- Advertisement -

ኃጢያታችንንና ሒሳባችንን እኩል ብናወራርድስ?

ሰላም! ሰላም! ውዷ ማንጠግቦሽ ስወጣ ስገባ፣ ‹‹አደራ ጠንቀቅ እያልክ?›› ስትለኝ ሰነበተች። ‘በተጠንቀቅና በመጠንቀቅ የምናመልጠው ስንቱን ይሆን?’ እያልኩ በውስጤ ‹‹ምኑን?›› ስላት፣ ‹‹ይኼን የሰሞኑን ቫይረስ ነዋ!›› አለች ጭንቅ ብሏት። ‹‹መቼ እኛ ዘንድ ደረሰ? ደግሞስ ከመጣ በአገር ነው በስንቱ ተሳቀን እንችለዋለን? ሲያመጣው መቀበል ነው እንጂ!›› ብላት ምን እንዳለችኝ ታውቀላችሁ? ኧረ አንዳንዴስ አለማወቅን የመሰለ ነገር የለም። ‹‹የለም እኛ ዘንድ በንክኪ ብቻ ሳይሆን በአስተሳሰብም ይጋባል እያሉ ናቸው፤›› ስትለኝ ደነገጥኩ። ያኔ ቋጥሬ በሃያ ቆርቆሮ የከደንኳትን ቤት በሳቅ ላፈርሳት ምን ቀረኝ! ‹‹ይሉኝታ በሚባል ደካማ ጎናችን እየተገባ አገር በብልጣ ብልጥነት የማንም መጫወቻ ትሁን?›› ስል የሰማኝ ምሁሩ የባሻዬ ልጅ ደግሞ፣ ‹‹አገር ሲያረጅ የጃርት መጫወቻ ይሆናል የሚለውን እኮ በዓይናችን አየነው፤›› ይለኛል። መቼም ቀለም የገባው እንደ እሱ ዓይነት ጠንቃቃ ሰው ባይኖረን እኮ አልቆልን ነበር። እስካሁንም ያለነው በኪነ ጥበቡ ነው፡፡

የባሻዬ ልጅ የአያት የቅድም አያቶቻችንን ታሪክ አጣቅሶ፣ ‹‹እነሱ ለአገራቸው በነበራቸው ወደር የሌለው ፍቅር በደስታ መስዋዕትነት መክፈላቸውን እያወቅን፣ እኔና አንተ ከእነ መሰሎቻችን የአገር መዥገር ስንሆን ያስቆጫል፤›› ባለኝ ቁጥር ኑሮን ለመቋቋም በሚል ሰበብ የተሰማራሁበትን የድለላ ሥራ እጠለዋለሁ። አቤት የመከራችን ብዛቱ? ቢል ቦርድና ፖስት ካርድ አሠርተን ኃጢያታችንን ካልተናዘዝን በስተቀር የእኛ ጉድ ተቆጥሮ የሚያልቅ አይመስልም። ታዲያ አደራችሁን ይህን ዓይነቱን ምክር ባላየ ባልሰማ እለፉት። ከባድ ነው እኮ፡፡ በዘመነ ውድድርና የብልፅግና ሩጫ ላይ ሆነን ባናይም እናያለን፣ እንዲሁም እናምናለን ካላልን ምን ተስፋ ይኖረናል? አይደል እንዴ? ብቻ አንዳንዴ ‹‹የማይመስል ነገር ለሚስትህ አትንገር›› እንደሚባለው፣ የሚመስለውን ከማይመስለው ብንለይ በጣም ጥሩ ነው፡፡ ካልሆነ ግን ይኼ ይሆን እንዴ በአስተሳሰብ የሚተላለፍ ቫይረስ የተባለው? የሚል ጥያቄ ይነሳል፡፡ ለሚነሳ ጥያቄ መልስ አለመስጠት ደግሞ ሌላ ጣጣ ይዞ መምጣቱ አይቀርም፡፡

ጨዋታን ጨዋታ ያነሳው አይደል? ይኼው በዚህ ሰሞን ያለብን እልፍ ችግር አልበቃ ብሎ የአገር አጥንት ተግጦ አለቀ፣ የገዛ ወገን በጭካኔ ፍዳውን ሲያይ ነበር ተብለን ስንተራመስ ሰነበትን። ማን አስጠንቃቂያችን፣ ማን አጥቂያችን እንደሆነ ሳናውቀው፣ አዳሜ አፍ ለአፍ ገጥሞ ‘ቹቹቹ’ ሲል ስንቱ ሥራውን በትኖት እንደሰነበተ አትጠይቁኝ። ያወቁበትና ያደላቸው የፋብሪካ ምርታቸውን በዓለም ገበያ ሲቸበችቡ፣ እኛ በድህነታችን ላይ ሥጋት ባጠላቸው መረጃዎች መናጣችንን ይዘን ቀጥለናል። ይኼን የሚታዘቡት አዛውንቱ ባሻዬ፣ ‹‹እሱ ያለው ላይቀር እንዲህ መጨናነቅ ምን ያስፈልጋል . . .›› ሲሉ ሰነበቱ። ባሻዬ ይህን ይበሉ እንጂ ከአጠፋፍ ሁሉ የማይወዱት እንደ ወጡ መቅረትን ነው። ለዚህ ሳይሆን አይቀርም አንድ ሰሞን በሠፈራችን በተካሄደ አንድ ስብሰባ ላይ ቀንደኛ ተሳታፊ የነበሩት። እና ያኔ የተናገሩት አይረሳኝም።

‹‹ . . .ሞሶሎኒ ሮም ተቀምጦ ባዘዛቸው አሽከሮቹ ብቻ አጠቃን? ጣሊያን ብቻውን መንገዱን አውቆት ፈልፍሎ አዲስ አበባ ገባ? . . . ባንዳ የት ሄዶ? ባዳ የማያውቀው ሰው ቤት ጓዳ ገብቶ ከእንስራ ይጠልቃል? . . . የሰው ጠላቱ አብሮት የበላ አብሮት የጠጣ ወዳጁ እንደሆነ ሁሉ፣ የአገርም ጠላቷ እትብታቸውን ከአፈሯ ቀብራ ያሳደገቻቸው፣ ማስተዋል የሚጎድላቸው ልጆቿ ናቸው፤›› ነበር ያሉት። አይ ባሻዬ! መቼም ነገር አዋቂ ታሪክ ዘካሪ ናቸው እኮ። ዳሩ ዛሬ ከነገሩም ከታሪኩም የሌለበት ‘ካለመናገር ደጃዝማችነት ይቀራል’ እያለ ያነካክሰን ያዘ እንጂ። ኧረ ተውኝ እናንተ! ስንቱን አውርተን፣ ስንቱን ተናግረን እንጨርሰዋለን ብላችሁ ነው። ‹‹ጠላት ከሩቅ አይመጣም›› ብሎ ሲተርት የድሮ ሰው ያልኖረውንና ያላየውን እንዳይመስላችሁ ታዲያ! ድህነትን ለማሸነፍ መላ ማጣት እስካሁን አሸነፈንና መታለልን ዘነጋነው ማለት አይደለም። ይህችን ይህችንማ እኛም እናውቃለን ‹‹ብንናገር እናልቃለን” አትሉኝም! ምን ላድርጋችሁ!

 አገር የተወረረ ይመስል ዙሩን አከረርኩት መሰል? የእኔ ነገር! ከሰሞኑን በአንዱ የሥራ ቀን የገጠመኝን ላውጋችሁ እስኪ (እህል ጠግበን እንደ ሠለጠኑት አገሮች ፈልሰስ እስከምንል ድረስ ወግ እንጠርቅ እንጂ)። ስዊዲን ከሚባል አገር ከመጣች ዳያስፖራ ጋር ድለላዬ አገናኘኝ። እሷ በስንት ትግልና ልፋት የሠራችውን ዘመናዊ መኖሪያ ቤት ልትሸጥ፣ እኔ ገዥ ላገናኛት መሆኑ ነው። አንድ ሁለት ቀን ተንከራትቼ ገዥ እንዳገኘሁ ቤቱን ማሳየቱና ማስማማቱ ብዙ ሰዓት ሳይፈጅ ‘ኮሚሽኔን’ ተቀበልኩ። ‘ከላይ ብላ ሲል እንዲህ በቀላሉ ሳይጠቀልሉ ይጎረሳል’ እያልኩ ለራሴ፣ ለሌላም ጊዜ ከፈለገችኝ ከዳያስፖራዋ ወይዘሮ ጋር ስልክ ተለዋውጠን ተለያየን። አደራ ውዴ ማንጠግቦሽ ሰምታ ደግሞ እንዳንቆራረጥ፡፡

ዳያስፖራዋ በስንተኛው ቀን ታዲያ ደወለች። ‹‹ምን ልታዘዝ?›› አልኩ። ‹‹ኧረ ጉድ ሆንኩ እኮ!›› አተነፋፈሷ ይቆራረጣል። የሆነችውን ለመስማት ቀጥሬ ሳገኛት በላይ በላዩ ይኼን ትምባሆ ትለዋለች። ለካስ ስም የማዘወርና የውሉን ሥርዓት ሙሉ ገንዘቧን ሳትቀበል ፈጣጥማ ኖሮ፣ ገዥው ስልክ አላነሳ እያለ ናላዋን አዙሮታል። ‹‹እንዲያው ይህች አገር መቼ ነው የሚያልፍላት?›› ትላለች በአናት በአናቱ ‘ኒኮቲኗን’ እየማገች። ቆይታ ደግሞ፣ ‹‹እኔ ያለሁበት አገር ሰው እንዲህ እንዳይመስልህ። ቃል ቃል ነው። እሱ የትም አይሄድም። አገኘዋለሁ እኮ! ግን ላያመልጥ ለምን የሰው ጉዳይ ያዘገያል? ይህችን አገር ከሌላው አገር ያዘገያት እኮ ሌላ አይደለም አንበርብር። ይኼ ይኼ ተጠራቅሞ ነው። ነውር አይደለም? እስኪ ፍረድ!” ትለኛለች ዓይን ዓይኔን እያየች። ውይ የእኔ ቆንጆ እኔማ ምኑን እፈርደዋለሁ እሱ ከላይ የተቀመጠው በሰላሳ ዲናር ተላልፎ የተሰጠው እያለ። ድሮም ሰውና ገንዘብ ፍቅር ሲጀማምሩ መስሎኝ አገር የተበላሸው! እኛም ብልሽትሽታችን የወጣው!

- Advertisement -

ከዚያማ የወር ቀለቤን ለማግኘት ያገኘኋቸውን ሥራዎች ለመጨራረስ ስሯሯጥ የማስበው የዘመኑን ሰው አጉል የገንዘብ ጥማት ሆኖ ሰነበተ። ከሁሉ የሚብሰው ደግሞ በንጥቂያና በአቋራጭ በሚገኝ ገንዘብ የሚታየው ጉራ ነው። የተጀመረው ዘመቻ ብዙዎችን ጉረኞችና እዩኝ እዩኝ ባዮች ፀጥ እረጭ አደረገልን እንጂ ሰብዓዊ ፍጡራንን የተፀየፉ በዝተው ነበር፡፡ ከላይ ሁሉንም ነገር የሚመለከት ፈጣሪ ባይኖር ኖሮ አልቆልን ነበር፡፡ ‹‹ለስሙ ስም ነበረን። ጥንትም አሁንም ለክብራችን ለዕምነታችን ሟች ነን። ብቻ በማጣት ተወልደን በንጣት ስለምናድግ ገንዘብ ኩሩ ልባችንን ገዝግዞ አውሬ አደረገን እንጂ፤›› ይለኛል ምሁሩ የባሻዬ ልጅ ስለግል ጥቅም አሳዳጅነት ስንጨዋወት። አይገርማችሁም! አያያዛችን ሁሉ ከድጡ ወደ ማጡ፣ ከነበርንበት ወዳልነበርንበት፣ ከአደግንበት መልካም መስክ ወደማናውቀው የክፋት ጥሻ ሲሆን ለማን አቤት እንደሚባልም ግራ ገባን እኮ? እኔ ደላላው አንበርብር ምንተስኖት ይህች ዛሬ ቀላል ሆና የምትወራ የዘራፊዎች ታሪክ፣ ውላ አድራ የአገር ለቅሶ ከመሆን የምትዘል አይመስለኝም። የምሬን ነው! ‘ዚስ ኢዝ ሲሪየስ!’ (መቼም የዘመኑ ሰው እንዲህ ከአማርኛው ይልቅ እንግሊዝኛው ይቀለዋል ብዬ እኮ ነው። ባይቀለውም ሲከብደው ጉዳዩን አክብዶ ሲያየው ታዝቤያለሁ) እናም እንዳልኳችሁ እንደኔ እንደኔ ከብዛት የጥራት ሰዎች ለመሆን ብንጥር መልካም ነው። ምን ይመስላችኋል? ግድ የለም ለመስማማት ከከበዳችሁም የማሰቢያ ጊዜ እሰጣችኋለሁ። ‹‹ሰው እኮ ቀላሉም ከባዱም ጥያቄ የፖለቲካ እንካ ሰላንቲያ እየመሰለው ስለተቸገረ የማጣሪያ ጊዜ ያስፈልገዋል፤›› የሚለኝ ማን ነበር? ዕዳ እኮ ነው ወዳጀ ብዙ መሆን!           

በሉ እስኪ እንሰነባበት። ወደ አመሻሹ ሁኑንም ነገር ትተን እኔና ወዳጄ የባሻዬ ልጅ ለማሟሟቅ ወደ ግሮሰሪያችን ገሰገስን። ስንደርስ ግሮሰሪዋ ጭር ብላለች፡፡ ‹‹እንዴት ነው ነገሩ የተነካካው ሰው በዝቶ ነው እንዴ ቤቱ ባዶ የሆነው፤›› ሲለኝ የባሻዬ ልጅ፣ የግሮሰሪዋ ባለቤት ጭር ያለውን ድባብ ለማጥፋት ሙዚቃ ሊከፍት ከጠመመው ቴፕ ጋር ይላፋል። የድምፁ መጠን እስከ መጨረሻው የተለጠጠው ቴፕ የጎረሰውን ሲዲ ማጫወት ሲጀምር ጆሮ የሚበጥስ የፍንዳታ ድምፅ ግሮሰሪያችን አሸበራት። እኛን ተከትለው የደረሱ ሁለት ሰዎች ደንግጠው ወደኋላ ተፈናጠሩ። ከግሮሰሪያችን ፊት ለፊት ያለው ዋና የመኪና መንገድ ላይ የከባድ መኪና ጎማ ሲፈነዳ  ደግሞ አስገራሚ ግጥምጥሞሽ ነበር።  ወዲያው የቴፑ ድምፅ ተመጥኖ ፍንዳታ የመሰለው የጎማ መሆኑ ሲታወቅ እኔ አለሁ ለማለት ያህል፣ ‹‹ዘራፍ ወንዱ!›› ስል ከሸሹበት ከተመለሱት አንዱ፣ ‹‹ከሞትን በኋላ ዘራፍ ይላል እንዴ ይኼ!›› ብሎ ነገር ቆሰቆሰ። ወዳጁ ቀበል አድርጎ፣ ‹‹በስፒከር ጩኸት እንዲህ ከሆንን፣ በጎማ ፍንዳታ በርግገን ከተተራመስን፣ ‘የወንድ ልጅ እናት ታጠቂ በገመድ ልጅሽን አሞራ እንጂ አይቀብረውም ዘመድ’ የሚባልበት ጊዜ ተመልሶ ቢመጣ ምን ልንሆን ነው?” ሲል ነቆራውን ለማባባስ ጠየቀ።

‹‹ወንድሜ!›› አለ ገና ገብቶ የተቀላቀለን ጎልማሳ፣ ‹‹ያን የአገር ፍቅር ስሜት ለመመለስ መሰለኝ ኢትዮጵያ፣ ኢትዮጵያ እያልን የምንዘምረው። ከእንግዲህ እኮ ወደፊት እንጂ ወደኋላ የለም፤” አለው። ‹‹አቦ ቺርስ! ከራስ ወዳድነት ወጥተን ለትውልድ የምናስብ ለመሆን ጀግና ትውልድ ማፍራት የእኛ ኃላፊነት እንደሆነ ንገረው እባክህ፤›› ብሎ ዘግይቶ የደረሰ አጨበጨበ። የግሮሰሪው የነገር ቅብብሎሽ ከበስተጀርባው የደበቀው ሀቅ ኖሮት ይሁን ወይም በዘፈቀደ የሚካሄድ መሆኑ አልገባኝ ቢለኝ፣ ‹‹ይኼ ሁሉ ምልልስ ምን ይሆን?›› በማለት የባሻዬን ልጅ ጠየቅኩት፡፡ ትከሻውን እየሰበቀ፣ ‹‹ወሬያችን ሁሉ በሰምና በወርቅ እየሆነ እያየህ በገባህ ወይም በተመቸህ መንገድ ተርጉሞ መረዳት ነው…›› እያለ ሲፈላሰፍብኝ ከወሬው ቀነስ አድርጌ ቢራዬን ማወራረድ ቀጠልኩ፡፡ ኃጢያታችንንና ሒሳባችንን እኩል ብናወራርድስ? መልካም ሰንበት!    

- Advertisement -

በማህበራዊ ሚዲያዎች ይከታተሉን

ከ ተመሳሳይ አምዶች

የዕውቀት ፏፏቴ!

ሰላም! ሰላም! ሁላችሁም በድርበቡም ቢሆን ሰላም እንደሰነበታችሁ ተስፋ በማድረግ፣ ትናንትን አልፈን ለዛሬ በመብቃታችን ለፈጣሪ ምሥጋና ይድረሰው እላለሁ፡፡ ምሥጋና የሌለበት ሕይወት የተራቆተ ነውና ተመሥገን ማለት...

ከኮሜዲ ወደ ትራጄዲ!

ሰላም! ሰላም! እንደምን ሰነበታችሁ ወገኖቼ? ዋናው ሰላም ነው፡፡ በዚያ ሰሞን የዩክሬኑን ፕሬዚዳንት ኮሜዲያኑ ቭሎድሚር ዘለንስኪ ከአሜሪካ ነጩ ቤተ መንግሥት ያስባረረው ለሰላም ተደራደር ሲባል አሻፈረኝ...

የፆም ትሩፋቶች!

 ሰላም! ሰላም! ወገኖቼ በሙሉ እንደምን ሰነበታችሁ እያልኩ ከጉልበቴ ሸብረክ ከአንገቴ ጎንበስ እያልኩ ሰላምታ አቀርባለሁ፡፡ የክርስትና እምነት ተከታዮች የኩዳዴ ፆም፣ እንዲሁም የእስልምና እምነት ተከታዮችም የረመዳን...

ጣዕም አልባ ሕይወት!

ሰላም! ሰላም! ደላላው አንበርብር ምንተስኖት ሰላም ከሌለ ምንም የለም ከሚሉ ሰላም ፈላጊዎች ተርታ ስለምመደብ፣ ‹‹ሰላም ጤና ይስጥልኝ እንደምን አላችሁ…›› እያልኩ በዕድሜ ጠገብ ዘፈን ሰላምታ...

ላይ ላዩን መውረግረግ!

ሰላም! ሰላም! ‹ከእንጨት መርጦ ለታቦት፣ ከሰው መርጦ ለሹመት› እንዲል ነባሩ ብሂል፣ እኔም ወጉ ደርሶኝ በድምፄ ተወካዬን ልመርጥ ተዘጋጅቻለሁ፡፡ እናንተስ እንዳልል ውሳኔው በእጃችሁ ነው፡፡ ‹ተቀመጥ...

ለጤናችን!

ሰላም! ሰላም! በቀደም ዕለት እንዲያው ግራ ግብት ብሎኝ የሆድ የሆዴን የማጫውተው ሰው ብፈልግ አጣሁ። ምሁሩ የባሻዬ ልጅ ሥራ ሥራ እያለ ቀልቡ ከእሱ ጋር የለም።...

አዳዲስ ጽሁፎች

የብሔርተኝነት ፖለቲካ ጡዘትና በአገር ላይ የሚደቅነው አደጋ

በነገደ ዓብይ ከአንድ ዓመት በፊት በሪፖርተር ዕትም “እኔ እምለው” ዓምድ ላይ፣ “ብሔር ተኮር ፌዴራሊዝሙ ረጅም ርቀት ይወስደናልን?” በሚል ርዕስ በአንድ ጸሐፊ የተሰናዳ አንድ ወቅታዊ ጽሑፍ...

[ክቡር ሚኒስትሩ ወደ ቢሯቸው ሲገቡ አማካሪያቸው ማኅበራዊ ሚዲያ ላይ በተመለከተው አንድ ጉዳይ ተገርሞ አገኙት] 

ምነው? ደህና አይደለህም? ኧረ ደህና ነኝ ክቡር ሚኒስትር። ፊትህ ላይ የማየው ግን እንደዚያ አይመስልም፡፡ ማኅበራዊ ሚዲያ የተመለከትኩት አንድ መረጃ አስገርሞኝ ነው።  ምን ዓይነት መረጃ ቢሆን ነው እንዲህ ያስገረመህ? ከሸዋ...

ተንቀሳቅሶ የመሥራት መብት ጉዳይ በአዲሱ የጎዳና ንግድ ደንብ መነጽር

በየቦታው ገመድ ወጥረው ‹‹ወዲህ በሉ›› እያሉ ገንዘብ የሚቀበሏቸው ሰዎች መብዛታቸውን የሚናገረው ስሙ እንዳይጠቀስ የፈለገ አንድ ሾፌር፣ በየቀኑ 4,000 እና 5,000 ብር መድቦ መንቀሳቀስ የእሱና...

ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የብድር ወለድ ማሻሻያ በፋይናንስ ዘርፍ ላይ የሚያሳርፈው ተሻጋሪ ተፅዕኖ

የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በቅርቡ የብድር ወለድ ምጣኔው ላይ ያደረገው ጭማሪ የብድርና ቁጠባ ተቋማት ላይ ጫና እንደሚያሳርፍ ተጠቆመ፡፡ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በተለያዩ ዘርፎች ከፋፍሎ ባደረገው...

በርዕደ መሬት የተመታው የከሰም ስኳር ፋብሪካ ሠራተኞችን የሥራ ውል የማቋረጥ ውሳኔ ተቃውሞ ቀረበበት

በኢትዮጵያ ውስጥ ሥራ ላይ ከሚገኙ የስኳር ፋብሪካዎች መካከል አንዱ ከሰም ስኳር ፋብሪካ ከሥራ ማቆም ጋር ተያይዞ የሠራተኞች ውል እንዲቋረጥ የተሰጠው ማስጠንቀቂያ እንዲነሳ የቀረበው ጥያቄ...

አንታበይ!

እነሆ መንገድ ከቦሌ ወደ ጎሮ ልንጓዝ ነው። በወርኃ መጋቢት በንፋስ የታጀበው ደመና ውስጥ ብቅ የምትለው ፀሐይ በወበቅ አለንጋዋ እየተጋረፈችም ቢሆን የእንጀራ ነገር ከመንገድ ጋር...
[the_ad id="124766"]

በማህበራዊ ሚዲያዎች ይከታተሉን

error: