Friday, September 22, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -

አባጣ ጎርባጣ የበዛበት የኢትዮጵያ ዓለም አቀፉን የንግድ ድርጅት የመቀላቀል ጉዞ

ከሳምንታት በፊት በአገሮች የንግድ ሥርዓት ፈተናዎች ላይ ምሥራቅ አፍሪካ ያለውን ምልከታ አስመልክቶ በኬንያ ናይሮቢ ሴሚናር ተካሂዶ ነበር፡፡ በወቅቱ በዓለም አቀፉ የንግድ ድርጅት ዙሪያ ያሉ ፈተናዎች፣ በድርጅቱ አባል አገሮች መካከል የንግድ ጦርነት እያንሰራራ መምጣቱና ንግድን በአካባቢ መወሰን የተነሱ ጉዳዮች ነበሩ፡፡ በሴሚናሩ ላይ የተገኘው ዮሐንስ አንበርብር መቀመጫውን በጄኔቭ ያደረገው ዓለም አቀፉ የንግድ ድርጅት የመረጃና የውጭ ግንኙነት ክፍል ዳይሬክተር ኬት ሮክዌልን ኢትዮጵያ ድርጅቱን በመቀላቀሉ ሒደት ያላትን ቦታ አስመልክቶ አነጋግሮአቸዋል፡፡

ሪፖርተር፡- የኢትዮጵያ መንግሥት ዓለም አቀፉ የንግድ ድርጅትን ለመቀላቀል ድርድር ከጀመረ ከአሥር ዓመት በላይ አስቆጥሯል፡፡ ሆኖም የመቀላቀሉ ሒደት ረዥም ጊዜ ወስዷል፡፡ ኢትዮጵያም አልተቀላቀለችም፡፡ ድርጅቱን የመቀላቀሉ ሒደት ምን ይመስላል? ኢትዮጵያስ እምን ላይ ናት?

ኬት ሮክዌል፡- ኢትዮጵያ ድርጅቱን የመቀላቀል ሒደትን የጀመረችው እ.ኤ.አ. በ2003 ነው፡፡ ሆኖም ቀላል አልነበረም፡፡ ይህ የሆነው የመቀላቀሉ ሒደት በራሱ በሚፈጥረው  ጫና ብቻ ሳይሆን የአገሪቱ ባለሥልጣናት ውሳኔም ጭምር ነው፡፡ በመሆኑም የመቀላቀል ሒደቱ በ2012 ተቋርጦ ነበር፡፡ ላለፉት ስድስት ዓመታት ማለትም በቅርቡ የኢትዮጵያ ባለሥልጣናት ድርጅቱን ለመቀላቀል ያቀረቡትን ውይይትና ሒደት ከመቀጠላቸው በፊት ግንኙነት አልነበረም፡፡ ለስድስት ዓመታት ያህልም ግንኙነት፣ ስብሰባም ሆነ ድርድር አልነበረም፡፡

ሪፖርተር፡- ድርጅቱን የመቀላቀል አሠራሩ እንዴት እንደሆነ ቢያስረዱኝ?

ኬት ሮክዌል፡- አሠራሩ የብዙዎችና የሁለትዮሽ ግንኙነትን ያማከለ ነው፡፡ ብዙዎችን ያማከለው ባብዛኛው የድርጅቱ ኅጎችና የአሠራር መዋቅሮች ላይ ያተኮረ ነው፡፡ ባጠቃላይ ስለድርጅቱ ቁመና የያዘ ነው ማለት እንችላለን፡፡ በመሆኑም በዚህ ደረጃ የሚደረጉ ድርድሮች መሠረታዊ በሆኑ መርሆዎች ለምሳሌ ድጎማ፣ ጥበቃ፣ ምርቶችን ሌሎች አገሮች ላይ መጣያ አለማድረግ፣ የግብርና ፖሊሲዎችና ተያያዥ ጉዳዮች ሊነሱ ይችላሉ፡፡ ከዚህ በኋላ ነው የሁለትዮሽ ጉዳዩ የሚነሳው፡፡ ይህ በአብዛኛው ገበያ ከማግኘት ጋር የተያያዘ ነው፡፡ የድርድሩ ሒደት ባጠቃላይ የሚወሰነው አገሮች ፕላትፎርሙን ለመቀላቀል ባላቸው አቅም ነው፡፡ ስለኢትዮጵያ ማውራት አልፈልግም፡፡ ሆኖም ሳላዳላ ሳየው ታሪፍን መቀነስና ከዚህ ጋር ተያይዞ የሚመጣ የታሪፍ ገቢ መቀነስ የኢትዮጵያ ሥጋት ይመስለኛል፡፡ በሌላ በኩል ቴሌኮም፣ የገንዘብ ተቋማት፣ ሎጂስቲክስንና ሌሎችንም አገልግሎቶች ለውጭ ክፍት ማድረግ ሌላው ፈተና ነው፡፡ የኢትዮጵያ መንግሥት ዘርፎችን አቅርቧል፡፡ ሆኖም አባል አገሮች ኢትዮጵያ ክፍት ዘርፎችን እንድታበዛ ይፈልጋሉ፡፡ አባል አገሮች በኢትዮጵያ ያለውን ከባድ ታሪፍም አይፈልጉትም፡፡ ኢትዮጵያ ደግሞ ያላት ታሪፍ ይዛ መቆየት ትፈልጋለች፡፡ እነሱ ደግሞ ኢትዮጵያ የታሪፍ ቅነሳ እንድታደርግ የኢትዮጵያን ምላሽ እየጠበቁ ነው፡፡ የመቀላቀል ሒደቱ ምንም አይልም ልንል እንችላለን፡፡ በኢትዮጵያ በኩልም ዳግም እንየው ተብሏል፡፡ ኢትዮጵያ ውሳኔዋን አሁን ለምን እንደቀየረች አላውቅም፡፡

ሪፖርተር፡-  ኢትዮጵያ በቅርቡ ለጀመረችው ግንኙነት የድርጅቱ ምላሽ ምንድነው?

ኬት ሮክዌል፡- ለእያንዳዷ የመቀላቀል ሒደት ከድርጅቱ የሚመለከት ኮሚቴ አለ፡፡ ይህ ኮሚቴ ‹‹ዎርኪንግ ፓርቲ›› ይባላል፡፡ ድርጅቱን በመቀላቀል ሒደት ላይ ያሉ አገሮችም ከሚመደብላቸው ኮሚቴ ጋር መነጋገር ግዴታቸው ነው፡፡ እንዳለመታደል ሆኖ የኢትዮጵያን ኮሚቴ የሚመራው በቅርቡ ነው ጡረታ የወጣው፡፡ በመሆኑም እስካሁን ለኢትዮጵያ ሕጋዊ መልስ አልተሰጠም፡፡ አሁን አዲስ ሊቀመንበር በመፈለግ ላይ ነን፡፡ መቼ እንደሆነ ባላውቅም ረዥም ጊዜ ሳንወስድ ሊቀመንበር አግኝተን ሌላ ውይይት ይኖረናል ብለን እናምናለን፡፡

ሪፖርተር፡- ኢትዮጵያ ድርጅቱን የመቀላቀል ሒደቱን ከጀመረች 15 ዓመት ብታስቆጥርም፣ ተጨባጭ ውጤት አልተገኝም፡፡ ድርጀቱን የመቀላቀል ሒደቱ እንዲህ ዓመታት መፍጀቱ የተለመደ ነው? አገሮች ሒደቱ እንዲፋጠንላቸው ምን ማድረግ አለባቸው?

ኬት ሮክዌል ፡- ድርጀቱን የተቀበሉ አገሮች ያላቸውን ምርት በአሥር ሺዎች የሚቆጠር ሊሆን ይችላል ይኼንንና ታሪፋቸውን ይልካሉ፡፡ ይህም አማካይ የታሪፍ ምጣኔያቸውን ያሳያል፡፡ አባል አገሮችም እያንዳንዱን የሚፈልጉትን ምርት ያያሉ፡፡ የድርጅቱ አባል አገር ከሆኑ 164 አገሮች ጋር መወያየት እንዴት የተወሳሰበ እንደሆነ ማሰብ ይቻላል፡፡ በእርግጥ አሜሪካ አውሮፓውያኑና በቅርቡ ቻይና የሚፈልጉትን የምርት ዓይነት አስቀምጠዋል፡፡ ለአሜሪካና አውሮፓ ምርትና አገልግሎት ዋና ነው፡፡ ለምሳሌ ኒውዚላንድ በቅቤ፣ በሱፍና በብርና ወርቅማ ቀለም የተሠሩ አብረቅራቂ ልብሶች ላይ ሁሌም ፍላጎት አላት፡፡ ምክንያቱም እነዚህን ምርቶች ለዓለም በብዛት በማቅረብ ቀዳሚ አገር ናት፡፡ ይኼንን ይዘው ኢትዮጵያ ጋር በመምጣት በታሪፍ ላይ ይደራደራሉ፡፡ ድርድሩ ላይ ኒውዚላንድ የማትፈልገው ዓይነት ምላሽ ከኢትዮጵያ በኩል ካለ ውይይቱ አይቀጥልም፡፡ እንዲህ ዓይነቱ ጉዳይ ነው ከድርጅቱ የመቀላቀሉን ሒደት የሚያሳጥረውም የሚያረዝመውም፡፡ አንዳንዴ በማደግ ላይ ባሉ አገሮች ላይ ጫና ሲፈጠር ቆይቷል፡፡ ሆኖም ከቅርብ ዓመት በፊት በተረቀቀው ጋይድላይን ያላደጉ አገሮች የተሻለ አማራጭ እንዲኖራቸው ተለዋዋጭ ፖሊሲዎችን አስቀምጧል፡፡

ሪፖርተር፡- ማለትዎ ኢትዮጵያም የፋይናንስ ዘርፉን ሳትከፍት ድርጅቱን የመቀላቀል ዕድል ይኖራታል ማለት ነው?

ኬት ሮክዌል፡- እንደተደራዳሪዎቹ ነው፡፡ አባላት በዚህ ላይ ይደራደራሉ፡፡ ለምሳሌ ኢትዮጵያ ያላደኩ አገር ነኝ፣ የገንዘብ ተቋማትን ክፍት ላደርግ አልችልም፣ በአገራችን ጥበቃ ልናደርግላቸው የሚገቡ ያላደጉ ኢንዱስትሪዎች አሉ ልትል ትችላለች፡፡ አሁን ድርጅቱን የሚቀላቀሉ አገሮች ቀድመው ‹‹የጀነራል አግሪመንት ኦን ታሪፍስ ኤንድ ትሬድ›› (ጂኤቲቲ) አባል የነበሩና ድርጅቱ ቀጥታ ከተቀላቀሉት ጋ ሊቃረኑ ይችላሉ፡፡ በጂኤቲቲ ጊዜ ደብዳቤ ብቻ በመጻፍ አባል መሆን ይቻል ነበር፡፡ ሆኖም ዓለም አቀፉ የንግድ ድርጅት ባለው መጠን ሕጋዊ አፈጻጸም አልነበረውም፡፡

ሪፖርተር፡- ካለዎት ልምድ አንፃር ኢትዮጵያ የድርጅቱ አባል የመሆን ሒደቷን እንዴት ልታፋጥን ትችላለች?

ኬት ሮክዌል፡- የንግድ ፖሊሲ የፖለቲካ ሒደት ነው፡፡ በሚፈለገው መልኩ  ለማመጣጠንም አዳጋች ነው፡፡ የገበያ መከፈትን ወይም ታሪፍን ስታይ እያንዳንዱ መንግሥት በአምራቹና ተጠቃሚው መካከል መመጣጠን እንዲኖር ይፈልጋል፡፡ ከፍተኛ ታሪፍ ቢጣል አገር ውስጥ ላሉ ስንዴ አምራቾች ጥሩ ነው፡፡ ሆኖም የዳቦ ዋጋ ይጨምራል፡፡ በማደግ ላይ ባሉ አገሮች ደግሞ ደሃ ተጠቃሚዎች መኖራቸውን ከግምት ማስገባት ያስፈልጋል፡፡ የዳቦ ዋጋ ሲጨምርና ከውጭ የሚገባ ዕቃ ላይ የታሪፍ ገደብ መጣልና ውድድር እንዳይኖር ማድረግ ነው፡፡ በሌላ በኩል የስንዴ አምራቾች ከውጭ በሚመጣ ስንዴ ምናልባትም በሚደጎመው ከጨዋታ ውጪ እንዲሆኑ አይፈልግም፡፡ ስለሆነም መንግሥት የማቻቻል ሥራ አለበት፡፡ ብዙ ደሃ ተጠቃሚ ባለበትም ከባድ ነው፡፡ በጥሞና ማየትና መወሰን የኢትዮጵያ መንግሥት ፈንታ ነው፡፡ ኢትዮጵያ የተለዋዋጭ ፖሊሲ ተጠቃሚ ከሆኑ ካላደጉ አገሮች ተርታ ናት፡፡ መንግሥትም ይኼንን ፖለቲካዊ ሒደት መረዳት አለበት፡፡

ተዛማጅ ፅሁፎች

- Advertisment -

ትኩስ ፅሁፎች ለማግኘት

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች