Thursday, June 1, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -

የተመረጡ ፅሑፎች

ሞራል ሲዘቅጥ አገር ይጠፋል!

እነሆ መንገድ ከፒያሳ ወደ አራት ኪሎ ልንጓዝ ነው። መንገዱን ስንጀምር ከወደ ሬዲዮው በዘረፋና በሰብዓዊ መብት ጥሰቶች ስለተያዙ ሰዎች የተጀመረው ዜና እያለቀ ነበር፡፡ ‹‹እነሱንማ በሕግ ልክ አስገብቶ ነው ዳይ ወደ ሥራ መባል ያለበት፤›› ይላሉ አንድ አዛውንት፡፡ በዚህ መሀል ሾፌራችን በወያላው ቅዝዝ ፍዝዝ ማለት የሚያደርገው ጠፍቶት፣ ‹‹ምን ዝም ትላለህ? ወይ አንተን አባርሬ ቻይና ልቅጠር መሰል፤›› ይላል። ‹‹እንዴት በአገርህ ስንት ሥራ አጥ ወገን እያለ ቻይና?›› ይሉታል አጠገቡ የተሰየሙት ባርኔጣ የደፉ አዛውንት። ‹‹ምን አባቴ ላድርግ? እንዲሁ በቆምኩበት ነዳጅ እየጨረስኩ ተቸገርኩ እኮ አባት?›› አላቸው። ‹‹እሱስ አንተ ብቻ አይደለህም አይዞህ። እኛም በቆምንበት ነው ዕድሜያችን ያለቀው፤›› አሉት። ‹‹የባሰ አታምጣ። ያውም የማይሞላውን ነዋ የጨረሱት?›› ብላ የደስ ደስ ያላት ወጣት የጋቢናውን በር ከፍታ እየዘጋች ተናገረች። ‹‹ዲስኮ ሰዓት መሰለሽ ታዲያ ዕድሜ?›› አባታዊ የፍቅር አስተያየታቸውን ገጿ ላይ እያረበቡ አናገሩዋት። ‹‹ምን የዘንድሮ ሰዓት እኮ ብንሞላውም ባንሞላውም አንድ ነው፤›› አለቻቸው። ‹‹ቢሳሳትም በቀን ሁለቴ  ልክ መሆኑ አይቀርም እያልሽኝ ነው?›› አሉዋት። ‹‹ምድረ ዘራፊና አሰቃይ አገሩን ተቆጣጥሮት እንዴት አይሳሳት…›› ስትል ሳቃቸው አጀባት፡፡

‹‹እሱ እንዳለ ሆኖ የመሙላትና የመጉደሉን ሒሳብ ገንዘብ ተክቶታል ለማለት ፈልጌ ነው፤›› ስትላቸው፣ ‹‹ጊዜና ገንዘብ አንድ መስለውኝ?›› ብለው ግራ በተጋባ መንፈስ አስተዋሏት። ‹‹እሱማ እኛም መስሎን ነበር። ግን ጎዳናውን ስናየው ጊዜና ገንዘብ፣ ዕድሜና ሥፍራ ገጥመው አይገኙም። አይደለም እንዴ?›› ብላ ተራዋን ቀና ብላ እያየቻቸው ቦርሳዋን መጎርጎር ጀመረች። አዛውንቱ ሲያወጡ ሲያወርዱ ከቆዩ በኋላ፣ ‹‹እሱማ እንኳን ጊዜና ሁኔታ ገንዘብና ዕድሜ ሊገጥሙ፣ ግጥሙ ራሱ አልገጥም ብሎን ተቸግረናል። ይኸው ታታታ፣ ላላላ፣ ሃሃሃሃ እያሉ አብደው ሲያሳብዱን ዝም ያልነው ለምን ሆነና? ተስፋ ብንቆርጥ አይደለም እንዴ?›› ብለው በሬዲዮ የሚንቆረቆረውን ዘመነኛ ዘፈን ጠቆሙ። ቢገጥም ባይገጥም እኛ ምን አገባን? አገር ባይኖረንም አገራችን ያግባን ሆኗል እኮ ነገሩ። ይኼን ያህል በጊዜና ገንዘብ አገጣጠም ተስፋ ቆርጠን መድረሻ ቢስ ሆነናል ማለት ነው? ከዚህ ይልቅ ገንዘብ የሰውን አቅል አስቶ አውሬ አድርጎት የተደረገውን እየሰማን ምን ሌላ ነገር ያስቀባጥረናል?

ታክሲያችን መንቀሳቀስ ጀመረች። ብዙም የማይናገረው ወያላ ንዴትና ቁጣ የተቀላቀለበትን የሾፌሩን ተግሳፅ የሚያዳምጥ አይመስልም። ‹‹ስማ … እኔ ለራስህ ብዬ ነው … መጀመርያ ከሰው ጋር የሚያኗኑር ፀባይ ይኑርህ … ሲቀጥል ሰው የሚነግርህን አዳምጥ… ጨው ለራስህ ስትል ጣፍጥ … እንቢ ካልክ…›› ብሎ ሳይጨርስ፣ ‹‹አሄሄሄ! ልፋ ቢልህ ነው ልጄ፡፡ ደግሞ ዘንድሮ ከሰው ጋር የሚያኗኑር ፀባይ ሊያስጨንቀን ቀርቶ መቼ ከራሳችን ጋር የሚያስታርቅ አመል ይወድልን ብለህ ነው?›› አለች ከጀርባው የተሰየመች ወይዘሮ። ‹‹ምን እናድርግ ታዲያ? በአንድ በኩል ልማት እየተባለ በሌላ በኩል ዝርፊያና ጭካኔ የተሞላበት ድርጊት እየሰማን ወፈፍ ቢያደርገን ምን ይገርማል?›› አላት አጠገቧ የተሰየመ ወጣት።

‹‹እኔ የምለው ፈጣን የኢኮኖሚ ዕድገት እያስመዘገብን እንደሆነ ስንቶቻችን እናውቃለን?›› ብሎ መሀል ረድፍ ላይ የተሰየመ ተሳፋሪ ጣልቃ ሲገባ፣ ‹‹ይቅርታ ጥያቄው ይስተካከል፤›› አለች ሦስተኛው ረድፍ ላይ ተብቃቅታ በምቾት የተንሰራፋች ዘመናይ። ‘ቀጥይ’ ሲላት ተሳፋሪው በዓይኑ፣ ‹‹ኢኮኖሚ ሲባል ትርጉሙንና ሥሌቱን የምናውቅ ስንቶቻችን ነን?›› አለች ጮክ ብላ። ‹‹አቦ ደህና ተገላገልን ስንል ሌላ ኮርስ ታስጀምሩናላችሁ እንዴ? አይደብራችሁም?›› አሉ መጨረሻ ወንበር የተሰየሙ ሁለት ወጣቶች እየተቀባበሉ። ‹‹ምኑን ነው የተገላገላችሁት?›› አላቸው ጥጉን ይዞ መስኮት በመክፈትና በመዝጋት የታክሲያችንን የአየር ሁኔታ የሚቆጣጠር ጎልማሳ። ‹‹የኢኮኖሚክስ ተማሪዎች ነን…›› ከማለቱ አንደኛው ያኛው ተቀብሎት፣ ‹‹እንዳያልፉት የለም ያ ሁሉ ታለፈ…›› ብሎ ዘፈነ። ‹‹እንዲህ እያሉ ማሾፍማ ድሮ ቀረ ወንድም፣ ያሳለፍነውን መከራ የምናውቀው እኛ ነን፡፡ የኢኮኖሚ ጥገኛ ተደርገን ልማት እያልን ስናሾፍ አይደብርም…›› ስትል ፀጥ አልን፡፡

ጉዟችን ቀጥሏል። በየመሀሉ ታክሲያችን ቆም ብላ ቦታ እያሸጋሸገች፣ እያጠጋጋች፣ እያራገፈች ደግሞ ትሄዳለች። ደግሞ ቆም፣ ደግሞ ሄድ ትላለች። ‹‹መቼ ይሆን ይኼ ሄድ እያሉ የመቆም ዘመን የሚያከትመው?›› አለች ወይዘሮዋ በለሆሳስ። ‹‹ዘመነኛ እንጂ ዘመን ያከትማል እንዴ? ባይሆን ያልፋል፤›› አላት ወጣቱ። ወጣቱ ላይ ተደርቦ የተሰየመ አዲስ ተሳፋሪ፣ ‹‹ጥቅሱን አላያችሁትም መሰል?›› ብሎ ወደ ጣራው ጠቆመን። ‘አሠላለፉ ካልጣመህ ወርደህ ባቡር ያዝ’ ይላል። ወይዘሮዋ ፈገግ ብላ፣ ‹‹አንተ ነህ የጻፍከው?›› አለችው ወያላውን እያየች። አልመለሰላትም። ሾፌሩ በግንባር መስተዋቱ አጨንቁሮ የወያላውን ሁኔታ እያየ፣ ‹‹ደንበኛ ክቡር ነው አላልኩህም?›› አለው ተለሳልሶ። ‹‹ለአጫዋችነት አልተቀጠርኩም፤›› አለው ወያላው ኮስተር ብሎ። እኛ በዚህ ጊዜ መቼ አጫዋች አሰኘን?

‹ይኼም አለ ለካ?› አለ ዘፋኙ። ‹‹ኧረ እኛ አጫዋችም ተጫዋችም አልፈለግንም። ሜዳውን ካገኘን በቂ ነው፤›› ብሎ ወጣቱ ሲያሸሙር፣ ‹‹ሜዳውንስ በየት በኩል አገኘነው? አታዩትም እንዴ ዙሪያውን አጥረው ምን ሲያደርጉ እንደነበር?›› ብሎ ጎልማሳው ተናገረ። ‹‹ታዲያ ለውጤትም ለጤናም ለሚጫወተው ሁሉ ሜዳው ከተከፈተማ ሣሩ አይሰነብትም፤›› ብላ ደግሞ ሦስተኛው ረድፍ ላይ ዘመናያችን መልስ ሰጠች። ‹‹እንዴት ነው ነገሩ የሕዝብ ነው አላሉም እንዴ?›› አሉ ከፊት ለፊት አዛውንቱ ዘወር ብለው እየቃኙን። ‹‹ምኑ?›› ሲላቸው መላው ተሳፋሪ በኅብረት ‹ሜዳውን!› አሉ። ‹‹ፅድቁ ቀርቶ በቅጡ በተኮነንን ጋሼ። እኛ እኮ በዘመናት አንዴ ቢያልፍልን መልካም ነበር፤›› ስትል ወይዘሮዋ፣ ‹‹እኮ እንደ ዘራፊዎቹ?›› አለች የጋቢናዋ። ‹‹ጎበዝ ኧረ ገና ብዙ ጉድ አለ እየተባለ ነው!›› ብለው አዛውንቱ ተረጋጉ አሉን፡፡

ወያላው ሒሳብ ተቀብሎ መልስ ይመልሳል። ‹‹አንተ በቃ ያ ልጅ እዚያው ገብቶ ቀረ?›› ይላል መጨረሻ ከተቀመጡት ጓደኛማቾች አንደኛው። ‹‹የት ይሆን የገባው?›› ብሎ አጠገቤ የተሰየመው ለወሬ ለቀማ ተመቻቸ። ‹‹ምን እባክህ ከአንዱም ሳይሆን ቀረ እኮ?›› አለው። ‹‹ቆይ ምንድነው የተፈጠረው? እኔ እኮ የሚነግረኝ ሰው አጣሁ። እኛ እንደሆንን አገር ስንለቅና ስንሞሸር ካልሆነ አናወራም፤›› አለ አጥብቆ የሦስተኛ ወዳጃቸውን ፍዳ ለመስማት የጓጓው። ‹‹ያው ያኔ እህቱ አልሞተችም? ሁለት ሱቆች ነበሯት። ተናዛለት ነው የሞተችው አሉ። አንድ ፍሬ ናት እኮ ብታያት፡፡ ምስኪን…። አላገባች አልወለደች። ፎቅ የላት ልጅ የላት። ሱቅ ብቻ። ኋላ እሱም ያለውን ነገር ጣጥሎ እዚያው ገባ። ምን ቢሆን ጥሩ ነው? ሱቆች ያሉበት ይዞታ ለልማት ስለታሰበ ፈራሽ ነው ብለው አፈረሱበታ። ግራ ገብቶታል ብታየው…›› አለው።

‹‹ምነው የእህቱን ቀን በሰጠው፤›› አለ ጨዋታውን የጀመረው ወጣት እያዘነ። ምነው አንተ? ምነው ምን አደረገህ? አለች ወይዘሮዋ ወደ ኋላ ዞራ። ‹‹ያዝ እንግዲህ…››› ይላል ከጎኔ የተቀመጠው አስተኳሽ። ‹‹እኔንማ ማን ይነካኛል መሬት የለኝ ንብረት የለኝ፤›› ሲል ጎልማሳው ቀበል አድርጎ፣ ‹‹አይዞህ ትንሽ ቀን ነው። ቦታና መሬት ለምቶ ሲያልቅ ሰው ፈርሶ መሠራት ይጀመርልሃል፤›› ሲለው፣ ‹‹መሠራቱን በለን እንጂ ከፈረስንማ ቆይተናል…›› ብሎ ተመራቂው ኢኮኖሚስት መለሰ። ይኼኔ ጋቢና ከአዛውንቱ ጋር የተሰየመችው ወጣት፣ ‹‹ውይ… ውይ… ውይ…›› ብላ ጮኸች። ‹‹ምነው አይጥ ዓይታ ነው?›› ብሎ በወይዘሮዋና በተደራቢው መሀል የተሰየመው ወጣት ከመጠየቁ፣ ኧረ አይጥስ ጥርስ አለው። እኔን የሚያስጮኸኝ የሰው አይጥ አገሬን ቀርጥፎ በልቶ በአጥንቷ ማስቀረቱ ነው፤›› አለችው። ‹‹እም! ይኼማ የሁላችንም እሪታና ዋይታ እኮ ነው፣ ወይ ነዶ …›› ባዮች መላ ተሳፋሪዎች ነበሩ።

ወደ መዳረሻችን ተቃርበናል። ጎልማሳው ተራውን ስልኩን ሲጎረጉር ቆየና ደውሎ ማውራት ጀመረ። ‹‹እሺ… እሺ… አዎ… አዎ…›› ሲል ቆይቶ፣ ‹‹ያው ዘመኑ አስገደደን እንጂ አድፍጠን መጠባበቅ አልሰለቸንም ብለህ ነው?›› ሲል ተሳፋሪዎች ክው ብለው መተያየት ጀመሩ። አጠገቤ የተሰየመው ወጣት እየተቁነጠነጠ፣ ‹‹ማን ነው? ምንድነው? ወይኔ ኮንዶሚኒየም ሳይደርሰኝ መንገድ ልቀር ይሆን?›› እያለ ተሸበረ። ሁሉም እርስ በእርሱ እየተንሾካሾከ ግን ማንም ደፍሮ ‘የምን ማድፈጥ ነው?’ የሚለው ጠፋ። ጎልማሳው ስልኩን ዘግቶ የታክሲውን ድባብ ሲቃኝ ነገሩ ገባው መሰል አጠገቤ ለተሰየሙት ወጣቶች፣ ‹‹ይገርማችኋል አንድ ሌት ተቀን ደም ተፍቶ የሚሠራ ወዳጅ አለኝ። እና እያደር ኑሮው ሲሻሻል እያዩ የገዛ ጓደኞቹ ቤቱ በር ላይ ጠብቀው አይዘርፉት መሰላችሁ?›› አለ። እንግዲህ የሀብት አመጣጡ ካልታወቀ ብዙ ማውራት ተገቢ ስላልሆነ ሌላ ወግ ተጀመረ፡፡

‹‹ሰማችሁ ግን…›› ብሎ አዲስ ወግ ያስጀመረን አንድ ለግላጋ ወጣት ነው፡፡ ‹‹እኔ የሰሞኑን የዘረፋና የጭካኔ ድርጊቶች ስሰማ ውስጤን እያመመኝ ነው፡፡ ትልልቅ ተብለው ስምና ማዕረግ የያዙ ሰዎች አገር ዘረፉ፣ በገዛ ወገናቸው ላይ ለማመን የሚከብድ ጭካኔ ፈጸሙ ተብሎ ሲነገር አቅለሸለሸኝ…›› ብሎ ተንገፈገፈ፡፡ ይኼኔ አዛውንቱ በወጣቱ ስሜት ተነክተው፣ ‹‹አንተን ፈጣሪ ለትልቅነት ያብቃህ፣ ትልቅ ሆነው ትንሽ በመሆን በአገር ላይ የወነበዱትን ደግሞ እሱው ይፋረዳቸው፤›› ብለው ዕንባ ያቀረሩ ዓይኖቻቸውን መደባበስ ጀመሩ፡፡ በአንድ ጊዜ የታክሲዋ ተሳፋሪዎች ስሜት ጎሸ መሰል ለአፍታ ፀጥታ ወረረን፡፡ በዚህ ሁኔታ ውስጥ ሆነን ሳይታወቀን ወያላው፣ ‹‹መጨረሻ›› ሲለን በእርጋታ መውረድ ጀመርን፡፡ ይኼኔ አዛውንቱ፣ ‹‹እስኪ እርስ በርስ እንቀራረብ፣ እንዋደድ፣ እንከባበር፣ ክፉ ነገሮችን እንፀየፍ፣ በሥነ ምግባር እንታነፅ፣ ልጆቻችንን በሥርዓት እናሳድግ እንጂ አናሳፍራቸው…›› እያሉ ሲሰናበቱን፣ የሞራልና የሥነ ምግባር ዝቅጠት ጉዳይ የብዙዎች መነጋገሪያ ሆኖ ነበር፡፡ አዎ! አገርን የሚያጠፋው የሞራልና የሥነ ምግባር ዝቅጠት ነው፡፡ ይኼንን ችግር ብሔራዊ አጀንዳ ማድረግ የግድ መሆን አለበት! መልካም ጉዞ!

 

Latest Posts

- Advertisement -

ወቅታዊ ፅሑፎች

ትኩስ ዜናዎች ለማግኘት