Sunday, June 23, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ማኅበራዊየለገሃር ተስፋ

የለገሃር ተስፋ

ቀን:

የኢትዮጵያና የጂቡቲ ምድር ባቡር ድርጅት የሚገኝበት የለገሃር አካባቢ እንደቀድሞው በአንበሳ አውቶቡስና በመኪኖች የተሞላ አልነበረም፡፡ ከአካባቢው ተነስተው ወደተለያዩ አቅጣጫዎች የሚነጉዱ ትራንስፖርቶችን ለመጠቀም ይተራመስ የነበረ እግረኛም እንደወትሮው አይደለም፡፡ ሥፍራውን መልሶ ለማልማት ይፋዊ ገለጻ ከተሰጠበት ኅዳር 10 ቀን 2011 ዓ.ም. ጥቂት ቀናት በፊት ጀምሮ ግርግሩና የመኪናው ትርምስ ቀለል ብሎ ሥፍራው ተለውጧል፡፡

ከዚህ ቀደም በምድር ባቡሩ መግቢያ ግራና ቀኝ ያዩዋቸው የነበሩ ግብይቶች፣ ሊስትሮዎች፣ ጀብሎዎች የኔቢጤዎች ዛሬ ላይ እምብዛም አይታዩም፡፡ የድርጅቱ መግቢያ ግራና ቀኙ በጌጠኛ መትከያዎች በተተከሉ ተክሎች ተውቦ አዲስ የተከፈተ መለስተኛ የመዝናኛ ሥፍራ መስሏል፡፡

ድርጅቱ ካለበት ተያይዘው የሚገኙት የድርጅቱ የቀድሞ ቤቶች ደግሞ ከጨርቆስ ገበያ አካባቢውን ለሁለት በከፈለው አውራ መንገድ እንደቀድሞዋቸው ተጎራብተው ሳይሆን ማዶ ለማዶ ይተያያሉ፡፡ ዋና መንገዱ የቀድሞውን የባቡር ሐዲድ ባለመንካቱም በግራና ቀኝ የተከፈሉትን መንደሮች አስተሳስሮ እንደያዘ ሰንሰለት አስፋልቱ ላይ ተጋድሞ ይታያል፡፡

ፖሊስ ሰፈር፣ አሸዋ ተራ፣ ገመቹ ሰፈር፣ ቆሎ ተራ፣ የጀርመን ግቢ፣ ድንጋይ ጣቢያና ዋንኬ ሰፈር በአካባቢው ከሚገኙ መንደሮች ይጠቀሳሉ፡፡ በአካባቢው አንዳንድ የግለሰብ ቤቶች ቢኖሩም አብዛኞቹ ቤቶች ምድር ባቡር የሠራቸውና የቀበሌ ናቸው፡፡ የምድር ባቡር ቤቶች በጭቃና በብሎኬት የተሠሩ፣ በብሎክ የተከፋፈሉና አንድ ቤት ከአንዱ የተያያዙ ናቸው፡፡ እዚህ ሥፍራ፣ ብሎኮቹ ብቻ ሳይሆኑ ነዋሪዎቹም ከ40 ዓመታት በላይ እጅ ለእጅ ተያይዘው በደስታና በሐዘን ተባብረው የኖሩበት መንደር እንደሆነ አካባቢውን በጎበኘንበት ወቅት ያገኘናቸው ነዋሪዋች ነግረውናል፡፡

ከጨርቆስ ገበያ አቅጣጫ አዲስ የተሠራውን አስፋልት ተከትለው ወደለገሃር ሲመጡ በስተቀኝ ካሉት ብሎኮች በአንዱ ላለፉት 32 ዓመታት የኖሩት የወይዘሮ አበራሽ በርሄና የባለቤታቸው ዋና ኢንስፔክተር ያይኑ ወልደሩፋኤል አካባቢው መልሶ ሊለማ በመሆኑ የተሰማቸውን ስሜት ለመጠየቅ ጎራ ያልንበት ቤት ነበር፡፡ እነሱን እያነጋገርን ጎረቤቶቻቸው በተየራ እየገቡ ሷሎኗን ሞሏት፡፡

‹‹የምንኖረው ኩባንያው በሰጠን ቤት ነው›› የሚሉት ወ/ሮ አበራሽ፣ ወልደው የዳሩበትን ቤታቸውንና መንደራቸውን የሚገልጹት ‹‹የሰፈሩ ማኅበራዊ ኑሮ በሐዘኑ በደስታው በመከራው የሚረዳዳ ነው፤›› በማለት ነው፡፡

ከዚህ ቀደም በነበረው የከተማው አስተዳደር አካባቢው መልሶ ይለማል ተብሎ ከተነገረ ወዲህ እሳቸውም ሆኑ የአካቢው ነዋሪዎች ‹‹የት ነው የምንወድቀው›› በማለት በሥጋት እንዳሳለፉም ይናገራሉ፡፡ ከዚህ ቀደም ከአካባቢው ተንስተው የተበታተኑ ጎረቤቶቻቸውን በማስታወስም ‹‹እኛም ልንበታተን ነው፣ ሰፈራችንን ለቀን ልንሄድ ነው በሚል የሥጋት ኑሮ ከጀመርን ሰንብተን ነበር፡፡ በቀደም ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) ነዋሪው አይነሳም እዚሁ ቤት ይሠራለታል ሲሉ ስንሰማ ተደስቻለሁ፤›› ብለዋል፡፡

ከአሁን በፊት አካባቢው ለልማት ስለሚፈለግ ትነሳላችሁ ተብሎ በቃል ከተሰማው በቀር ትነሳላችሁ የሚል ወረቀት እንዳልደረሳቸው የሚናገሩት ወ/ሮ አበራሽ፣ አካባቢው ሊለማ፣ እነሱም በቴሌቪዥን አካባቢው ይሆናል ተብሎ የታየውን ዲዛይን ሲያዩት መደሰታቸውን ያክላሉ፡፡

እነሱ መሀል ላይ ከገደገዱት ኩሽና በተጨማሪ አንድ ሳሎንና መኝታ ቤት ካለው ቤታቸው ስድስት ልጆችን ወልደው አሳድገዋል፡፡ አብዛኛው ኑሮዋቸውም ከጎረቤቶቻቸው ጋር በደስታ የተሞላ ነው፡፡ ‹‹ዶክተር ዓብይ ደግሞ ተስፋ ሰጥቶናል፡፡ ፈጣሪ አምስት ወይም ሰባት ዓመት ዕድሜ ሰጥቶን የፕሮጀክቱን ፍጻሜ ለማየት ጓጉተናል፤›› ብለዋል፡፡

ባለቤታቸው ዋና ኢንስፔክተር ያይኑ ‹‹ከሁሉም በላይ ማኅበራዊ ሕይወታችንን እወደዋለሁ፡፡ በአካባቢው የለመድነውን ኅብረተሰብ ተለይተን እንዴት እንኖራለን፡፡ በማንኛውም ሁኔታ እንደኛ ሰፈር አንድ የሆነ ይኖራል ብዬ አልገምትም፡፡ የሚታየኝም የማኅበራዊ ሕይወታችን ጉዳይ እንጂ ቤቱ አይደለም፡፡ ቤት እዚህም ሆነ እዚያ ያው ነው፡፡ እዚህ ተግባብተን እንደምንኖረው ሌላ ሰፈር ስንሄድ እንዴት እንሆን ይሆን እያልን በአምዕምሮአችን ስንጨነቅ ከርመናል፡፡ የተነገረው ቃል ያረካል፡፡ ማኅበረሰቡ ከአካባቢው ሳይፈናቀል ቤት ይሠራለታል፡፡ በአንድ አካባቢ የሚኖርበት ሁኔታ ይመቻቻል ተብሏል፡፡ ነገር ግን ካለኝ ልምድ አንፃር የቀድሞ ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ ስለመልሶ ማልማት ሲናገሩ እድር እንዳይፈርስ በአንድ አካባቢ እንዲሆን እናደርጋለን ብለው ነበር፡፡ ቃሉ ግን አልተጠበቀም፡፡ አስፈጻሚው አካል ሕዝብ እያስቸገረ እያፈናቀለና እያስለቀሰ ኖሯል፡፡ አሁን ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር ዓብይ ያሉት ከተተገበረ በደስታ ነው የምንቀበለው፡፡›› ብለዋል፡፡

ተስፋ ሰጪው ንግግር በተግባር እንዲሆን እንደሚመኙና እንደሚፀልዩ፣ ከአምስት እስከ ሰባት ዓመት ይቆያል የተባለው ፕሮጀክት ሰኞ ኅዳር 10 ቀን 2011 ዓ.ም. ዲዛይኑ በቴሌቪዥን ሲታይ ከተማችን የተዋበች ልትሆን ነው ብለናል፡ ዕድሜ ሰጥቶን እናይ ይሆንም? ዕድሜ ሰጥቶን ለማየት ይፍቀድልን ማለታቸውንም አክለዋል፡፡   

እዛው ተወልዶ አድገውና ትዳር መሥርተው የሦስት ልጆች አባት ለመሆን መብቃታቸውን የነገሩኝ የ42 ዓመቱ አቶ ሊሻን አበበ ደግሞ የሚኖሩበትን ፖሊስ ሠፈር ‹‹ትንሽ ትልቁ ተከባብረን፣ ተሳስበን የምንኖርበት›› ይሉታል፡፡

መልሶ ማልማት በከተማዋ ከተጀመረ ወዲህ እሳቸው አብሮ አደጎቻቸው እናትና አባታቸው በሕይወት ባይኖሩም እንደ እናትና አባት አብሮዋቸው የሚኖሩ ጎረቤቶቹ ሥጋት ላይ እንደነበሩ ይናገራሉ፡፡ ‹‹የት ሄደን እንወድቅ ይሆን የሚል ሥጋት ነበረን፡፡ ሥጋታችን አሁን ላይ በጎ ምላሽ አግኝቷል፡፡ ይህንንም ያደረጉልን ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር ዓብይ አህመድ ናቸው፡፡›› ብሏል፡፡

አቶ ሊሻን እንደነ ወ/ሮ አበራሽ ‹‹ፈጣሪ ዕድሜ ሰጥቶን ፍፃሜውን እናይ ይሆን›› ብለው አልሠጉም፡፡ ይልቁንም ፈጣሪ የጎረቤታቸውንም የእሳቸውንም ሕይወት እንደሚያለመልም፣ ከነበረው ጭንቀትና ሥጋት በመላቀቃቸው ረዥም ዕድሜ እንደሚጨምሩ ያምናል፡፡ ‹‹የሰው ልጅ የሚኖረው በተስፋ ነው፡፡ ፕሮጀክቱ በዓለም አቀፍ ኮንትራክተር ተይዞ ለአገራችንም ለአፍሪካም ውበት እንደሚሆን፣ እኛ ዕድለኞች ሆነን የልማቱ ተመልካች ሳይሆን ተቋዳሽ እንደምንሆን አምናለሁም›› ብለዋል፡፡ ሕዝቡ ሆነ ቅርሱ የምድር ባቡር ድርጅትም ሆነ ሃዲድ ሳይነካ ይሠራል በመባሉ ተደስተናል ሲልም አክሏል፡፡

ወ/ሮ ሽታዬ ገብረማርያም ከ40 ዓመት በላይ በአካባቢው ኖረዋል፡፡ በሞት የተለዩዋቸው ባለቤታቸው የምድር ባቡር ሠራተኛ እንደነበሩም ይናገራሉ፡፡ ‹‹አካባቢው ላይ ለውጥ ሲመጣ ተደስተናል፡፡ ዶ/ር ዓብይ አህመድ ሕዝቡ ሳይፈናቀል እዚሁ ቦታ ላይ ቤት ይሠራለታል በማለታቸው ደስተኛ ነኝ፡፡ ሳንፈናቀል እዚሁ መኖር ከቻልን ከዚህ በላይ ምን ደስታ አለ?›› ይላሉ፡፡

ዋና ሳጅን ደብሪቱ ተሰማ ከ30 ዓመት በላይ በድርጅቱ ያገለገሉ የክብር ተጧሪ ናቸው፡፡ እሳቸው መናገርን የመረጡት ሁሉን ነገር ስላደረገላቸው ፈጣሪያቸው ምሥጋና በማቅረብ ነበር፡፡ ሠፈራቸው ለሳቸው ልዩ ትርጉም አለው፡፡ ተቀጥረው ይሠሩበት የነበረው የኢትዮጵያና ጅቡቲ ምድር ባቡር ድርጅት ግቢ፣ የባቡሩ ሃዲድ የባቡሩ ድምፅ የመንገደኛው እሳቸው ይሠሩ የነበሩት የአጃቢነት ሥራ፣ ከአዲስ አበባ ደወሌ ጅቡቲ ያለው መንገድ ሁሉ ለእሳቸው የሕይወት ዘመን ትዝታ ነው፡፡ ከሁሉም በላይ ደግሞ ከሥራ መልስ አረፍ የሚሉበት በፖሊስ ሠፈር ለሚገኘው ቤታቸውና በደስታ በችግር ደራሾቹና ለቡና አጣጮች ጎረቤቶቻቸው ልዩ ሥፍራ አላቸው፡፡

ከምንም በላይ ከቤት ወጥተው በገቡ ቁጥር የድርጅቱ ቢሮ ከነበረበት ሥፍራ ጎራ ሳይሉ ወደ ቤት አይገቡም፡፡ ድርጅቱ ጋር ሄዶ የቀድሞ መሥሪያ ቤታቸውን አይቶ መመለሱ ለሳቸው የመንፈስ እርካታ ነው፡፡ ይህ የሁሌም ልምዳቸው ሲሆን፣ አካባቢው መልሶ ሊለማ ነው መባሉን እንደሰሙም የቀድሞ ፖሊስ ነኝ አስገቡኝ በማለት የተሠራውን ዲዛይን ለማየት ችለዋል፡፡

‹‹ዲዛይኑን ሳይ በጣም ተደሰትኩ፣ ዶ/ር ዓብይም የአካባቢው ሰው አይፈናቀልም ማለቱም አስደስቶኛል ሠፈራችን ከሞትና ደስታ ባለፈም የታመመንና የተቸገረን በመርዳትም የሚታወቅ ነው፡፡ ይህንን ሁሉ እሴታችንን እንዳናጣ ስላደረገን ለእኛ ሳይሆን ለኢትዮጵያ ሕዝብ እንደተደረገ ነው ያስደሰተኝ››

‹‹የተስፋ ቃል ትልቅ ጉዳይ ነው በተስፋ እንኖራለን፡፡ ሰባትም ዓመት ቢፈጅ በተስፋ እንጠብቃለን›› የሚሉት ዋና ሳጅን ደብሪቱ፣ በድርጅቱ የሚገኝ ከ100 ዓመት በላይ ያስቆጠረ ቅርስ እንዲጠበቅ አደራ ሳይሉም አላለፉም፡፡ ‹‹አፄ ምኒልክ፣ ጣይቱ ብጡልን ዘውዲቱን ነፍሳቸውን ይማርና ለኢትዮጵያ ሥልጣኔን አምጥተዋል፡፡ ከመኪና የማይገናኝን ሕዝብ ባቡሩ ሲመግብ ኖሯል፡፡ ለውጥና ዕድገት በመኖሩ የኤሌክትሪክ ባቡር መጥቷል፡፡ ተደስተናል፡፡ ድርጅቱ አለመነካቱ ያስደስታል፡፡ ውስጥ የሚገኙት ለቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ የተሰጡ ባቡሮችም የአንድ ግለሰብ ሳይሆኑ የኢትጵያ ቅርሶች ናቸው፡፡ እነዚህ ሳይነኩ የሚቆዩ በመሆኑ ደስተኛ ነኝ፡፡ ሃዲዱ እንዲሁም የመጀመሪያው የምድር ባቡር ቢሮ ከ100 ዓመት በላይ ስላስቆጠሩ ቅርስ ናቸው፡፡ ይታያሉ ባቡሮቹም የቱሪስት መስህብ ሆነውም ገቢ ያስገኛሉ፡፡ በዚህ ላይ ጭስ አልባው ኢንዱስትሪ በመግባቱ ደስተኛ ሆኛለሁ፤›› ሲሉ ደስታቸውን ገልጸዋል፡፡

በአካባቢው ተዘዋውረን ያነጋገርናቸው ነዋሪዎች በፕሮጀክቱ መምጣትና እነሱ ከአካባቢው የማይነሱ በመሆኑ ደስተኛ መሆናቸውን ነግረውናል፡፡ ለእንደዚህ ዓይነቱ ዕድል የመጀመሪያ በመሆናቸውም ለዶ/ር ዓብይ ምሥጋና ማቅረብን ይፈልጋሉ፡፡

ከዚህ ቀደም በመልሶ ማልማት እንደተነሱ ሰዎች ከማኅበራዊ እሴታቸው ሳይስተጓጎሉ እዛው በሚሠራላቸው ቤት በአንድ ላይ የሚኖሩ መሆናቸው ከሁሉም በላይ ያስደስታቸው ነው፡፡ ለየብቻ ሻወር፣ ዘመናዊ መፀዳጃ ያለው ቤት ማግኘትና መኖርም ምኞታቸው ነው፡፡ ከዚህ ቀደም እንደፈረሱ ሠፈሮች ነዋሪዎች በየቀበሌ ቤት አሊያም እንደ እንግዳ ከሚላመዱትና በርቀት ከሚገኙ ኮንዶሚኒየም ቤት ትገባላችሁ አለመባሉ፣ ቤቱ ተሠርቶ ሲሰጣቸው ልማቱ ለሕዝብ በመሆኑ ገንዘብ ትከፍላላችሁ አለመባሉም በጡረታና በልጆቻቸው ዕርዳታ የሚኖሩትን አስደስቷል፡፡

አካባቢያቸው አራት ኪሎ ቱሪስት ጀርባ ያሉ መንደሮች ፈርሰው እነ አዝማሪ ሠፈር፣ ጋዕላ ለጋሲዮንና ሌሎችም የአዕምሮ ትዝታ ብቻ ሆነው አካባቢው ፆሙን ካደረ ዓመታት እንደተቆጠረ በማስታወስም፤ አካባቢያቸው እንደዚያ እንደማይሆንና ልማቱ ተሳክቶ አገርም፣ እነሱም ተጠቃሚ እንደሚሆኑ ተስፋ ሰንቀዋል፡፡ ይህን ተስፋቸውን ዕውን ያደርጋል ብለው በዶ/ር ዓብይ ተስፋ የሰነቁ የአካባቢው ወጣቶች ፕሮጀክቱን የሚሠራውን ኢግል ሒልስ በየድረ ገጹ እየፈለጉ መረጃ ማግኘቱን ተያይዘውታል፡፡ ወጣቶቹ ድርጅቱ ማነው? ያሳካ ይሆን? የሚለውን ከዶ/ር ዓብይ ከሰሙትም ባለፈ ከመረጃ መረብ ያገኙትን በመተንተን ሠፈራችን ስንመኘው እንደነበረው ሊለወጥ ነው ብለዋል፡፡

በሠፈሩ አለመልማት ለዓመታት ስቆጭ ነበር የሚለው የወንዶች የውበት ሳሎን ያለው የ39 ዓመቱ ባህሩ ክፍሌ በሥፍራው ተወልዶ አድጓል፡፡ በቀበሌ ቤት የሚኖረው ባህሩ፣ ‹‹ቢኖረኝ፣ ለሚቀጥለው ትውልድ ቢኖረው ብዬ የምመኘው ዓይነት ልማት ወደ ሠፈራችን በመምጣቱ ደስተኛ ነኝ፤›› ብሏል፡፡

ከማኅበራዊ ሕይወት፣ ከእሴት፣ ከአኗኗር ከአብሮነት፣ ከአካባቢው ሳይርቅና ሳይገለል በተሻለ ቤት፣ በተሻለ ማንነትና በተሻለ የአኗኗር ዘይቤ የመኖር ዕድል ማግኘትን ትልቅ ኢትዮጵያዊነት ይለዋል፡፡

ይለማል በተባለው አካባቢ መኖርና የተሻለ ነገርን ማየት የተሻለ ለመሥራትና ለመለወጥ እንደሚያነሳሳ፣ ገንዘብ ያለው ገንዘብ ከሌለው ተቀይጦ የተሻለ የኢኮኖሚ ተጠቃሚ መሆንና ማድረግ እንደሚቻልም ከዚህ በኋላ የሚመጡ ባለሀብቶች ሊያስቡበት እንደሚገባና ልማት ለግል ጥቅም ብቻ ሳይሆን ማኅበረሰቡን ያማከለ መሆን እንዳለበት ያምናል፡፡

‹‹የመሠረት ድንጋይ ሲቀመጥ ተስፋ ነው ያየነው፡፡ ኢግል ሒልስ የተባለውን ኩባንያ በድረ ገጽ እንዳነበብነውም ብዙ የሥራ ልምድ ያለው ነው፡፡ እንዲህ ዓይነት ድርጅትን መንግሥት ተነጋግሮ በማምጣቱም ዕድለኞች ነን›› የሚለው ባህሩ፣

25 ሺሕ ሰዎች ይቀጠራሉ መባሉም ለወጣቱ መልካም መሆኑን፣ የወጣቱ ጉልበትም አገሩ ላይ መፍሰስ ቢችል ከፉከራ ባለፈ ትልቅ የዕድገት አቅም እንደሚሆንም ተናግሯል፡፡

በአካባቢው ሁሌም ስለልማት እንደሚወራ፣ ከዚህ ቀደም የነበረው ልማት ንግድ እንጂ የኅብረተሰቡን እሴት፣ ማኅበራዊ ሕይወት ያላገናዘበና ከቀዬው ያፈናቀለ እንደነበር፣ የአሁኑ ከነበረው በተቃራኒ ለአካባቢው ነዋሪ ቅድሚያ የሰጠና ሕዝቡን ያከበረ እንደሆነም አክሏል፡፡

ኅብረተሰቡ በተሟላና በተደራጀ አካባቢ ሲኖር ንቃተ ህሊናው እንደሚጨምር፣ የአዲስ አበባ ወጣት ሥራ አይችልም፣ አይሠራም እየተባለ የሚወቀሰው ለአዲስ አበባ ወጣት የተመቻቸ መልካም የሥራ ዕድል ባልነበረበት እንደነበር፣ የለገሃር አካባቢ ወጣቶች ምን ያህል ልማት እንደጠማቸው ሥራ መሥራት እንደሚችሉ ፕሮጀክቱ በሰላም እንዲጠናቀቅ እጅ ለእጅ ተያይዘው እንደሚጠብቁና ሥራ ሠርተው መለወጥ እንደሚችሉ የምናስመሰክርበት ፕሮጀክት መጥቷልም ብሏል፡፡

ከመኖሪያ መንደራቸው ሳይፈናቀሉ አካባቢው ለምቶ በተሻለ የኑሮ ድባብ እዚያው መኖራቸው በራሱ የሰውን አመለካከት በአዎንታዊ መንገድ እንደሚቀይረው ያወሳው፣ ሸራተን ሲለማ ከአካባቢው ተነስተው ሲኤምሲ አልታድ አካካባቢ የሠፈሩትን በማስታወስ ነው፡፡ በወቅቱ ከአራት ኪሎ ተነስተው አልታድ አካባቢ የሠፈሩ ሰዎችና እዚያው ሳይነሱ በቀሩት መካከል የአኗኗር ዘይቤ ለውጥ መኖሩን፣ አልታድ የገቡት በተሻለ የመኖሪያ ቤት በመግባታቸው አኗኗራቸው እንደተቀየረ የሚያውቃቸውን በመጥቀስ ይናገራል፡፡

‹‹ይህ ፕሮጀክት አኗኗራችንን፣ አስተሳሰባችንን ይቀይረዋል፡፡ ታዳጊ ሕፃናትም መልካም ሥራ ዓይተውና በንፅህናና በሠለጠነ አካባቢ ሲኖሩ ለወደፊት ሕይወታቸው ከሚያዩት የተሻለ ለአገራቸው እንዲሠሩ ይረዳቸዋል፣ ለኑሮ በማይመጥን፣ ተስፋ በሌለበት ባልለማ አካባቢ እየኖሩ ለአገራቸው የተሻለ ነገር ለማምጣት ዕድሉ አይኖርም ብሏል፡፡

መኖሪያ መንደሩ መዝናኛን፣ አረንጓዴ ሥፍራን፣ መጫወቻን ያካተተ ስለሚሆንም በአንዳንድ አካባቢዎች እንደሚታዩት ኮንዶሚኒየሞች ለኑሮ የማይመች እንደማይሆንም ተስፋ አለኝ ብሏል፡፡ ለነዋሪዎች የሚያውቋቸው ሰዎች እየደወሉ እንኳን ደስ አላችሁ ከአካባቢያችሁ አትለቁም እንደሚሉ በመግለጽም ‹‹የእኛ መደሰት የሁሉም ደስታ ነው›› ሲል ተናግሯል፡፡ ከዚህ ቀደም የነበረው የመልሶ ማልማት ሥራ እሴትን አኗኗርን ያላማከለ በመሆኑም ከአካባቢያቸው ለልማት የተነሱ ሰዎች ሩቅ ሥፍራ ተበታትነው መቅረታቸውን በማስታወስ የአዳዲስ ሐሳብና የአዲስ ፕሮጀክት የመጀመሪያ ተጠቃሚ በመሆናቸው መታደላቸውን ይናገራል፡፡

የመልሶ ማልማት ሳይንስ ሕዝብን ከሚኖርበት አባርሮ ሌላን ማምጣት ሳይሆን፣ ሕዝቡን ያማከለ መሆኑን ሆኖም ያለፈው አሠራር ይህንን ባለማድረጉ የብዙዎች ሕይወት መቃወሱን ያክላል፡፡

ባለፉት 27 ዓመታት አዲስ አበባም ሆነች ሌሎች ከተሞች አሁን ካለው በተሻለ ሊለሙ ይችሉ እንደነበር፣ ግልጽነት ባለመኖሩ ግን አብዛኛውን ያላስደሰተ ልማት መከናወኑን ይናገራል፡፡   

በአካባቢው ሆቴል፣ ሞል፣ መዝናኛ ሥፍራና ሌሎችም መኖራቸው ፕሮጀክቱ ሲያልቅ ሰፊ የሥራ ዕድል ይዞ እንደሚመጣ፣ ሠርቶ የሚያድር ኃይል ደግሞ ለሌላ ልማት እንደሚነሳሳም ይናገራል፡፡

ከአምስት እስከ ሰባት ዓመት ይፈጃል የተባለው የለገሃር የግንባታ ፕሮጀክት ከ20 ዓመት በላይ የዘመናዊ ግንባታ ልምድ ባለው ኤግል ሒልስ የሚሠራ ሲሆን፣ ፕሮጀክቱ 50 ቢሊዮን ብር እንደሚፈጅ ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) ተናግረዋል፡፡

የፕሮጀክቱ ይፋ መሆንን አስመልክቶ ኅዳር 10 ቀን 2011 ዓ.ም. የኢትዮጵያና ጂቡቲ ምድር ባቡር ድርጅት ፊት ለፊት ለገሃር ላይ በተዘጋጀ ሥነ ሥርዓት የተገኙት ዶ/ር ዓብይ፣ ፕሮጀክቱ የኢግል ሔልስን ጥንካሬ የሚያሳይ፣ የአካባቢውን ታሪካዊነት የጠበቀ፣ ሕዝቡን ያላገለለ የልማት ሥራ ነው ብለዋል፡፡

ከአራት ሺሕ በላይ አፓርትመንቶች፣ ሦስት ሆቴልና ሌሎች ግንባታዎችን ከሚያጠቃልለው ከዚሁ ግንባታ ጎን ለጎን ለአካባቢው አባወራዎች በዚያው ሥፍራ መኖሪያ እንደሚገነባ፣ ለዚህም ከኤግል ሔልስ ኩባንያ 1.8 ቢሊዮን ብር እንደተሰጠም ተናግረዋል፡፡ 

መንግሥት ከፕሮጀክቱ የ27 በመቶ ድርሻ ያለው ሲሆን፣ ግንባታውም በ36 ሄክታር ላይ የሚያርፍ ነው፡፡

የአካባቢው ሰው ሳይፈናቀል ልማት መምጣቱን አስመልክቶ የአካባቢ ነዋሪዎች ደስተኛ መሆናቸውን ሲገልጹ፣ በየሶሻል ሚዲያው በአብዛኛው የተስተጋባውም ልማቱ የአካባቢውን ነዋሪዎች የማያፈናቅል መሆኑ ከዚህ ቀደም ከነበረው አሠራር የተለየ እንደሚያደርገው ነው፡፡ አንዳንድ ያነጋገርናቸው የአከባቢው ነዋሪዎች እንደ ሥጋት ያነሱት፣ በአንድ ቤት ከእናትና አባት በተጨማሪ ልጆች አግብተውና ወልደው በየግቢው ባገኙት ክፍት ቦታ ጣራ ቀልሰው እንደሚኖሩ፣ ፕሮጀክቱ ቤት ሲሠራ በአንድ ግቢ በአንድ ቤት ቁጥር ሆኖ በርካታ ቤተሰቦች ጣራ ቀልሰው የሚኖሩበትን ሁኔታ በመኖሩ በምን አግባብ እንደሚነሱ አለማወቃቸው ነው፡፡ ሆኖም ዶ/ር ዓብይ ልማቱ የሕዝብ ነው ከማለታቸው አንፃር መፍትሔ እንዲሚያበጁላቸው ተስፋ ጥለዋል፡፡

ዶ/ር ዓብይ ለሕዝቡ ያላቸውን ቀና አመለካከት የገለጹት፣ የኤግል ሒልስ ሊቀመንበር መሐመድ አላባር ጠቅላይ ሚኒስትሩ ለሕዝቡ ያላቸውን አክብሮትና በተሻለ አካባቢ እንዲኖር የማብቃት ፍላጎት ሳያደንቁ አላለፉም፡፡

ሊቀመንበሩ አላባር ‹‹የሕዝብ የቀን ተቀን ሕይወት እንዲቀየር ያለዎትን ምኞት አይተናል፡፡ ይህም ምቹ የመኖሪያና የመዝናኛ፣ እንዲሁም ዕፀዋትና አዕዋፋት የሚኖሩበት መንደር በብቃት እንድንሠራ አነሳስቶናል›› ብለዋል፡፡

ያነጋገርናቸው ነዋሪዎችም የፕሮጀክቱን መምጣት ደግፈው፣ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ሐዲዱ እንደማይነሳ፣ ቢሮው ጥገና ተደርጎለት እንደሚኖርና የአካባቢው ማኅበረሰብ ለዓመታት ከኖረበት ቀዬው ሳይፈናቀል እዚያው ቤት እንደሚገነባለት የገቡት ቃል ተፈጻሚ እንደሚሆንም ተስፋ ሰንቀዋል፡፡  

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

አስጨናቂው የኑሮ ውድነት ወዴት እያመራ ነው?

ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ የኑሮ ውድነት እንደ አገር ከባድ ፈተና...

‹‹ወላድ ላማቸውን አርደው ከደኸዩት ወንድማማቾች›› ሁሉም ይማር

በንጉሥ ወዳጅነው   የዕለቱን ጽሑፍ በአንድ አንጋፋ አባት ወግ ልጀምር፡፡ ‹‹የአንድ...

የመጋቢቱ ለውጥና ፈተናዎቹ

በታደሰ ሻንቆ ሀ) ችኩሎችና ገታሮች፣ መፈናቀልና ሞትን ያነገሡበት ጊዜ እላይ ...

ጥራት ያለው አገልግሎት መስጠት የሚያስችል ሥርዓት ሳይዘረጉ አገልግሎት ለመስጠት መነሳት ስህተት ነው!

በተለያዩ የመንግሥትና የግል ተቋማት ውስጥ ተገልጋዮች በከፈሉት ልክ የሚፈልጉትን...