Sunday, June 16, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

ይድረስ ለሪፖርተርትዝብትና ተስፋ በአዲስ አበባ ዕድገት

ትዝብትና ተስፋ በአዲስ አበባ ዕድገት

ቀን:

እኔ ዕድሜዬ አሁን 83 ነው፡፡ ከልጅነት ጀምሮ ዕድሜዬን ሙሉ አዲስ አበባ ውስጥ ነው የኖርኩት፡፡ በእነዚህ ዓመታት አራት መንግሥታት ሲለዋወጡ ዓይቻለሁ፡፡ አዲስ አበባ በበኩልዋ አዳዲስ ማስተር ፕላን እየተሠሩላት፣ አዳዲስ ኢንቨስተሮች እየገቡባትና መንግሥትም በተለይ ማዘጋጃ ቤቱ በሚያቅደው ዕቅድ መሠረት በየጊዜው በርካታ ለውጦች እንዳደረገች ለማየት ችያለሁ፡፡ ታዲያ እነዚህ ለውጦች አንዳንዶቹ ዓላማ ያላቸውና ተገቢ ሲሆኑ፣ አንዳዶቹ ደግሞ ዓላማቸውን የሳቱ ነበሩ፡፡ ማለትም ማስተር ፕላን ካለም ያልተፈጸመበት ከሌለም በትክክለኛ አዕምሮ ለሚያስተውል ሰው ሊገነዘበው በሚችል መልኩ ያልተሠራ ነበር፡፡ በተለይም የመንገዱ ስፋት፣ አቀማመጥና አቅጣጫ እንዲሁም የሚሠሩት ቤቶች ወይም ሕንፃዎች አቅጣጫን ያልተከተሉና ያፈነገጡ ሆነው ይታዩ ነበር፤ አሁንም ይታያሉ፡፡

በተለይም ደግሞ ለሰው መኖሪያ የሚመቹ መናፈሻዎችና መንሸራሸሪያ ቦታዎች አለመኖራቸው በጣም ከሚያሳዝኑኝ ሁኔታዎች ውስጥ አንዱና ትልቁ ጉዳይ ሆኖ አግኝቼዋለው፡፡ በድሮ ጊዜ መሬት በባላባቶችና በግለሰቦች በተያዘበት ጊዜ፣ መሬት ሲቀየስ በባላባት መሬት ላይ ማለፍ ስለማይችል እየተጣመመ ሲሠራ የዓይን ምስክር ነበርኩ፡፡ ከዚያ በኋላ ደርግ መጥቶ ሥልጣን ሲይዝና መሬት የመንግሥትና የሕዝብ ሀብት ነው ብሎ ሲያውጅ፣ አዲስ አበባ አሁን ቀን ወጣላት ሁሉም ነገር በትክክል ይሠራል ብዬ ነበር፡፡ መንገዱም በፕላን መሠረት ተቀይሶ ቀጥ ባለ አሠራር ይሠራል እያልኩ ስገምት፣ የደርግ መንግሥት አንድ ሳይሆን ተበጣጥሶ በቀበሌ ሹመኛና ማን አለብኝነት መሬት እየተቆራረሰ ሲታደል ለመንገድ ቅያስ፣ ለሰው መደሰቻ የሚያስፈልጉ መናፈሻዎችና መንሸራሸርያ ቦታዎች ገደል ግቡ ተባሉ፡፡ ሐዘኔታዬም በዝቶ ስቆጭና ስናደድ ቆየሁ፡፡ ሆኖም አንድ ቀን ሌላ መንግሥት መምጣቱ ስለማይቀር ቀን ይወጣለታል ብዬ ማሰቤ አልቀረም ነበር። ከዚህ በኋላ ደግሞ የኢሕአዴግ መንግሥት ሲመጣ አዲስ አበባ ቀንሽ መጣልሽ እያልኩ ስቋምጥ እንዳልሆኑ ሆኖ የሀብታሞችና የኢንቨስተሮች መቀረማመቻና ቅጡን ያጣ፣ ግራ የሚያጋባ መንገድና ሕንፃ ሲጣመምና ሲገነባ ማየት ምኞቴንና ፍላጎቴን አቀጨጨውና መልሶ ሐዘን ውስጥ አስገባኝ፡፡

አሁን ደግሞ የጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) መንግሥት በተለይም የማዘጋጃ ቤቱ አስተዳደር ምክትል ከንቲባ ታከለ ኡማ (ኢንጂነር) አዲስ አበባን ለማዘመንና እንዲሁም ለማሳመር ባሳዩት ፍላጎትና ጥረት፣ ሰሞኑን ለዓመታት ታጥረው የተቀመጡትን ቦታዎች ጥቅም ላይ እናውለዋለን በማለታቸው ደስታዬ እጥፍ ድርብ ሆኖልኛል፡፡ በተለይም የፒያሳው/አራዳ ቦታ ለወጣቱ፣ ለአዛውንቱና ለማንኛውም ነዋሪ ጠቃሚ በሚሆን መልኩ ይውላል በመባሉ፣ ‹‹እልል እልል›› ማለት ብቻ ነው የቀረኝ። ሆኖም ይህን የተቀደሰ ዓላማ ሥራ ላይ ከማዋሉ በፊት ከዚህ በታች የማቀርባቸውን ሐሳቦች ቢከተሏቸው ደስታዬ እጥፍ ድርብ እንደሚሆን በትህትና መግለጽ እፈለጋለሁ፡፡

- Advertisement -

በዚህም መሠረት የሚከፈልባቸው የመኪና ማቆሚያዎች በየቦታው ቢሠሩ፣ የልጆች የእግር ኳስ መጫወቻዎች ቢኖሩ፣ በጥቂት ክፍያ የምንጠቀምባቸው ንፅህናቸው የተጠበቀ መፀዳጃ ቦታዎች ቢገነቡ፣ የሕዝብ መናፈሻዎች ቢስፋፉ፣ መንገዶች በተቻለ መጠን ሳይንጋደዱ በቀጥታ ቢቀየሱ፣ ሕንፃዎች ሲሠሩ ከመንገድ የሚርቀርቡበት ስፋት በማስተር ፕላን በወጣው መሠረት ርቀው እንዲሠሩ፣ እንዲሁም ሕንፃዎች ሲሠሩ የመንገዱን አቅጣጫ ሳይለቁና ሳይጣመሙ ትይዩነታቸውን ተከትለው እንዲሠሩ ለማሳሰብ እፈለጋለሁ፡፡

ትልቁ ነገር ደግሞ ሕንፃዎች ሲሠሩ አስገዳጅ የምርድ ቤት የመኪና ማቆሚያ እንዲኖራቸውና፣ ከተሠሩም በኋላ በዓላማቸው መሠረት እንዲያስተናግዱ ቢደረግ፣ መንገድ ላይ ፓርክ እያደረጉ የሚቆሙትን መኪኖች መንገድ ከማጣበብ እንደሚያድኑ መታወቅ ይኖርበታል፡፡ ሌላው በጣም የሚያሳስበኝ ጉዳይ ደግሞ አዲስ አበባ ዋና ከተማ ሆና እንዲያውም የአፍሪካ ዋና ከተማ እየተባለች የውኃ ማዳረስ ጉዳይ እንደሆነ ለማስገንዘብ እፈልጋለሁ፡፡

በተለይም ደግሞ የፒያሳ ጉዳይ ስለሚያሳስበኝ ከዚህ የሚከተሉትን ሐሳቦች ማዘጋጃ ቤቱ እንዲመለከተውና እንዲጠቀምበት በትህትና እጠይቃለሁ፡፡ አዲስ አበባን ያማረችና ያሸበረቀች ለማድረግ በተለይም መሀል ፒያሳን በተመለከተ ማዘጋጃ ቤቱ ከዚህ በታች የማቀርባቸውን ሐሳቦች በመከተል ውጤቱ መልካምና ጥሩ እንደሚሆን ጥርጥር የለኝም። በዚህም መሠረት ቀድሞ የነበረውን የፒያሳ ዕይታ መልሶ እንዲጎናፀፍ አጥንተው የሚያስተካክሉና ሐሳብ ለማቅረብ ችሎታና ልምድ ያላቸው የታወቁ  
 የመልሶ ማልማት ልምድ ያላቸውን አርክቴክቶችና የከተማ ፕላነሮች ማሳተፍ፣ መሀል ፒያሳን ማለትም ከቅዱስ ጊዮርጊስ አደባባይ እስከ ደጎል አደባባይ ያለውን አካባቢ ለእግረኛ መጠቀምያ ብቻ ማድረግ፣  ደኅንነቱ የተጠበቀ የልጆችና የሕዝብ መናፈሻ መገንባትና በተጨማሪም ታዋቂ አርክቴክቶች፣ የታሪክ አዋቂዎች፣ ታላላቅ ሰዎች፣ ደራሲያን፣ ፖለቲከኞች፣ የሚዲያ ሰዎች፣ የከተማ ፕላነሮች እንዲሁም በዚህ ጉዳይ ላይ ያገባናል ወይም አስተዋጽኦ እናደርጋለን የሚሉ ኢንተርናሽናል ፕላነሮች ቢገቡበትና ሐሳባቸውን እንዲያቀርቡ ቢጋበዙና ቢካፈሉ ውጤቱ ያማረና ዘላቂ እንደሚሆን እምነቴ የጸና ነው፡፡ መሪ ቃላችንም ‹‹ፒያሳን/አራዳን በድሮ አቋሟ በአዲስ መንፈስና ራዕይ በአዲስ ዓላማና ሕይወት እንድትኖር እናድርጋት፤›› የሚል ነው፡፡

(ኢንጅነር ተሰማ ያኢ ዱላ፣ ከአዲስ አበባ)

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የምግብ ዋጋ ንረት አጣዳፊ ዕርምጃ ያስፈልገዋል!

መንግሥት የሚቀጥለውን ዓመት በጀት ይዞ ሲቀርብ በአንገብጋቢነት ከሚነሱ ጉዳዮች...

ከባለአንድ ዋልታ ወደ ባለብዙ ዋልታ የዓለም ሥርዓት የመሸጋገራችን እውነታ

በአብዱ ሻሎ አንገት ማስገቢያ እ.ኤ.አ. በፌብሩዋሪ 2022 የሩሲያ መንግሥት በዩክሬን ‹‹ልዩ...

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የውጭ ግንኙነት የሺሕ ዘመናት ታሪኳና እሴቶቿን የሚመጥን መሆን ይኖርበታል

(ክፍል አንድ) በተረፈ ወርቁ (ዲ/ን) እንደ መንደርደሪያ ለዛሬው የግል ትዝብቴንና ታሪክን ላዛነቀው...

ከአገር ግንባታ ጋር የተያያዙ ወሳኝ የቅርብ ታሪካችን አንጓዎች

በታደሰ ሻንቆ በአያሌው የተመረጡና ልጥ የሌላቸው ነጥቦች የተደራጁበት ይህ ታሪክ...