግ በደላቸውን በመካስ ሥነ ልቦናዊ ፈውስ እንዲያገኙ ነው፡፡ በዚህም መሠረት በዕርቅ ማኅበራዊ መስተጋብራቸውን እንዲቀጥሉ የፖለቲካ ሽግግሩን የሚመሩ መንግሥታት ተግባራዊ የሚያደርጉት ከቅርብ ዓመታት ወዲህ በዓለማችን የተለመደ፣ ፖለቲካዊና ሕጋዊ መፍትሔዎችን አነባብሮ የያዘ የማኅበራዊ ፍትሕ መሣሪያ ነው።
መቀመጫውን በኒውዮርክ አሜሪካ ያደረገው ኢንተርናሽናል ሴንተር ፎር ትራንዚሽናል ጀስቲስ (International Center for Transitional Justice) የተሰኘ ተቋም እንደሚገልጸው፣ ይህ የሽግግር ወቅት ፍትሕ በቀደመው የፖለቲካ ሥርዓት የሰብዓዊ ጥቃት ይደርስባቸው የነበሩ ማኅበረሰቦች እንዲካሱና ሥነ ልቦናዊ እረፍት እንዲያገኙ፣ የደረሰባቸው በደል ተገላልጦ እውነቱ እንዲወጣ በማድረግ ላይ የተመሠረተ ፈውስን የሚሰጥና በተገቢው ሕጋዊ ሥርዓትም ፍትሕ እንዲያገኙ የሚያስችል መሆኑን ይገልጻል።
በሕግ አግባብ ከሚሰጥ ፍትሕ በተጨማሪ ያለፈው እንዳይደገምና የሕግ የበላይነት እንዲሰፍን ተቋማትን መልሶ ማደራጀት፣ በሕዝቦች መካከል ማኅበረሰባዊ ዕርቅና መግባባትን ማውረድ እንደሚጠይቅ ያስረዳል።
ይኼንን ጉዳይ በመንተራስ የኢትዮጵያን ወቅታዊ ሁኔታ በተመለከተ ሪፖርተር ያነጋገራቸው ሁለተኛ ዲግሪያቸውን በሰብዓዊ መብት ጉዳዮች ላይ ስዊድን ከሚገኝ ዩኒቨርሲቲ ያገኙ አንድ ባለሙያ፣ በኢትዮጵያ ከሰሞኑ እየተወሰዱ የሚገኙ ዕርምጃዎች እነዚህን መገለጫ ባህሪያት በተወሰነ ደረጃ እንደሚወክሉ ይገልጻሉ።
መንግሥት ሰሞኑን እያከወናቸው ከሚገኙ ተግባራት ለአብነትም ኢሰብዓዊ ጥሰቶች የፈጸሙ በቁጥጥር ሥር ውለው በሕግ እንዲጠየቁ፣ የዴሞክራሲ ተቋማት እንዲጠናከሩ የተጀመሩ የሕግ ማሻሻያዎችና ብሔራዊ ዕርቀ ሰላም ኮሚሽን እንዲቋቋም መወሰኑ የሽግግር ወቅት ፍትሕ መገለጫ ባህርያትን እንደሚያሟሉ አስረድተዋል።
የሽግግር ወቅት ፍትሕ መገለጫ ባህርያት በማኅበረሰቦች ላይ የደረሱ ማኅበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ በደሎች የሚታረሙበት መሆኑን የገለጹት ባለሙያው፣ በማኅበረሰቦች ላይ የደረሰውን በደል በመደበኛ የሕግ ሥነ ሥርዓት በመጠየቅ መካስ ስለማይቻል በመፍትሔነት የመጣ አዲስ አማራጭ መሆኑን ያስረዳሉ።
ይህ ማለት ግን በተለይ ከፍተኛ የሰብዓዊ ጥሰት የደረሰባቸው በሕግ እንዲካሱ፣ እንዲሁም የደረሰባቸው በደል ሙሉ እውነት ግልጥልጥ ብሎ እንዲገለጽ ማድረግን የሚያካትትና በይፋም ይቅርታ የሚጠየቁበት መሆኑን አስረድተዋል፡፡
ይኼንን ሥርዓት ለመፈጸም አንዳንድ አገሮች የሽግግር ወቅት ፍትሕ ትግበራ ሥርዓት መጀመራቸውን በይፋ እንደሚገልጹ፣ ከዚህ አኳያም በአፍሪካ ለአብነት ደቡብ አፍሪካና ሩዋንዳ ተጠቃሽ እንደሆኑ ገልጸዋል።
ይህ ማለት ግን መንግሥታት የሽግግር ወቅት ፍትሕ ትግበራን በይፋ ሳይገልጹ አያካሂዱም ማለት እንዳልሆነ ያስረዳሉ።
በኢትዮጵያ በአሁኑ ወቅት እየተካሄዱ የሚገኙ ተግባራት የሽግግር ወቅት ፍትሕ ባህሪያት በተወሰነ ደረጃ እንደሚስተዋልባቸው የሚገልጹት እኚሁ ባለሙያ፣ በተለይ ብሔራዊ የዕርቀ ሰላም ኮሚሽን መቋቋሙ ዋነኛ ማሳያ መሆኑን ጠቁመዋል።
የድንበር ወይም የአስተዳደር ወሰን ኮሚሽን እንዲቋቋም መወሰኑ ከሚስተዋሉ ግጭቶች አኳያ ተገቢ ቢሆንም፣ ከሽግግር ወቅት ፍትሕ ትግበራ አንፃር ለመመዘን አስቸጋሪ እንደሆነ ያስረዳሉ፡፡ ምክንያቱ ደግሞ የኮሚሽኑ ሕጋዊ ሥልጣን የማይታወቅ መሆኑና ጉዳዩ ሕገ መንግሥታዊ የብሔር ብሔረሰቦች መብት ከመሆኑ አንፃር፣ መሠረታዊ መፍትሔ እስካላገኘ ድረስ ኮሚሽን በማቋቋም ብቻ የሚፈታ እንዳልሆነ ያብራራሉ፡፡
በሌላ በኩል የሽግግር ወቅት ፍትሕን ለማሟላት የተፈጸሙ በደሎች በግልጽ ተዘርዝሮ የበዳዩ ማንነትና ተበዳዮች ተጠቅሰው መገለጽ እንደሚገባ ያስረዳሉ።
ከዚህ አኳያ በተለይ ኢኮኖሚያዊ በደል ፈጽመዋል በሚል የሚወሰደው ዕርምጃ ተገቢነቱ ባያጠያይቅም፣ ከሽግግር ወቅት ፍትሕ አንፃር ግን በደሉ የደረሰው ማን ላይ እንደሆነ፣ እነ ማንስ አደረሱት የሚለው በዝርዝር እስካልተገለጸ ድረስ ሚዛኑን እንደማይጠብቅ ይገልጻሉ።
ይህም ሆኖ በፖለቲካ ልዩነት ምክንያት በግለሰብና በቡድኖች ላይ የሕግ ተጠያቂነት እየተፈጸመ እንደሆነ መረጃዎችን የሚያሠራጩ ሊኖሩ ስለሚችሉ፣ የሽግግር ወቅት ፍትሕ በሚገባ ተብራርቶ ሥራ ላይ መዋል ይኖርበታል ሲሉም ያሳስባሉ፡፡