Sunday, March 26, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ዜናበሥራ ላይ የሚገኙ አብዛኞቹ ዳኞች በገዛ ፈቃዳቸው የሚለቁበት ሥርዓት እንዲዘጋጅላቸው ተጠየቀ

በሥራ ላይ የሚገኙ አብዛኞቹ ዳኞች በገዛ ፈቃዳቸው የሚለቁበት ሥርዓት እንዲዘጋጅላቸው ተጠየቀ

ቀን:

የሕግ ባለሙያዎችና ጠበቆች በፍትሕ ሥርዓቱ ዙሪያ ከጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዚዳንት ወ/ሮ መዓዛ አሸናፊና ምክትል ፕሬዚዳንቱ አቶ ሰለሞን አረዳ ጋር ቅዳሜ ኅዳር 8 ቀን 2011 ዓ.ም. ለአንድ ቀን ባደረጉት ውይይት፣ በሥራ ላይ የሚገኙት አብዛኛዎቹ ዳኞች ሥራቸውን በራሳቸው ፈቃድ ወይም የመልቀቂያ ሥርዓት እንዲዘጋጅላቸው ጠየቁ፡፡

የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዚዳንትና ምክትል ፕሬዚዳንት ከተሾሙ ወዲህ፣ የተለያዩ የፍትሕ ተቋማትን በመጎብኝትና የፍትሕ አጋሮችን በማነጋገር ተጠምደዋል፡፡ ባለፉት 20 ቀናት ከዳኞች፣ ከሕገ መንግሥት አጣሪ ጉባዔ አባላትና ከጠበቆች ጋር የግማሽና የአንድ ቀን ውይይት አድርገዋል፡፡ ከተቋማትም የፌዴራል ማረሚያ ቤትንና የፌዴራልና የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን እስር ቤቶችንና የተለያዩ በወንጀል የተጠረጠሩ ዜጎችን ጎብኝተዋል፣ አነጋግረዋል፡፡

ባለፈው ቅዳሜ ‹‹የዳኝነት አካሉ ያጣውን የሕዝብ አመኔታ ለመመለስ ከጠበቆችና ከሕግ ባለሙያዎች ጋር የሚደረግ ምክክር›› በሚል መነሻ ሐሳብ የሙሉቀን ውይይት በጠቅላይ ፍርድ ቤት መሰብሰቢያ አዳራሽ አድርገዋል፡፡ በውይይቱ ላይ በርካታ ጠበቆችና የሕግ ባለሙያዎች የተገኙ ቢሆንም፣ አብዛኛው የውይይታቸው አጀንዳ በፍርድ ቤቶች ነፃነትና በዳኞች ገለልተኛነት ላይ ያተኮረ ነበር፡፡

ባለፉት በርካታ ዓመታት በፌዴራል ፍርድ ቤቶች ላይ ተመድበው የሚሠሩ ዳኞች፣ ለአስፈጻሚው አካል የተንበረከኩና የዳኝነት ክብራቸውንም ያጡ መሆናቸቸውን ተናግረዋል፡፡ አብዛኞዎቹ ዳኞች በሥነ ልቦና ችግር ላይ መሆናቸውን ጠበቆቹ ጠቁመው፣ ሲሠሩ የከረሙት ወይም አሁንም እየሠሩ ያሉት በሕግ ሳይሆን የአስፈጻሚውን ትዕዛዝ መሠረት አድርገው እንደነበር አስረድተዋል፡፡

ምንም እንኳን በዳኝነት ሁሉንም ማስደሰት ባይቻልም ‹‹ነጩን›› ነገር ‹‹ጥቁር›› ማድረግ ማንንም እንደማያሳምን ጠቁመው፣ ወደ ኋላ ያሉ ፍርዶችና ውሳኔዎችን መመልከት በቂ ምስክር እንደሚሆኑ አስረድተዋል፡፡ በተለይ ሰበር ሰሚ ችሎት በእንደዚህ ዓይነት ውሳኔ ቁጥር አንድ መሆኑን የጠቆሙት የሕግ ባለሙያና ጠበቆቹ፣ አሥር ፍርድ ቤቶች የተወሰኑ ውሳኔዎች በይግባኝ ወደ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሲመጡ፣ ከውሳኔው ጋር ተቀይረው በመቅረብ ነጩን ነገር ጥቁር በማስባል ያልሠሩት ድርጊት እንደሌለ ተናግረዋል፡፡ በዚህ ሥርዓት ውስጥ የነበሩ ዳኞችን ይዞ የትም መድረስ ስለማይቻል፣ ቢቻል የሥራ አስፈጻሚ ሹማምንት እንዳደረጉት በገዛ ፈቃዳቸው እንዲለቁ ወይም የሚለቁበት ሥርዓት እንዲዘጋጅላቸው ጠይቀዋል፡፡ ይኼንን ሁሉ ሲሉ ግን ሁሉንም ዳኞች የማያካትትና ሥነ ምግባርና ጥሩ ዕውቀት ያላቸው ዳኞች መኖራቸውንም መጠቆም ይገባል ብለዋል፡፡ የሕግ ባለሙያዎቹ አዲሱ አመራር ይኼንን ማድረግ ካልቻለ ግን የዳኞቹን ማንነት ለዳኞች አስተዳደር ጉባዔ በማሳወቅ፣ የፍትሕ ሥርዓቱን ለመታደግ ዝግጁ መሆናቸውንም ተናግረዋል፡፡

‹‹ኢትዮጵያና የኢትዮጵያ ሕዝብ በሕግ ሙያ ተገልግለው አያውቁም፤›› ያሉት የሕግ ጠበቃው አቶ ሞላ ዘገዬ፣ ጥንትም ትናንትናም ሆነ ዛሬ የሕግ ሙያተኛው በሴራ፣ በአመፅና በሽፍትነት ሥልጣን የሚይዙትን ፖለቲከኞች እያገለገለ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ እስካሁን ደረሱ የሚባሉት በደሎች፣ ጥፋቶችና ጉዳቶች የፖለቲከኞች ብቻ አለመሆናቸውን የገለጹት አቶ ሞላ ጎሬላዎች፣ ወታደሮችና ‹‹ከእግዚአብሔር ተልኬያለሁ›› የሚሉ ነገሥታቶችን ሁሉ ዕውቅና  ለመስጠት ሌት ተቀን ሲለፋ የኖረው የኢትዮጵያ የሕግ ባለሙያ መሆኑን አስረድተዋል፡፡ የሕግ ባለሙያው ሕግ የፍትሕ መሣሪያ ነው ብሎና አምኖ አምባገኖችን አላገለግልም በማለት ወስኖ የሕዝብን ጥቅም የሚጎዳ ነገር አላደርግም በማለት እስካልተነሳ ድረስ፣ ሹሞች ቢለዋወጡ ለውጥ ይመጣል ብለው እንደማያምኑ ተናግረዋል፡፡ ‹‹እውነት እንነጋገር ከተባለ የምፈራው እንጂ የማከብረው ዳኛ የለም፤›› ብለዋል፡፡ ይኼንን ሲሉ ግን ጥቂት የሚከበሩ ዳኞች መኖራቸውን በመመስከር ዕውቅና ሰጥተዋል፡፡

ሹመኞች ፍርድ ቤትና ፍትሕ መኖሩን የሚረዱት ራሳቸው ሲዋረዱና እነሱ ሲሠሩት የነበረው ግፍ በእነሱ ላይ ሲደርስባቸው እንጂ፣ ከዚያ በፊት ትዝ እንደማይላቸው የገለጹት አቶ ሞላ፣ ዕድሜ ልካቸውን ሲያደርጉት የኖሩት እነሱን ሲነካቸው እንደ አዲስ እንደሚጮሁ ገልጸዋል፡፡ አካልን ነፃ በማውጣት የሕግ ሒደት አንድ ሰው ተፈትቶ ቤተሰቡን ለመቀላቀል በሩ ላይ ሲደርስ አንገቱ ተይዞ እንደገና ሲታሰር ዝም ያሉ ሹመኞች (ዳኞች)፣ እነሱ ላይ ሲደርስ ግን መጮህ ብቻ ሳይሆን አንዳንዶቹማ መጽሐፍም እየጻፉ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡ ሕግ የፈላጭ ቆራጭ መሣሪያ ሆኖ በመክረሙ የኢትዮጵያ ሕዝብ ሹምና ዳኛ ይፈራል እንጂ እንደማያከብር አስረድተዋል፡፡

ወ/ሮ መዓዛ አሸናፊ የመጀመሪያዋ ሴት ፕሬዚዳንት ብቻ ሳይሆኑ የመጀመሪያዋ የኢትዮጵያ ፍርድ ቤትን ነፃ ያወጡ ‹‹የፍትሕ እናት›› ለመባል ጠንክረው በመሥራት፣ ፍትሕን ነፃ ማውጣት እንዳለባቸው አሳስበዋል፡፡ የዳኝነት አሿሿም ላይ ትኩረት አድርገው በመሥራት በሰው ነፍስ፣ መብት፣ ክብርና ነፃነት ላይ የሚወሰን ዳኛ፣ በፖለቲካና በዘመድ አዝማድ ወይም በብሔር ተዋፅኦ መሾም ስለሌለበት አሿሿሙ እንደገና ሊፈተሽ እንደሚገባው አቶ ሞላ አስረድተዋል፡፡ የዳኞቹ አስተዳደር ጉባዔ አባላት ስብጥርና ችሎታ መፈተሽ እንዳለበትም አክለዋል፡፡ ተደማጭና ተሰሚነት ያላቸው የተከበሩ ብቁ ሰዎች ሊገቡበት እንደሚገባም ጠቁመዋል፡፡

የመንግሥት ልዩ አስፈጻሚ የሆነው ዓቃቤ ሕግና ፍርድ ቤት ተጣምረው ‹‹የፍትሕ አካል›› ተብለው አብረው በአንድነት ሊሠሩ እንደማይገባ ሌሎች አስተያየት የሰጡ ጠበቆች ጠቁመው፣ ፍርድ ቤት ሕግ ተርጓሚ በመሆኑ ገለልተኛ ሆኖ ለብቻው መሥራት እንዳለበት አሳስበዋል፡፡ በፍርድ ቤት የዓቃቤ ሕግና የጠበቆች ክብር እኩል እንዳልሆነና መስተካከል እንዳለበትም ተናግረዋል፡፡ ግለሰቦች እስካልተፈረደባቸው ድረስ ተጠርጣሪ እንጂ ወንጀለኞች ባለመሆናቸው፣ ወደ ፍርድ ቤት ሲቀርቡ ዩኒፎርም መልበስ እንደሌለባቸውና ነፃ ሆነው መታሰብ እንዳለባቸውም አስረድተዋል፡፡

የዳኝነት ሥራ ከምንም በላይ ነፃነት እንደሚጠይቅ የጠቆሙት ጠበቆቹ፣ ነፃነት ደግሞ የዳኝነት ሥራና የህሊና ጉዳይ መሆኑን ገልጸዋል፡፡ ዳኞች ራሳቸውንም ሆነ ፍርድ ቤቱን ለማስከበር በዕውነት ላይ የተመሠረተና የተደገፈ ሥራ መሥራት እንዳለባቸው ተናግረዋል፡፡ በተለይ የፍትሕ ሳምንት በማለት በየዓመቱ የሚዘጋጅ ድግስ አሠራሩን ለማጠናከር የሚረዳ ቢመስልም፣ በፍትሕ ሥርዓቱ ላይ ግን ምንም ዓይነት ለውጥ እንደማያመጣና ይልቁንም ተፅዕኖ ከመፍጠር ባለፈ የፍትሕ ሥርዓቱን የሚያበላሽ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡ እንዲያውም ፍርድ ቤቱ ይዞት የነበረውን ነፃነትና ገለልተኝነት አሳልፎ የሚሰጥበት ዝግጅት እንደሆነም አክለዋል፡፡ ምክንያቱም ተጠርጣሪዎች በታሰሩባቸው ፖሊስ ጣቢያዎችና ማረሚያ ቤቶች ‹‹ተገረፍን፣ ተደበደብን፣ ተገደልን›› እና ሌሎችንም የሚደርሱባቸውን ኢሰብዓዊ ድርጊቶች ለፍርድ ቤቱ ሲያመለክቱ፣ ፍርድ ቤቱ ትዕዛዝ ለመስጠት አቅም ሲያጣ እንደነበር የቅርብ ቀን ትዝታ መሆኑን ጠበቆቹ ገልጸዋል፡፡

ፍርድ ቤቱ ሌሎች ተቋማትን ማለትም ፖሊስ ኮሚሽን፣ ማረሚያ ቤትና ዓቃቤ ሕግን የሰብዓዊ መብት አያያዝና ነፃነት ምን ማለት እንደሆነ ሥልጠና መስጠት ሲገባው፣ ‹‹የፍትሕ ሳምንት›› እያለ አብሮ ሆያ ሆዬ ውስጥ መግባቱ ተገቢና ከሕግ ውጪ መሆኑን አስረድተዋል፡፡

ፍርድ ቤት ምን ጊዜም ቢሆን የሚከበር ተቋም መሆን እንዳለበትና አስፈላጊ በመሆኑ፣ ጠንክሮ መሥራት እንዳለበት ጠበቆቹ ትኩረት ሰጥተው ተናግረዋል፡፡ ዳኞች ሲሾሙ በዋናነት ችሎታ፣ ብቃት፣ ባህሪና የሥር መሠረትን የሚያጠና ኮሚቴ ተቋቁሞ ማጥናትና በደንብ መተቸት ተገቢ መሆኑን ጠቁመው፣ የፖለቲካ ሹመት ተገቢ እንዳልሆነና አገርንም እንደሚያጠፋ ገልጸዋል፡፡ በፍትሕ ሥርዓቱ ውስጥ ተወቃሾች ዳኞች ብቻ ሳይሆኑ ራሳቸው ጠበቆችም መሆናቸውን ጠቁመው ጉቦ አቀባይ፣ ውሳኔ ሠርቶ የሚሰጥ፣ መዝገብ ይዞ ውስኪ ቤትና ጫት ቤት ጉዳዮችን የሚያስጨርስ ጠበቃም መኖሩን አስረድተዋል፡፡ የሕግ ባለሙያውና ደንበኞች ግብር ከፋይ በመሆናቸው ከዳኞች ጀምሮ የፍርድ ቤት ሠራተኞች ተገቢውን ክብር ሊሰጧቸው እንደሚገባ ጠቁመው፣ አንዳንድ ዳኞች የጥብቅና ሥራ ለቢዝነስ እንጂ የፍትሕ ሥርዓቱን የሚያግዝ አድርገው እንደማያዩትም ተናግረዋል፡፡

የፍትሕ ሥርዓቱን ለማስተካከል መጀመር ያለበት ከሕገ መንግሥቱ መሆን እንዳለበት የጠቆሙት ጠበቆቹ፣ ሕገ መንግሥቱ የተዋቀረው የፖለቲካ ሥርዓቱ በዘረጋው ሲስተም መሆኑን ተናግረዋል፡፡ በሕገ መንግሥቱ አጣሪ ጉባዔ ውስጥ የተመደቡ አባላት ስብጥርን መመልከት ቢቻል፣ ከቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ጊዜ ጀምሮ የቀረበላቸውን ሕግና አዋጆች ‹‹በጣም ጥሩ ሕጎች›› ሲሉ የኖሩና እንደ ሥርዓቱ አብረው የሚቀያየሩ፣ በጥብቅና ሥራ ላይ የተሰማሩና በአንድም ሆነ በሌላ በዳኛው ላይ ተፅዕኖ መፍጠር የሚችሉና ሌሎችም የተለያዩ ተልዕኮች ያላቸው በመሆኑ እንደገና ፈርሶ መዋቀር፣ አባላቱም ለአገርና ለሕዝብ በሀቅ የሚሠሩ መሆን እንዳለባቸው አስተያየት ሰጥተዋል፡፡

እስካሁን በጉባዔው በኩል ምንም የሚሠራ ፍትሕ እንደሌለና የጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዚዳንትና ምክትል ፕሬዚዳንት ሰብሳቢ ቢሆኑም፣ ለይስሙላ እንጂ የፖለቲካ ተፅዕኖው እንደማያሠራቸው የታወቀ መሆኑን ገልጸዋል፡፡ አብዛኛው ውሳኔም ሲወሰን የቆየው በፓርላማ የሕግና ፍትሕ ኮሚቴ ሊቀመንበር በኩል እንደነበር አክለዋል፡፡ ጠበቆቹ የተለያዩ ጥያቄዎችን በማቅረብ ውይይቶችን ያደረጉ ሲሆን፣ ተመሳሳይ ግንኙነት ቢያንስ በዓመት ሁለትና ሦስት ጊዜ እንዲደረግ ጠይቀዋል፡፡ ወ/ሮ መዓዛና ምክትላቸው አቶ ሰለሞን ውይይቱ ገንቢ እንደነበር ተናግረው አብረው እንደሚሠሩ ቃል በመግባት ውይይቱ ተጠናቋል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ለፋይናንስ ዘርፉ ብቃት ያለው የሰው ኃይል የማፍራት የቤት ሥራን የማቃለል ጅማሮ

የአገሪቱ የፋይናንስ ዘርፍ እያደገ ለመሆኑ ከሚቀርቡ ማስረጃዎች ውስጥ  የግል...

የምድር ባቡርን የሚያነቃቃው የመንግሥት ውሳኔ

በኢትዮጵያ ወደብ አልባነት ላይ የተደመረውን የሎጀስቲክስ ችግር ለመፍታት ግዙፍ...

የፓርላማ አባላት ስለሰላም ስምምነቱ አፈጻጸም ግልጽ መረጃ የለንም አሉ

‹‹ሕወሓትን ለፍረጃ አብቅተውት የነበሩ ጉዳዮች በአብዛኛው መልክ ይዘዋል›› ሬድዋን...