የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ለረዥም ጊዜ አጥረው የያዙትን ቦታ በመንጠቅ ካርታ ቢያመክንባቸውም፣ በተሰጣቸው ቀነ ገደብ የግንባታ ዕቃዎችን አንስተው መሬት ባላስረከቡ ድርጅቶች ላይ ሰኞ ኅዳር 10 ቀን 2011 ዓ.ም. ዕርምጃ መውሰድ ጀመረ፡፡
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የመሬት ልማትና ማኔጅመንት ቢሮ ባለፈው ሳምንት፣ ለመጨረሻ ጊዜ የአንድ ሳምንት ቀነ ገደብ አስቀምጦ ነበር፡፡
ነገር ግን ዕርምጃ ከተወሰደባቸው መካከል 14 ድርጅቶች በተሰጣቸው ጊዜ ውስጥ፣ የግንባታ ቁሳቁሳቸውንና ሌሎች ንብረታቸውን ባለማንሳታቸው ዕርምጃ ተወስዶባቸዋል፡፡
የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽንና የአዲስ አበባ ደንብ ማስከበር አገልግሎት በጋራ በመሆን ነው ዕርምጃ መውሰድ የጀመሩት፡፡
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ ጽሕፈት ቤት እንዳስታወቀው፣ አስተዳደሩ ሕግና ሥርዓትን የማስከበር ኃላፊነት አለበት፡፡ በዚህ መሠረት ግንባታ ባለማከናወናቸው ካርታ የመከነባቸው፣ ነገር ግን በወቅቱ ንብረታቸውን አንስተው ቦታቸውን ባላስረከቡ ድርጅቶች ላይ ዕርምጃ መውስድ መጀመሩን፣ የከንቲባ ጽሕፈት ቤት አስታውቋል፡፡
ምክትል ከንቲባ ታከለ ኡማ (ኢንጂነር) እንዳስታወቁት፣ የሕዝብ ሀብት የሆነውን መሬት በመሀል ከተማ አጥረው ለዘመናት ፆም ማሳደር ሌብነት ነው፡፡
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ካቢኔ መስከረም 12 ቀን 2011 ዓ.ም. ባካሄደው ስብሰባ የሚድሮክ ቦታዎችን ጨምሮ በግል፣ በመንግሥትና በዲፕሎማቲክ ተቋማት ለዓመታት ታጥረው የተቀመጡ 154 ቦታዎች የሊዝ ውል ተቋርጦ ወደ መሬት ባንክ እንዲገቡ መወሰኑ ይታወሳል፡፡
ነገር ግን ሚድሮክና የተወሰኑ ድርጅቶች የአስተዳደሩን ውሳኔ የተቃወሙ ቢሆንም፣ በወቅቱ ምክትል ከንቲባው በጥንቃቄ በተካሄደ ጥናት ውሳኔው መወሰኑን አስታውቀው ነበር፡፡
ዕርምጃ ከተወሰደባቸው 154 ኩባንያች እስካሁን 14 ያህሉ ባለማንሳታቸው ሕግ የማስከበር ዕርምጃ ተጀምሯል፡፡
ምክትል ከንቲባው እንዳሉት፣ ‹‹አንዳንዱ እንደ ከዚህ በፊቱ መስሎት የአጥር ቆርቆሮዬን አላነሳም ይላል፣ እኛ እናነሳለን፤›› ሲሉ አስተዳደሩ በጭራሽ እንደማይታገስ አስታውቀዋል፡፡