Wednesday, November 30, 2022
ሌሎች ዓምዶች
  - Advertisement -
  - Advertisement -
  ዜናየብሔራዊ መረጃና ደኅንነት መምርያ ኃላፊ በሰብዓዊ መብት ጥሰትና ሙስና ወንጀሎች ተጠርጥረው ቀረቡ

  የብሔራዊ መረጃና ደኅንነት መምርያ ኃላፊ በሰብዓዊ መብት ጥሰትና ሙስና ወንጀሎች ተጠርጥረው ቀረቡ

  ቀን:

  የሰኔ 16 ቀን 2010 ዓ.ም. የመስቀል አደባባይ የቦምብ ፍንዳታን በማስተባበር ተጠርጥረው ላለፉት አምስት ወራት በእስር ላይ የሚገኙት የብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎት የፀረ ሽብር ግብረ ኃይል መምርያ ኃላፊ፣ በሰብዓዊ መብት ጥሰትና የሙስና ወንጀሎች ተጠርጥረው ሰኞ ኅዳር 10 ቀን 2011 ዓ.ም. ፍርድ ቤት ቀረቡ፡፡

  የመምርያ ኃላፊው አቶ ተስፋዬ ኡርጌ ሲሆኑ፣ በተጠረጠሩበት አሰቃቂ የሰብዓዊ መብት ጥሰትና ከመንግሥት ከሚከፈላቸው ወርኃዊ ደመወዝ በላይ ከፍተኛ የሆነ ሀብት በማካበት ከፍተኛ የሙስና ወንጀል መጠርጠራቸውን ለፍርድ ቤት ያስረዳው፣ የፌዴራል ፖሊስ ወንጀል ምርመራ ቢሮ ምርመራ ቡድን ነው፡፡

  መርማሪ ቡድኑ ለፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ አስረኛ ወንጀል ችሎት እንዳስረዳው፣ የብሔራዊ መረጀና ደኅንነት ፀረ ሽብር ግብረ ኃይል መምርያ ኃላፊ ሆነው ሲሠሩ፣ ያልተሰጣቸውን ሰዎች የማሰርና የመፍታት ሥልጣን በራሳቸው እንደተሰጣቸው በማድረግ በርካታ ዜጎችን አስረዋል፣ አስገርፈዋል፣ ገርፈዋል፡፡ ዜጎችን በመመልመል ወደ ውጭ እንዲሄዱ (ወደ ኤርትራ ድንበር) በማድረግና ከድንበር ላይ አገር ከድተው ሊወጡ ሲሉ እንደተያዙ በማስመሰል፣ ከአምስት ወራት እስከ አንድ ዓመት በሚደርስ ጊዜ ውስጥ በስውር እስር ቤት እንዲታሰሩ ማድረጋቸውን መርማሪ ቡድኑ ገልጿል፡፡

  የታሰሩት ሰዎችን በመደብደብ፣ በማሰር፣ ቆሻሻ ገንዳ ሥር በማሰርና በጉንዳን እንዲበሉ ማድረጋቸውንም መርማሪዎቹ አስረድተዋል፡፡ ሰዎችን በወንጀል እንደተጠረጠሩ በማድረግ፣ በማሰርና በማስፈራራት ገንዘብ እየተቀበሉ የገቢ ምንጭ ማድረጋቸውንም መርማሪው አስረድተዋል፡፡

  በድብደባ ሕይወታቸው ያለፈ፣ አካላቸው የጎደለ፣ ለረዥም ጊዜ በጨለማ ቤት ውስጥ በመታሰራቸው ዓይናቸው ማየት የተሳነው በርካታ ዜጎች መኖራቸውንም፣ መርማሪ ቡድኑ በሰነድና በሰዎች ምስክርነት እንዳረጋገጠ አስረድቷል፡፡

  አቶ ተስፋዬ ከእነ አቶ ጎሃ አጽብሃ ጋር ተጠርጥረው መቅረባቸውን መርማሪ ቡድኑ አስረድቷል፡፡ በመሆኑም በአቶ ተስፋዬ ላይ ምርመራውን አለማጠናቀቁን ጠቁሞ፣ በተጠረጠሩበት ከፍተኛ የሆነ የሰብዓዊ መብት ጥሰትና ከባድ የሙስና ወንጀሎች ተጨማሪ ምርመራ ለማድረግ 14 ቀናት እንዲፈቀድለት ጠይቋል፡፡

  አቶ ተስፋዬ በበኩላቸው ለችሎቱ መርማሪ ቡድኑ የሚለው ሁሉ ለእሳቸው አዲስና የማያውቁት መሆኑን ጠቁመው፣ ከኅዳር 7 ቀን 2011 ዓ.ም. ጀምሮ ፍርድ ቤት እየቀረቡ ያሉት ከአምስት ወራት በፊት ተጠርጥረው የታሰሩበት ወንጀል ምርመራ በመጠናቀቁ፣ ፍርድ ቤት ክስ እንዲመሠረትባቸው ባዘዘው መሠረት ክስ ለመስማት እንደነበር አስረድተዋል፡፡

  ነገር ግን መርማሪ ቡድኑ በጠቀሰው ተቋም ውስጥ እሳቸው ፈላጭ ቆራጭ እንዳልነበሩም ተናግረዋል፡፡ መርማሪ ቡድኑ በጥቅሉ ከመናገር ባሻገር እሳቸው ስለሠሩት ነገር በተናጠል ባለማቅረቡ እሳቸውን እንደማይመለከትም አስረድተዋል፡፡ ለብቻቸው ስለሠሩት ነገር ተለይቶ ካልተገለጸላቸው ምላሽ መስጠት እንደማይችሉም አክለዋል፡፡ ሀብት ስለማፍራት መርማሪ ቡድኑ የተናገረውን በሚመለከት በሕገ መንግሥቱ ሀብት ማፍራት መፈቀዱን ገልጸው፣ እሳቸውም የተለየ ሀብት ሳይሆን እንደ ማንኛውም ዜጋ ቤት መሥራታቸውን ተናግረዋል፡፡ ከዚህ ውጪ ግን ምንም ነገር እንደሌላቸው አስረድተዋል፡፡ እሳቸው ከሰኔ 16 ቀን ቦምብ ፍንዳታ ጋር በተገናኘ ሲታሰሩ ከፍርድ ቤት የተቆረጠው የመያዣ ትዕዛዝ ዕለት ዓይነት እንደነበር አስታውሰው፣ አንደኛው በፍንዳታው መጠርጠራቸውን የሚገልጽ ሲሆን ሌላኛው ደግሞ ያላቸውን ሀብት ለማጣራት እንደነበር ገልጸዋል፡፡ በመሆኑም በዚያን ጊዜ ማጠቃለል ሲቻል አሁን እንደገና 14 ቀናት እንዲፈቀድ መጠየቁ ተገቢና አሳማኝ ስላልሆነ፣ መርማሪ ቡድኑ የጠየቀው ተጨማሪ ጊዜ ወድቅ እንዲደርግላቸው ጠይቀዋል፡፡ መርማሪ ቡድኑ ባቀረበባቸው የወንጀል ዝርዝር ጉዳዮች ላይ ምላሽ ለመስጠትም በተናጠል እሳቸው የሠሩትን ለይቶ እንዲያቀርብላቸው ጠይቀዋል፡፡ መርማሪ ቡድኑ ስለ ሰኔ 16 ቀን ድርጊት የሚያውቀው ነገር እንደሌለ አስረድቶ፣ ከኅዳር 6 ቀን 2011 ዓ.ም. ጀምሮ ግን በተጠረጠሩበት የሰብዓዊ መብት ጥሰትና የሙስና ወንጀል እየመረመራቸው እንደሚገኝ አስረድቷል፡፡ ፍርድ ቤቱም የተጠርጣሪውን አቤቱታ ውድቅ በማድረግ መርማሪ ቡድኑ የጠየቀውን 14 ቀናት ፈቅዶ ለኅዳር 24 ቀን 2011 ዓ.ም. ቀጠሮ ሰጥቷል፡፡

  የፌዴራል ፖሊስ ወንጀል ምርመራ ቡድን ሌላው ለፍርድ ቤቱ ያቀረበው የምርመራ መዝገብ የእነ ሜጀር ጄኔራል ክንፈ ዳኘውና የወንድማቸው አቶ ኢሳያስ ዳኘውን መዝገብ ነው፡፡ መርማሪ ቡድኑ በተለይ ቀደም ብሎ በነበረው ችሎት አቶ ኢሳያስ ምንም ዓይነት ሀብትም ሆነ ገቢ እንደሌላቸው ለፍርድ ቤቱ በማስረዳት፣ መጽሐፍ ቅዱስ ይዘው በመማል ያረጋገጡ ቢሆንም መርማሪ ቡድኑ ግን አዲስ መረጃ ይዞ ቀርቧል፡፡

  እንደ መርማሪ ቡድኑ ገላጸ፣ አቶ ኢሳያስ በ2003 ዓ.ም. በፌዴራል የሥነ ምግባርና ፀረ ሙስና ኮሚሽን ሀብት ማስመዝገቢያ ቅጽ ላይ ያስመዘገቡትን የሀብት ዝርዝር አቅርቧል፡፡ በወቅቱ ግምቱ ሁለት ሚሊዮን ብር የሆነ ባለአንድ ፎቅ ሕንፃ በባለቤታቸው ስም የተመዘገበና ግምቱ 1.7 ሚሊዮን ብር የሆነ ቪላ ቤት፣ 115 ካሬ ሜትር የጋራ መኖሪያ ቤት፣ ግምቱ 240 ሺሕ የሆነ ቶዮታ ኮሮላ መኪና፣ ግምቱ 1.2 ሚሊዮን ብር የሆነ ሎደር፣ በአንበሳና በዳሸን ባንኮች የአክሲዮን ድርሻ፣ በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ፣ በአዋሽና በሌሎች ባንኮችም ተቀማጭ ገንዘብ (መጠኑ ተጠቅሷል) እንዳላቸው በሰነድ የተደገፈ መረጃ አቅርቧል፡፡

  ፍርድ ቤቱ መረጃውን ዓይቶ ከተመካከረ በኋላ፣ በቂ ሀብት እንዳላቸውና ጠበቃ አቁመው መከራከር እንደሚችሉ በመገለጽ፣ ቀደም ባለው ችሎት ተከላካይ ጠበቃ እንዲመደብላቸው የሰጠውን ትዕዛዝ አንስቷል፡፡ አቶ ኢሳያስ ንብረቱን ያስመዘገቡት ከስምንት ዓመታት በፊት መሆኑንና ይኑር አይኑር ሳይረጋገጥ ድምዳሜ ላይ መድረስ ተገቢ አለመሆኑን ቢናገሩም፣ ፍርድ ቤቱ አልተቀበላቸውም፡፡ መርማሪ ቡድኑም የሀብት ምዝገባን በሚመለከት የወጣው አዋጅ ሀብት ያስመዘገበው አካል በየሁለት ዓመቱ እየቀረበ ስለሀብቱ ሁኔታ ካላስረዳ፣ የተመዘገበው ሀብት እንዳለ እንደሚቆጠር መደንገጉንም አስረድቷል፡፡ በመሆኑም ሕጉ የሚያውቀው የተመዘገበው ሀብት የአቶ ኢሳያስ መሆኑንም አክሏል፡፡ አቶ ኢሳያስ የወንድማቸው ጠበቃ አቶ ዘረሰናይ ምስግና ለጊዜው እንዲከራከሩላቸው ጠይቋቸው ፍቃደኛ ሆነው ተከራክረውላቸዋል፡፡

  መርማሪ ቡድኑ ሜጄር ጄኔራል ክንፈ ዳኘው ከ2002 ዓ.ም. ጀምሮ የሜቴክ ዋና ዳይሬክተር ሆነው ሲሠሩ ፈጽመዋል ያላቸውን ሕገወጥ ግዥዎችና የተፈራረማቸውን ውሎች በሚመለከት በድጋሚ ካስረዳ በኋላ ምላሽ ሰጥተዋል፡፡

  በጠበቃቸው አማካይነት በሰጡት ምላሽ መርማሪ ቡድኑ ያቀረበው የወንጀል ድርጊት የተደፋፈነ ነው፡፡ ዳይሬክተሩ ከ2002 ዓ.ም. ጀምሮ በርካታ ውሎችን ከበርካታ ድርጅቶች ጋር መፈጸማቸውን ጠቁመው፣ የትኛውን ውል ከማን ጋር እንደሆነ አለመገለጹን አስረድተዋል፡፡ መርማሪ ቡድኑ የገለጸው ድርጊት በሙሉ በመገናኛ ብዙኃን በዶክመንተሪ ፊልም፣ በኤሌክትሮኒክ ሚዲያና በኅትመት ሚዲያ ከመገለጹም በተጨማሪ ጠቅላይ ዓቃቤ ሕጉ ምርመራው መጠናቀቁን ተናግረው እያለ ፖሊስ እንደገና ለምርመራ ተጨማሪ ጊዜ ቀጠሮ መጠየቁ ተገቢ አለመሆኑን አስረድተዋል፡፡ እነሱ በእስር ላይ እያሉና ምላሽ መስጠት በማይችሉበት ሁኔታ መርማሪ ቡድኑ ማስታወቂያ ሠርቶ ሲያበቃ፣ እንደገና 14 ቀናት የምርመራ ጊዜ መጠየቅ ተገቢ አለመሆኑን ተናግረዋል፡፡ ጄኔራሉ ከቅርብ ዘመዶቻቸውና ወገኖቻቸው ማለት ምን ማለት እንደሆነ ማለትም እህት፣ ወንድም፣ ልጅ ወይም ሚስት መሆኑ ሳይገለጽ በድፍኑ ከቅርብ ዘመዶቻቸውና ጓደኞቻቸውን በመጥቀምና መጠቀም የሚለው ተገቢ አለመሆኑን አስረድተዋል፡፡ በመሆኑም መርማሪ ቡድኑ ሥራውን መጨረሱንና በሕጉ መሠረት መከራከር ካለባቸውም በዋስትና ጉዳይ እንጂ፣ ስለተጨማሪ ምርምራ መሆን እንደሌለበት ገልጸው ዋስትናቸው እንዲከበርላቸውም ጠይቀዋል፡፡

  አቶ ኢሳያስም ቢሆኑ የሜጄር ጄኔራል ክንፈ ወንድም በመሆናቸው ካልሆነ በስተቀር፣ የኢትዮ ቴሌኮም የአንድ ክፍል ኃላፊ በመሆናቸውና ሥራ ለሜቴክ በመስጠታቸው ሊያሳስራቸው የሚችል ነገር እንደሌለም ገልጸዋል፡፡ ምክንያታቸው ደግሞ 185 ታወሮችን ለመትከል የ54 ሚሊዮን ብር ውል ቢፈጽሙም፣ የተተከለውና የቀረው ሥራ ስለሚታወቅ ቀሪ ምርመራ ባለመኖሩ መሆኑን አስረድተዋል፡፡

  መርማሪ ቡድኑ የተጠርጣሪዎች ጠበቃ ማስታወቂያ ማስነገር የሚሉትን ቋንቋ ተቃውሟል፡፡ የተሠራውን ምርምራና የሚቀረውን እያስረዳ ለተጨማሪ ምርመራ ጊዜ መጠየቁ ማስታወቂያ መሥራት እንዳልሆነ በማስረዳት፣ የቀረውን ሥራ በድጋሚ ገልጾ የጠየቀው 14 ቀናት እንዲፈቀድለት ጠይቋል፡፡

  የተጠርጣሪው ጠበቃ አቶ ዘረሰናይ በሰጡት ምላሽ ተጠርጣሪዎችን የሚጎዳ ማስታወቂያ ተሠርቷል ማለት የሕግ ቋንቋ ወይም (Self Advertisement) ማለት እንደሆነ በማስረዳት፣ የፖሊስን ተቃውሞ መልሰው ተቃውመዋል፡፡ ፍርድ ቤቱ የግራ ቀኙን ክርክር ካዳመጠና በመሀልም የማጣሪያ ጥያቄ ለሁለቱም ወገኖች ካቀረበ በኋላ፣ የተጠርጣሪዎችን ሐሳብ ውድቅ በማድረግ መርማሪ ቡድኑ የጠየቀውን 14 ቀናት ፈቅዶ ለኅዳር 24 ቀን 2011 ዓ.ም. ቀጠሮ ሰጥቷል፡፡

  ሌላው መርማሪ ቡድኑ የሜቴክ የሰው ሀብት መምርያ ኃላፊ ኮሎኔል ሰጠኝ ካህሳይ፣ እንዲሁም ኮሎኔል ጉደታ ኦላና የተባሉ የኢትዮጵያ ቴሌኮም የጥበቃና የደኅንነት ዲቪዥን ኃላፊን አቅርቧል፡፡

  ኮሎኔል ሰጠኝ ብርጋዴር ጄኔራል ሃድጉ ጌቱ የተባሉ ተጠርጣሪን ሰነድ በማሸሽ የሙስና ወንጀል መጠርጠራቸውን ጠቁሟል፡፡ ኮሎኔል ጉደታ ደግሞ የኢትዮ ቴሌኮም የጥበቃ ኃላፊ ሆነው ሲሠሩ በሙስና የተጠረጠሩ ሰዎችን በሚመለከት ጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ የጀመረውን ምርመራ በማደናቀፍና ከገቢያቸው በላይ ሀብት አጠራቅመዋል ተብለው የተጠረጠሩ መሆናቸውን አስረድቷል፡፡ ተጠርጣሪዎቹ ፈጽመውታል የተባለው የወንጀል ድርጊት ከተነገራቸው በኋላ ጠበቃ የሚያቆሙበት ምንም ሀብት እንደሌላቸው በመሃላ ለፍርድ ቤቱ በማረጋገጣቸው፣ መንግሥት ተከላካይ ጠበቃ እንዲያቆምላቸው ትዕዛዝ ከተሰጠ በኋላ ለኅዳር 13 ቀን 2011 ዓ.ም. ቀጠሮ ተሰጥቷል፡፡ የተጠረጠሩበት የወንጀል ድርጊት ባይነገራቸውም ፍርድ ቤት ቀርበው የነበሩት የዓለም ገነት ቆርቆሮ ፋብሪካ ባለቤት አቶ ዓለም ፍፁም ገብረ ሥላሴና ሌሎች አራት ግለሰቦች የችሎት ሰዓት በመጠናቀቁ፣ ለኅዳር 12 ቀን 2011 ዓ.ም. ተቀጥረዋል፡፡

  spot_img
  - Advertisement -

  ይመዝገቡ

  spot_img
  spot_img

  ተዛማጅ ጽሑፎች
  ተዛማጅ

  በችግር የተተበተበው የሲሚንቶ አቅርቦት

  ሲሚንቶን እንደ ግብዓት ተጠቅሞ ቤት ማደስ፣ መገንባት፣ የመቃብር ሐውልት...

  ‹‹የናይል ዓባይ መንፈስ›› በሜልቦርን

  አውስትራሊያ ስሟ ሲነሳ ቀድሞ የሚመጣው በተለይ በቀደመው ዘመን የባህር...

  ‹‹ልብሴን ለእህቴ››

  ለሰው ልጅ መኖር መሠረታዊ ፍላጎት ተብለው ከተዘረዘሩት ውስጥ ልብስ...

  የአዲስ አበባ ትምህርት ቤቶች የምርመራ ውጤት እስከምን?

  በፍቅር አበበ የትምህርት ጥራትን፣ ውጤታማነትንና ሥነ ምግባርን ማረጋገጥ ዓላማ አድርጎ...