Saturday, June 22, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ኪንና ባህልጥገናው የተቋጨው የቤተ ጎልጎታ ሚካኤል ዘላሊበላ

ጥገናው የተቋጨው የቤተ ጎልጎታ ሚካኤል ዘላሊበላ

ቀን:

ቅዱስ ወንጉሥ ላሊበላ በ12ኛው ክፍለ ዘመን ካነፃቸው ውቅር አብያተ መቅደሶች አንዱ የሆነው የቤተ ጎልጎታ ሚካኤል ጥገናው ተጠናቆ በክብረ በዓሉ ወቅት ኅዳር 12 ቀን 2011 .ም. በቤተ ማርያም የነበረው ታቦተ ሕጉ ወደ መንበሩ ገብቷል፡፡

የቤተ መቅደሱ ጥገና የፊዚካል ፕሮጀክት በቅርስ ጥናትና ጥበቃ ባለሥልጣን (ቅጥጥባ) በተደራጀ የሳይንቲፊክና የአካባቢ ኮሚቴ የተመራ ሲሆን፣ የቤተ ክርስቲያኑን የጉዳት መጠን የሚያሳይ ስትራክቸራል ጥናት ከጣልያኑ ስቱዲዮ ክሮቺ ኩባንያ በመጡ መሐንዲሶች ተዘጋጅቶ መቅረቡ፣ ጥገና እና እንክብካቤውን የዓለም ቅርስ ፈንድ በባለቤትነት አከናውኗል፡፡

ባለሥልጣኑ በክብረ በዓሉ ወቅት እንዳስታወቀው፣ ለጥገናው ፕሮጀክት የተመደበው ከ700 ሺሕ በላይ ዶላር ውስጥ በኢትዮጵያ የአሜሪካ አምባሳደር ፈንድ 580 ሺሕ ዶላር ሲመድብ ቀሪውን 150 ሺሕ  ዶላር ከሌሎች ለጋሽ ድርጅቶች ተገኝቶ ፋይናንሱን በኤምባሲው በኩል እየተዳደረ ቆይቷል፡፡

የቤተ ጎልጎታ ሚካኤል ጥገና ተግባር ለመሰል ጥንታውያን መካነ ቅርሶችን ለመጠገን የሚያስችል ተሞክሮ የተገኘበት ነው ሲሉ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የቴክኖሎጂ ፋክሊቲ ተባባሪ ፕሮፌሰርና 2006 .ም. ጀምሮ በላሊበላ ውቅር አብያተ ክርስቲያናት ላይ በሚከናወነው የቅርስ ጥገናና እንክብካቤ በፕሮጀክት ገምጋሚነት ሲሳተፉ የነበሩት ኢሳይያስ ገብረ ዮሐንስ (ዶ/ር) ተናግረዋል፡፡

በላሊበላ መስቀል አደባባይ በርካታ ምዕመናንና እንግዶች በተገኙበት ሥነሥርዓት ላይ የተገኙት የሰሜን ወሎ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ ኤርሚያስ፣  የተከናወነውን ሥራ አወድሰውና ለወደፊቱም አብያተ መቅደሶቹን ለመንከባከብ ሁሉም ጥረት ማድረግ እንደሚገባው ካሳሰቡ በኋላ ‹‹ልጆቻችን የጥርስ ሐኪም ብቻ ሳይሆን የቅርስም ሐኪም መሆን ይገባቸዋል›› ብለዋል፡፡  

የቅዱስ ላሊበላ ደብር ዋና አስተዳዳሪ አባ ጽጌ ሥላሴ መዝገቡ በበኩላቸው የሥራው አፈጻጸምና የፋይናንስ ሪፖርትም ወደፊት መቅረብ እንደሚገባው ሳይገልጹ አላለፉም፡፡

ከዘጠኝ ወር በፊት የፕሮጀክት ስምምነት በተፈረመበት አጋጣሚ ‹‹ላሊበላ ትናንትን ከዛሬ ጋር ያገናኘ መንፈሳዊ ድልድይ ነው!›› በማለት ተናግረው የነበሩት በኢትዮጵያ የአሜሪካ አምባሳደር ማይክል ራይነርም በክብረ በዓሉ ወቅት ‹‹የላሊበላ ቤተ መቅደሶች ጥላዎች፣ ከለላዎች እናንተ ናችሁ›› በማለት ለኅብረተሰቡ አመላክተዋል፡፡  

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ለአምባሳደር ማይክል ሬይነርና ለባለቤታቸው የክብር ካባ አበርክተውላቸዋል፡፡

በቅዱስ ሚካኤል ዓመታዊ ክብረ በዓል ጋር በገጠመው የጥገናው ፕሮጀክት መጠናቀቅ ምዕመኑና ኅብረተሰቡ ደስታውን በዝማሬና በሆታ በዕልልታም ሳይገልጽ አላለፈም፡፡                                               

ቅጥጥባ ከወርልድ ሞኒዩመንት ፈንድ (የዓለም ቅርስ ድጋፍ) ጋር በመሆን በቤተ ጎልጎታና ቤተ ሚካኤል ላይ የጥገናና እንክብካቤ ሥራ ለመሥራት የሚያስችለውን የጥገና ፕሮጀክት ጥር 26 ቀን 2010 .. ይፋ ማድረጉ ይታወሳል፡፡

የቤተ ጎልጎታ ሚካኤል ጥገና ፕሮጀክት አንግቧቸው የነበሩት ሦስት ዋና ግቦች  በቤተ ክርስቲያናቱ ላይ የጥገና ተግባር በማከናወን ቅርሱን ከጉዳት መታደግ፤ በቤተ ገብርኤል ሩፋኤል ላይ የተገኘውን ተሞክሮ ማጎልበትና  የአገር ውስጥ የእጅ ሙያ ባለቤቶችን አቅም ማሳደግ መሆናቸው የባለሥልጣኑ ዋና ዳይሬክተር አቶ ዮናስ ደስታ ተናግረዋል፡፡

በቀጣይም በአምስቱ አብያተ መቅደሶች (ቤተ ማርያም፣ ቤተ መስቀል፣ ቤተ መድኃኔዓለም፣ ቤተ አማኑኤልና ቤተ አባ ሊባኖስ)  ላይ የሚታዩት ጊዜያዊ የብረት ጣራ ከለላዎች  የሚያስነሳ ፕሮጀክት ለመጀመር እየተሠራ መሆኑም ቅጥጥባ ገልጿል፡፡

ጥገናው የተቋጨው የቤተ ጎልጎታ ሚካኤል ዘላሊበላ

የላሊበላ ገጽታ

‹‹…የምገልጽበት ቋንቋ የለኝም፡፡ የዚህን ክቡር ሰው፣ ከሁሉም መሬታውያን በጥበብም ሆነ በሥነ ጽድቅ የከበረ ላሊበላ ከአንድ ደንጊያ፣ ከአንድ አለት ፈልፍሎ ዐሥር አብያተ ክርስቲያናትን ያነፀው ዐቢይ ሥራ የምገልጽበት ልሳን የለኝም::›› ከስምንት መቶ ዓመታት በፊት በዛጒዬ ሥርወ መንግሥት ዘመን በላስታ ላሊበላ የተሠሩትን ዕፁብ ድንቅ ውቅር አብያተ ክርስቲያናትን ያከናወናቸው የቅዱስ ላሊበላን ገድል በኋላ ዘመን ላይ የጻፈው ደራሲ ውሳጣዊ ስሜቱን የገለጸበት ነበር፡፡

የነዚህ አብያተ ክርስቲያናት ሥራ አስደናቂነት ለመግለጽ ቃል እንዳነሰው እነዚህ ላሊበላ ባንድ ቋጥኝ ያሠራቸው፣ ሰሎሞን በጢሮስ ንጉሥ በኪራም እየተረዳ በኢየሩሳሌም ካሠራው ቤተ መቅደስ እንደሚበጥልም አመስጥሯል፡፡ የላሊበላም ጥበብ ከሰሎሞን መብለጡን ጭምርም በመግለጽ ሰው ሁሉ እየመጣ ባይኑ እያየ ሊያደንቃቸው የሚገባ መሆኑንም ‹‹በላሊበላ እጅ የተሠሩትን ዕፁብ ድንቅ ግብረ ሕንፃዎችን ለማየት የሚፈቅድ ይምጣና በዓይኖቹ ይይ (ይምጻእ ወይርአይ በአዕይንቲሁ) ነበር፤›› ያለው፡፡

አቶ ተክለ ጻድቅ መኩሪያ ‹‹የኢትዮጵያ ታሪክ ኑቢያ አክሱም ዛጒዬ›› በሚባለው መጽሐፋቸው እንደገለጹት፣ የቅዱስ ላሊበላን ገድል የጻፈው ጸሐፊ ምንም ያህል የተሳሳተው ነገር የለም፡፡ የነዚህን የአብያተ ክርስቲያናት ሥራ የተመለከቱ የውጭ አገር ሰዎች እሥፍራው ድረስ እየመጡ ባይናቸው እያዩ ተደንቀዋል፡፡ ከተመለከቱትም ውስጥ ይኼን የመሰለ በቋጥኝ ውስጥ እየተፈለፈለ የተሠራ ብዙ አብያተ ክርስቲያናት በዓለም አለመኖሩን የገለጹም ብዙ ናቸው፡፡

‹‹አዲሲቱ ኢየሩሳሌም›› የሚል ተቀጽላ ያገኙት የመካከለኛው ዘመን ውቅር አብያተ ክርስቲያናት በዐረፍተ ዘመኑ ካገር ቤት እስከ ባሕር ማዶ የብዙዎች ጎብኚዎችን፣ ተሳላሚ ምዕመናን ቀልብ መያዝ ችለዋል፡፡ በዚህም ሳይገደብ በተባበሩት መንግሥታት የትምህርት፣ የሳይንስና የባህል ድርጅትዩኔስኮ የዓለም ቅርስ ሆኖ መመዝገብ መሥፈር ችለዋል፡፡

በኢትዮጵያ በርካታ አስደናቂ አብያተ ክርስቲያናት ይገኛሉ፡፡ ከነዚህም መካከል ገናና የሆኑት ካንድ አለት ተፈልፍለው የታነፁት ናቸው፡፡ የአገሪቱ የክርስትና መነሻ መዲና ከሆነችው አክሱም ደቡባዊ ምሥራቅ አቅጣጫ በተለያዩ መንገዶች 240 ኪሎ ሜትር እስከ 394 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ በምትገኘው ቅዱስ ላሊበላ ከተማ የሚገኙት ውቅር አብያተ ክርስቲያናት የኢትዮጵያን ጥንታዊ የኪነ ሕንፃ ትውፊትን በግሩም ሁኔታ የሚያንፀባርቁ ናቸው፡፡  ውቅር አብያተ ክርስቲያናትን በጉያዋ የያዘችው ላሊበላ በኦርቶዶክሳዊቷ የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ምዕመናን በየወቅቱ የሚዘልቁባት የሚሳለሙበት ሥፍራ ናት፡፡

በታሪክ እንደሚወሳው የከተማዋ የመጀመሪያ መጠሪያ ሮሃ ሲሆን 12ኛው ምዕት ዓመት የነገሠው ንጉሥ ላሊበላ አብያተ ክርስቲያናቱን ያነፀው እርሱ በመሆኑ ከተማዋ ስሙን አግኝታለች፡፡

አብያተ መቅሶቹ በሦስት የተለያዩ ሥፍራዎች ሲገኙ፣ ስድስቱ በሰሜን አቅጣጫ፣ አራቱ በሊባ (ደቡባዊ ምሥራቅ) አቅጣጫ ሆነው የሚገናኙበት መስመር አላቸው፡፡ 11ኛው በኖኅ መርከብ አምሳል የተሠራው ቤተ ጊዮርጊስ ግን ብቻውን ተነጥሎ ነው ያለው፡፡

በሰሜናዊ ክበብ የሚገኙ (1) ቤተ መድኃኔ ዓለም (2) ቤተ ማርያም  (3) ቤተ መስቀል (4) ቤተ ደናግል (5) ቤተ ሚካኤል (6) ቤተ ጎልጎታ ሲሆኑ፤ በሊባ በኩል (7) ቤተ አማኑኤል (8) ቤተ አባ ሊባኖስ (9) ቤተ መርቆርዮስ (10) ቤተ ገብርኤልና ቤተ ሩፋኤል ይገኛሉ፡፡ በምዕራባዊ አቅጣጫ ለብቻው ያለው ከላይ ወደታች ተፈልፍሎ የታነፀው 11ኛው ቤተ ጊዮርጊስ ይገኛል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የንብረት ማስመለስ ረቂቅ አዋጅና የሚስተጋቡ ሥጋቶች

ከሰሞኑ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የቀረበው የንብረት ማስመለስ ረቂቅ...

የመጨረሻ የተባለው የንግድ ምክር ቤቱ ምርጫና የሚኒስቴሩ ውሳኔ

በአገር አቀፍ ደረጃ ደረጃ የንግድ ኅብረተሰቡን በመወከል የሚጠቀሰው የኢትዮጵያ...

ሚስጥሩ!

ጉዞ ከካዛንቺስ ወደ ስድስት ኪሎ፡፡ የጥንቶቹ አራዶች መናኸሪያ ወዘናዋ...