- Advertisement -

የበዕውቀቱ ሥዩም ‹‹መግባት እና መውጣት››

በሽብሩ ተድላ

መግባት እና መውጣት በሚል ስያሜ በበዕውቀቱ ሥዩም የተዘጋጀች (እንደ ደራሲው፣ ከአስተናጋጁ ማስታወሻ የተቀነጨበ) ትንሽ መጽሐፍ የግል አስተያየት እነሆ፡፡ የመጽሐፏ ስያሜ ከክረምት በርነት ከቤትሆቨን ካፌ መስተንግዶ ነው የተወሰደው፤ ክረምት በር ሆኖ መግባትና መውጣት ሲቀጥል ተስተናጋጁም በካፌ መግባትና መውጣት፣ እንዲሁ፡፡ 

የመጽሐፏ አካል በገጽ ብዛት፣ በወረዱ ስፋት፣ በጣም መጠነኛ ቢሆንም፣ መጽሐፏ ያዘለችው ቁም ነገር፣ ያካበተችው ሥዕላዊ አቀራረብ፣ የአጻጻፉ ለዛ፣ ግንትር ባህል ሰበር፣ አንቱ የሚያሰኝ የአጻጻፍ ስጦታና የላቀ ዕውቀት፣ ጸሐፊው እንደተካነ ያመለክታሉ፡፡ አስተያየት መስጠት መብት ከሆነ፣ ደራሲው ቁንጮ የአማርኛ ደራሲነትን ተቀናጅቷል፡፡ ከአጻጻፉ ስልቶች ጎልተው የሚታዩ የተለያዩ ድርጊቶችን የማገናኛ ስልት ድልድይ ምቹነትና ቀጥተኛነት ለተቃራኒ ሁኔታዎች መግለጫ ስንኝ መሰል ግንኙነት (ኢፍትሐዊነትን እንጂ ፍትወትን አላስከተለም የወ/ ይርገድ ሽቶ የተሸመተበት ዋጋ ገጽታ ሲታይ) መወርወር መጽሐፏን ከቁንጮ የአማርኛ ድርሰቶች አልጋ ላይ፣ በትራስ አካባቢ ያስቀምጣታል፡፡

ድርሰቱ እንደተለመደው አንድ ግለሰብ ወይም ጥቂት ግለሰቦች ዙሪያ የሚያጠነጥን አይደለም፡፡ ምንም ባጻጻፍ ሥልት ከዚያ መላቀቅ ባይቻልም፣ የዛሬው ትውልድ የቀን ተቀን ገጠመኞች ቁልጭ ብለው ይታያሉ፣ እንዲሁም የአባባል ዘዴዎች፣ ምኞቶች፣ ቀልዶችና ፌዞች. ወዘተ፡፡ በእኔ ዕድሜ ክልል ላለ ግለሰብ፣ ትውልዱን የመመልከቻ መስኮቶች ናቸው፡፡ ስለ መጽሐፍ አስተያየት ለመስጠት መጠቀሚያ አንዱ ዘዴ፣ ከጽሑፉ አንኳር አንኳርን አውስቶ አስተያየት መሰንዘርን ነበር፡፡ ሆኖም ጽሑፍ በጠቅላላ ፍሬ ነገር፣ እንክርዳድ ቢስ ሲሆን፣ ግን ይህን ማድረግ አይቻልም፡፡ እንዲሁ ለተምሳሌነት የሚያገለግል በድርብ ከተንደረበበው ፍሬ ይዘት፣ እፍኝ ሙሉ ቆንጥሮ ማቅረብ ነው እንጂ በዚህ መሠረት የተቆነጠረው እነሆ፡፡

‹‹መግባት እና መውጣት›› ከተለያዩ አንፃር ለመዳሰስ እሞክራለሁ፣ ቋንቋን ከማዳበር፣ የቋንቋ ለዛን ከማንፀባረቅ፣ የአገላለጽ ሥልትን ከመቀየስ፣ የአስተዋይነት ክህሎት፣ ጉልድፍ ውይይት በከተሜና በገጠሬ የትዝብት የሽሙጥ ፍላፃ አወራወር ወዘተ. መጸሐፏ ነባራዊ ከሆነው ባህል ዘለል ትችት ወቅታዊ የፖለቲካና ማኅበራዊ ችግሮችም ዳሳለች፡፡ በአጭሩ በመጽሐፏ ያልተንኳኳ ኑሮ ነክ ጉዳይና በር የለም ቢባል ከእውነት ብዙ አይርቅም፡፡

ቋንቋ አዳዲስ ቃላት እየተጨመሩበት አዲሶች ቃላት ከጊዜ በኋላ እየተለመዱ እንዳንዴም ነባራዊዎችን ቃላት እየተኩ፣ አንዳንዴም የተለየ ገጽታ ገለጣ ባለቤት ሆነው፣ ከነባሮች ጋር ይደመራሉ፡፡ በዕውቀቱ ሥዩም ጥቂት የቋንቋ ማዳበሪያ ቃላትን አበርክቷል፡፡ ለምሳሌ ዲሽን የወሬ መግላላት፣ የእንጀራ አባት ለሰው፣ የሳር አባት ለበግ፣ ሊፍትን የዕርገት ማሽን፣ የወንድነትን ብልት አልአዛር በማለት፡፡ በነባራዊ አነጋገር ነውር የሚሆነውን፣ ስሙን በመቀየር፣ ከነውርነት ወደ ኢነውርነት አወጣው፣ አልአዛር በማለት፡፡ አዲሱ ስም ነባርዊ ኮተቱን አራግፎ፣ ጥሎ፣ ከነውርነት ፀድቶ፣ አደባባይ ወጣ፡፡ በአማርኛ ተመሳሳይ ስም የሌላቸው ቀጥታ ከእንግሊዝኛ ወርሷል፣ ለምሳሌ ሰርፕራይዝ፡፡ አንዳንድ ቃላትም አርጅተው ስላላለፉ፣ በአሁኑ ወቅት አስተርጓሚ እንደሚያስፈልጋቸውም ይገልጣል፣ ከጠንቋይ ጋር አያይዞ፣ አሽከር ወደ ትንሽ ልጅ እንደተቀየረ፣ ትዳር በሙያ እንደተተካ ይገልጣል፡፡

- Advertisement -

ደራሲው አንዳንድ ድርጊቶችን ሲገልጽ፣ የሥነ ጽሑፍ ምሁር መሆኑን ቁልጭ አድርጎ ያሳያል፡፡ ለምሳሌ መክሊት ለማውራት አፏን አቀባበለች፣ እንደ ወፍ ጉባዔ የተደበላለቀው ህምህምታ ቀስ በቀስ እየጠራ መጣ (የአካባቢው ፀጥታ እየሰፈነ ሲመጣ) ተንኮለኛ ፈገግታ (ምስጢር አዘል ፈገግታ) በማለት፡፡ እያንዳንዱ ዓረፍተ ነገር በተመሳሳይ ሁኔታ ነው የተቀረፀ፡፡ ደራሲው የቋንቋ ለዛን በግጥም አዘል፣ ቅኔ መሰል፣ ይዘት ባላቸው ዓረፍተ ነገሮች አበርክቶልናል፡፡ ይህም የጽሑፍ ሥልቱን ያጎላዋል፡፡ ለምሳሌ የግብፅንና የኢትዮጵያን ግንኙነት ታሪክ በጥቂት ቃላት ቁልጭ አድርጎ ያሳያል፣ ‹‹ዓባይን ወሰደው ዓባ ሆይን ስጡን›› በማለት፡፡ ሐኪም ከምርመራ በኋላ ‹‹ራሱን ነቅንቆ፣ ጓንቱን አውልቆ›› ይላል፣ ስለአዲስ አበባ የመብራት ችግር ሲገለጥ አዲስ አበባ በጥቂት በርታ በብዙ ጠፍታ ይላል፡፡ የአገር ባለቤትነትን ከተለያዩ አንፃር ፈትሾ ‹‹ጀግናው ተዋግቶ፣ ደካማው ተራብቶ የሌሎችን አገር ይቀማል›› በማለት የአንድ ገጽ ይዘት ሊኖረው የሚችለውን በአንድ አጭር ዓረፍተ ነገር ያሰፍራል፡፡ በትያትር የአፄ ቴዎድሮስን ባለቤት እትየ ተዋበችን በመድረክ ላይ የምትተካ ሴት ማግኘት አንካራ ስለበዛበት፣ ችግሩን ለመፍታት አፄ ቴዎድሮስ የሚለውን ላጤ ቴዎድሮስ ብሎ እትየ ተዋበችን የቴአትር ሚና ማሳጣት፡፡ በተመሳሳይ ሁኔታ ክፍሉ ቀዘቀዘ፣ ፍቅረኛ ያላችሁ ፍቅረኞቻቸውን እቀፉ፣ ፍቅረኛ የሌላችሁ ኮታቸውን ቆልፉ፡፡ አስተማሪ የነበረ ግለሰብ አስከሬኑን ለሕክምና ትምህርት ቤት ስለአወረሱ፣ ጋሼ አወቀ ድሮ ቆሞ፣ ዘንድሮ ተጋድሞ፣ ማስተማር ይላል፡፡ ከአባት የተገኘ ውርስን ሲገልጽ፣ የታደለው የስኳር ፋብሪካ ይወርሳል ያልታደለው የስኳር ሕመምን፡፡ ስለራስ ማጥፋት ሲወሳ ‹‹በዘመድ ተስፋ ያጣ ሰው፣ በገመድ ተስፋ ቢያደርግ አይደንቀኝም፤›› ስለ አቶ ከበደ ሚካኤል የቤትሆቨን ካፊ ደንበኝነት ጋር ተያይዞ ‹‹የሚናገሩትን መዝግቢ የሚጥሉትን ሰብስቢ›› ይላል፡፡ ለጀርመኑ ያን ወዳጅ ለመክሊት የቀረበ ጥያቄ ‹‹ከጀርመኑ ያለሽ ግንኙነት የምር ነው የብር›› የመክሊት ፍቅረኛ ለመሆን የሚሻው ደራሲው (የቤትሆቨን ካፌ አስተናጋጅ ምንም ጉዳዩን ግልጥ አድርጎ ባያወጣውም)፡፡ መክሊት ለወንድሟ ጫማ መግዛት ስትፈልግ፣ ለጫማ መለኪያነት ገበያ ይዛው ትዞራለች፣ በዚህ የተቆጨ አስተናጋጅ መመኪያ ታደርገኛለች ብዬ ስጠብቅ፣ መለኪያ አደረገችኝ ይላል፡፡

ደራሲው ያያቸውን ክስተቶች በጽሑፍ ሲገልጽ፣ የሚጠቀምባቸው ሥልቶች በጣም ማራኪ ናቸው፡፡ በብዛት በቋንቋው ውስጥ የማይንሸራሸሩ ቃላትንም የመጠቀም ከፍ ያለ ችሎታ ያሳያል፡፡ ለምሳሌ ‹‹በጆሮዬ ቀዳዳ አጮልቆ አዕምሮዬን የሚሰልል ይመስል ግማሽ ሰዓት ተለግቦ ቆሞ›› ይላል የጆሮ ሐኪም ምርመራን ሲገልጽ፡፡ የደራሲው ቤት አከራይ ‹‹/ ይርገዱ ቅንድባቸውን በጥርጣሬ ከፍ አድርገው መመልከት›› የወሬውን እውነተኝነት ስለተጠራጠሩ፡፡ የመክሊት ወንድም ከቤት እንዲወጣ ተገዶ ዝናብ ስለደበደበው ተከታይ ድርጊት አገላለጥ፣ ጠፈጠፉን ከፀጉሩ ላይ እያራገፈ፣ ጠሉን ከፊቱ ላይ እየጨመቀ፣ ይላል፡፡ የቤትሆቨን ካፊ አዘውታሪው ምዑዝ ለፍቅር የሚመኛትን ሔለንን በግርግር መሀል መሳም፣ ቀነኒሳ ሪከርድ ሲሰብር በቴሌቪዥን ሲታይ ‹‹ሔለን ብድግ ብላ ስትጮህ፣ ምዑዝ ዘሎ ከተጠመጠመባት በኋላ፣ በግርግር መሀል ሩብ ከንፈሯን ግማሽ ጉንጯን ይስም ጀመር፤›› ይላል፡፡

ሥዕላዊ አቀራረቡ በበርካታ በመጽሐፏ ገጾች ሰፍረዋል፣ ደራሲው የሥራ ጓደኛ፣ ለፍቅር የሚመኛትን፣ ለጥቂት ደቂቃ ያህል ተጋልጦ የቆየውን ሰውነቷን ከፊቴ እየለቃቀመች፣ በጡት ማስያዣ ውስጥ በከናቴራዋ ውስጥ፣ በጅንስ ውስጥ ትከታለች (ራቁቷን የነበረችው መክሊት ልብስ ስትለብስ)፡፡ በተመሳሳይ የተቀባችው ሮዝ የከንፈር ቀለም የተቀባችው እንደ ሉባንጃ የሚያውድ ሽቶ የለበሰችው ስስ ወንፊታማ ታይት ሱሪ፣ ለእኔ እንዳልሆነ ገባኝ፣ አጠገቤ የተቀመጠ አልፎ ሄያጅ ውበት ነው፣ ይላል፡፡ ደራሲው የተለያዩ የማኅበረሰብ ገጽታ ሲገልጥ የጉዳዩን ዙሪያ ጥምጥሞ ካየ በኋላ ነው፡፡ እያንዳንዱ ዓረፍተ ነገር እንዲሁ ተነቦ የሚታለፍ ሳይሆን፣ ቆም ተብሎ የሚዳሰስ፣ የሚመረመር ነው፡፡ አንድን ድርጊት ብዙዎቻችን በምንመለከትበት ገጽታ ብቻ ሳይሆን፣ አገላብጦ ዓይቶ፣ ከዚያም መዝግቦ፣ ሲተነተንልን እኔ በዚያ ገጽታ ለምን አላየሁትም የሚል መንፈሳዊ ቅናት በሁሉም ሰው ላይ የሚያሳድር ይመስለኛል፡፡ ለምሳሌ በአደባባይ (ማለት በሰው ፊት) ልጇን የምታጠባ እናት ተመልክቶ ‹‹እናትነት ለሴቶች ከሚሰጣቸው መብቶች አንዱ፣ ጡትን በአደባባይ መግለጥ ነው፣ ይገርማል ወር ባልሞላ ጊዜ ውስጥ ዝንብን የሚያስረጅ አምላክ በዘጠኝ ወር ውስጥ ጡትን ከውበት ወደ ምግብነት ያሸጋግራል›› ይላል፡፡ የዝንብን ዕድሜ እጥረት፣ አጢኖ ከሁለት ሳምንት የማይበልጥ ‹‹ይህችም ዕድሜ ሆና ነፃነቱን እንገፈዋለን›› የዝንብን፣ ‹‹በበኩሌ እንኳን በወተቴ በሕይወቴ ቢገባ አልፈርድበትም፤›› ይላል፡፡

በዝናብ መንስዔ ብዙ ጉዳዮችን ደራሲው ዳሷል፤ እግረ መንገዱን በየቦታው የደራሲነት ክህሎትንም አንፀባርቋል፡፡ ሰማዩ ላይ ሳይሆን፣ ዛፎች ላይ አድፍጦ የቆየ የሚመስል ድንገተኛ ዝናብ ወውረድ ጀመረ፡፡ ምንጫቸው ያልታወቀ ቡቱቷም ከሲታ ሕፃናት፣ ሎተሪ አዟሪዎችና ፓርኪንግ የሚሠሩ ሴቶች በካፌው በረንዳ ላይ ተጠራቀሙ፡፡ የሚበሉ፣ የሚጠጡ፣ የሚያፈቅሩና የሚያጠኑ፣ ተስተናጋጆች ካፊው ውስጥ ቁጭ ብለዋል፡፡ በረንዳው ላይ የሚተክዙናና የሚያዛጉ ድሆች ቆመዋል፡፡ በተስተናጋጁና ከዝናብ በሸሹ ድሆች መካከል ከውኃ የጠራ የመስታዋት ግድግዳ ቆሟል፡፡ በድሆችና በሀብታሞች መካከል ያለውን ርቀት የሚያጠበው ብቸኛ ኃይል ዝናብ እንደሆነ ገባኝ ይላል፡፡

ትችቱን ይቀጥላል ክረምት አየሩን ብቻ ሳይሆን የሰዎችንም ሙያ ቀየረ፣ የጉልት ሴቶች ወደ በቆሎ ጠባሽነት፣ አዲስ አበባ ከመዲናነት ወደ ትልቅ ማዕድ ቤትነት፣ አስፋልቱ ሰው ሠራሽ ወንዝ፣ አንበሳ አውቶብስ የኖህን መርከብ ይሆናል ይላል፡፡ የመጽሐፉን ስያሜ ተንተርሶ ስለ ‹‹መግባትና መውጣት›› ሲያወሳ፣ ክረምትና ፀደይን አጣቅሶ፣ እንዲህ ይላል፣ ‹‹አገር ውስጥ የነበሩ ሽሮና ትዝታ ይዘው ወጡ ከአገር ውጭ የነበሩ አይፖድና የአሳማ ጉንፍን ይዘው ገቡ፤›› መብትና ግዴታን ማወቅ ባህል እንዳላደረግነውም ያሳያል፡፡ የአገራችን ሴቶች ከፈረንጅ ጋር ሲታዩ፣ በአገር መጋራት ላይ ተመሥርቶ፣ ወንድ ሁሉ ያገባኛል ይላል፤ ይህን መክሊት ስትፈርጅ ‹‹አንድ ወንድ በአጋጣሚ የአንድ አገር ልጆች ስለሆንን ብቻ፣ በገላዬ ላይ ይገባኛል ጥያቄ ማንሳት መብት አለው፤›› ብላ ትጠይቃለች፡፡

በአዲስ አበባ ውስጥ ያለውን የትራንስፖርት ችግር የተሳፋሪ ትግል/ግፊያ ሲገልጥ፣ ሌብነትን ጭምር በጨረፍታ አጣቅሶ፣ እንዲህ ይላል፣ በዚያ ግፊያ ውስጥ የዚህ ሰውዬ እግር፣ በዚያ ሰውዬ ጫማ ውስጥ ይገባል፣ የዚች ሴትዬ አምባር በዚያች ሴትዬ ክንድ ዙሪያ ይገባል፡፡ አንድ አንድ ባህላዊ ድርጊቶችንም አንስቶ ምንም ነባራዊ ባይሆንም፣ የልደትን በዓል ማክበር፣ የቤት አያያዝና ፅዳትን ተንተርሶ፣ በከተሜና በገጠሬ ውይይት ከልዩነት የመነጨ አለመግባባት፣ የተለመዱ አባባሎችን ይዳስሳል፡፡ ከነኝህም ነጥረው የሚወጡ ቁጭቶችና አስተያየቶች አሉ፡፡ ለምሳሌ የልደት በዓልን ማክበር ላይ ተንተርሶ በወጣትነት ልደት ሰርፕራይዝ ሲሆን፣ ወጣትነት ካለፈ በኋላ ግን መርዶ ነው ብሎ ይቋጫል፡፡ በመፀዳጃ ቤት ንፅህና ይዘት አተኩሮ ከአገር ክብር ጋር አነፃፅሮ፣ ብዙ ምክር አዘል፣ ወቀሳ መሰል፣ አስተያየት ይሰነዝራል፡፡ ድርሰቱ የተመሠረተው ከቤትሆቨን ካፌ አካባቢ ስለሆነ እንዲህ ይላል፣ ስለ ሽንት ቤት ጣጣ ሲያወሳ ‹‹ጀርመኖች ሽንት ቤታችን ሲገቡ እንዴት ይደነቁ! የላሊበላ ሕንፃችንን ክብር የተጨማለቀ ሽንት ቤታችን ይጋርደዋል፤›› ይላል፡፡ ተስፋን ብቻ መመኪያ ያደረገ ባህላችንንም መርምሮ በተስፋ ብቻ መኖርን ሲኮንን ‹‹ጥፋቴ ተስፋን ሙጥኝ ማለቴ ተስፋ የገቢ ምንጭ የሚሆነው ለሎተሪ አዟሪነት ብቻ ነው፣ ይላል፡፡

በቃል በመመሳሰል ብቻ ላይ የተመሠረቱ፣ እንደ እውነትነት የሚወሰዱ፣ ሎጂክ አልባ አስተሳሰቦች አሉ፡፡ ለምሳሌ መቋዲሾን ወስዶ በስሙ መቀደሻ ማለት ነው፣ እንደማለት፡፡ ደራሲው ይህን ጉዳይ በመክሊት ተዋናይነት ያቀርበዋል፣ በጀርመንኛ ካፌ በእንግሊዝኛ ኮፌ መባሉ ቡና በእርግጥ ከከፋ እንደተገኘ ይገልጣል በሚል ሎጂክ፡፡ ይህን ስትል ፍቅረኛዋ ሚስተር ያን በፍቅር መግለጫ አረጋጋጭነት ሲል (አወን አወን) ምዑዝ በቅናት የተላበሰ ገለጣ ሰጠበት፣ በመክሊት አስተያየት ሎጂክ አልባነት ተመሥርቶ የቡና ማፍያ ‹‹ከማፊያ›› ጅብ ‹‹ከጅቡቲ›› እንደተገኘም ያመለክታል በሚል ፌዝ አዘል ትችት፡፡ ደራሲው በታሪክ ይዘት ላይም ይተቻል፡፡ ‹‹ታሪክ ጸሐፊዎች በድሮና በዘንድሮ መካከል ያለውን ልዩነት በጊዜ መጠን ሲለኩት ይገርመኛል፡፡ እንደ እኔ አዲስ አበባ መቶ ኪሎ ሜትር ስትርቅ ድሮን ቁጭ ብሎ ታገኘዋለህ›› በማለት፡፡

ባህላችንን ከአንካሳ ጎኑ ተመልክቶ ደራሲው ወደ መክሊት ትካዜን ሲወረውር ይመዘግባል፡ ‹‹ይኸው እንግዲህ ትካዜዬን አስረክቤያት ወደ ፈገግታዬ ተሻገርሁ›› በማለት፡፡ እንዲሁም ባህላዊ ትችትን ሲተርብ ‹‹ሠርግና ሞት አንድ ከሆነ፣ ፍችና ትንሣኤ አንድ መሆን አለበት›› ይላል፡፡ ተጨባጭ የፖለቲካ ሁኔታን ተንተርሶ ስለጦርነት፣ ስለ ፖለቲከኝነት፣ ስለልማት ከሹማምንት ጋር የተደረገ ቃለ መጠይቅንም ይዳስሳል፣ ሁሉንም መተንተን አይቻልም፣ ከቦታ ጥበት አንፃር፡፡ ስለ ጦርነት አላስፈላጊነት ሲተች ዋናው ወደ ጦርነት መሄድ ነው፣ የምትዋጋበትን ምክንያት መንገድ ላይ ታገኘዋለህ ይል ነበር አባቴ ብሎ ይደመድማል።

በቀልድ አዘል ዓረፍተ ነገሮች ፖለቲካን ይተርባል፣ አንድ ችግረኛ ልጅ በቤትሆቨን ካፌ ሻይና ዳቦ ተጋብዞ ሳለ፣ ደራሲው የችግረኛውን በከፊል በእድፍ የተላበሰ ሸርት ዓይቶ ሸርቱ ላይ የተጻፈውን በከፊል የጋረደ ‹‹የጥበብ መጀመርያ ብሔርን መፍራት ነው›› እግዚአ የሚለውን እድፍ ሸፍኖታል፡፡ የአማርኛ አባባሎች ከወቅቱ ሁኔታ ጋር እያገናዘበ ይተነትናል፡፡

‹‹ሊነጋ ሲል ይጨልማል!›› እንዲሉ የመብራት ሠራተኞች፣ ‹‹ልጅና ወረቀት ያስያዙትን አይለቅም›› እንዲሉ መሠረተ ትምህርትን የተማሩ እናቶች፣ ‹‹የማይተማመን ባለእንጀራ በየወንዙ ይማማላል›› እንዲሉ የናይል ተፋሰስ አገሮች፣ ‹‹ህልም ተፈርቶ ሳይተኙ አያድሩም! እንዲሉ›› የአልቤርጎ አከራዮች፡፡ የአማርኛ ድርሰት አጻጻፍ ሥልት እንደተለመደ ጉዳይ፣ እንደ ባህል ይዘት ያለው አስመስሎ ተችቷል፡፡ ስለአማርኛ ድርሰት አዝጋሚነት አንስቶ፣ የአማርኛ መጽሐፎች ‹‹በጣም አዝጋሚ ታሪክ ስላላቸው ላነባቸው ስፈልግ ታክሲ ውስጥ እገባለሁ፣ ከደራሲው ያጣሁትን ፍጥነት ከሾፌሩ አገኛለሁ›› በማለት፡፡ ከዚህ ትንሽ በተለየ መልኩ በአቶ ሐዲስ ዓለማየሁ መጽሐፍ ላይ ያተኮረ አስተያየት ይሰጣል፡፡ ‹‹የመጸሐፍ ሻጩ በደረቱ ከተሸከመው መጽሐፍ ነዶ መሀል፣ ፍቅር እስከ መቃብር የሚል ወፍራም ጥራዝ ታየኝ፡፡ አቶ ሐዲስ መጽሐፋቸው እንደ አጠና በሸክም ገበያ የሚወጣ መሆኑን ቢያውቁ ኖሮ፣ የገጹን መጠን ያሳንሱት ነበር ብዬ አሰብኩ›› በማለት፡፡ ሆኖም ይህን ትችት ዝም ብሎ ለማለፍ ያዳግታል፡፡

ሁሉም መጽሐፍ ፈጣን ሒደት ያዘለ ወይም ገጸ አጭርና ወርደ ጠባብ መሆን የለበትም፣ የመጽሐፉ አዝጋሚነትም የገጽ ብዛትም ውበት አዘል ሊሆኑ እንደሚችሉ ስለማምን፡፡ አዝጋሚነት የራሱ የሆነ ለዛ አለው፣ ጉጉትንና ናፋቂነትን ይጨምራል፡፡ በሥልት ከተያዘ እንዲሁም ገጸ ብዙነት፣ የአገላለጽን ገጽታ ያበረክታል፣ ያሰፋል፡፡ የጽሑፍ አገላለጽ ውበት ሁሉም አጠር መጠን ማለት የለበትም፤ ትረታው እንደ ባህር የተንጣለለም ቢሆን፣ ፍቅር እስከ መቃብርን የሚመጥን ከሆነ ገጹ ቢበረክትም የማያጠግብ፣ ቢንጣለልም የማያሰለች ከድርሰት አኳያ ከፍተኛ ቦታ ይሰጠዋል፡፡

ከተጨባጭ ሁኔታዎች ውስጥ ለሕዝብ ብዛት ትኩረት ሰጥቷል፣ ሒደቱንም ይተነትናል፡፡ ‹‹ሕፃናት ክረምት ከበጋ ሳይመርጡ ተዘርተው ይበቅላሉ፡፡ ወላጆች የበኩር ልጃቸው አንደኛ ዓመት ልደት ዕለት በግብረ ሥጋ ይከበራል›› ብለውም ሌላ ጽንስ ይሠራል፡፡ ይኸው ችግር በቤትሆቨን ካፌ ሲንፀባረቅ፣ ተጠጋግተው የተቀመጡ የቡና ቤቱ ተስተናጋጅ አንድ ላይ ከነሲኒ ያለፈቃዳቸው ይጋጫሉ፡፡ በዚህን ጊዜ ትከሻ ለትከሻ ሲጋፉ፣ የራሱን አፍ ስቶ ከጎኑ የተቀመጠ ሰው አፍ ውስጥ ጉርሻ የሚጥል አይጠፋም፡፡ በተመሳሳይ ሁኔታ ከገጠር ወደ ከተማ የሚጎርፈውን ሕዝብ ድርጊት ሲያብራራ፣ ገበሬው ጠፍ መሬቱን ትቶ ሞፈሩን ተሸክሞ፣ ወይፈኑን እየነዳ፣ ከገጠር ወደ መዲናይቱ ይመጣል፡፡ ወይፈኑን ወደ ቄራ፣ ሞፈሩን ወደ ቤተ መዘክር አሰናብቶ፣ ሎተሪ ማዞር ይጀምራል፡፡

በገጠሬና በከተሜ መሀል የአነጋገርን ሥልትን ተንተርሶ የሚታይ ክስተትን ለመግለጽ የተደረገው የአባተን በፖሊስ ጣቢያ ምርመራ እንመልክት፡፡ ፖሊሱና ከተማ ቀመስ ገጠሬውን አባተ፡፡ አባተ በወንጀል መከሰት ምክንያት ፖሊስ ጣቢያ ተወስዶ ሲመረመር፣ የፖሊስ ጥያቄ፣ ‹‹በጊዜው በሟች ፊት ላይ የተስፋ መቁረጥ ስሜት አንብበሃል፤›› መልስ በአባተ ‹‹ንባብ ላይ ያን ያህል ነኝ ጌትዬ››፡፡ በተለያዩ መድረኮች የቀረቡ ጥያቄዎችና በባለጉዳዮች የተሰጡ መልሶች፣ ጠያቂና ተጠያቂ የተለያዩ አምባዎች ላይ የመሸጉ መሆናቸውን ያመለክታል፡፡ በአሜሪካ ኤምባሲ ቪዛ ፈላጊ ባልቴት የባንክ ደብተር ይኖረዎታል ተብለው ሲጠየቁ ‹‹የለም የመሠረተ ትምህርት ደብተር አለኝ›› ብለው ይመልሳሉ፡፡

ስለ በጎ አድራጊ መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች ብዙ ተወስቷል፡፡ ምዑዝ የሚሠራበት በጎ አድራጊ ድርጅት በእከክ ለተቸገሩ ድሆች የእከክ ማከኪያ እንጂ መድኃኒት እንደማይሰጧቸው፣ በሌሎች መሥሪያ ቤቶች የተጋበዙ ሕፃናት ምግብ በመጠባበቅ ላይ እንዳሉ፣ ሁኔታውን መዝጋቢ የሆኑ ጋዜጠኞች አለመምጣታቸው ሲታወቅ፣ ዛሬ ራት የለም ተብሎ መባረራቸው፣ ሽልምልማቸው የደበዘዘ የሜዳ አህዮችን ቆዳ አድማቂ ድርጅት ወዘተ. በዚህ አጋጣሚ ጥሩ ጥሩ ሥራ ስለሚሠሩም በጎ አድራጊ ድርጅቶች ቢወሳ ጥሩ ነበር፡፡

የአዲስ አበባ ከተማ የትራንስፖርት እጥረትን ሲያብራራ ነዋሪዎች ሚኒባስ የሚጠብቁበትን ናፍቆት የመድኃኔዓለምን ምፅዓት አይጠባበቁም ይላል፡፡ ወደ ፖለቲካ ዞር ብሎ ከሕክምና ይዘት ፖለቲካ መሳተፍ ሽግግር ሲደረግ ሒደቱን ለማቃናት የሚከተሉትን ይሰነዝራል፡፡ ‹‹በወር ቢያንስ አንድ ጊዜ ሰላማዊ ሠልፍ ማድረግ የደም ዝውውርን እንደሚያሻሽል ተገለጸ›› ‹‹የብረት ቆብ ከሚያደርጉ አድማ በታኝ ፖሊሶች በበለጠ የሚያደርጉት ለጭንቅላት ካንሰር የተጋለጡ መሆናቸው ተመለከተ››፡፡ ‹‹ነዋሪነታቸው በባህር ዳር የሆነው የባህል ሐኪም መሪጌታ በልስቲ አሻግሬ ለመጪው ምርጫ እንደሚወዳደሩ ተጠቆመ፡፡ 

የኢትዮጵያን በቴክኖሎጂ ድህነት አሳይቷል፣ በሽሙጥ መልክ ቢሆንም፡፡ በኢትዮጵያ ውስጥ የተመናመነ የሳይንስ ቴክኖሎጂ ሥርዓት ላይ ተመርኩዞ የሚከተሉት ዓረፍተ ነገሮች አስፍሯል። ‹‹ሳይንስና ቴክኖሎጂ እንደ ቀንዳም ፈርስ ተረት በሆነበት›› ይላል፡፡ አንድ ቀን ገጠር ወርጄ ሴቶች ከወደቀ የመድፍ ቀላህ የቡና መውቀጫ ሠርተው ቡና ሲወቅጡ ዓይቼ እንባዬን መቆጣጠር አቃተኝ፣ የመገለጥ እንባ ነበር›› ይላል፡፡ ‹‹ዓለም አቀፍ ግኝቶችን ያበረከቱ ሁለት ኢትዮጵያውያን አውቃለሁ፣ አንደኛው የቢላሃርዚያን መድኃኒት ያገኘው አክሊሉ ለማ ሲሆን፣ ሌላው ቡናን ያገኘው ፍየል ነው›› ይላል፡፡ በመጽሐፉ ውስጥ የተሰነዘሩ ጥቂት ዓረፍተ ነገሮች ከግንዛቤ ሰጪነት ዘለው እንደ ቁስል መጎርጎር የታዩኝን ሳልጠቅስ አላልፍም፡፡ ለምሳሌ የቤትሆቨንን ካፌ ተስፈኛ ሻለቃውን እንውሰድ፡፡ በእንጀራ ፍለጋ ምክንያት ሰዎች በተለያዩ ሥራዎች እንዲሰማሩ ኑሮ ታስገድዳቸዋለች፤ አንዱም ወታደርነት ነው ከባድ መጥፎ ሥራ፣ እንጀራ ፈላጊውን ለሞት የሚዳርግ ከዚያ በመልስ አካል የሚያጎድል፡፡ በዚህ ሥራ ላይ ተሰማርተው የነበሩ ግለሰቦች ሙገሳው ይቅር ዝምታ ግን አይነፈጋቸው እላለሁ፤ ፌዙ ሽሙጡ ተከልቶ፣ ደራሲው (አስተናጋጁ) የዝንብን ዕድሜ አጭርነት በተረዳ ጊዜ ስንኳን በወተቴ በሕይወቴም ቢገባ አልፈርድበትም እንዳለው፡፡

ድርሰቱ በትምህርት ቤት የጀርመን ቋንቋ መማሪያ ተጀምሮ፣ አንድ ኢንትርኔት ካፊ ውስጥ ይጠናቀቃል፡፡ ደራሲው መጽሐፉን የሚደመድመው በምሽት ነው። የመጨረሻ ጥቂት ዓረፍተ ነገሮች እነሆ፣ ሥዕላዊ ያገላለጽ ሥልትን ቁልጭ አድርገው ስለሚያሳዩ፡፡ ‹‹እየመሸ ነው በማስታወሻዬ ላይም መሸበት፡፡ በመስኮት በኩል ስመለከት ከውጭ ያሉት ሕንፃዎች ዛፎችና አጥሮች ቀለማቸውና ዝርዝራቸው ተውጦ ንድፋቸው ብቻ ቀረ፣ ማዶ ካለው ቀለበት መንገድ ላይ መኪናዎች እንደ አብሪ ጥይት በጨለማ ውስጥ ውር ውር ሲሉ ታየኝ፡፡ ከምሥራቅ ሰማይ በኩል አንድ ጉማጅ ብርሃን እየተጎተተ ብቅ አለ፣ የአውሮፕላን ፍሬቻ ወይም እግዜር በዛለ ክንድ የወረወረው ኮከብ ይሁን አላውቅም፤›› ይላል፡፡ 

ድርሰቱን በፍልስፍና አዘል፣ ውበት አንፀባራቂ ዓረፍተ ነገሮች ይቋጫል፡፡ ‹‹የናፈቀ ሰው በር በሩን፣ የታከተ ሰው መስኮት መስኮት ያያል›› ይላል፡፡ በዚህ አጋጣሚ ለደራሲው ልመና አዘል፣ ምክር ተኮር መልዕክት ለመላክ በር በር እያየን ነው፣ ሌሎችም መጻሕፍት ደርሰህ ታደገን እያልኩ ጣመን ድገመን እንደማለት፡፡

ከአዘጋጁጸሐፊው ሽብሩ ተድላ (ፒኤችዲ) የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የባዮሎጂና የፓራሲቶሎጂ ልሂቅ (ኢመረተስ) ፕሮፌሰር ሲሆኑ፣ በርካታ የጥናትና ምርምር ሥራዎቻቸውን አሳትመዋል፡፡ በቅርቡም ጥልቅ ማኅበራዊና ሰብአዊ (ሶሺያል ኤንድ ሂዩማኒስት) ጉዳዮችን በጥልቀት ያቀረቡበት ከጉሬዛም ማርያም እስከ አዲስ አበባ፡የሕይወት ጉዞ እና ትዝታዬ የተሰኘ መጽሐፍ ለኅትመት አብቅተዋል፡፡ ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ ሲሆን፣ ጸሐፊውን በኢሜይል አድራሻቸው [email protected] ማግኘት ይቻላል፡፡

- Advertisement -

በማህበራዊ ሚዲያዎች ይከታተሉን

ከ ተመሳሳይ አምዶች

እስቲ ስለንፅህና አጠባበቅ በትንሹ እንነጋገር

በአቤቶ በዛወርቅ መግቢያ “ባገኘበት የሚሸና ከውሻ አይተናነስም” የሚል ማስታወቂያ ማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ምዕራብ ጉራጌ ዞን ደቡብ ሶዶ ወረዳ ኬላ ከተማ ውስጥ ከእነ መስፍን ደበላ ምግብ...

የነገው ሰው እንዴት ይታነፅ?

በሳህሉ ባዬ በዚህ መጣጥፍ የምንመለከተው ዓብይ ነጥብ ጨዋታ በሕፃናት አስተዳደግ ላይ መሠረታዊ መማሪያ መድረክ መሆኑንና የማሰብ ችሎታቸው እንዲዳብር፣ የግንዛቤ አድማሳቸው እንዲሰፋ፣ የቋንቋ ክህሎታቸው እንዲጠናከር፣ ጥበብን...

የ‹‹ስፒሩሊና›› ምንነት ጥቅምና አመራረት

በአምኃ በላይ (አድጀንክት ፕሮፌሰር) እና ሽብሩ ተድላ (ኤመሪተስ ፕሮፈሰር)                                               መግቢያ ሳይንሳዊ አስተሳሰብን፣ ብሎም የሳይንስን ዕውቀት በማኸዘብ (ብዙ ሰው በቀላል መንገድ እንዲገነዘብ በማድረግ)፣ በምክንያት ላይ የተመሠረቱ፣...

ሰማንያ ሰባተኛው ቋንቋችን የኢትዮጵያ ምልክት ቋንቋን ለሥራ ቋንቋነት

በቻላቸው ወልዴ መግቢያ በተለያዩ ክፍለ ዓለማት በሚገኙ ዕውቅ ዩኒቨርሲቲዎች ውስጥ ከሥነ ቋንቋ ጋር በተያያዘ ምርምር ከሚያደርጉ ጠበብት የሚቀርቡ የጥናት ውጤቶች ላይ ተመሥርቶ ስለዓለማችን ቋንቋዎች መረጃ የሚያወጣው...

ጥላሁን ግዛው ማን ነው?

በያሬድ በርሔ አንዳንድ ወዳጆቼ ጥላሁን ግዛው ጓደኛህ ነበር፡፡ ‹‹ለምን ስለእሱ ትንሽ ነገር በጽሑፍ አታቀርብም›› እያሉ በየጊዜው ያሳስቡኛል፡፡ እኔም ማሳሰቢያው አግባብነት ያለው መሆኑን ተገንዝቤ ስለጥላሁን የማውቀውን፣...

አገሬ ምንተባልሽ – ልብ ያለው ልብ ይበል

በቶማስ በቀለ ይቺ አገራችን ብዙ ተብሎላታልም፣ ብዙ ተወርቶባታልም፣ አገሪቱ በቅኝ ያልተገዛች ብቸኛ አገር (ላይቤሪያን ጨምሮ) ከመሆኗ አኳያ የሚነገርላት ብዙ ጥሩና የሚገርሙ ነገሮች ያሉትን ያህል፣ ከረሃብ...

አዳዲስ ጽሁፎች

የዓለም ኢኮኖሚ ከቀውስ ሥጋት የሚወጣው መቼ ነው? የኢትዮጵያስ እንዴት?

በጌታነህ አማረ የዚህ ጽሑፍ ዓላማ ኢትዮጵያ ለምታበስረውና ለምትከውነው ትንሳዔ ይረዳ ዘንድ ስለዓለም ኢኮኖሚ ችግር ሁኔታና መፍትሔ ሊሆኑ ስለሚችሉ ነገሮች ግንዛቤ መፍጠር ነው፡፡ ስለዓለም አገሮች የኢኮኖሚ...

‹‹በትግራይ ከሕወሓት የተለየ አንድ ትልቅ የፖለቲካ ኃይል እየመጣ ነው›› አቶ አምዶም ገብረ ሥላሴ፣ የአረና ትግራይ ለዴሞክራሲና ለሉዓላዊነት ፓርቲ ሊቀመንበር

የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የታሪክ ትምህርት ክፍል ምሩቁ አቶ አምዶም ገብረ ሥላሴ፣ በትግራይ ክልል ፖለቲካ ሕወሓትን በመፎካከር የመጀመሪያ የነበረውን አረና ትግራይ ለዴሞክራሲና ለሉዓላዊነት ፓርቲን ከ2000...

የንብረቶች ዋጋ ማሽቆልቆልና የምግብ ነክ ሸቀጦች ዋጋ ንረት ተቃርኖ የነገሰበት የአገራችን ገበያ

በኢትዮጵያ ገበያ ውስጥ ያልተቋረጠ የዋጋ ዕድገት እያሳዩ ሲጓዙ ከነበሩ ንብረቶች ውስጥ ተሽከርካሪዎች፣ የመኖሪያ ቤቶችና ለተለያዩ አገልግሎቶች የሚውሉ ሕንፃዎች በዋናነት ይጠቀሳሉ፣ የመሬት ዋጋም እንዲሁ ከዓመት...

ቀጣናዊ ቀውስ ሊፈጥር የሚችለው ውጥረት ይርገብ!

ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በትግራይ ክልል ውስጥ በስፋት እየተስተዋለ ያለው አለመግባባት፣ እንዲሁም ከኢትዮጵያ የባህር በር ጥያቄ ጋር ተያይዞ ከኤርትራ ጋር ሊፈጠር ይችላል ተብሎ የሚታሰበው ግጭት...

እስቲ ስለንፅህና አጠባበቅ በትንሹ እንነጋገር

በአቤቶ በዛወርቅ መግቢያ “ባገኘበት የሚሸና ከውሻ አይተናነስም” የሚል ማስታወቂያ ማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ምዕራብ ጉራጌ ዞን ደቡብ ሶዶ ወረዳ ኬላ ከተማ ውስጥ ከእነ መስፍን ደበላ ምግብ...

በአዲስ አበበ ከተማ ኢ-መደበኛ ንግድ የሚካሄድበት ሰዓት በአምስት ፈረቃ ተከፋፍሎ ይፋ ተደረገ

ኢ-መደበኛ ሆኖ የሚመዘገብ ነጋዴ መሥራት የሚችለው ሁለት ዓመት ብቻ ነው የትርፍ ጊዜ ክፍያ በደንቡ ላይ አለመቀመጡ ጥያቄ አስነስቷል በሃይማኖት ደስታ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ካቢኔ በአራተኛ ዓመት...
[the_ad id="124766"]

በማህበራዊ ሚዲያዎች ይከታተሉን

error: