ከኤችአይቪ ቫይረስ ነፃ የሆኑ ነገር ግን ለቫይረሱ ተጋላጫ የሆኑ ሰዎች እንዳይጠቁ የሚያደርግ ቅድመ መከላከያ የሚዋጥ መድኃኒት በሙከራ ደረጃ መስጠት መጀመሩን፣ ጤና ጥበቃ ሚኒስቴር አስታወቀ፡፡ በፕሮግራሙ የሚካተቱት ተመርምረው ነፃ የሆኑ ሴተኛ አዳሪዎች፣ እንዲሁም በደማቸው ውስጥ ኤችአይቪ ካለባቸው ሰዎች ጋር በትዳር የሚኖሩ እንደሆነ ታውቋል፡፡
የዓለም ጤና ድርጅት ባወጣው መሥፈርት መሠረት የተመረጡ የፀረ ኤችአይቪ መድኃኒት ተጋላጭ ናቸው ለሚባሉት የኅብረተሰብ ክፍሎች ነው የሚሰጠው፡፡ መድኃኒቱ የሚሰጠው ተጋላጫነታቸው እስከሚቀንሰበት ጊዜ ድረስ እንደሆኑ ለሪፖርተር የገለጹት፣ በሚኒስቴሩ የኤችአይቪ መከላከልና መቆጣጠር ቡድን አስተባባሪ ወ/ሮ ምርቴ ጌታቸው ናቸው፡፡ መድኃኒቱ በሙከራ ደረጃ መሰጠት የሚጀመረው በዘጠኝ የጤና ተቋማትና በስድስት ሴተኛ አዳሪዎች በሚገኙባቸው ሥፍራዎች ነው ብለዋል፡፡
በአዲስ አበባና በክልሎች ተግባራዊ ለማድረግ ዝግጅት መጠናቀቁን፣ በአዲስ አበባ ግን ቀደም ብሎ መጀመሩን አስተባባሪዋ ገልጸዋል፡፡ ‹‹በተባሉት አካባቢዎች ያገኘነውን ሁሉ ለመድረስ አስበናል፤›› የሚሉት ወ/ሮ ምርቴ፣ የሙከራ ፕሮግራሙ ሲጠናቀቅ በሁሉም የአገሪቱ ክፍሎች ታካሚዎች በሚበዙባቸው የጤና ተቋማት አገልግሎት እንደሚሰጥ አስረድተዋል፡፡
‹‹የፀረ ኤችአይቪ ሕክምና የሚሰጠው በነፃ ነው፡፡ ይህም የቅድመ መከላከል መድኃኒት በነፃ ይሰጣል፡፡ የመድኃኒቱን ወጪ የሚችለውም የፀረ ኤችአይቪ ሕክምና ወጪን የሚችለው ግሎባል ፈንድ ነው፡፡ ግሎባል ፈንድ ለአዲሱ ፕሮጀክት አዲስ የሚይዝልን በጀት አይኖርም፡፡ እኛም ተጨማሪ ሳያስፈልገን ባለው መሄድ እንችላለን፤›› ቢሉም፣ ሙከራው ተጠናቆ በስፋት ተግባራዊ ሲደረግ ግን ድጋፍ እንደሚያስፈልግ ጠቁመዋል፡፡
በተመረጡት የጤና ተቋማት የሚሠሩ ባለሙያዎች ሥልጠና የተሰጠ ሲሆን፣ ኦሮሚያ፣ ጋምቤላና አማራ ክልሎችና አዲስ አበባ ከተማ በሙከራ ፕሮጀክቱ የታቀፉ የአገሪቱ ክፍሎች ናቸው፡፡ መድኃኒቱ ሰዎች በኤችአይቪ ቫይረስ እንዳይያዙ የሚከለክል ቢሆንም፣ ልቅ የግብረ ሥጋ ግንኙነት ማድረግና የመሳሰሉት ድርጊቶች ግን የመድኃኒቱን ውጤታማነት ሊቀንሱት እንደሚችሉ አክለዋል፡፡
በዓመት ሦስት በመቶና ከዚያ በላይ የቫይረሱ ሥርጭት ያለባቸው አገሮች ቅድሚያ ሰጥተው የቅድመ መከላከል መድኃኒቱን በአገራቸው እንዲያስጀምሩ፣ የዓለም ጤና ድርጅት ያዛል፡፡ ይኼንን መድኃኒት ለአገራቸው ሕዝቦች ማቅረብ ከጀመሩ የአፍሪካ አገሮች መካከል ደቡብ አፍሪካ የመጀመሪያዋ መሆኗ ታውቋል፡፡
የቫይረሱን ሥርጭት ለመግታት የቅድመ መከላከል ፖሊሲ የሚከተለው የጤናው ዘርፍ፣ በአንድ ወቅት በርካቶችን እንደ ቅጠል ያረገፈውን ኤችአይቪ ለመቆጣጠር ኮንዶም በገፍ ያቀርብ ነበር፡፡ ሰፊ የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥራዎችም በዘመቻ መልክ ይከናወኑ እንደነበር ይታወሳል፡፡ ወረርሽኙን መቆጣጠር እንደተቻለ ሲታወቅ ግን፣ ሙሉ በሙሉ ማለት በሚቻል ደረጃ አስፈላጊ ድጋፍ ያደርጉ የነበሩ የተለያዩ ዓለም አቀፍ ተቋማት ትኩረታቸውን ወደ ሌሎች ወቅታዊ ጉዳዮች አድርገዋል፡፡
ትልቁን ድጋፍ እያደረገ የሚገኘው ግሎባል ፈንድም ከሕክምና ጋር የተያያዙ ነገሮችን ከማድረግ ባለፈ፣ የቅድመ መከላከል ኃላፊነቱን ለመንግሥት እንደተወለት ይነገራል፡፡ መንግሥትም ሁሉንም ማኅበረሰብ ለመድረስ ያለው ውስን አቅም ስለማይፈቅድለት ሥጋት ያለባቸው የማኅበረሰቡ ክፍሎችን ለይቶ የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥራዎችን በማከናወን ተመርምረው ራሳቸውን እንዲያውቁ፣ በሴተኛ አዳሪነት ሕይወት ውስጥ ለሚኖሩ ደግሞ ኮንዶም ያቀርባል፡፡ ይሁንና የተደራሽነት ችግር እንዳለ መዘገባችን አይዘነጋም፡፡ እስከ 23 በመቶ የቫይረሱ ሥርጭት በሚታይባቸው ሴተኛ አዳሪዎችና የመያዝ ዕድላቸው ሰፊ ለሆነው የኅብረተሰብ ክፍሎች አዲሱ ፕሮጀክት ዕፎይታ ነው ተብሏል፡፡