Friday, December 2, 2022
ሌሎች ዓምዶች
  - Advertisement -
  - Advertisement -
  ዜናየትግራይ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳድር የሰሞኑ ዕርምጃ ተቀባይነት የለውም አሉ

  የትግራይ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳድር የሰሞኑ ዕርምጃ ተቀባይነት የለውም አሉ

  ቀን:

  የትግራይ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳደር ደብረ ጽዮን ገብረ ሚካኤል (ዶ/ር) ሰኞ ኅዳር 10 ቀን 2011 ዓ.ም. በጽሕፈት ቤታቸው ለጋዜጠኞች በሰጡት መግለጫ፣ ሰሞኑን በፌዴራል መንግሥት እየተወሰደ ያለው ዕርምጃ ከሕግ የበላይነት ውጪ ስለሆነ ተቀባይነት እንደሌለው አስታወቁ፡፡

  ምክትል ርዕሰ መስተዳድሩ ይህንን ያሉት፣ መሰንበታቸውን የፌዴራል መንግሥት በሰብዓዊ መብት ጥሰቶችና በአገር ሀብት ላይ ተፈጽሟል በተባለው ዝርፊያ የጀመረውን ዕርምጃ በሚመለከት ነው፡፡

  ምክትል ርዕሰ መስተዳድሩ፣ ‹‹በኢሕአዴግ ደረጃ የታገልነው ለሕግ የበላይነት ነው፡፡ ያጠፋ ካለ ሊጠየቅ ይገባል ብለናል፡፡ መንግሥት ከመረጣቸው ሜቴክና የደኅንነት መሥሪያ ቤቱ ብቻ ሳይሆን፣ ሕገ መንግሥት የሚጥሱ ክልሎችም ይፈተሹ ብለናል፤›› በማለት፣ አሁን እየተወሰደ ያለው ዕርምጃ በሰፊው መካሄድ እንደሚኖርበት አስታውቀዋል፡፡

  ከይቅርታና ከምሕረት ጋር በተያያዘ በኢሕአዴግ ደረጃ ለጥፋተኞች ሁሉ ምሕረትና ይቅርታ መኖር እንዳለበት በመተማመን፣ እንዲሁም ለፖለቲካውም ይጠቅማል ከሚል እሳቤ ዕርምጃዎች መወሰዳቸውን ያስታወሱት ምክትል ርዕሰ መስተዳድሩ፣ አሁን አንደኛውን ፈትቶ ሌላኛውን ማሰር ግን አግባብ አይደለም ብለዋል፡፡

  ‹‹አንዱን እየፈታህ ሌላውን አታስርም፡፡ ከዚህ ቀደም በተለያዩ ወንጀሎች በቁጥጥር ሥር የነበሩት በምሕረት ከተፈቱ በዚህ መልኩ ነገሩን እንያዘው ብለን ነበር፡፡ ካልሆነ ግን ከዚህ ቀደም የተፈቱትም ቢሆን ዳግም ሊታሰሩ ይገባል፤›› ሲሉ በመግለጫቸው አስታውቀዋል፡፡

  የሜቴክ ዋና ዳይሬክተር የነበሩትን ሜጀር ጄኔራል ክንፈ ዳኘውን ለመያዝ የተሄደበት መንገድን አስመልክቶም የሕግ የበላይነት መከበር እንዳለበት ምክትል ርዕሰ መስተዳድሩ ገልጸው፣ ‹‹ሜጀር ጄኔራል ክንፈን ለመያዝ ለመጡት የመከላከያ ኃይል አባላት እንደማንሰጥ አሳውቀን ነበር፡፡ ነገር ግን የሕግ የበላይነት መከበር ስላለበት የፍርድ ቤት ማዘዣውን ተመልክተን ለፌዴራል ፖሊስ አስረክበናል፤›› ብለው፣ ሜጀር ጄኔራል ክንፈ በቁጥጥር ሥር ስለዋሉበት ሒደት አስረድተዋል፡፡

  ከዚህ ጋር በተያያዘ የቀድሞ የኢንሳ ኃላፊ የነበሩት ሜጀር ጄኔራል ተክለ ብርሃን ወልደ አረጋይም አብረው ተይዘው የነበሩ መሆናቸውን ጠቁመው፣ የወጣባቸው የፍርድ ቤት ትዕዛዝ ስላልቀረበ ለማሰርም ሆነ ለማስረከብ እንደማይቻል ምላሽ መስጠታቸውን አክለው ገልጸዋል፡፡

  ሆኖም ሜጀር ጄኔራል ክንፈ በሰላም በቁጥጥር ሥር ውለው ሳለ በካቴና አስሮ በሚዲያ ማቅረብ ፖለቲካዊ ጥቃት ነው ያሉት ምክትል ርዕሰ መስተዳድሩ፣ ‹‹በመቀጠልም ተዘጋጅቶ የነበረን ዶክመንተሪ ማስተላለፍ ፖለቲካዊ ጥቃት ነው፡፡ ተጠርጣሪ የሚቀርበው ወደ ፍርድ ቤት እንጂ ወደ ሚዲያ አይደለም፡፡ በዚህም የሕግ የበላይነት ተበርዟል፡፡ ወደ አንድ ግለሰብ ሳይሆን ወደ ብሔርና ድርጅት ያነጣጠረ መሆኑ አደባባይ ወጥቷል፤›› ሲሉ ተቃውሞአቸውን አሰምተዋል፡፡

  ‹‹የትግራይ ክልል ለሕግ የበላይነት ይሠራል፡፡ የፌዴራል መንግሥት ግን የሕግ የበላይነትን ጥሶ እየሄደ ስለሆነ እየተወሰደ ያለው ዕርምጃ በማንኛውም መንገድ ተቀባይነት የለውም፤›› ብለዋል፡፡

  የሕግ የበላይነት ጥሰትን አስመልክቶ በሰጡት መግለጫ፣ ዕርምጃው የውጭ ኃይሎች ጣልቃ ገብነት ያለበት በመሆኑ ፖለቲካዊ አንድምታው እየሰፋ መጥቷል ብለዋል፡፡

  ‹‹ትግራይን ለማጥቃት እየተሠራ ነው፡፡ ከዚህ ቀደም በተለያዩ መልኮች ሲሞከር የነበረው ትግራይን የማጥቃት ዘመቻ፣ አሁን ደግሞ በሕግ የበላይነት ስም መጥቷል፡፡ የትግራይ ሕዝብ ሌባ እንዲባልና አንገቱን እንዲደፋ ነው እየተሠራ ያለው፤›› ሲሉም ተናግረዋል፡፡

  ‹‹አሁን እየተካሄደ ያለውን ዕርምጃ አንቀበለውም ብቻ ሳይሆን ሊታረምም ይገባዋል፡፡ ከሁሉም በላይ የሕግ የበላይነት ሊሰፍን ይገባል፤›› ሲሉ መግለጫውን አጠቃለዋል፡፡

  የእሳቸው መግለጫ ይፋ ከሆነ በኋላ በርካቶችን እያነጋገረ ሲሆን፣ በትግራይ ክልልና በፌዴራል መንግሥት መካከል የተካረረ ልዩነት እየተፈጠረ መሆኑ እየተወሳ ነው፡፡ በተለይ በማኅበራዊ ሚዲያ በሁለት ጎራዎች ጭቅጭቅ አስነስቷል፡፡ ለመግለጫቸው ድጋፋቸውን በሚሰጡና አምርረው በሚቃወሙ መካከል የተስተዋለው የተካረረ ጭቅጭቅ፣ የአገሪቱን ወቅታዊ ሁኔታ ማመላከቻ ሆኗል፡፡

  spot_img
  - Advertisement -

  ይመዝገቡ

  spot_img

  ተዛማጅ ጽሑፎች
  ተዛማጅ

  [በተቋሙ ሠራተኞች የተወከሉ አንድ ባልደረባ ሚኒስትሩን ለማነጋገር ቀጠሮ ይዘው ወደ ቢሯቸው ገቡ]

  ጤና ይስጥልኝ ክቡር ሚኒስትር? ሰላም ሰላም ... ተቀመጥ! አመሠግናለሁ ክቡር ሚኒስትር!...

  የጉራጌ ዞን ጥያቄና የክላስተር አደረጃጀት የገጠመው ተቃውሞ

  መንግሥት የደቡብ ብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ክልል አካል የነበሩ ዞኖችንና...

  አዋሽ ባንክ ካፒታሉን ወደ 55 ቢሊዮን ብር ለማሳደግ ያስገደደው ምክንያት ምንድን ነው?

  ባለፈው ቅዳሜ ጠቅላላ ጉባዔውን ያካሄደው አዋሽ ባንክ የ43 ቢሊዮን...

  አቢሲኒያ ባንክ ካለፈው ዓመት የ127 በመቶ ብልጫ ያለው ትርፍ በማግኘት አዲስ ታሪክ አስመዘገበ

  አቢሲኒያ ባንክ ከቀደሚ የሒሳብ ዓመት የ127 በመቶ ብልጫ ያለው...