Friday, June 2, 2023
- Advertisment -
- Advertisment -

አገር ሊወድቅና ሊነሳ የሚችለው መንግሥት በሚተገብረው የኢኮኖሚ ፖሊሲ ነው!

በፈቃዱ በቀለ (ዶ/ር)

ክፍል አራት
ከውጭ የሚመጣ መዋለ ንዋይ የአንድን አገር ኢኮኖሚ ማሳደግ ይችላል ወይ?
ከውጭ የሚመጣ የመዋለ ንዋይ (Direct Foreign Investment) የተለያየ መልክ አለው። አንዱ የአገልግሎት መስጫ ወይም አምራች ድርጅት ውስጥ ድርሻ መግዛት ሲሆን፣ ድርሻን የሚገዛ ግለሰብም ሆነ ድርጅት ተፅዕኖ ለማሳደር ቢያንስ አሥር በመቶ የሚሆነውን ከአገልግሎት መስጫ ውስጥ መግዛት አለበት። ኢንዱስትሪዎችን ወስዶ በቀጥታ መትከልና ምርት እዚያው አገር ውስጥ እንዲመረት ማድረግ። ለዚህ ዋናው ምክንያት፣ የማምረቻን ዋጋ ለመቀነስ ሲሆን፣ በተለይም የሥራ አበልን ይመለከታል። በአብዛኛዎቹ የሦስተኛው ዓለም አገሮች የሚመረቱት፣ በተለይም እንደ ጨርቃ ጨርቅና ጫማ የመሳሰሉት ምርቶች በርካሽ ጉልበት የሚመረቱና በዓለም አቀፍ ገበያ ላይ የሚሸጡ ናቸው። ይህ ዓይነቱ ርካሽ ጉልበት የትርፍ ትርፍ (Surplus Value) ዋናው ምንጭ ነው። ከዚህ ባሻገር አብዛኛዎቹ የሦስተኛው ዓለም አገሮች በፋብሪካ ደረጃና በአገር አቀፍ ደረጃ የተደራጀ የሠራተኛው የሙያ ማኅበር የላቸውም። ቢኖራቸውም በጣም የተዳከመ ነው። የተጠናከረና የተደራጀ ምሁራዊ ባህሪ የሌለው እንቅስቃሴ በሌለበት አገር ውስጥ የውጭ ኩባንያዎች ኢንዱስትሪዎቻቸውን አምጥተው በመትከል ምርት እንዲመረት ያደርጋሉ። የማኅበራዊና የኢኮሎጂ ስታንደርድ በማይጠበቅበት ወይም የጠበቀ ሕግ በሌለባቸው አገሮች ትላልቅ ኩባንያዎች ኢንዱስትሪዎቻቸውን አምጥተው በመትከል ምርትን ያመርታሉ። የቀረጥ ዝቅተኛ መሆንና ትርፍን እዚያው እንደገና መልሶ ለመዋለ ንዋይ አለማዋል ወይም ወደ ውጭ ማውጣት ሌላው የውጭ ኩባንያዎችን የሚገፋፋ ጉዳይ ነው። ስለሆነም የሚያገኙትን ትርፍ ሳይቀረጥ እንዳለ ወደ ውጭ ማውጣት ይችላሉ። የገቢ ቀረጥ እንዲከፍሉ በሚገደዱባቸው አገሮች ደግሞ ከአገሮቻቸው የሚያመጡትን ኢንዱስትሪዎቻቸውንና የመለዋወጫ ዕቃዎችን ዋጋ ከፍ በማድረግና የማምረቻ ዋጋን ከፍ አድርጎ በማስላት ኢንዱስትሪው ዝቅተኛ ትርፍ እንዳገኘ አድረገው በማቅረብ ድብቅ በሆነ መልክ ትርፍ ወደ ውጭ እንዲወጣ ያደርጋሉ። ሌላው የውጭ መዋለ ንዋይ (FDI) አካል የሆነው የተለያዩ መገጣጠሚያዎችን በተለያዩ አገሮች ማምረትና ኩባንያው ተቀማጭ በሆነበት አገር ውስጥ አንድን ትልቅ ምርት ገጣጥሞ ለገበያ ማቅረብ ነው። በተለይም እንደዚህ ዓይነቱ የመኪናን ምርት ይመለከታል። ሌላው ቀጥተኛ የመዋለ ነዋይ ክንዋኔ ዓይነት የጥሬ ሀብትን ማውጣትና እንዳለ ወደ ካፒታሊስት አገሮች፣ ወደ ቻይና እና፣ እንዲሁም ወደ ሌሎች በዕድገት ላይ የሚገኙ እንደ ህንድ ወደ መሳሰሉት አገሮች መጫን ነው። በተለይም በዚህ ዓይነቱ የጥሬ ሀብት ቁፋሮ የሚሰማሩ ትላልቅ ኩባንያዎች (Multinational Companies) ከጥፋት በስተቀር ለአንድ አገር የኢኮኖሚ ዕድገት የሚያበረክቱት አስተዋጽኦ ከዜሮ በታች ወይም አሉታዊ ነው ማለት ይቻላል። በጥሬ ሀብት ቁፋሮ ውስጥ የሚሰማሩት ሠራተኞች የሚያገኙት ደመወዝ በጣም ዝቅተኛ ነው። በሙያ ማኅበር የመደራጀት መብታቸውም እንደዚሁ ዝቅ ያለ ነው።

ኩባንያዎቹ በሚሰማሩባቸው አካባቢዎች ከፍተኛ የሆነ የአካባቢና የማኅበራዊ ቀውስን ያስከትላሉ። በመጥፎ ድርጊታቸውም በሕግ የሚጠይቃቸው መንግሥት ወይም መሥሪያ ቤት የለም፡፡ ሌላው የውጭ ኩባንያዎች የመዋለ ንዋይ እንቅስቃሴ በአበባ ተከላ ላይና በሌሎች ለውጭ ገበያ በሚቀርቡ የእርሻ ምርቶች ላይ ያተኮረ ነው። የአበባ ተከላ ደግሞ ለአንድ አገር ኢኮኖሚ ዕድገት የሚያበረክተው አስተዋጽኦ ዜሮ ነው ማለት ይቻላል። ምክንያቱም አበባ ለጠቀሜታ በፋብሪካ ውስጥ በመፈበረክ ለምግብነት ስለማይውል ነው። በዚህ መልክ የአንድ አገር ድንግል መሬት ለምግብ የሚሆኑ ሰብልና ፍራፍሬዎች ከሚበቅሉበት ይልቅ የኢንዱስትሪ አገሮችን ሰዎች ለማስደሰት ሲባል የተለያዩ መርዛማ የሆኑ ኬሚካሎች እየተረጨበት አካባቢ ይወድማል፡፡ በዚያ ተቀጥረው የሚሠሩ ሠራተኞች ደግሞ ለበሽታ ይደረጋሉ። የአበባን ተከላንና ጠንቁን አስመልክቶ በአቶ መሳይ አዱኛ ካሳዬ በቀረበው የምርምር ውጤት መሠረት የአበባ ተከላ በተስፋፋባቸው አካባቢዎች የሚረጨው የተባይ ማጥፍያ መድኃኒት በሰውና በአካባቢው ላይ የጤንነትን መቃወስና መዛባትን ሲያደርስ፣ ማዳበሪያው ደግሞ በመሬት ውስጥ የሚገኘውን ውኃና ወንዞችን ሊበርዝ ችሏል። በተጨማሪም አበባውን ለማጠጣት እየተባለ በብዛት የሚረጨው ውኃ ከመሬት ውስጥ የሚገኘውን የውኃ መጠን በከፍተኛ ደረጃ እንደቀነሰው ጥናቱ ያመለክታል። ይህ ብቻ ሳይሆን ለእርሻ ምርት ምርታማነትና ለማር ምርት የሚያገለግሉ ነፍሳትና ንቦች በጅምላ እየወደሙ እንደሆነ ጥናቱ ይጠቁማል። መስኩ 85,000 ሠራተኞች የሥራ መስክ የከፈተ ቢሆንምና አገሪቱም አበባን ወደ ውጭ በመላክ በዓመት ወደ $200 ሚሊዮን የሚጠጋ የአሜሪካ ዶላር ብታገኝም የዚህ ንዑስ መስክ መስፋፋት ከጥቅሙ ይልቅ ጉዳቱ እንደሚያመዝን ነው ጥናቱ የሚያረጋግጠው።

በሌላ አነጋገር፣ የአበባ ተከላና የሌሎች ፕላንቴሽን ኢኮኖሚዎች መስፋፋት እርስ በርሱ ለተሳሰረና ሰፋ ባለመልክ ለሚገለጽ የሥራ ክፍፍል መዳበርና ለማኅበረሰብ ምሥረታ እንቅፋት ነው። የገበያ ኢኮኖሚ ወይም ካፒታሊዝም ሊያድግ አይችልም። መስኩ የዓለም ካፒታሊዝም ተቀጥያና የካፒታሊስት አገሮችን በሀብት የሚያደልብና የተስተካከለና ተከታታይነት የሚኖረውን የኢኮኖሚ ዕድገት የሚፃረር ነው።

በአጠቃላይ ሲታይ የእርሻ ምርት ውጤት እንዳለ ወደ ውጭ ስለሚላክ በዚያ ምርቱ በተመረተበት አገር ውስጥ እርስ በርሱ የተሳሰረ (Value Added Chain) የኢንዱስትሪ ዕድገት እንዳይዳብር ይደረጋል። ለምሳሌ የአገራችንን ቡና ተፈጭቶና ታሽጎ ቢላክ የሚሰጠው ጥቅም፣ የአገር ውስጥ ገበያ ሊስፋፋ ይችላል፣ ከውጭ የሚገኘው ምንዛሪ ከፍ ያለ ይሆናል። የቡና አምራቹም ገቢ በየጊዜው ያድጋል፣ ቡናን እየቆላ፣ እየፈጨና አሽጎ ወደ ውጭ የሚልክ ፋብሪካ ተጨማሪ የሰው ኃይል ስለሚያስፈልገው ለሠራተኞች የገቢ ምንጭ ይሆናል፡፡ የተፈጨውን ቡና ማሸጊያ ልዩ ዓይነት የማሸጊያ ወረቀት ስለሚያስፈልግ ማሸጊያውን የሚያመርት ፋብሪካ ይቋቋማል። በዚህ መልክ እርስ በርሱ የተያያዘ የምርት ክንውንና ተከታታይ ገቢ ለአገር ውስጥ ገበያ መስፋፋት አመቺ ሁኔታን ይፈጥራል። ይሁንና ግን የአገር ውስጥ ገበያ እንዲስፋፋ ጥረት ከማድረግ ይልቅ በቸልተኝነት ወይም ካለማወቅ የተነሳ የአገር ውስጥ ሀብት በቀላሉ ይባክናል፡፡ የአገር ውስጥ ገበያም እንዳያድግ ከፍተኛ መሰናክል ይፈጠራል።

ያም ተባለ ይህ የውጭ ኩባንያዎች በቀጥታ የመዋለ ንዋይ እንቅስቃሴ በሚያደርጉባቸው አገሮች ውስጥ ለየአገሩ የኢኮኖሚ ዕድገት የሚያበረክቱት አስተዋጽኦ እጅግ ዝቅተኛ ነው። ከአንዳንድ አገሮች በስተቀር፣ በተለይም እንደ ቻይና ከመሳሰሉ ጠንካራ፣ ብልህና የመደራደር አቅም ካላቸው መንግሥታትና አገሮች በስተቀር በአፍሪካ ውስጥ የሚካሄዱት የመዋለ ንዋይ ክንዋኔዎች ለዕድገትና ለኅብረተሰብ ለውጥ የሚያበረክቱት አስተዋጽኦ እጅግ ዝቅተኛ ወይም አሉታዊ ነው ማለት ይቻላል።

ሁሉም ኩባንያዎች ምርምራቸውን የሚያካሂዱት በየአገሮቻቸው ውስጥ ስለሆነ የቴክኖሎጂ መተላለፍ (Transfer of Technology) አይኖርም። ይህም ማለት አብዛኛዎቹ የአፍሪካ አገሮች ለዕድገታቸው የሚያመቻቸውን ቴክኖሎጂ ሊኮርጁና ሊጠቀሙበት አይችሉም፡፡ አብዛኛዎቹ ኢንዱስትሪዎች አገር ውስጥ ካሉ ሌሎች ኢንዱስትሪዎች ጋር በቀጥታ የሚያያዙ አይደሉም። ተነጥለው የሚካሄዱ የኢኮኖሚ እንቅስቃሴዎች በመሆናቸው ለአጠቃላይ የሀብት ክምችት የሚያበረክቱት አስተዋፅዖ አልቦ ነው ማለት ይቻላል። በእነዚህ ኢንዱስትሪዎች፣ የጥሬ ሀብት ማውጫዎችና የአበባ ማሳዎች ውስጥ ተቀጥረው የሚሠሩት ሠራተኞች ደመወዛቸው በጣም ዝቅተኛ ስለሆነ ራሳቸው የሚያመርቱትን ወይም ደግሞ ዘመናዊ ከሚባለው መስክ የሚመረተውን ምርት ገዝተው የመጠቀም ኃይል የላቸውም። የአገር ውስጥ ገበያን አያስፋፉም ወይም ለማዳበር አይችሉም። አብዛኛውን ጊዜ ከባንኩ መስክ ጋር ምንም ዓይነት ግንኙነት የላቸውም። ስለሆነም ለባንክ ዕድገትና ለገንዘብ በፍጥነት መሽከርክር ምንም አስተዋጽኦ አያበረክቱም። ከዚህና ከሌሎች አያሌ ምክንያቶች ስንነሳ ቀጥተኛ የሆነ የውጭ የመዋለ ንዋይ እንቅስቃሴ (Direct Foreign Investment) ከጥቅሙ ይልቅ ጉዳቱ ያመዝናል። አንድን ኅብረተሰብ ከማዘበራረቅና ማኅበራዊ ቀውስ እንዲፈጠር ከማድረግ በስተቀር የዕድገት አራማጅ አይሆንም። የውጭ ኩባንያዎች በሚንቀሳቀሱባቸው የሦስተኛው ዓለም አገሮች በሙሉ የሰብዓዊ መብት ረገጣ የተስፋፋና፣ ሠራተኞችም በአገራቸው ውስጥ እንደ ሁለተኛ ዜጋ የሚቆጠሩ ናቸው። አብዛኛውን ጊዜ በሦስተኛው ዓለም አገሮች ውስጥ አምባገነናዊና ፋሺስታዊ አገዛዞች የሚነሱትና የሚጠናከሩት ከካፒታሊስት አገሮች ጋር ስለሚቆላለፉና በጥቅም ስለሚገዙ ነው። ስለሆነም የየአገሩ መንግሥታትም የሚያደሉት ለውጭ ኩባንያዎች እንጂ ለአገራቸው ሕዝቦች አይደለም።

ብዙ የሚወራለትን የሐዋሳን የኢንዱስትሪ ፓርክ ደግሞ እንመልከት። የኢንዱስትሪ ፓርኩ በዘጠኝ ወራት ጊዜ ውስጥ ... በጁላይ (ሐምሌ) 2016 ተጠናቆ ሥራውን የጀመረ ነው። ፓርኩ በቻይናዎች የተሠራ ሲሆን፣ ከቻይና ኩባንያዎች በተጨማሪ ፊሊፕስ ቫን ሆይሰን ኮርፖሬሽን (PVH) የሚባል ዘመናዊ ልብሶችን በመስፋትና በዓለም አቀፍ ደረጃ የሚሸጥ የአሜሪካ ኩባንያ ልብሶችን በሐዋሳ የኢንዱስትሪ ፓርክ ያሰፋል። ኢንዱስትሪዎቹ የሚያመርቱት በብዛት የጨርቃ ጨርቅ ውጤቶችና ጫማዎች ሲሆኑ፣ ጥጥና ፈትሎችም ሆነ ልዩ ልዩ የመለዋወጫ ዕቃዎች ከቻይና የሚመጡ ናቸው። ከኢትዮጵያ የሚገዙት የጥሬ ሀብት ሶዲየም ሐይድሮክሳይድ ብቻ ነው። ኩባንያዎቹ ከኢትዮጵያ የሚገዙት የጥሬ ሀብት ከቻይናው ጋር ሲወዳደር ውድ ስለሆነ ሶዲየም ሐይድሮክሳይድን ከቻይና ለማስመጣት በማውጣት በማውረድ ላይ ናቸው። በእነዚህ ፋብሪካዎቹ ውስጥ የሚመረቱት ምርቶች ለውጭ ገበያ ተብለው ስለሆነ እዚያው ተቀጥረው የሚሠሩት ሠራተኞች የሚከፈላቸው ደመወዝ በጣም ዝቅተኛ ነው። ለምሳሌ አንድ ሠራተኛ በወር 650 የኢትዮጵያ ብር፣ በዶላር ደግሞ $22 ብቻ የሚከፈለው ሲሆን፣ ይህ ደመወዝ አንድ ተመሳሳይ ሥራ ከሚሠራ ቻይናዊ ጋር ሲወዳደር አንድ አራተኛውን ብቻ የሚያክል ነው። በሌላ ወገን የውጭ ሠራተኞች ከፍተኛ ደመወዝ ማግኘታቸው ብቻ ሳይሆን ለአምስት ዓመት ያህል ከቀረጥ ክፍያ ነፃ ናቸው። በተጨማሪ የሚኖሩት በልዩ ቤቶችና በውኃ አካባቢ ነው። በሌላ ወገን ግን ጥሩ ሥራ አገኘን ብለው ከገጠር የሚመጡና ፋብሪካዎቹ ውስጥ ተቀጥረው የሚሠሩት ሠራተኞች በሚያገኙት ደመወዝ ቤት ተከራይተው ለመኖር አይችሉም። ከዚህ በላይ ኩባንያዎቹ ሥራቸውን ለማንቀሳቀስ ለኃይል (Electricity) የሚከፍሉት በጣም ዝቅተኛ ዋጋ ሲሆን፣ ለውኃ ደግሞ ምንም ሳንቲም እንደማይከፍሉ ማስረጃዎች ያረጋግጣሉ። በተጨማሪም የኩባንያዎች ባለቤቶች ኩባንያዎቹ በተተከሉባቸው መሬት ላይ በካሬ ሜትር $25 የአሜሪካን ዶላር ብቻ የሚከፍሉ ሲሆን፣ በመሠረቱ በሐዋሳ ነዋሪው ሕዝብ ለአንድ ካሬ ሜትር መሬት $245 እንዲከፍል ይገደዳል።

በአጠቃላይ ሲታይ እንደዚህ ዓይነቱ የኢንዱስትሪ ፓርክ ለአገራችን የተስተካከለ ዕድገት የሚያመጣው ውጤት እዚህ ግባ የሚባል አይደለም። የኢንዱስትሪው ፓርክ ላይ ለአንድ አገር ዕድገት የሚያስፈልጉ እንደ ማሽን ኢንዱስትሪዎች፣ ልዩ ልዩ መሣሪያዎችን የሚሠሩ ኢንዱስትሪዎች፣ የመለዋወጫ ዕቃዎችን የሚያመርቱ ኢንዱስትሪዎች፣ የተለያዩ ለኃይል ማመንጫ የሚሆኑ መሣሪያዎችንና ኬብሎችን የሚያመርቱ. . .ወዘተ. እርስ በርሳቸው የተያያዙ ኢንዱስትሪዎች በፍፁም አልተተከሉም። ከዚህም በላይ አንድን የኢንዱስትሪ ፓርክ የኢንዱስትሪ ፓርክ የሚያሰኘው በዚያው ቦታ ላይ ምርምርና ዕድገት (Research and Development) ሲካሄዱና አዳዲስ ቴክኖሎጂዎች ሲፈጠሩና በሥራ ላይ ሲውሉ ብቻ ነው። ሐዋሳና ሌሎች ቦታዎች የተተከሉት የኢንዱስትሪ ፓርኮች እርስ በርሳቸው የተያያዙ (Integrated Industrial Development) አይደሉም።

ስለሆነም ለአንድ አገር የተስተካከለና ተከታታይነት ላለው የኢኮኖሚና የማኅበረሰብ የሚያበረክቱት አስተዋጽኦ እጅግ ዝቅተኛ ነው። በአንፃሩ በዝቅተኛ ደሞዝና በርካሽ አገልግሎት ከፍተኛ ትርፍ ወደ ቻይናና ወደ ተቀሩት አገሮች የሚተላለፍበትን አመቺ ሁኔታ ነው አገዛዙ የፈጠረው ማለት ይቻላል። መንግሥት የኢንዱስትሪ ፓርኩን ለማቋቋም $250 ሚሊዮን የአሜሪካን ዶላር ያወጣ ሲሆን፣ በዚህ ገንዘብ ተከታታይነት ያላቸውን ማሽኖችንና ልዩ ልዩ መሣሪያዎችን የሚያመርቱ አነስተኛና መካከለኛ ኢንዱስትሪዎችን ማቋቋም ይቻል ነበር። በተጨማሪም የተግባረዕድ ትምህርት ቤት በማቋቋም በኢንዱስትሪዎች ውስጥ ተቀጥረው ሊሠሩ የሚችሉ በተለያየ ሙያ የሚሠለጥኑ ወጣቶችን ማስመረቅ ይቻላል። አገዛዙ ይህን ዓይነቱን ለአንድ አገር የውስጥ ገበያ ዕድገትና ለኅብረተሰብዓዊ ለውጥ (Social Transformation) አስፈላጊ የሆነውን የኢንዱስትሪ ፖሊሲ ከመከተል ይልቅ የውጭ ምንዛሪ ለማግኘት ብቻ የተቋቋመው የኢንዱስትሪ ፓርክ ዕድገትን የሚያመጣ ሳይሆን፣ በራሱ በዚያ አካባቢ የሚኖረውን ማኅበረሰብ የሚያዘበራርቅ ነው፡፡ ከዕድገት ይልቅ ኋላ ቀርነትንና ድህነትን የሚያጠነክር ነው። ከዚህ ወጣ ብለን በእርሻው መስክ የሚካሄደውን መዋለ ንዋይ ክንዋኔ ስንመለከት የሕዝባችንን የኑሮ ሁኔታ ሊያሻሽልና ሁለገብ የሆነ የኢኮኖሚ ዕድገት ሊያመጣ የሚችል አይደለም።

በአበባና በሩዝ ተከላ የተሰማሩ የውጭ ኩባንያዎች ያደረሱት ጉዳት ለሁላችንም ግልጽ ነው። እንደሚድሮክ የመሰለው የሼህ መሀመድ ሁሴን አላሙዲን ኩባንያ 25 ንዑስ መስኮች ውስጥ ከፍተኛ እንቅስቃሴ ሲያደርግ፣ ጎልቶ የሚታየው በእርሻው መስክና በወርቅ ቁፈራ የሚያደርገው እንቅስቃሴ ነው። ኩባንያው በብዙ የኢኮኖሚ ዘርፎች ውስጥ የሚንቀሳቀስ ቢሆንም ለቴክኖሎጂ ዕድገትና ለሥራ ክፍፍል መዳበር የሚያበረክተው አስተዋጽኦ አልቦ ነው ማለት ይቻላል። በአንፃሩ ኩባንያው የተሰማራው ተቆፍሮ የወጣውን ወርቅና የእርሻ ምርት በቀጥታ ወደ ውጭ በማውጣት ራሱንና የውጭ ከበርቴዎችን ማደለብ ነው። የእርሻውን መስክ ጠጋ ብለን የተመለከትን እንደሆን አሁን በቅርቡ ‹‹አረንጓዴው ወርቅ›› (The Green Gold) በመባል የታየው የዶክሜንተሪ ፊልም የሚያረጋግጠው፣ ኩባንያው ገበሬውን ከመሬቱ በማፈናቀልና በመሬቱ ላይ ሩዝና ሌሎች የእህል ዓይነቶችን በማምረት የሳዑዲ ገበያ ላይ እንደሚያቀርብ ነው። በሌላ ወገን ግን አገራችን ከውጭ በዕርዳታ መልክ እህል ታገኛለች። አገዛዙም በተጨማሪ ከኢንዱስትሪ አገሮች ስንዴ በመግዛት ራሱ በአገራችን ገበያ ላይ ይሸጣል። ከመሬቱ የሚፈናቀለው ገበሬ የተወሰነው እዚያው ተቀጥሮ በዝቅተኛ ደመወዝ ሲሠራ፣ የሥራ ዕድል ያላገኘው ደግሞ ወደ አካባቢው ባሉ ከተማዎች በመሸሽ በሥራ ፈትነት እንዲንቀዋለል ተደርጓል። ይህም ማለት ተቋሙ እውነተኛ የእርሻ ባህል የሚያከናውንና አካባቢውን የሚያለማ ሳይሆን፣ ዋና ዓላማው ትርፍ ማካበት ብቻ ነው። በአካባቢው ማኅበረሰብዓዊ ክንዋኔዎች አይታዩም። አንድን ሕዝብ በአካባቢው እንዲኖር የሚያደርጉት ቤቶች፣ ትምህርት ቤቶች፣ ክሊኒኮችና ሌሎች መዝናኛ ቦታዎችና የባንክ ሲስተም በፍፁም አይታዩም። ስለሆነም ሼህ መሀመድ ሁሴን አላሙዲን ከመንግሥቱ መዘውር ጋር ባላቸው የጠበቀ ግንኙነት የፈለጉትን የሚያደርጉና በብዙ ሚሊዮን የሚቆጠር ሀብት ወደ ውጭ እንዲሸሽ ያደረጉና የሚያደርጉ ነው። ተቋሙ የሥራ መስክ የከፈተ ቢመስልም ጠቅላላው ድርጊቱ አንድ የሠለጠነና የመዋለ ንዋይ ክንዋኔን ደረጃዎችንና ደንቦችን ጠብቆ እንደሚንቀሳቀስና ምሳሌ ሊሆን እንደሚችል ዓይነት የከበርቴ ወይም አነስተኛ ከበርቴ መደብ አይደለም። ድርጊቱ የዘረፋነትና ባህልን የማበላሸት ባህሪ ያለው ነው። ስለሆነም ጤናማ ለሆነ የኢኮኖሚና የኅብረተሰብ ዕድገት የሚያበርክተው አስተዋጽኦ እዚህ ግባ የሚባል አይደለም። ሰውየውና ኩባንያው በቀጥታ ከፍተኛ የሆነ የማኅበራዊና የባህል እንዲሁም የአካባቢ ቀውስ ያደረሱና የሚያደርሱ ናቸው። በቀላሉ ሊታረም የማይችል የባህልና የማኅበራዊ ቀውስ በአገራችን ምድር ማስፋፋት ችለዋል።

ከዚህ በተረፈ የአገራችን ጥንታዊ ዘሮች እንዳሉ በመዘረፍ ሞንሳቶ ላቦራቶሪው ውስጥ በሚያዳቅላቸው የዘር ዓይነቶች (Genetically Modified Seeds) ተተክተዋል። በተለይም ጥንታዊው የጥጥ ዘር በላቦራቶሪ ውስጥ በተደቀለ ዘር እንደተተካ አሁን በቅርቡ በእርሻ ሚኒስትር ውስጥ ተቀጥሮ የሚሠራ አንድ ግለሰብ ጥያቄ ቀርቦለት ዘሩን መጠቀሙ ምንም ጉዳት እንደማያመጣ ለማብራራት ሞክሯል። በሌላ ወገን ግን በአውሮፓ አገሮች ላቦራቶሪ ውስጥ የተደቀሉ ዘሮችን መጠቀም ክልክል ነው። ይሁንና ግን በእኛ አገር እስከዚህም የሳይንስ ምርምር ባልተስፋፋበትና ባልዳበረበት አገር ማንም ተቃዋሚ ኃይል የለም በማለት ለገበሬው ዘሩን እንዲጠቀም ማደል ከፍተኛ ኃላፊነት የጎደለው ተግባር ነው። በተለይም ይህንን ዓይነት ዘር በብዛት የሚጠቀሙ እንደ ብራዚልና አርጀንቲና የመሳሰሉ አገሮች ውስጥ ገበሬዎችና ቤተሰቦቻቸው ተባዮችን ለማጥፋት በሚረጨው መርዝ በመበከል ለበሽታ እንደተጋለጡ ዶክመንተሪ ፊልሞችና ጥናቶች ያረጋግጣሉ። በእርሻው አካባቢ የሚወለዱ ሕፃናት የአካል ጉድለቶች ይታይባቸዋል። ያም ሆነ ይህ አገራችን በዘር ብቻ ሳይሆን ጥገኛ ለመሆን የበቃችው የተባይ ማጥፊያም ከውጭ የሚመጣ ነው። እንደሚባለው በላቦራቶሪ ውስጥ የተዳቀሉ ዘሮች ከተባይ የሚከላከል ውስጣቸው የተተከለ ልዩ ነገር የለም ቢኖርም አይሠራም። ይህ ቢሆን ኖሮ በላቦራቶሪ የተዳቀሉ ዘሮች በሚዘራባቸው ማሳዎች ውስጥ ተጨማሪ የተባይ ማጥፊያ ኬሚካሎች ባልተረጩ ነበር።

ሰሞኑን የጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድን ሥልጣን መያዝ አስመልክቶ ከሃያ በላይ የሚቆጠሩ የአሜሪካን ኩባንያዎች ወደ አገራችን ምድር መጥተዋል። ዋና ዓላማቸውም የተለያዩ የመዋለ ንዋይ ክንውኖችን ለማጥናት ሲሆን፣ አትክሮአቸውም በተለይም በእርሻው መስክና በጥሬ ሀብት ቁፈራ ላይ ይመስላል። አንዳንድ ቦታዎች ገበሬውን በማፈናቀል ሙዝ በብዛት ተመርቶ ወደ አሜሪካ እንዲጫን ይፈልጋሉ። ይህም ማለት ዩናይትድ ፍሩት ካምፓኒ (United fruit Company) በመካከለኛው አሜሪካ አገሮች ውስጥ የሠራው ወንጀልና ያካሄዳቸው የመንግሥት ግልበጣዎችና የደገፋቸው ፋሺሽታዊ አገዛዞች በአገራችንም ሊደገም ይችላል። በመካከለኛው አሜሪካ አገሮች የሙዝ ማሳ ውስጥ ተቀጥረው የሚሠሩ ለአቅመ አዳም ያልደረሱ ልጆችና አዋቂዎች በሚሠራጨው መርዝ ለበሽታ እንደተጋለጡ እንደዚሁ ጥናቶችና ዶክመንተሪ ፊልሞች ያረጋግጣሉ። ይህ ብቻ ሳይሆን በሙዝ ማሳ ውስጥ ተቀጥረው የሚሠሩት ሠራተኞች መብታቸውን የሚያስከብርላቸው የሙያ ማኅበርም ሆነ መንግሥት የላቸውም። ልጆቹም ትምህርት ቤት የመሄድ መብታቸው የተነፈገ ነው። ከዚህ ሁኔታ ስንነሳና ከእውነተኛ የኢኮኖሚ ዕድገት አንፃር የውጭ አገር ኩባንያዎች በእርሻው መስክ መሰማራት ብሔራዊ ነፃነታችንን የሚቀናቀን ብቻ ሳይሆን በቀላሉ ሊከፈል የማይችል አደጋ ውስጥ ልንወድቅ እንችላለን። በቤተሰብና በመካከለኛ አራሾች የሚካሄድ የእርሻ ባህል እንዳይስፋፋ ያግዳል። ቀስ በቀስ ለብዙ መቶ ዓመታት ያካበትነው የእርሻ ባህላችን መውደሙ ብቻ ሳይሆን የአመጋገብ ባህላቸው በመቀየር ሰፊው ሕዝባችን ለበሽታ እንዲጋለጥ ይደረጋል። ከዚህም ባሻገር የውጭ ኩባንያዎች በወርቅና በሌሎች ማዕድኖች ቁፈራ ላይ ለመሰማራት ይሹ ይሆናል። በተለይም የአሜሪካ፣ የፈረንሣይና የእንግሊዝ ኩባንያዎች በላቲን አሜሪካ፣ እንደ ፔሩ በመሳሰሉት አገሮችና፣ አፍሪካ ውስጥ ደግሞ በመካከለኛው አፍሪካ አገሮች፣ በኮንጎ በማዕድን ቁፈራ በመሰማራት የሚያደርሱት የአካባቢ ውድመትና የማኅበረሰብ ቀውስ ሠለጠን ከሚሉ አገሮች የሚጠበቅ አይደለም። የአሜሪካ ኩባንያዎች በተለይም ፔሩ ውስጥ ነዋሪውን ሕዝብ በማፈናቀልና አካባቢውን በመመረዝ የሚፈጽሙት ወንጀል በቀላል ቋንቋ የሚገለጽ አይደለም። ዩራኒዩም የሚያወጡ የፈረንሣይ ኩባንያዎችም እንደዚሁ በኒጀርና በማሊ እንዲሁም በመካከለኛው አፍሪካ መሬቱን በመመረዝ የሚፈጽሙት ወንጀል ተዘርዝሮ የሚያልቅ አይደለም። ከዚህ ሁኔታ ስንነሳ የኢትዮጵያ ሕዝብ ሳያውቀውና፣ ምሁሩ ሳይከራከርበት፣ እንዲሁም ሕገ መንግሥቱን መሠረት ያላደረገ ማንኛውም የውጭ አገር የመዋለ ንዋይ እንቅስቃሴ መካሄድ ያለበት አይመስለኝም። የጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አገዛዝ በዚህ ላይ በቂ ግንዛቤ ይኖረዋል ብዬ እገምታለሁ። ይህ ብቻ ሳይሆን የጥሬ ሀብት አላቂ እንደመሆኑ መጠን ጥንቃቄን የሚጠይቅ ነው። ሊያገለግልና መዋል ያለበትም ለአገር ግንባታ ብቻ ነው። የዓለም አቀፍ ኩባንያዎች በሚንቀሳቀሱባቸው የሦስተኛው ዓለም አገሮች በሙሉ የጥሬ ሀብቶች እየተሟጠጡ እንደሆነ ጥናቶች ያመለክታሉ። ለእርስ በርስ ጦርነቶችና ላለመረጋጋት ምክንያቶች ናቸው። ከዚህ በመነሳት ሰሞኑን 36 የኢሕአዴግ የሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባላት የአገር ውስጥ ሰባት ኩባንያዎችን ድርሻ ለአገር ውስጥና ለውጭ ከበርቴዎች የመሸጡ ጉዳይ ብዙዎቻችንን ያነጋገረ ነው። በመጀመርያ ደረጃ፣ ኮሚቴው አንዳች ውሳኔ ላይ ከመድረሱ በፊት ጉዳዩ ፓርላማ ውስጥ ለክርክር መቅረብ ነበረበት። በሁለተኛ ደረጃ የሕዝብን ንብረት በድርሻ መልክ መሸጥ በሕገ መንግሥቱ የሚደገፍ መሆኑን መረጋገጥ ነበረበት። በሦስተኛ ደረጃ፣ የተለያየ አመለካከት ያላቸው ምሁራን አስተያየታቸውን እንዲሰጡ መጋበዝ ነበረባቸው። በአራተኛ ደረጃ ሕዝቡ እንዲያውቀውና እንዲወያይበት አስፈላጊ ነበር። ይህም ማለት አንድ መንግሥት አንድ ኮሚቴ በመፍጠር ኮሚቴው በዚህ መልክ ተስማምቷል ብሎ የዱብ ዕዳ ማውረድ ያለበት አይመስለኝም። ዴሞክራሲያዊ አሠራርም አይደለም። ሀብቱ የመንግሥት ሳይሆን የኢትዮጵያ ሕዝብ እንደመሆኑ መጠን መንግሥት ሕዝብን የሚጎዳ ውሳኔ ላይ መድረስ ያለበት አይደለም። ያም ሆነ ይህ የሚነሱት ጥያቄዎች አሁን አገሪቱ ባለችበት ያልተረጋጋ ሁኔታ የእነዚህን ኩባንያዎች ድርሻዎች መሸጡ ጥቅሙ ምን ላይ ነው? የሚለው አብዛኛዎቻችንን እያነጋገረ ይገኛል። ከዚህም በላይ ከኢኮኖሚ ግንባታ አንፃር ሲታይ ሌሎች ቅድሚያ የሚሰጣቸው፣ ድህነትን መቅረፍና ቀስ በቀስ ማውደም የመሳሰሉት የተወሳሰቡ ችግሮች እያሉ ለምን የኩባንያዎችን ድርሻ መሸጡ ላይ ቅድሚያ ተሰጠ? ሰፋ ያለ ኢኮኖሚያዊ ዕቅድ ከማውጣት ይልቅ በአሁኑ ወቅት በነዚህ መስኮች ላይ ለምን አትኩሮ ተሰጠ? መንግሥትና ሕዝብስ በዚህ ዓይነቱ ሒደት ምን ጥቅም ሊያገኙ ይችላሉ? የሚነሳው ጥያቄ የመሸጥና ያለመሸጥ ወይም የአገርን እሴት ለውጭ ከበርቴዎች አሳልፎ የመስጠቱ ጉዳይ ሳይሆን፣ ከዕድገት አንፃር ጥቅሙ ምንድነው? የሚል ነው። ድርሻዎችን በመሸጥ መንግሥት የሚፈልገውን የውጭ ምንዛሪ ሊያገኝ ይችላል ወይ? መንግሥትስ ድርሻዎችን በመሸጥና ዶላር በማግኘት አገሪቱ ያላትን የውጭ ምንዛሪ እጥረት መፍታት ይችላል ወይ? ድርሻ መሸጡ የአንድ ጊዜ ሒደት ብቻ ወይስ ተከታታይነት ይኖረዋል ወይ? በእነዚህ ዙሪያ እንቅስቃሴዎች ይስፋፋሉ ወይ? በዚህ መልክስ አዲስ ዓይነት የቴክኖሎጂ ምጥቀት ሊታይ ይችላል ወይ? በተጨማሪም የሥራ መስክ በመክፈት ለአጠቃላዩ የኢኮኖሚ እንቅስቃሴ ልዩ ዓይነት እምርታ ሊሰጠው ይችላል ወይ? እንደዚህ እያልን ብዙ ጥያቄዎችን ለማንሳት እንችላለን። አብዛኛውን ጊዜ የሦስተኛው ዓለም አገሮች በመንግሥት ቁጥጥር ሥር ያሉ የአገልግሎት መስጫ ድርጅቶችን ወደ ግል በሽያጭ ሲያዘዋውሩ ወይም ድርሻ በመሸጥ የአገር ውስጥና የውጭ ከበርቴዎች ተካፋይ እንዲሆኑ ሲያደርጉ ተስፋ የሚያደርጉት ነገር አለ። ይኸውም የውጭ ምንዛሪ ይገኛል፣ ኢንቨስተሮች የበለጠ ሀብታቸውን በማፍሰስ ለዕድገት አመቺ ሁኔታን ይፈጥራሉ፤ በዚያው መጠንም የቴክኖሎጂ ልውውጥ በማድረግ ለአጠቃላይ ዕድገት አስተዋጽኦ ለማድረግ ይችላሉ ከሚለው በኢምፔሪካል ደረጃ ካልተረጋገጠ ሁኔታ በመነሳት ነው። ባላፉት 30 ዓመታት ግሎባላይዜሽን የሚሉት ጽንሰ ሐሳብ ከተስፋፋና የኢኮኖሚ ተዋንያን (Global Players) በዓለም አቀፍ ደረጃ ሲሽከረከሩ የሚሰብኩት ነገር በግሎባላይዜሽን አማካይነት የዓለም ሕዝብ አዲስ የሆነ የዕድገት ምዕራፍ ውስጥ ገብቷል፤ ሁሉም ነገር ለገበያው መለቀቅ አለበት፤ መሽጥ መለወጥና የመንግሥታትን ሀብት ወደ ግል ማዘዋወር (Deregulation) አማራጭ የሌለው አካሄድ ነው እያሉ በመስበከ ነው ብዙ መንግሥታትን መቀመቅ ውስጥ የከተቷቸው። በተጨማሪም የገበያን ኢኮኖሚ የሚያራምዱ አክራሪ አቋም ያላቸው አማካሪዎች ደግሞ እንደ ውኃ ማሠራጫ፣ እንደ ኃይል ማመንጫ፣ ቴሌኮሙዩኒኬሽን፣ የባቡር መስመሮችንና ባቡሮች በመንግሥት ቁጥጥር ሥር መዋላቸው የገበያን ሕግ የሚፃረርና ተፈጥሯዊ ያልሆነ ኢኮኖሚያዊ ክንዋኔ ነው በማለት በመንግሥታትና በኢኮኖሚ ኤሊቱ ላይ ጫና ያደርጋሉ። ግፊቱን መቋቋም የማይችሉና በሰበካው የሚታለሉ መንግሥታት እውነት እየመሰላቸው የመንግሥትን ሀብት ለሽያጭ ያቀርባሉ። ይሁንና ግን ሁኔታዎችን በጥብቅ የተከታተለና ያጠና በተለይም በሦስተኛው ዓለም አገሮች ውስጥ የመንግሥት ሀብቶችን ወደ ግል ማዘዋወሩ የተጠበቀውን ውጤት እንዳላመጣ ነው በየአገሮች ውስጥ በገሃድ የሚታዩት ተጨባጭ ሁኔታዎች የሚያረጋግጡት። በተለይም የውጭ ከበርቴዎች ዋና ዓላማ ከፍተኛ ትርፍ ለማካበት ስለሆነ በየመስኩ የሚሠራውን ሠራተኛ ትርፍ ነው (Redundant) በማለት ሲያባርሩ ነው የሚታዩት። ይህም ማለት ተጨማሪ የሥራ መስክ መክፈት ቀርቶ ተቀጥሮ ይሠራ የነበረውን የተወሰነውን የሰው ኃይል እንደሚያባርሩ ነው ጥናቶች የሚያረጋግጡት። ይህ አንደኛው ሲሆን፣ በሁለተኛ ደረጃ ለውጭ ከበርቴዎች የሚሸጡት ኩባንያዎች ውስጥ መሠረታዊ የሆነ የቴክኖሎጂ መሻሻል ሲደረግ አይታይም። ይህም ማለት የቴክኖሎጂ ልውውጥ በማድረግ ምርት በጥራትም ሆነ በብዛት ምጥቀት አያገኝም። የውጭ ኩባንያዎች ዋናው ዓላማም በተለይም እንደ ቴሌኮሙዩኒኬሽን የመሳሰሉትን በመግዛት ወይም በድርሻ በመካፈል የተንቀሳቃሽ ስልክ (Mobile) ለማስፋፋት እንጂ ኬብሎችን በማስፋፋት በእያንዳንዱ ቤት ውስጥ ቋሚ ስልክ ለመትከል አይደለም። እንደምናውቀው በአንድ አገር ውስጥ ቋሚ ስልክ ከተስፋፋ የተሻለ የስልክ ግንኙነት መፈጠሩ ብቻ ሳይሆን የኬብል ቴክኖሎጂም በዚያው አገር ውስጥ ሊስፋፋና ምርምርም ሊደረግበት ይችላል። በተለይም አንድ አገር ኬብሎችንና ዋየሮችን፣ እንዲሁም መደወያዎችን ራሷ የምታመርት ከሆነ አዲስ ቴክኖሎጂን መማሯ ብቻ ሳይሆን፣ በዚህ አማካይነት ለብዙ መቶ ሺሕ ሰዎች የሥራ መስክ ሊከፈት ይችላል። በተጨማሪም የቋሚ ስልክ መስፋፋት ለፈጣን የኢንተርኔት ሥርጭት (Broad Band) መስፋፋት አመቺ ነው። ከዚህም በላይ ከተንቀሳቃሽ ስልክ ይልቅ የቋሚ ስልክ መስፋፋት ለጤንነት በጣም ጠቃሚ ነው። ተንቀሳቃሽ ስልክን ለማስፋፋት ሲባል በየቦታው የሚተከሉ ቋሚ ብረቶችና የማግኔቱ ኃይል ለጤንነት አደገኛ እንደሆኑ ጥናቶች ያረጋግጣሉ።

ወደ ሌሎች እንደ ውኃና እንደ ባቡር የመሳሰሉትም ስንመጣ ወደ ግል ሀብትነት በተዘዋወሩት በእነዚህ መስኮች ውስጥ መሻሻል አይታይም። የውኃ ሥርጭትን ሁኔታ ስንመለከት ኔስትለስ የሚባለው የስዊዘርላንድ የምግብና የውኃ አምራችና አከፋፋይ ኩባንያ ከሦስተኛው ዓለም መንግሥታት ጋር በመመሰጣጠር ውኃ የማውጣት መብት (Water Grabbing) በመግዛት ንፁህ ውኃ በየቤቱ የሚያዳርስ ሳይሆን፣ ውኃውን በፕላስቲክ ጠርሙሶች በመሙላትና በመሸጥ፣ ከፍተኛ ትርፍ ሲያካብት፣ አብዛኛው ሕዝብ ደግሞ ንፁህ ውኃ የማግኘት መብቱ እንዳለ ተነጥቋል። ኩባንያው ውኃ እንዲያወጣ መብት በገዛበት እንደ ፊሊፒንስ በመሳሰሉ አገሮች ውስጥ አብዛኛው ሕዝብ ንፁህ ውኃ ገዝቶ የመጠጣት አቅም ስሌለው የደፈረሰ ውኃ እንዲጠጣ ተገዷል። በፕላስቲክ የታሸጉ ውኃዎችን ገዝቶ መጠጣት የሚችለው የየአገሩ ኢሊት ብቻ ነው። የኔስትለስን ሕገወጥና ሥነ ምግባር የሌላቸውን ሥራዎች የሚያጋልጡ ዶክመንተሪ ፊልሞችና ጥናቶች እንደሚያረጋግጡት ኩባንያው ካለምንም ይሉኝታ የአንዳንድ የሦስተኛውን ዓለም አገሮችን የውኃና የምግብ ኢንዱስትሪዎች በመቆጣጠር ለጤንነት መቃወስ ምክንያት እንደሆነ ነው። ወደ ባቡር መንገድና ኔት ሲስተሙ ስንመጣ በተለይም ከእንግሊዝ ልምድ እንደምናየው ወደ ግል ሀብትነት የተሸጠው ይህ የመመላለሻ መንገድ እንዳልተሻሻለና ሐዲዶችና ባቡሮቹ ባለመታደሳቸው በብዙ ሰዎች ላይ አደጋ እንዳደረሱ ነው መረጃዎች የሚያረጋግጡት። በአንፃሩ የባቡር መስመሮችና ባቡሮች ወደ ግል ሀብትነት ባልተዘዋወሩባቸው እንደ ጀርመንና ስዊዘርላንድ፣ ኦስትሪያና በስካንዲኔቢያን አገሮች በተቀላጠፈ መልክና በትርፍ የሚሠሩ ናቸው። በየጊዜውም አዳዲስ ባቡሮች በመስመር ውስጥ ሲካተቱና ሐዲዶችም ሲጠገኑ ወይም በአዲስ ሲተኩ ነው የምንመለከተው። በሌላ ወገን ግን በኦስትሪያም ሆነ በጀርመን የግል ባለሀብቶች አዳዲስ ባቡሮች በመግዛትና ሐዲዶችን በመከራየት በመንግሥት ቁጥጥር ሥር ካሉ ባቡሮች ጋር ሊወዳደሩ ይችላሉ።

ለማንኛውም ከዚህና ከሌሎች አያሌ ምክንያቶች ስንነሳ፣ በተለይም እንደ ኢትዮጵያ በመሳሰሉት በቴክኖሎጂና በኢንስቲቱሽን፣ እንዲሁም በውድድር ወደ ኋላ በቀሩ አገሮች ውስጥ በመንግስት ቁጥጥር ሥር ያሉ የአገልግሎት መስጫ ድርጅቶችን ድርሻቸውን መሸጥ ወይም እንዳሉ ወደ ግል ሀብትነት ማዘዋወር ከጥቅሙ ይልቅ ጉዳቱ ነው የሚያመዝነው። በመንግሥት ቁጥጥር ሥር ያሉ ተጨባጭ ምርትን የሚያመርቱ ኢንዱስትሪዎች ለአገር ውስጥ ከበርቴዎች ቢሸጡ ለዕድገት ያመቻሉ። ያም ሆነ ይህ የአንድ መንግሥት ዋና ተግባር የአገሩን ሕዝብ ደኅንነት መጠበቅ፣ አስፈላጊውን አገልግሎት እንዲያገኝ የአገልግሎት መስጫ ድርጅቶችን በየቦታው ማስፋፋት ስለሆነ በመንግሥት ሥር ያሉ የአገልግሎት መስኮች ባይሸጡ ይሻላል። በሌላ ወገን ግን የግል ባለሀብቶችና የውጭ ኩባንያዎች በአገራችን ምድር የባቡር መስመር እንዘረጋለን፣ ባቡሮችም በብዛት እናስገባለን፣ እዚያውም እንዲመረቱ እናደርጋለን፣ ሰዎችንም እናሠለጥናለን የሚሉ ከሆነ ኢንቬስት ማድረግ ይችላሉ። በተጨማሪም ቋሚ ስልክ በመትከል ሰፊው ሕዝብ እንዲጠቀም እናደርጋለን፣ በየቤቱ ንፁህ ውኃ ማስገባት እንፈልጋለን ካሉ ገበያውን ክፍት ማድረግ ይቻላል። ይሁንና ግን የውጭ ኩባንያዎች ለአንድ አገር ዕድገት በሚጠቅሙ እንደባቡር በመሳሰሉ መስመሮች መዘርጋት ላይ በምንም ዓይነት አይሳተፉም። ዋና ዓላማቸውም ትርፍ ማግኘት ብቻ ስለሆነ ለአንድ አገር ዕድገት በሚጠቅሙ መሠረታዊ ነገሮች ላይ በፍፁም ሊሳተፉ አይፈልጉም። በታሪክ እንደታየው በአውሮፓ ምድርና በአሜሪካም ጭምር የባቡር መስመሮች የተስፋፉትና ባቡሮችም የተመረቱትና የሚመረቱት በመንግሥት መነሳሳትና ከፍተኛ ተሳትፎ ብቻ ነው። ሰለሆነም በእኔ እምነት እንደ አየር መንገድ የመሳሰሉት የተገለሉ ኢኮኖሚዎች (Enclave Economy) በድርሻ መልክ በመሸጣቸው አየር መንገዱ መሻሻልንና መስፋፋትን ያገኛል ብየ አላምንም። አሁን ባለው የጦፈ ዓለም አቀፋዊ ውድድር የበለጠ ትርፍ ለማምጣትና ድርሻ ገዥዎችንም ለማስደሰት ሲባል (Share Holder Value) ሠራተኞችን ማባረርና መስመሮችንም ወደ መዝጋት ሊደረስ ይቻላል። እንደ ኢትዮጵያ የመሳሰሉ ደካማ አገሮች ቀርቶ ራሳቸው እንደ ጀርመን የመሳሰሉ ከፍተኛ ዕድገት ላይ የደረሱ አገሮች አንዳንድ ኩባንያዎች የድርሻ ገዥዎችን ግፊት መቋቋም አቅቷቸዋል። በዚህም የተነሳ የተለያዩ የምርት ዓይነቶችን የሚያመርቱና በቴክኖሎጂ ገፍተው የሄዱ የብረታ ብረት ፋብሪካዎች የመጨረሻ መጨረሻ ሊከስሩ ችለዋል። ባጭሩ ከአጠቃላይ የኢኮኖሚ ዕድገት ሁኔታ ስንነሳ ከላይ የተጠቀሱትን ድርጅቶች ወደ ግል ማዘዋወር ወይም የተወሰነ ድርሻ መሸጥ የተጠበቀውን ውጤት ሊያመጣ አይችልም። ከዚህ ጋር ተያይዞ የመንግሥት ሀብቶችን ወደ ግል ለማዘዋወር የሚያመቻቹና ጥናት የሚያቀርቡ፣ እንዲሁም የሚያማክሩ 21 የሚሆኑ የታወቁ አገር ቤት ውስጥ የሚኖሩና በዓለም አቀፍ ተቋማት ውስጥ የሚሠሩ ግለሰቦችን የጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ አገዛዝ መርጧል። የአብዛኛዎችን ስም ዝርዝር ስንመለከት አብዛኛዎች የኒዎሊበራል አለመለካከት ያላቸው ሲሆኑ፣ ሌሎች በተለይም በውጭ ተቋማት ውስጥ የሚሠሩ ይህንን ያህልም ኅብረተሰብን በሚመለከት ግልጽ አቋም ያላቸው አይደሉም። እምነታቸውና ርዕዮተ ዓለማቸው ንፁህ የሆነ የገበያ ኢኮኖሚ በመሆኑ ለአንድ አገር ሁለንታዊና እኩልነትን በሚያመጣ መልክ ለማሳደግ የሚችል የኢኮኖሚ ፖሊሲ የሚያፈልቁ አይደሉም። እስካሁን እንዳየነውና ተግባሮችም እንደሚያረጋግጡት በዓለም አቀፍ ተቋማት ውስጥ ለብዙ ዓመታት የሠሩና የሥራ ልምድም ያካበቱ ግለሰቦች ሥልጣን ላይ በሚወጡበት ጊዜ አገራቸውን በተስተካከለ መልክ ሊገነቡ እንደማይችሉና የሕዝቦቻቸውን ፍላጎትና ህልም ማሟላት እንደማይችሉ ነው የምንገነዘበው። ዓለም ባንክ ውስጥ ይሠራ የነበረውና በኋላ የጋና ፕሬዚዳንት የሆነው ኩፎርና (Kufuor) የላይቤሪያው ሴት ፕሬዚዳንት የሆኑት ኤለን ጆንሰን (Ellen Johnson) እንዳረጋገጡት እነዚህ ሁለት ፕሬዚዳንቶች አገሮቻቸውን የሳይንስና የቴክኖሎጂ ባላቤቶች በማድረግ ሕዝቦቻቸው ተከብረውና ተደስተው እንዲኖሩ ለማድረግ የቻሉ አይደሉም። የዓለም አቀፍ ኮሙዩኒቲው ተገዥዎችና ትዕዛዝ ተቀባዮች በመሆናቸው የየአገሮቻቸው የጥሬ ሀብት፣ ወርቅ ጋና ውስጥ፣ የጎማ ወተት ደግሞ ላይቤሪያው ውስጥ እንዲመረትና እንዲዘረፉ ያደረጉ ናቸው። በኩፎር የአገዛዝ ዘመን የጋና ዋና ከተማ ውዳቂ የኤሌክትሮኒክስ ጥሬ ሀብቶች መጣያ በመሆን በአፍሪካ ውስጥ ተቀዳሚ ቦታ ይዟል። የተለያዩ ጥሬ ሀብቶችን ለመፈለግ እዚያ ተሰማርተው የሚለቅሙ ሕፃናትና ወጣት ልጆች የሰውነት አካሎቻቸው፣ እንደ ጉበትና ሳምባ የመሳሰሉት በበሽታ ተለክፈዋል። ኩፎር ጋናን የቆሻሻ መጣያና ሀብቷም በውጭ አገር ኩባንያዎች እንዲዘረፍ በማድረጉ የተከበረ መሪ በመባል ይታወቃል። በፕሬዚዳንት ኤለን ጆንሰን ስምንት የአገዛዝ ዘመን የላይቤሪያ ወጣት የጎማ ወተት ማምረቻ ፕላንቴሽን ውስጥ ተቀጥሮ በመሥራት የሚበዘበዝ ነበር። ለዚህ ተግባራቸውና ላይቤሪያን በማደህየታቸው ኤሊን ጆንስን የኖቤል ተሸላሚ ለመሆን በቅተዋል። በአጭሩ በዓለም አቀፍ ተቋማት ውስጥ ተቀጥረው ሠላሳና ከዚያም ዓመታት በላይ የሠሩ ግለሰቦች በየአገሮቻቸው ሲሾሙ ታሪክ የሠሩበትና ጤናማ ኅብረተሰብ የገነቡበት ዘመን የለም። ዕውቀታቸው በኒዎሊበራሊዝም ላይ የተመሠረተ በመሆኑ ሹመት ሲሰጣቸው ይህንኑ ተግባራዊ ከማድረግና ኅብረተሰብን ከማዘበራረቅ በስተቀር አንድን አገር የሳይንስና የቴኮኖሎጂ፣ እንዲሁም የባህል አገር በማድረግ አገሮቻቸውን ያስከበሩበት ጊዜ የለም። ስለሆነም በተቻለ መጠን አገር ውስጥ በሠለጠኑና በተለይም በውጭ አገሮች ዩኒቨርሲቲዎች ውስጥ በሳይንስና በቴክኖሎጂ ሥራ ተሰማርተው ምርምር የሚያደርጉና የሚያስተምሩ ኢትዮጵያኖችን መሰብሰቡና ምክር መጠየቁ የተሻለ አማራጭ ነው ብዬ አምናለሁ። በተለይ የፊዚክስ፣ የማቲማቲክስ፣ የማቴሪያል ሳይንስ፣ የመካኒካል ኢንጂነሪንግና የኤሌክትሮኒክስ ሙያ ያላቸውና፣ ሌሎች ከተፈጥሮ ሳይንስ ጋር የተያያዘ ሙያ ያላቸው ምሁራን ለዕድገት የበለጠ ይጠቅሙናል። ለማንኛውም የዛሬውም ሆነ ወደፊት ሊመጣ የሚችለው አገዛዝ በአገራችን ምድር በሳይንስና በቴክኖሎጂ ላይ የተመሠረተ ለውጥ እንዲመጣ የሚፈልግ ከሆነ በተለይም የብረታ ብረት ቴክኖሎጂዎችን፣ የተለያዩ መሣሪያዎችን የሚሠሩ የማሽን ኢንዱስትሪዎችን፣ የሕክምናን መሣሪያ የሚያመርቱና የሕክምና መሣሪያዎችንም መለኪያዎችን፣ ማለትም እንደ ፋይን ሜካኒክ የመሳሰሉት እንዲቋቋሙ ከኦስትሪያ፣ ከጀርመንና ከስዊዘርላንድ ከመሰሳሉት አገሮች ጋር ልዩ ዓይነት ስምምነቶች ማድረግ ይችላል። የምንፈልገው መሠረታዊና ሥነ ሥርዓት ያለው ለውጥ እስከሆነ ድረስ ስትራቴጂካሊ ማሰብ ያለብን ይመስለኛል። የለም ይህ አይደለም የሚያስፈልገን፣ የሚያስፈልገን የውጭ ምንዛሪ ለማግኘት በሚያስችሉን የኢኮኖሚ መስኮች ላይ ብቻ ነው መረባረብ ያለብን የምንል ከሆነ የድህነቱ ዘመን ይራዘማል። ስለሆነም ምርጫችን ከሁለት አንዱ መሆን አለበት። ወይ ሳይንሳዊ መሠረት ወዳለውና ወደ ተስተካከለ የኢኮኖሚ እንቅስቃሴና ወደ አገር ግንባታ ላይ ማትኮር፤ አልያም ደግሞ ቡና፣ አበባ፣ ሙዝና ሌሎች ፍራፍሬዎችን በመትከል የድህነቱንና የጥገኝነቱን ዘመን ማራዘም፡፡ ይህንን አወዛጋቢ ጉዳይ ትተን ወደ ነፃ ንግድ ስምምነት (Free Trade Agreement) ስንመጣ እንደ ኢትዮጵያ የመሳሰሉ አገሮች ከፍተኛ አጣብቂኝ ውስጥ የገቡ ይመስላሉ፡፡ በአብዛኛዎቻችን ዘንድ ያለው እምነት የነፃ ንግድ ስምምነት የአንድን አገር የኢኮኖሚ ዕድገት ማፋጠን እንደሚችል ነው።
ይቀጥላል

ከአዘጋጁጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እየገለጽን፣ በኢሜይል አድራሻቸው [email protected] ማግኘት ይቻላል፡፡

spot_imgspot_img
- Advertisment -

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

Related Articles