Sunday, March 26, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ዜናየዓለም ገነት ቆርቆሮ ፋብሪካና የቀድሞ የሪቬራ ሆቴል ባለቤት ታስረው 14 የምርመራ ቀናት...

የዓለም ገነት ቆርቆሮ ፋብሪካና የቀድሞ የሪቬራ ሆቴል ባለቤት ታስረው 14 የምርመራ ቀናት ተጠየቀባቸው 

ቀን:

‹‹ከምንም ዓይነት ወንጀል ጋር ንክኪ ስለሌለኝ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ሾመውኝ ነበር››

የቀድሞ የብሔራዊ መረጃና ደኅንነት ምክትል ዋና ዳይሬክተር

ከብረታ ብረት ኢንጂነሪንግ ኮርፖሬሽን (ሜቴክ) ጋር ሕገወጥ የሽያጭ ውል በመግባትና ግብይት በመፈጸም ያላግባብ ጥቅም በማግኘት የተጠረጠሩት የዓለም ገነት ቆርቆሮ ፋብሪካና የቀድሞ የሪቬራ ሆቴል ባለቤት፣ ፍርድ ቤት ቀርበው 14 ቀናት ለተጨማሪ ምርመራ ተጠየቀባቸው፡፡

ተጠርጣሪው አቶ ዓለም ፍፁም ሪቬራ ሆቴልንና ፕላስቲክ ፋብሪካ ያለ ምንም ጨረታ በ128 ሚሊዮን ብር ለሜቴክ ለመሸጥ ውል የተፈራረሙ ቢሆንም፣ ክፍያ የተፈጸመው ግን 195 ሚሊዮን ብር መሆኑን የፌዴራል ፖሊስ ወንጀል ምርማሪ ቡድን ለፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ አሥረኛ ወንጀል ችሎት አስረድቷል፡፡ ሜቴክ አቶ ዓለም የነበረባቸውን 67 ሚሊዮን ብር የባንክ ዕዳም እንደከፈለላቸው አክሏል፡፡ ተጠርጣሪው ከሜጀር ጄኔራል ክንፈ ዳኘው ጋር ባላቸው ዝምድና ምክንያት፣ ለመንግሥት መክፈል የነበረባቸውን 11 ሚሊዮን ብር ታክስ እንደተሸፈነላቸው መርማሪ ቡድኑ ተናግሯል፡፡ በመሆኑም መንግሥትን ላልተፈለገ ከባድ ኪሳራ መዳረጋቸውን በመጠቆም፣ በከባድ የሙስና ወንጀል በመጠርጠራቸው ለተጨማሪ ምርመራ 14 ቀናት እንዲፈቀድለት ጠይቋል፡፡

የተጠርጣሪው ጠበቆች ለፍርድ ቤቱ ባቀረቡት ክርክር መርማሪ ቡድኑ ተፈጽሟል የሚለውን የወንጀል ድርጊት መርምሮ ማጠናቀቁን በመግለጽ፣ ተጨማሪ የምርመራ ጊዜ መጠየቁ ተገቢ አለመሆኑን አስረድተዋል፡፡ ፍርድ ቤቱ የግራ ቀኙን ክርክር ከሰማ በኋላ፣ መርማሪ ቡድኑ ከጠየቀው 14 ቀናት ውስጥ አሥር ቀናት በመፍቀድ ለኅዳር 22 ቀን 2011 ዓ.ም. ቀጠሮ ሰጥቷል፡፡

በሌላ በኩል በከፍተኛ የሰብዓዊ መብት ጥሰትና የሙስና ወንጀል ተጠርጥረው የታሰሩት የቀድሞ የብሔራዊ መረጃና ድኅንነት አገልግሎት ምክትል ዋና ዳይሬክተርና የአገር ውስጥ ደኅንነት ኃላፊ አቶ ያሬድ ዘሪሁን፣ ‹‹ከምንም ዓይነት ወንጀል ጋር ንክኪ ስለሌለኝ ጠቅላይ ሚኒስትሩ የፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽነር አድርገው ሾመውኝ ነበር፤›› አሉ፡፡

አቶ ያሬድ ለፍርድ ቤት እንዳስረዱት፣ የተቀጠሩት በ1988 ዓ.ም. ነው፡፡ ከቀድሞው ዋና ዳይሬክተር ከአቶ ጌታቸው አሰፋ ጋር ለሁለት ዓመት ያህል እንኳን እንዳልሠሩ፣ የተመደቡትም በብሔር ተዋጽኦ መሆኑንና ተፅዕኖ ስለነበረባቸው መልቀቂያ አስገብተው እንደነበር ተናግረዋል፡፡ በተቋሙ ውስጥ በተቃርኖና በሕመም መቆየታቸውን የገለጹት አቶ ያሬድ፣ ‹‹መከራዬን በላሁ እንጂ ያተረፍኩት ነገር የለም፤›› ብለዋል፡፡ ለለውጡ ብዙ አስተዋጽኦ ማበርከታቸውን ጠቁመው፣ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ጠርተው እንዳመሠገኗቸውም አስረድተዋል፡፡ የፌዴራዴል ፖሊስ ኮሚሽነር ጄኔራል ተደርገው የተሾሙትም፣ የለውጡ ኃይል መሆናቸው ታውቆ ቢሆንም ስላልፈለጉ ለቀው ሌላ ምድባ እየተጠባበቁ እንደነበር ገልጸዋል፡፡ በደኅንነት ተቋሙ ውስጥ የነበራቸው የሥራ ድርሻ መረጃ ወደ ላይና ወደ ታች ማስተላለፍ ብቻ እንደነበርም አክለዋል፡፡ ከእስረኞች ጋር ምንም የሚያገናኛቸው ነገር እንዳልነበረም ገልጸዋል፡፡

ምደባ እየተጠባበቁ ቤታቸው ተሰብሮ አራት ልጆቻቸው እንደታገቱ ሲሰሙ ከልፋታቸው አንፃር ተደውሎ ሊጠሩ ሲገባ እንዴት እንዲህ ሊሆን ይችላል በሚል ራሳቸውን መቆጣጠር ካለመቻላቸውም በተጨማሪ ራሳቸውን ሊያጠፉ ቢያስቡም፣ ልጆቻቸውን በማሰብ ነገሩን እስከሚረዱት ድረስ ወደ ባለቤታቸው ቤተሰቦች ቤት ዱከም መሄዳቸውን ተናግረዋል፡፡ ዱከም ደግሞ ዳር ድንበር ሳይሆን በቅርበት ያለ ከተማ መሆኑን አስረድተው፣ ፈላጭ ቆራጭ ተደርገው የሚዘገብባቸው ነገር እንዲታረም ጠይቀዋል፡፡

ጠበቆቻቸውም አቶ ያሬድ በቁጥጥር ሥር ከዋሉ ስምንት ቀናት ቢሞሉም፣ መርማሪዎች ቃላቸውን እንዳልተቀበሏቸው ተናግረዋል፡፡ በወንጀለኛ መቅጫ ሥነ ሥርዓት ሕግ ቁጥር 22፣ 26፣ 56 እና 59 መሠረት ተጠርጣሪውን በቁጥጥር ሥር ለማዋል በቂ ማስረጃ መኖር እንዳለበት እንደሚደነግግ ጠቁመው፣ አቶ ያሬድን ቃላቸውን ያልተቀበሏቸው ምንም ዓይነት መረጃም ሆነ ማስረጃ ስለሌላቸው መሆኑን ተናግረዋል፡፡ በመሆኑም ከእስር ሊለቀቁ እንደሚገባ አክለዋል፡፡ ንፁኃንን አስሮ ማስረጃ መጠበቅ ተገቢ አለመሆኑንም ገልጸዋል፡፡

መርማሪ ፖሊስ በበኩሉ የ60 የምስክሮች ቃል መቀበሉንና ገና ብዙ ማስረጃዎችን መሰብሰብ እንደሚቀረው አስረድቷል፡፡ ከተፈጸመው ወንጀል አንፃር ሰፊ ምርመራ ማድረግ እንደሚቀረውና ምስክሮችም እየቀረቡና ቃላቸውን እየሰጡ መሆኑን በማስረዳት፣ ተከራክሮ የጠየቀው 14 ቀናት እንዲፈቀድለት ጠይቋል፡፡ ፍርድ ቤቱ የፖሊስን የምርመራ መዝገብ በአዳር አስቀርቦ ከተመለከተ በኋላ፣ ተገቢ ምርመራ እየተደረገ መሆኑንና ቀሪ ሥራዎች እንዳሉ የሚያሳይ መሆኑን ግንዛቤ መውሰዱን ገልጾ፣ የተጠየቀውን 14 ቀናት በመፍቀድ ለኅዳር 27 ቀን 2011 ዓ.ም. ቀጠሮ ሰጥቷል፡፡

የፌዴራል ፖሊስ ወንጀል ምርመራ ቡድን ሌሎች በቁጥጥር ሥር አውሎ ፍርድ ቤት ያቀረባቸው የብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎት ምክትል ዋና ዳይሬክተር የነበሩትን ሐሺም ቶፊቅ (ዶ/ር) ባለቤት ወ/ሮ ዊዳት አህመድና ዶ/ር ሐሽምን በመኪና መቀሌ ከተማ አድርሷል የተባለውን አቶ ሰሚር አህመድን ነው፡፡

ወ/ሮ ዊዳት ባለቤታቸው በተጠረጠሩበት ከባድ የሰብዓዊ መብት ጥሰትና የሙስና ወንጀል እንደሚፈለጉ እያወቁ ለሕግ ባለማሳወቃቸው፣ ሁለት ሽጉጥና ሰነዶች ማሸሻቸውን መርማሪ ቡድኑ ገልጿል፡፡ አቶ ሰሚርም ተጠርጣሪው በሕግ እንደሚፈለጉ እያወቁ፣ በመኪና ጭነው ወደ ትግራይ ክልል በመውሰዳቸው መጠርጠራቸውን አክሏል፡፡ ተጠርጣረዎቹ ከታሰሩ 13 ቀናት እንዳለፋቸው ጠበቆቻቸው ገልጸው፣ በፌዴራል የመጀመርያ ደረጃ ፍርድ ቤት አራዳ ምድብ ቀርበው መርማሪ ፖሊስ የምስክሮች ቃል መቀበል ብቻ እንደቀረው በማስረዳቱ አምስት ቀናት ብቻ ተፈቅዶለት እንደነበር አስረድተዋል፡፡ ለምን ወደ ከፍተኛ ፍርድ ቤት እንዳመጣቸው እንዳልገባቸው ጠበቆቹ ገልጸው፣ የጦር መሣሪያ መደበቅና ተጠርጣሪ በመሸሸግ መጠርጠራቸው የተገለጸ በመሆኑ፣ ይኼ ደግሞ ደንብ መተላለፍ ስለሆነ የዋስ መብታቸው እንዲከበርላቸው ጠይቀዋል፡፡

ፍርድ ቤቱ የግራ ቀኙን ክርክር ከሰማ በኋላ በአራዳ ፍርድ ቤት የተከፈተው የምርመራ መዝገብ በከፍተኛው ፍርድ ቤት ከተከፈተው መዝገብ ጋር እንዲጣመር ትዕዛዝ ሰጥቶ፣ መርምሮ ብይን ለመስጠት ለኅዳር 17 ቀን 2011 ዓ.ም. ቀጠሮ ሰጥቷል፡፡

ፊልሞን ግርማዬና ቴዎድሮስ ጣዕም አለው የተባሉ ተጠርጣሪዎች ደግሞ የብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎት የአንድ መምርያ ኃላፊ የነበሩትን አቶ ተስፋዬ ገብረ ጻድቅ፣ በተጠረጠሩበት የሰብዓዊ መብት ጥሰት እንደሚፈለጉ እያወቁ፣ የጦር መሣሪያዎችና ሰነዶች በመደበቅና በመሸሸግ መተባበራቸውን መርማሪ ቡድኑ አስረድቷል፡፡ ተጠርጣሪዎቹ በበኩላቸው ፈጽመዋል የተባለው ድርጊት ደንብ መተላለፍ በመሆኑ ዋስትና ስለማይከለክል እንዲፈቀድላቸው ጠይቀዋል፡፡ ፍርድ ቤቱም ብይን ለመስጠት ለኅዳር 17 ቀን 2011 ዓ.ም. ቀጠሮ ሰጥቷል፡፡

የሜቴክ የሰው ሀብት ልማት ኃላፊ የነበሩት ሌቴና ኮሎኔል ሰጠኝ ካህሳይን በሚመለከት ፖሊስ ሀብት እንዳላቸውና በመሃላ አስደግፈው ደሃ መሆናቸውን ለፍርድ ቤት የገለጹት ሐሰት መሆኑን በመግለጽ፣ ተከላካይ ጠበቃ ይቁምልኝ ያሉት ውድቅ ተደርጎ በራሳቸው ጠበቃ አቁመው እንዲከራከሩ ፍርድ ቤቱን ጠይቋል፡፡ እሳቸውም የተናገሩ እውነት መሆኑን አስረድተው፣ መርማሪ ቡድኑ እንዳላቸው እየገለጸ ያለው ዕግድ የተጣለበትን ሀብት በመሆኑ ጠበቃ ማቆም እንደማይችሉ ገልጸዋል፡፡

ፍርድ ቤቱ የሁለቱን ወገኖች ክርክር ከሰማ በኋላ የመርማሪውን ክርክር ውድቅ በማድረግ፣ ትክክለኛው ነገር ተጣርቶ እስከሚቀርብ በሕግ ባለሙያ መወከላቸው መብት መሆኑን አስታውቋል፡፡ በመሆኑም ፖሊስ ከጠየቀው 14 ቀናት ውስጥ ሰባት ቀናት በመፍቀድ ለኅዳር 20 ቀን 2011 ዓ.ም. ቀጠሮ ሰጥቷል፡፡           

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ለፋይናንስ ዘርፉ ብቃት ያለው የሰው ኃይል የማፍራት የቤት ሥራን የማቃለል ጅማሮ

የአገሪቱ የፋይናንስ ዘርፍ እያደገ ለመሆኑ ከሚቀርቡ ማስረጃዎች ውስጥ  የግል...

የምድር ባቡርን የሚያነቃቃው የመንግሥት ውሳኔ

በኢትዮጵያ ወደብ አልባነት ላይ የተደመረውን የሎጀስቲክስ ችግር ለመፍታት ግዙፍ...

የፓርላማ አባላት ስለሰላም ስምምነቱ አፈጻጸም ግልጽ መረጃ የለንም አሉ

‹‹ሕወሓትን ለፍረጃ አብቅተውት የነበሩ ጉዳዮች በአብዛኛው መልክ ይዘዋል›› ሬድዋን...