የአፍሪካውያንን ዘርፈ ብዙ ችግሮች ለመቅረፍና የእርስ በርስ መደጋገፍን መርህ በማድረግ የተመሠረተው የአፍሪካ አንድነት ድርጅት (አአድ)፣ የተነሳለትን ዓላማ ብዙም ሳያሳካ ወደ ኅብረትነት መሸጋገሩን የሚገልጹ በርካታ ትንታኔዎች ይቀርባሉ፡፡
ድርጅቱ ከምሥረታው የአፍሪካውያንን ኢኮኖሚያዊ፣ ፖለቲካዊ፣ ማኅበራዊና ባህላዊ ማንነቶችን በማጎልበት አኅጉሪቱ ባላት ዕምቅ ሀብትና የሰው ኃይል ልክ በዓለም የዲፕሎማሲ መስክ የበኩሏን አስተዋፅኦ ማበርከት ትችል ዘንድ ምን መደረግ አለበት? በሚል ማዕቀፍ ውስጥ ነበር ድርጅቱ ምሥረታውን በአዲስ አበባ ያደረገው፡፡
በምሥረታው ወቅት አብዛኞቹ የአኅጉሪቱ አገሮች በቅኝ ግዛት ቀንበር ሥር የሚሰቃዩ ከመሆናቸው አንፃር፣ የድርጅቱ ዋነኛ የትግል ማጠንጠኛም አፍሪካውያን ከተጫነባቸው የቅኝ ግዛት ቀንበር ማላቀቅ ነበር፡፡
በዚህ ሥሌት ብቻ የሚለካ ከሆነ የአፍሪካ አንድነት ድርጅት የሚጠበቅበትን ተወጥቷል ማለት ይቻላል በማለት፣ ድርጅቱ ሕልሙን ሳያሳካ ወደ ኅብረትነት ተለውጧል የሚለውን ትችት የሚቃወሙ አስተያየት ሰጪዎች አሉ፡፡
እንዲህ ካለው መከራከሪያ በተቃራኒው የሚቆሙ ወገኖች ደግሞ፣ የአብዛኞቹ የአፍሪካ አገሮች ከቅኝ ግዛት መላቀቅ ቅኝ ገዥዎቹ በተራዘመ የነፃነት ጦርነት መሰልቸትና የሚፈልጉዋቸውን አሻንጉሊት መንግሥታት በአኅጉሪቱ መመሥረታቸው እንጂ፣ የድርጅቱ የተጠናከረ ግፊት ባስተካከለው ጫና አይደለም በማለት ይሞግታሉ፡፡
ለዚህም እንደ መከራከሪያ የሚያቀርቡት ነጥብ ደግሞ ድርጅቱን ለመመሥረት እንኳን የነበረውን የተቃረነና ሊቀራረብ የማይችል የሚመስለውን፣ ሁለት ቡድኖች በምሥረታው ወቅት የያዙትን አቋም ነው፡፡ ለዚህ የተካረረ ሁለት ቡድን ወደ አንድ መምጣትና ድርጅቱ እንዲመሠረት ላደረጉት ከፍተኛ አስተዋፅኦ፣ የኢትዮጵያ መሪ የነበሩት አፄ ኃይለ ሥላሴ በታሪክ ሲዘከሩ የሚኖሩትም ለዚህ ነው፡፡
ከዚህ በተጨማሪም ድርጅቱ ከምሥረታው ጀምሮ ሲያራምደው የነበረው በአገሮች የውስጥ ጉዳይ ጣልቃ አለመግባት በሚለው መርህ፣ ጠንካራ ውሳኔዎችንና ጫናዎችን በአገሮች ላይ መውሰድ ባለመቻሉም ትችት ይቀርብበት የነበረ ሌላው ጉዳይ ነው፡፡ በዚህም ምክንያት የተነሳ በመፈንቅለ መንግሥት አማካይነት ሥልጣን የያዙ መሪዎችን እንኳን ከድርጅቱ የመሪዎች ጉባዔ ለመከልከል አለመቻሉ፣ እንደ አንድ ትልቅ ድክመት ይቆጠርበት ነበር፡፡
ከሁሉም በላይ ደግሞ ከጥንስሱ ከፀረ ቅኝ ግዛት ዓላማ ተላቋል ለማለት አስቸጋሪ እንደሆነ የሚሞግቱትና ድርጅቱ ምንም አልሠራም ወደሚል ድምዳሜ የሚደርሱ አስተያየት ሰጪዎች፣ አባል አገሮች የሚጠበቅባቸውን ዓመታዊ መዋጮ እንኳን አስገድዶ ሊያስከፍል የሚችል አቅም የለውም በማለት ይተቹታል፡፡
በዚህም መሠረት በአኅጉሪቱ የሚከናወኑ ዓበይት የሰላምና የደኅንነት ማስጠበቅ፣ ለሰው ሠራሽና ተፈጥሮአዊ አደጋዎች፣ ለመሠረተ ልማት ግንባታ፣ እንዲሁም የአኅጉሪቱን በርካታ ችግሮች ለመቅረፍ የሚካሄዱ መነሳሳቶችን ወጪ ለመሸፈን በአኅጉሪቱ አገሮች መዋጮ ሳይሆን ከአውሮፓ አገሮችና አሜሪካን ከመሳሰሉ ለጋሽ አገሮች የሚገኝ ዳረጎት ላይ የተንጠላጠለ መሆኑ፣ ከመነሻው የተፀየፈውን ቅኝ ግዛት በሌላ መንገድ እንዲተገበር አድርጓል በማለት ይተቻሉ፡፡
በእነዚህ ሁሉ ወጣ ውረዶች መካከል ሲዋልል የነበረው የአፍሪካ አንድነት ድርጅት (አአድ)፣ እ.ኤ.አ. በ2002 በደቡብ አፍሪካ ደርባን በተደረገ የመሪዎች ጉባዔ ወደ አፍሪካ ኅብረት መሸጋገሩን አውጆ ነበር፡፡
ከአአድ ወደ አፍሪካ ኅብረት የተሸጋገረው የአኅጉሪቱ ከፍተኛ ተቋም በአኅጉሪቱ አዲስ አደረጃጀት በመከተል፣ የአኅጉሪቱን ዜጎች ዘርፈ ብዙ ችግሮች ለመፍታት እሠራለሁ ካለ 16 ዓመታት ተቆጥረዋል፡፡ ወደ ኅብረት ተሸጋግሮ የአንድ ጎረምሳ ዕድሜ የተጓዘው ይህ ተቋም፣ አሁንም ቢሆን በርካታ ችግሮች በተለይ ከሰላምና ከፀጥታ ጉዳዮች ጋር፣ እንዲሁም ጤናና ትምህርት የመሳሰሉ ጉዳዮች ከማሳካት አንፃር ስንዝር ያህል መጓዙን የሚጠይቁ በርካቶች ናቸው፡፡
ምንም እንኳን ኅብረቱ እንደ ድርጅት በአገሮች ጉዳይ ጣልቃ ያለመግባት መርህን ቢሽረውም፣ ይህ ነው የሚባል ተፅዕኖ በአገሮች ላይ ለማሳረፍ ግን አሁንም ቢሆን አልቻለም፡፡ ሆኖም ቢያንስ በመፈንቅለ መንግሥት ሥልጣን የጨበጡ መሪዎችን፣ ከኅብረቱ አባልነት የማገድ ዕርምጃው የሚያስመሠግነው እንደሆነ ይገልጻሉ፡፡
ይሁን እንጂ እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ ኅብረቱ የዕለት ተዕለት የሥራ ማስኬጃ ወጪውን እንኳን በለጋስ አገሮች ይሁንታና ዳረጎት ላይ በመመርኮዝ መጓዙ፣ የድርጅቱን ጥንካሬና ለተነሳላቸው ግቦች መሳካት ያለውን ቁርጠኝነት ጥያቄ ምልክት ውስጥ ከቶታል፡፡
ከ60 በመቶ በላይ የኅብረቱ ወጪ ከዚህ ቀደም ቅኝ ገዥ ከነበሩ የአውሮፓ አገሮችና ከአሜሪካ እየመነጨ፣ እንዴት ነው ኅብረቱ ያለ ምንም እጅ ጥምዘዛ የአኅጉሪቱን ሕዝቦች ብቻ ጥያቄ ሊያስተናግድና ሊመልስ የሚችለው የሚለው ጥያቄ አሁንም ምላሽ ያላገኘ፣ ግን አፋጣኝ ምላሽና መፍትሔ የሚሻ ዓብይ አጀንዳ እንደሆነ በርካቶች ያስረዳሉ፡፡
በእነዚህ ሁሉ ውጣ ውረዶች እየተጓዘ የሚገኘው የአፍሪካ ኅብረት እ.ኤ.አ. ከ2016 ጀምሮ ግን ቢያንስ በውጪ ረገድ ራሱን ለመቻልና አኅጉሪቱን ወደ አንድነት ለማምጣት በርካታ ሥራዎች እያከናወኑ እንደሆነ ይገልጻል፡፡
በሩዋንዳ ፕሬዚዳንት ፖልካ ጋሜ አስተባበሪነት የተጀመረው ኅብረቱን የማሻሻል ሥራ፣ ቢያንስ በዕቅድ ደረጃ ከዚህ ቀደሙ በተሻለ ሁኔታ ነገሮችን እያጠበበና የትኩረት አቅጣጫውን በማጥራት በመጓዝ ላይ ያለ ይመስላል፡፡
በዋነኛነት አምስት የማሻሻል ዓምዶች ያሉት የፖል ካጋሜ ዕቅድ በአኅጉሪቱ አንድነት፣ ሰላምና ፀጥታ መስፈን፣ ተቋማዊ አደረጃጀት፣ ዓመታዊ ጉባዔዎችን መቀነስ፣ እንዲሁም ለአኅጉሪቱ የሰላም ፈንድ እያንዳንዱ አባል አገር ከገቢ ንግዱ 0.2 በመቶ ታክስ ለኅብረቱ ማዋጣት ላይ ያተኩራል፡፡
በዚህ ማዕቀፍ የተለያዩ ሥራዎችን ሲያከናውን የከረመው ኅብረቱን ማሻሻል የሚለው ሐሳብ ባለፈው ሳምንት መጨረሻ፣ የኅብረቱ መቀመጫ በሆነችው አዲስ አበባ በተካሄደ አስቸኳይ የመሪዎች ጉባዔ ወደ አዲስ ምዕራፍ ተሸጋግሯል፡፡
ቅዳሜ ኅዳር 8 ቀን የጀመረውና እሑድ ኅዳር 9 ቀን 2011 ዓ.ም. የተጠናቀቀው የአፍሪካ ኅብረት አስቸኳይ የመሪዎች ጉባዔ፣ በተለይ የኅብረቱን የሰላም ፈንድ መዋጮን በተመለከተ ጠንከር ያሉ ውሳኔዎችን አሳልፏል፡፡
በዚህም መሠረት ለሁለት ቀናት የተካሄደው አስቸኳይ የመሪዎች ጉባዔ በዋነኛነት የኅብረቱን ማሻሻያዎች ቅርፅ ማስያዝ ላይ፣ እንዲሁም በይፋ ሥራ ስለጀመረው የሰላም ፈንድ የተመለከቱ ጠንካራ ውሳኔዎችን አሳልፏል፡፡
የኅብረቱ ማሻሻያዎችን በተመለከተ እየተካሄዱ ያሉ ጥናቶችን መሠረት በማድረግ ዕርምጃዎች እንዲወሰዱና የኮሚሽኑ የሥራ መደቦች በመታጠፍ፣ አልያም በመዋሀድ አዲስ አደረጃጀት እንዲፈጠር የሚያስችሉ አሠራሮች እንዲተገበሩ ወስኗል፡፡
ከዚህ በተጨማሪም ስምንት የነበሩት የኅብረቱ ኮሚሽኖች ወደ ስድስት ዝቅ እንዲሉ፣ የኅብረቱ ኮሚሽነር ሆኖ የሚመረጠው ሰው ወንድ ከሆነ ምክትሉ ሴት እንድትሆን ወስኗል፡፡
ባለሙያና የካበተ ልምድ ያላቸውን አፍሪካውያንን ወደ ኅብረቱ ለማምጣት በሚደረገው ጥረት ደግሞ፣ ኮሚሽነሩን የሚያግዙ ዋና ጸሐፊና ማኔጂንግ ዳይሬክተር ብቃትን መሠረት ባደረገ መሥፈርት ተወዳድረው እንዲቀጠሩ በሰሞኑ 11ኛው አስቸኳይ የአፍሪካ መሪዎች ጉባዔ ከተወሰኑ ዓበይት ውሳኔዎች አንዱ ነው፡፡
ይህ ውሳኔ ጥናት እየተደረገበትና እየተሞከረ የሚሄድ ሲሆን፣ ኅብረቱን ሙሉ በሙሉ የማሻሻል ውሳኔ ተፈጻሚ የሚሆነው ግን እ.ኤ.አ. ከ2021 ጀምሮ እንደሚሆንም በአስቸኳይ ስብሰባው መቋጫ ወቅት ተነግሯል፡፡
የኅብረቱን የሰላም ፈንድ አስመልክቶ ውሳኔ ያሳለፈው ይህ አስቸኳይ ጉባዔ፣ የሚጠበቅባቸውን መዋጮ በማይከፍሉ አገሮች ላይ ደግሞ ከኅብረቱ እስከ ማገድ የሚደርስ ዕርምጃ እንዲወሰድ ወስኗል፡፡
የአፍሪካ ኅብረት የሰላም ፈንድ የተጠነሰሰው እ.ኤ.አ. በ1993 ሲሆን፣ በዋነኝነት በአኅጉሪቱ የሚከናወኑ የሰላምና የፀጥታ እንቅስቅሴዎችን በገንዘብ ለመደገፍና ለማስተባበር የታለመ አወቃቀር ነበር፡፡ ድርጅቱ ወደ ኅብረትነት ሲቀየር ከተቋቋሙት የኅብረቱ አምስት ዓምዶች መካከል አንደኛው ይህ የሰላም ፈንድ ነበር፡፡ ነገር ግን በተለያዩ ምክንያቶች ይፋዊ ምሥረታው እዚህ ድረስ ዘልቋል፡፡
የአፍሪካ ኅብረት ጠቅላላ ጉባዔ ይህ የሰላም ፈንድ በዋነኛነት ሦስት መሠረታዊ ሥራዎችን እንዲያከናውን አቅዷል፡፡ እነዚህም የድርድርና የቅድመ መከላከል ዲፕሎማሲ፣ ተቋማዊ አቅምን መገንባት፣ እንዲሁም የሰላም ግንባታ ድጋፍ እንቅስቃሴዎች የሚባሉት ናቸው፡፡
በዚህ ማዕቀፍ ውስጥ ባለፈው ቅዳሜ ይፋ የሆነው የኅብረቱ ፈንድ 100 ሚሊዮን ዶላር በጀት እንደተያዘለትና በቅርቡም ወደ ሥራ ይገበል ተብሎ እንደሚጠበቅ ይፋ ተደርጓል፡፡
የሰላም ፈንዱ አደረጃጀት ከአምስት የአፍሪካ አገሮች የተውጣጣና በዳይሬክተሮች ቦርድ የሚመራ ሲሆን፣ ከእነዚህ የቦርድ አባላት መካከል ኢትዮጵያዊቷ እሌኒ መኰንን አንዷ ናቸው፡፡
የአኅጉሪቱን ዘርፍ ብዙ ችግሮች ከመቅረፍ አኳያ ከፍተኛ ድርሻ ይወጣል ተብሎ የሚገመተው ይህ የሰላም ፈንድ ተፈጻሚ ይሆን ዘንድ፣ መሪዎቹ ቁርጠኛ የሚባል ውሳኔ መወሰናቸው በብዙ ተንታኞች ዘንድ እየተወደሰ ነው፡፡
በተለይ አጀንዳ 2063ን ለማሳካት እንደ መልካም መደላድል ሊሆን እንደሚችልም የሚገምቱ በርካቶች ናቸው፡፡ ለዚህ የሚያቀርቡት ምክንያት ደግሞ የአፍሪካ አገሮች ቢያንስ ሰላምና ደኅንነት ለማረጋገጥ የሚከናወኑ ሥራዎችን ወጪ መሸፈን ከቻሉ፣ የእኔነት ስሜትን በመጨመር ወደ ሌሎች አኅጉራዊ ትብብሮች ለማደግ መልካም አጋጣሚን ይፈጥራል ከሚል ነው፡፡
በዚህም መሠረት ለዚህ የሰላም ፈንድ ዕቅዶች መሳካት የሚጠበቅባቸውን መዋጮ የማያዋጡ አገሮች ላይ ጠንከር ያሉ ዕርምጃዎች እንዲወሰዱ የተወሰነ ሲሆን፣ ውሳኔው ማዕቀብንም ያካተተ እንዲሆን ተስማምተዋል፡፡
ከዚህ አንፃር በውሳኔው መሠረት ለተከታታይ ስድስት ወራት ከሚጠበቅባቸው መዋጮ ግማሹንና ከዚያ በላይ ያልከፈሉ አገሮች፣ የተለያዩ ደረጃዎችና ተፈጻሚነት ያላቸው ማዕቀቦች ይጣልባቸዋል፡፡
ማዕቀቡም በዋናነት የማስጠንቀቂያ፣ የረዥም፣ እንዲሁም የአጭር ጊዜ ማዕቀቦች በሚሉ ምዕራፎች የተከፋፈለ ነው፡፡
በማስጠንቀቂያ የማዕቀብ ምዕራፍ የሚጠበቅባቸውን መዋጮ መክፈል ያልቻሉ አባል አገሮች፣ በኅብረቱ የተለያዩ ስብሰባዎች ሐሳብ የመስጠት መብታቸው ይታገዳል፡፡
በመካከለኛው ምዕራፍ ማስጠንቀቂያ ዳግም በኅብረቱ ሥር ከሚገኙ ተቋማት አባልነት፣ የተቋማት መቀመጫ የመሆን፣ ዜጎቻቸው ከአፍሪካ አገሮች ምርጫ ታዛቢነት፣ እንዲሁም በኅብረቱ የተለያዩ ሥራ መደቦች የመቀጠር ዕገዳ እንደሚጣልባቸው የተገለጸ ሲሆን፣ የረዥም ጊዜ ማዕቀቡ ደግሞ ከኅብረቱ አባልነት እስከ መታገድ የሚደርስ መሆኑ ተገልጿል፡፡
አሁን ለዚህ ሰላም ፈንድ ተገቢውን መዋጮ እያዋጡ ያሉ አገሮች ኢትዮጵያን ጨምሮ አሥራ አንድ ሲሆኑ፣ አኅጉራቱ የራሷን ጉዳይ በራሷ ለመፍታት በምታደርገው ጥረት የአባላት መዋጮ ዝቅተኛ መሆን ዋና ራስ ምታት ነው፡፡ ምንም እንኳን አዲሱ ውሳኔ ችግሮችን ያሻሽላል የሚል ተስፋ የተጣለበት ቢሆንም፣ አሁን ተገቢውን መዋጮ የሚፈጽሙ አገሮች ቁጥር አነስተኛ መሆን የውሳኔውን ተፈጻሚነት አስቸጋሪ እንደሚያደርገው የሚናገሩ አሉ፡፡ ለማንኛውም የዚህ ውሳኔ ውጤትና ለአኅጉሪቱ ሰላም፣ ደኅንነት አንድነት የሚያበረክተው አስተዋፅኦና ውጤት በቀጣዩ የመሪዎቹ ጉባዔ የሚታይና የሚለካ ይሆናል፡፡