Thursday, June 13, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

ሥነ ፍጥረትየጥርኝ ቡና የዓለማችን ውዱ ቡና

የጥርኝ ቡና የዓለማችን ውዱ ቡና

ቀን:

ታምሩ አ.

የጥርኝ ቡና ባህል በመቶዎች በሚቆጠሩ ዓመታት ወደ ኋላ መለስ ብለን ሆላንዶች ኢንዶኔዥያን ቅኝ ግዛት ወደ ያዙበትን ዘመን ይወስደናል፡፡ በደቡብ ምሥራቅ የምትገኘው ኢንዶኔዥያ 240 ሚሊየን ሕዝብ የሚኖርባት አገር ስትሆን በዓለማችን የጥርኝ ቡና አምራች ከሆኑ አገሮች መካከል ዋነኛዋ አገር ነች፡፡

በ18ኛው ከፍለ ዘመን መባቻ ላይ ሆላንዳውያን በቅኝ ግዛት በያዝዋት ኢንዶኔዥያ ለውጭ ገበያ የሚቀርብ ቡና ልማት በስፋት ይካሄድ ነበር፡፡ ታዲያ እነዚህ ሆላንዳውያን፣ የኢንዶኔዥያ ገበሬዎችና የቡና ልማት ሠራተኞች አንዲት ፍሬ ቡና ለግላቸው እንዳያደርጉና እንዳይጠጡ ይከለክሏቸው ነበር፡፡ ችግር ብልኃትን ይወልዳል እንዲሉ ኢንዶኔዥያውያን አካባቢያቸውን ማማተር ሲጀምሩ ዘወትር ዘንባባ ዛፍ ላይ የማያጧት ጥርኝ ዓይነ ምድሯ በቡና ፍሬ የተሞላ ነው፡፡ የአካባቢው ጥርኞች ዘወትር የቡና ፍሬ ስለሚበሉ ነበር ዓይነ ምድራቸው የቡና ፍሬ ብቻ የሆነው፡፡ ከዚያ በኋላ ኢንዶኔዥያውያን ይህንን ዓይነ ምድር ከየሜዳው እየሰበሰቡ በማጠብ ቡናውን ቆልተው በመጠጣት የቡና አምሮታቸውን ማርካት ችለዋል፡፡ ልብ ብለው ሲያስተውሉ ደግሞ ይህ ዓይነቱ ቡና ከዚህ በፊት ሲጠጡት ከነበረው በጣም የተሻለ ጣዕም እንዳለው ተገነዘቡ፡፡ ይህ ታዲያ የጥርኝን ዓይነ ምድርን በጣም ተፈላጊ አድርጎታል፡፡ ቀስ በቀስ ወሬው ቅኝ ገዥዎች ጆሮ ሲደርስም ተፈላጊነቱ በእጥፍ ጨምሮ ገበያ ላይ ሲቀርብ ዋጋው ውድ ሆነ፡፡ ይህንን  የተረዱት ገበሬዎች እየሰበሰቡ አጥበው በመቁላት ምርጥ ጣዕም ያለው ቡና ያዘጋጁበታል፡፡ የጥርኝ ኑሮ በዱር በገደል ቢሆንም ገበሬዎች ሜዳና ቆንጥሩን እያሰሱ ቡናውን ይለቅማሉ፡፡ ይህም ቡና በተለያዩ ዓለም አገሮች የተለያየ ስያሜ ያለው ሲሆን፣ በኢንዶኔዥያና በተቀረው ዓለም ኮፒ ሉዋክ (Kopi Luwak) በማለት ይታወቃል፡፡ ትርጓሜውም የጥርኝ ቡና ማለት ነው፡፡

- Advertisement -

ጥርኝ የምትመገበው በተገቢው የበሰለ ቀይ እሸት ቡና እየመረጠች ሲሆን ከተመገበችም በኋላ ጨጓራዋ የቡናውን ገለባ ከፍሬው ይለየዋል፡፡ በዚህ የምግብ ውህደት ሒደት ፍሬው ተለይቶ  በሰውነትዋ ውስጥ በሚገኘው ኤንዛይም እየተለወሰ ወደ አንጀት ይሄድና ከዚያም በዓይነ ምድር መልክ ይወጣል፡፡ ከጥርኝ ጨጓራ የሚወጣው ኤንዛይም በቡና ፍሬው ውሰጥ በመዝለቅ የቡናውን ጣዕምና መዓዛ  ሚዛኑን የጠበቀና መልካም እንዲሆን ያደርገዋል፡፡ ይህን ሒደት አልፎ በደንብ ከታጠበና በተገቢው መንገድ ከተቆላ መደበኛ ቡና ውስጥ የሚታየውን የሚመር ጣዕም እንዲጠፋ በማድረግ ቡናው የተለየ ጣዕምና ለስላሳ መዓዛ እንዲኖረው ያደርጋል፡፡

ራሱን የጥርኝ ንጉሥ በማለት የሚጠራው ኢንዶኔዥያዊው ጉዋን ሱፕራዱ በየጊዜው እያደገ የመጣውን የጥርኝ ጥሬ ቡና ፍላጎት ለሟሟላት ከፍተኛ ጥረት ሲያደርግ መቆየቱን ይናገራል፡፡ ከጥርኝ ዓይነ ምድር የተዘጋጀ ቡና ፍላጎት በእጅጉ እየጨመረ መሆኑን እርሱና ሌሎች ቡና ላኪዎች ይናገራሉ፡፡ በኢንዶኔዥያ ሱማትራ ግዛት ምዕራብ ለምቻንግ ወረዳ በሚገኝ እርሻ ቦታው የሚገኙ የራሱ ንብረት የሆኑትን ጥርኞች የዚህ ሰው ልዩ መለያውና ግዛቷን ደግሞ የጥርኞች ልዩ መናኸሪያ አስብሏታል፡፡ አሁን ያለኝ አርባ ጥርኞች ሲሆኑ የእኔ ፍላጎት ግን የእነዚህን ጥርኞች ቁጥር አንድ መቶ ሃምሳ ማድረስ ነው የሚለው ሱፕራዱ አክሎም ሲገልጽ ይህ ፍላጎቴ የመነጨው የዚህ ቡና ዓይነት ፍላጎት ከጊዜ ወደጊዜ ማሻቀቡ እንደሆነ ይናገራል፡፡

ይህ ዝናውና ተፈላጊነቱ እየገነነ የመጣው የጥርኝ ቡና ለደቡብ እስያ አገሮች የገቢ ምንጭ ሆኗል፡፡ የጥርኝ ቡና ያለው ልዩ ጣዕምና መዓዛ  የተለየ መሆኑ በእጅጉ ተፈላጊ አድርጎታል፡፡ በዓለም ገበያ አንድ ኪሎ የጥርኝ ቡና እስከ 800 ዶላር ይሸጣል፡፡ ይህ ደግሞ አሁን በኢትዮጵያ ባለው የውጪ ምንዛሪ ምጣኔ መሠረት አንዱ ኪሎ ብር 21,600  በላይ ያወጣል ማለት ነው፡፡ ከጥርኝ የተዘጋጀ ቡና አንዱ ሲኒ በችርቻሮ በለንደን የእስፔሻሊቲ ቡና መሸጫ ሱቆች 100 ዶላር ያስገኛል ወደ ኢትዮጵያ ብር ሲመነዘር አንዱ ስኒ ከብር 2,700 በላይ ያወጣል ማለት ነው፡፡ የጥርኝ ቡና ገዥዎች ዋነኞቹ ጃፓን፣ ታይዋን፣ ደቡብ ኮሪያ ሲሆኑ እንግሊዝ፣ አሜሪካ፣ አውስትራሊያና ሌሎቹም እንደየአቅማቸው የሚሸምቱ ናቸው፡፡ ቡናው እንዲህ ውድ ዋጋ ወጥቶበትም እንደ ልብ የማይገኝ መሆኑ ይነገራል፡፡ በአውስትራሊያ የሚገኝ አንድ ካፌ በሳምንት ውስጥ ሊሸጥ የቻለው ሰባት ስኒ ብቻ ነው፡፡ ኢንዶኔዥያዊው ሱፕራዱ ሲናገር የጥርኝ ቡና ከገበያ እንደምንገዛው ተሸከርካሪ ሆኖ ቢቆጠር ሮልስሮይ የተባለውን መኪና ዓይነት ተደርጎ ሊወሰድ ይችላል በማለት በጣም ውድነቱን ይገልጻል፡፡

ኢርዊን የተባለ ቡና ወደ ውጪ ላኪ ኢንዶኔዥያዊ ነጋዴ በአንድ ወቅት ሽያጩ 50 በመቶ እንዲጨምር ያደረገ መሆኑን ይገልጻል፡፡ ለዚህም ምክንያቱ ቡናው በገበያ ከሚገኙ የቡና ዓይነቶች ቀዳሚ የቡና ዓይነት እየሆነ በመምጣቱ እንደሆነ ይናገራል፡፡ ቡናው ከፍተኛ ተፈላጊነት ያለውና በአቅርቦቱም ውስን መሆኑ የብዙዎችን ትኩረት እየሳበ ይገኛል፡፡ በአገሪቱ በቡና ችርቻሮ የተሰማሩ ነጋዴዎችም እንደሚሉት ከፍተኛ ገቢ ያላቸው የኢንዶኔዥያ ዜጎች የዚህ ቡና ፈላጊዎች መሆናቸው ሌላው የቡናው ተፈላጊነት መጨመር አንዱ ምክንያት መሆኑን ይገልጻሉ፡፡

የኢንዶኔዥያ ዋና ከተማ ነዋሪ የሆነው ጋላንግ ሱሱንግ ለአዣንስ ፍራንስ ፕሬስ (ኤኤፍፒ) ሐሳቡን  ሲገልጽ ቡና የመጠጣት ልምድ በፍፁም የለኝም፤ ሆኖም ግን የጥርኝ ቡና መጠጣት ከጀመርኩ የኑሮ ዘይቤዬ ተቀይሯል፡፡ በዚህም ምክንያት የቡና ሱሰኛ ልሆን ችያለሁ፡፡ የጥርኝ ቡና የምጠጣው ለጤና ጠቃሚ በመሆኑ ከአስም፣ ከፓርኪንሰን፣ ከትልቁ አንጀት ካንሰርና ስኳር በሽታ የሚከላከል መሆኑን በማመኔ ነው ሲል ይናገራል፡፡

የጥርኝ ቡና ንግድ በደራባቸው እንደ ኢንዶኔዥያ ያሉ አገሮች በጫካ ከሚኖሩ ጥርኞች ከሚመረተው በተጨማሪ የዶሮ ቤት መሳይ ኬጆች ጥርኞችን በማኖር ቡና የማምረት የቆየ ልምድ አላቸው፡፡ በነዚህ አገሮች ጥርኞች በተለያየ መንገድ እየተጠመዱ ይያዛሉ፡፡ በሚያዙበት ጊዜ ከሚደርስባቸው የመቁሰል አደጋ በተጨማሪ ከተያዙ በኋላ በበቂ የቡና ፍሬ በምግብነት የማይቀርብላቸው ከመሆኑም በላይ በከፋ የአያያዝ ምክንያት ለጉዳትና ለሞት  እንደሚዳረጉ የእንስሳት መብት ተሟጋቾች ይናገራሉ፡፡ በዓለም ላይ የተለያዩ የጥርኝ ዝርያዎች ያሉ ሲሆን፣  በዚሁ አደን ምክንያት አንዳንዶቹ ዝርያቸው ለመጥፋት መቃረቡ ነገራል፡፡

በወጥመድ የተያዙ ጥርኞች የቡና ምርት ጉዳይ ሲነሳ ከዚሁ ጋር ተያይዞ የሚነሳው በዚህ መንገድ የሚመረተው የቡና ጥራት ዝቅተኛ የመሆኑ ጉዳይ ነው፡፡ በጫካ የሚመረት ቡና በዚህ መልኩ ከሚመረት ቡና ጋር ሲነፃፀር ከፍተኛ የጥራት ልዩነት ያለው መሆኑ ይነገራል፡፡ አሁን አሁን ትክክለኛውን የጫካ የጥርኝ ቡና በወጥመድ ከተመረተው ለመለየት በሚያስቸግር መልኩ ገበያውን እያጥለቀለቀው መሆኑን ይጠቁማሉ፡፡ እንደ ‹‹World Society for Protection of Animals›› ያሉ ተሟጋቾች ይህን ችግር ለመከላከል የጥርኝ ቡና ችርቻሮ ላይ የተሰማሩ ነጋዴዎች የጥርኝ ቡና ሲረከቡ ትክክለኛ ካልሆነው ጋር መለየትና ትክክለኛ ያልሆነውን ምርት ከመደርደሪያቸው ማስወገድ ያለባቸው ሲሆን ለትክክለኛው የጥርኝ ቡና የሰርተፍኬሽን ሥርዓት መዘርጋትና በሥራ ላይ ማዋል እንዲሁም በመንግሥታት በኩል ጠንካራ ቁጥጥርና ሕግን በሥራ ላይ ማዋልን በመፍትሔነት ይጠቁማሉ፡፡

ክብደቱ ከ25 እስከ 45 ፓውንድ የሚደርሰው የአፍሪካ ጥርኝ ከሴኔጋል እስከ ሶማሊያ፣ በደቡባዊው የአፍሪካ ክልል ደግሞ በናሚቢያና በምዕራባዊ ደቡብ አፍሪካ እንደሚገኝ ጥናቶች ይጠቁማሉ፡፡ በአፍሪካ የሚኖረው ጥርኝ በኢንዶኔዥያ ከሚገኘው የሚለየው በዛፎች፣ ረዣዥም ሳሮችና ቁጥቋጦዎች ውስጥና ውኃ ገብ መሬቶች ላይ የሚኖር መሆኑ ነው፡፡ በኢትዮጵያ ጥርኝን በማጥመድ ዝባድ ማምረት የቆየ ልምድ ነው፡፡ ይህ የዝባድ ምርት ለሽቶ ምርት ይውላል፡፡ ቡና አብቃይ በሆኑ የአገራችን ክፍሎች የሚገኙ ጥርኞች ልክ ኢንዶኔዥያ እንደሚገኙት ጥርኞች ጥሬ ቡና የሚመገቡና ከዓይነ ምድር ጋር የተቀላቀለ ቡና እንደሚጥሉ የተደረጉ ጥናቶች ይጠቁማሉ፡፡

በመሆኑም በአገራችን የጥርኝ ቡና በጥናት፣ ምርምርና በሥልጠና  ተደግፎና በመስኩ የሠለጠነ የሰው ኃይል በመመደብ እንዲመረት ተደርጎ ለውጪ ገበያ ቢቀርብ አገራችን በዘርፉ የምታገኘውን ጥቅም ከፍ የሚያደርገው፣ ለብዙ ዜጎቻችን የገቢ ምንጭና የሥራ ዕድል ስለሚፈጥር በዘርፉ በትኩረት ሊሠራ ይገባል፡፡

ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እየገለጽን፣ በኢሜይል አድራሻቸው   [email protected] ማግኘት ይቻላል፡፡

 

 

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

[ክቡር ሚኒስትሩ በመንግሥት የሚታወጁ ንቅናቄዎችን በተመለከተ ባለቤታቸው ለሚያነሱት ጥያቄ ምላሽ ለመስጠት እየሞከሩ ነው]

እኔ ምልህ? እ... ዛሬ ደግሞ ምን ልትይ ነው? ንቅናቄዎችን አላበዙባችሁም? የምን ንቅናቄ? በመንግሥት...

የመንግሥት የ2017 ዓ.ም በጀትና የሚነሱ ጥያቄዎች

የ2017 ዓመት የመንግሥት ረቂቅ በጀት ባለፈው ሳምንት መገባደጃ ለሚኒስትሮች...

ከፖለቲካ አባልነትና ከባንክ ድርሻ ነፃ የሆኑ ቦርድ ዳይሬክተሮችን ያካተተው ብሔራዊ ባንክ ያዘጋጃቸው ረቂቅ አዋጅና መመርያዎች

የኢትዮጵያ የብሔራዊ ባንክ የፋይናንስ ተቋማትን የተመለከቱት ድንጋጌዎችንና የባንክ ማቋቋሚያ...

የልምድ ልውውጥ!

እነሆ መንገድ ከቦሌ ሜክሲኮ። አንዱ እኮ ነው፣ ‹‹እንደ ሰሞኑ...