Tuesday, July 16, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
እኔ የምለዉየዴሞክራሲ ተቋማት አደረጃጀት ቢሻሻል

የዴሞክራሲ ተቋማት አደረጃጀት ቢሻሻል

ቀን:

በተስፋዬ ጎይቴ

ውድ አንባቢያን! ረቡዕ ጥቅምት 28 ቀን 2011 ዓ.ም. ታትሞ የወጣው ሪፖርተር በርዕሰ አንቀጹ ይኼንን ትኩረት የሚሻ ወቅታዊ ጉዳይ በተመለከተ የማንቂያ ደወል አሰምቷል፡፡ የዚህ ጽሑፍ አቅራቢ የጋዜጣው ሐሳብ መነጋገሪያ መድረክ የሚከፍት ስለሆነ፣ ምዕራፉ ዝም ብሎ መዘጋት የለበትም የሚል እምነት ስላደረበት እነሆ የበኩሉን ብሏል፡፡ መቼም ቢሆን በምድር ላይ መልካም አስተዳደር እንዲሰፍን ከልቡ የሚመኝ ሰው የአስተዳደሩን ሕዝባዊነት የሚያረጋግጡ ተቋማት መኖራቸውን በፅኑ ይደግፋል ተብሎ ይታሰባል፡፡ ተጠያቂነት ፈረንጆቹ እንደሚሉትም ‘አካውንቴቢሊቲ’ ወይም ‘ቼክ ኤንድ ባላንስ’ ሳይኖር የሰማዩ አይታወቅም እንጂ በምድር ላይ ዴሞክራሲን፣ የሕግ የበላይነትን፣ ፍትሕንና መልካም አስተዳደርን ማስፈን ከቶም መቻሉ ያጠራጥራል፡፡ አገራችንም ከዚህ እሳቤ በመነሳት ፍትሕን፣ ዴሞክራሲንና መልካም አስተዳደርን ለማረጋገጥ የሚያግዙ ተቋማትን ፈጥራለች፡፡

ከተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የሰብዓዊ መብት ድንጋጌዎች እስከ አፍሪካው ቻርተር፣ ከዚያም እስከ አገራችን ሕገ መንግሥት በወርቃማ ቀለም የተጻፉትንና በየትኛውም መንገድ በማንም ባለሥልጣን፣ ቱባ ባለሀብትም ሆነ የሃይማኖት መሪ ፈቃድ ሊጣሱ የማይችሉትን  የዜጎች ሰብዓዊ መብቶች ለማስከበር እንዲሠራ የተቋቋመ የሰብዓዊ መብት ኮሚሽን አለን፡፡ ከፌዴራል እስከ ቀበሌ የተዘረጋው ጡንቸኛው የመንግሥት አስፈጻሚ አካል በዜጎች ላይ የአስተዳደር በደል እንዳያደርስ እንዲከላከል፣ ለመልካም አስተዳደር ዘብ እንዲቆም፣ በደል ደርሶም ከተገኘ መርምሮ ዕንባን እንዲያብስ የሕዝብ ዕንባ ጠባቂ ተቋም ተመሥርቷል፡፡ ሁለቱ ተቋማት የአንድ ጀንበር ትውልዶች፣ የተከታታይ አዋጆች ፍጡራን መሆናቸውንም ልብ ይሏል፡፡

ለሁለቱ ተቋማት በዕድሜ ታላቃቸው የሆነው የሥነ ምግባርና ፀረ ሙስና ኮሚሽንም የተቋቋመው ለዚህች አገር እጅግ አስፈላጊ ተቋም ነው፡፡ የዴሞክራሲ አንዱ መገለጫ ነው፡፡ ለዜጎቻችን ጨዋ ሥነ ምግባር፣ ጉቦን መጠየፍና የራስ ያልሆነ ንብረትን በተለይም ደግሞ የሕዝብ ሀብትን መንካት ቀርቶ መመኘት ነውር መሆኑን ለማስተማር በእጅጉ ያስፈልገናል፡፡ ዘረፋን ያስታግስልናል፣ የባለጊዜ ባለሥልጣናትን ቅሚያና ምዝበራ ያስቆምልናል፣ የአገራችንን ጥሪት ያስጠብቅልናል ተብሎ ነው፡፡

የመጀመርያዎቹ ሁለቱ ተቋማት ለሕግ አውጭ አካሉ ተጠሪ ተደርገው ቆይተዋል፡፡ ሦስተኛው ደግሞ የአስፈጻሚዎቹ ሁሉ የበላይ በሆነው በጠቅላይ ሚኒስትሩ ሥር ሲተዳደር ኖሯል፡፡ እዚህ ላይ ሦስቱ ተቋማት ባለፉት ዓመታት ከተሰጣቸው ኃላፊነት አንፃር ያስገኙት ፋይዳም የቱን ያህል እንደሆነ ሁላችንም አይተነዋል፡፡ የዚህች አገር የመጨረሻው የሥልጣን አካል የሆነው የተከበረው የሕዝብ እንደራሴዎች ምክር ቤትም መኖር፣ ያው የሕግ የበላይነትን ለማስከበርና የሕዝቡን ሉዓላዊ ሥልጣን ለማስጠበቅ መሆኑ ግልጽ ነው፡፡ አንዳንድ ጊዜ አስፈጻሚው በማወቅም ሆነ ባለማወቅ ካልተጋፋው፣ ወይም ፈላጭ ቆራጭ የነበረው ፓርቲ ከፈሪኃ እግዚአብሔር ተጣልቶ ምን አገባህ ካላለው በቀር የሉዓላዊ መንግሥታችን የበላይ ነው፡፡ የተከበረው ፓርላማ የተፈጠረው አስፈጻሚውን እንዲያርም፣ እንዲመክር፣ እንዲቆጣ፣ እንዲገስጽ፣ ፍትሕና ፍትሐዊነት ከምንም በላይ ገዝፎና ነግሦ እንዲቆይ እንዲያደርግ ነው፡፡ ሰንደቅ ዓላማችን በዓይን የሚታይ ብቻ ሳይሆን በደም፣ በአጥንትና በሥጋችን ውስጥ ሰርፆ እንዲኖር፣ አንድነታችን በፅኑ መሠረት ላይ እንዲገነባ ለማድረግ እንዲሠራ ነው የቆመው፡፡ ሌላም ልንጨምርለት እንችላለን፡፡ ሕገ መንግሥቱ ላይ ተጽፏል፡፡ በይሁንታ ማኅተም ተረጋግጧል፡፡ ሰብዓዊ መብትና ዕንባ ጠባቂ ለአገራችን ፓርላማ ተጠሪ ሆነው የቆዩትም ቢሳካ ኖሮ እሳቤው ማንም እንዳሻው ጣልቃ እንዳይገባባቸው ለመከላከል ነበር፡፡

የዚህ ጽሑፍ ጠበብ ያለ ሐሳብም ከፍ ብሎ መጀመርያ ላይ በተጠቀሱት ሦስት የዴሞክራሲ ተቋማት ተልዕኮ ተቀራራቢነት ላይ ለመነጋገር ብቻ በመሆኑ፣ ለጊዜው ትኩረታችንን በዚሁ ላይ ብቻ ሰብሰብ ብናደርግ ይሻላል፡፡ ሌላውን ሌላ ጊዜ እንመለከተዋለን፡፡ ታዲያ እነዚህ ሦስት የዴሞክራሲ ተቋማት ከተቀረፁላቸው ዓላማዎች፣ ሥልጣንና ተግባራት ከዚያም ከፍ ብሎ ተቋማቱን ለማቋቋም እሳቤ ከተደረገው ዋነኛ መነሻ ከሚጠበቀው ግብ ወይም ውጤትና ለኅብረተሰባችን እንዲያስገኙ ከሚፈለገው ፋይዳ አንፃር፣ አንድ ተቋም ሆነው ቢዋቀሩ አይቻልም ይሆን የሚለው ጉዳይ የዛሬው ዋነኛ መነጋገሪያችን ነው፡፡ ፍፁም ተመሳሳይ የሆነ፣ ዓላማ ባይኖራቸውም የተቋቋሙባቸውን አዋጆች መቅድሞች ስንመለከት፣ የዴሞክራሲ ተቋማት በመሆናቸው ብቻ ሳይሆን፣ የዓላማ ተቀራራቢነት ስላላቸውና የሥራ ባህሪያቸው ስለሚሳሳብ አንዳንዴም ድንበሩን ለመለየት ስለሚያስቸግር ለየብቻቸው ራሳቸውን ችለው ከሚቆሙ በአንድ ተቋም ቢተዳደሩ ምን ችግር ይኖረው ይሆን፣

ኢትዮጵያ ለዘመናት በድህነት ማጥ ውስጥ ስትዳክር ኖራለች፡፡ ሕዝቦቿ ዛሬም ድረስ በምግብ እህል ራሳቸውን መቻልና ጠግበው መብላት አልቻሉም፡፡ የመጠለያው፣ የሕክምናው፣ የንፁህ የመጠጥ ውኃ ዕጦት የሚነሳ አይደለም፡፡ በዚህ ዓይነት የከፋ የኑሮ ደረጃ ላይ ላለ ኅብረተሰብ ደግሞ ከምኑም ከምኑም በተለይ ከአስተዳደራዊ ወጪው ቀንሶ ወደ ልማት በማዞር ሕዝቡ ከአስከፊው ኑሮ እንዲላቀቅ ማገዝ እንጂ፣ የተገኘው ውስን ሀብት እምብዛም ፋይዳ በማይጨምሩ ነገሮች ላይ መባከን የለበትም፡፡ የነበርንበትንና ያለንበትን ሁኔታ ለመቀየር እንኳን ሦስት ይቅርና አሥርም መሰል ተቋማት ቢቋቋሙ አይችሉትም፡፡ ሦስት ተቋማትም ሆነው ችግሩን እስከ ዛሬም አላስወገዱትም፡፡ ከቅርብ ቀናት ወዲህ የፌዴራል ጠቅላላ ዓቃቤ ሕግ እያሳየን ያለው ጉድ ይህንኑ ያረጋግጣል፡፡ እስከ ዛሬ የት ነበርን ያሰኛል፡፡ ከዚህ አንር መንግሥት ጉዳዩን ዘንግቶት ነው ለማለት አይደለም፡፡ ብሶት ያንገበገበው ሕዝብ ጥያቄዎቹ ምላሽ እንዲያገኙ መሠራት ስለነበረበት፣ መሠረታዊ መነሻው በወቅቱ ትክክልና ተገቢ ነበር ማለት ይቻል ይሆናል፡፡ በተቋማቱ አደረጃጀት ረገድ የትኛውም አማራጭ ቢመረጥና በየትኛውም መንገድ ቢኬድ በጣም አክሳሪ ሆኖ ላይሆን ይችላል፡፡ ተቋማቱ በጣም አትራፊ ነበሩ ለማለት ግን አያስደፍርም፡፡ ስለዚህ ዛሬ ላይ ቆም ብሎ የትኛው መንገድ የበለጠ አትራፊ ወይም አዋጭ ነው ብሎ ማየቱ ግን ብልህነት ነው፡፡

በክልሎች ጭምር ትልልቅ ቅርንጫፎች ያሏቸውን ሦስት ግዙፍ ተቋማት ይዞ ከመቀጠል ይልቅ አንድ ወይም ሁለት ተቋም አድርጎ በማዋሀድ ሙስናን መከላከል፣ ሰብዓዊ መብትን ማስከበርና የአስተዳደር በደልን መከላከል፣ የመረጃ ነነትንም ማስተግበር ለምን አይቻልም? አንድ ተቋም አድርጎ ሥራዎቹን በሦስት ባለቤት ዘርፎች ወይም ዳይሬክቶሬቶች (በምክትሎች ወይም በዳይሬክተሮች) ለማደራጀት ለምን አይሞከርም? ውጤታማነቱ ገና በተገቢው ባይመዘንም የመገናኛ ብዙኃንና የመረጃ ነፃነት አዋጅ (ክፍል ሦስት) ራሱን የቻለ አስፈጻሚ ተቋም ከሚፈጠርለት ተብሎ የሕዝብ ዕንባ ጠባቂ ተቋም ደርቦ እንዲሠራው መደረጉ፣ አሁን ለቀረበው ሐሳብ አዋጭነት ትልቅ ማሳያ ነው፡፡

ለሦስት ተቋማት የኮሚሽነሮችና የምክትል ኮሚሽነሮች ብዛት፣ የዳይሬክተሮች ስፋት፣ ሦስቱም ዘንድ የዓላማ አስፈጻሚ፣ የሰው ሀብት፣ የግዥና ፋይናንስ፣ የኦዲት፣ የለውጥ፣ የሴቶች ጉዳይ፣ ወዘተ. ተደጋጋሚ አደረጃጀቶች፣ የቢሮ ኪራይ፣ ተሽከርካሪ፣ ደመወዝና ሌላው ሥራ ማስኬጃ የትየለሌ መሆኑን ልብ ማለት ያስፈልጋል፡፡ ሦስቱም ተቋማት የመከላከልም የምርመራም ዳይሬክቶሬቶች አሏቸው፡፡ የእነዚህን ተቋማት ዓላማዎች አስተሳስሮ በአንድ አደረጃጀት ጥላ ሥራ ማምጣት አይቻልም ወይ? ነው የዚህ አስተያየት ዋና ሐሳብ፡፡ ለየብቻም ተደራጅተው እምብዛም መሠረታዊ ለውጥ ካላመጡ ፋይዳው ምንድነው? ውህደቱስ ሳይሞከር ለምን ይፈራል? በጉዳዩ ላይስ የውይይት መድረክ ለምን አይከፈትም? ባለፉት ዓመታት እንዳየነው ቀድሞ መምርያና ዋና ክፍል የነበሩትን የአንድ ተቋም የሥራ ክፍሎች በታትነንና አሳብጠን ራሳቸውን አስችለን ስላደራጀናቸው ብቻ ለውጥ አላመጣንም፡፡ ተቋማትን ማብዛት በቁሙ ለውጥ ሊያመጣ ይችላል ወይ? ብሎ በጥንቃቄ ማሰብ ያስፈልጋል፡፡

በአንድ በኩል ለጉዳዮቹ የበለጠ ትኩረት ተሰጥቶና ባለቤት ተፈጥሮላቸው ውጤት ሊያመጡ በሚችሉበት መንገድ እንዲሠሩ መደረጉ ድንቅ ቢሆንም፣ ይህ አስተሳሰብ በተግባር እንደታየው በራሱ ምንም ያህል ለውጥ አላመጣም፡፡ የመጻሕፍት ቤቶች መብዛት አንዳንዴም በሥራ ሒደት በተገልጋዩ ላይ ጭምር መደነጋገርን ከመፍጠሩ በቀር ለዚህች አገር ዜጎች ፍትሕ አላሰፈነም፡፡ የሕግ መደፈር፣ የአስተዳደር በደል፣ የሰብዓዊ መብቶች ጥሰት፣ ሙስናና ሥርዓት አልበኝነት በእነዚህ ተቋማት አቅም ምን ያህል ተቀነሰ? አዝማሚያው የሚያሳየው ዕያደገ መምጣቱን ነበር ወይስ እየቀነሰ? አፈጻጸማቸው በገለልተኛ አካል ጥልቅ ጥናት ተደርጎበታል ወይ? ይኼንን ሁሉ ማየት ያስፈልጋል፡፡ ሰሞኑን መንግሥት እየወሰደ ያለው መሠረታዊ ዕርምጃ ባለፉት ዓመታት ምን መሠረት ላይ ቆመን እንደነበረ በግልጽ ያሳያል፡፡ በተነሳው ሐሳብም እንዲገፋበት ድፍረት ይሰጣል፡፡

በሦስቱም ተቋማት አደረጃጀት ውስጥ ‹‹መከላከል›› እና ‹‹ምርመራ›› የሚባሉ አስፈጻሚ የሥራ ዘርፎች አሉ፡፡ የሙስና፣ የሰብዓዊ መብት ጥሰትና የአስተዳደር በደል መከላከል ሥራን አንድ ላይ ተጣምሮ፣ የምርመራውም ሥራ እንደዚሁ አንድ ዘርፍ ወይም ቢሮ ሆኖ ወይም በዴስኮች ተለይቶ ሊሠራ አይችልም ወይ? ዞሮ ዞሮ አስተምህሮና መልካም ሰብዕናን የመገንባት፣ በሥነ ምግባር የታነፀ አስፈጻሚና አጠቃላይ ትውልዱን የመቅረፅ ጉዳይ ነው፡፡ ስለዚህ ተቋማቱ ተዋህደውና ተጠናክረው ጉልበት ኖሯቸው በአንድ ድምፅ አትስረቅ፣ ሕዝብን አትበድል፣ አትጨቁን፣ አትግፋ፣ ካለዚያ በምድርም በሰማይም ተጠያቂነት አለብህ ብለው ቢያስተምሩ የመብት ጥሰት፣ ሙስናና በደል መኖሩን በጥናት ቢያረጋግጡ፣ መፍትሔውን ቢያመለክቱ አይሻልም ወይ? የሰረቀ፣ የበደለና መብትን የጣሰ ሲያጋጥም በአንድ ተቋም በተለያዩ ክፍሎች ተደራጅተው የምርመራውን ሥራ ቢያከናውኑስ ምን ይከፋል? እንኳን ከድህነቷ ለመውጣት የምትታትር አገር ይዘን አደጉ በሚባሉ አንዳንድ አገሮችም ቢሆን፣ እንደ ተጨባጭ ሁኔታቸው  ሦስቱ ወይም ሁለቱ ተቋማት በአንድ ላይ የተደራጁበት ውስን ተሞክሮ አለ፡፡ ሦስቱን ወይም ሁለቱን ተቋማት አጣምረው ያደራጁት ጥቂት አገሮችም ቢሆኑ ጠቀሜታውን ተገንዝበውታል፡፡ ዓለም አቀፍ ተሞክሮ ባይኖርም እንኳን እኛ ከጠቀሜታው አንፃር ብናጣምራቸው ማን ይቀየመናል?

እስቲ በእነዚህ ሦስት ተቋማት ተጠቅመን ያመጣነውን ለውጥ ካሰማራነው ባለሙያ ብዛትና ለተቋማቱ ከወጣው ወጪ ጋር እናነፃፅር፡፡ በአንድ ተቋም ቢደራጅም ዋናው ነገር ተቋሙ ‹‹ጥርስ›› ኖሮት፣ ጡንቻው እንዲሠራ ተደርጎ ውጤታማ እንዲሆን የማስቻል ጉዳይ ነው፡፡ ለሪፖርት ፍጆታ ከሆነ የትም አያደርሰንም፡፡ ለተከበረው ፓርላማ ወይም ለጠቅላይ ሚኒስትሩ ሲቀርቡ የኖሩት የዚህ ጽሑፍ አቅራቢ ጭምር የተሳተፈባቸው የተሽሞነሞኑ ትልልቅ ሪፖርቶች ውስጣቸው ምን ነበር? ምን ለውጥስ አመጡ? የሚለው ጉዳይ በደንብ መገምገም አለበት፡፡ እስከ ዛሬ ከአሥር ዓመታት በዘለለ ጊዜ የተገኘውን ውጤት ሰሞኑን የፌዴራል ጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ በጥቂት ቀናት ውስጥ ከወሰደው ዕርምጃ ጋር እናነፃፅረው፡፡ ጉዳዩን በቀናነት ወስዶ በጥሞና መነጋገርንና መግባባት ላይ መድረስን ይጠይቃል፡፡

መልካም ሥነ ምግባር ወይም ጥሩ ሰብዕና ያለው ትውልድ ለመፍጠር ያግዛል በሚል፣ በየትምህርት ቤቶቻችን የሥነ ዜጋና የሥነ ምግባር ትምህርቶች ይሰጣሉ፡፡ ትምህርቶቹን ፈትሾ ለፖለቲካ ፍጆታ ሳይሆን፣ ለጠንካራ ሰብዕናና ለጥሩ ሞራል ግንባታ ተጠቅሞ ዘላቂነት ያለው የሥነ ምግባር ግንባታ መሥራትና ተጨባጭ ለውጥ ማምጣት ይቻላል፡፡ በትምህርት ቤቶች (እስከ ከፍተኛ ትምህርት)፣ በሁሉም የሃይማኖት ተቋማት፣ በሁሉም የመገናኛ ብዙኃን፣ በሁሉም የፖለቲካ ፓርቲዎች፣ በኪነ ጥበባት መድረኮች፣ በቤተሰብ፣ በዕድሮች፣ በሠፈር ሳይቀር ከሌላው የፖለቲካ አጀንዳ ይልቅ ይህንን ዓብይ ጉዳይ በማስቀደም በተለይ በሕፃናትና በወጣቶች ላይ ሰፋፊ የአስተምህሮ ሥራዎች ቢሠሩ ምንኛ ውጤታማ በሆንን፡፡ የተወላገደን ወይም የጎበጠን አሠራር በማቃናት ብዙ ጉልበት ከማባከን ገና ከጅምሩ መሠረተ ሰፊ የሆነ ሥራ በማከናወን ጎባጣ ሥርዓት እንዳይፈጠር መከላከል ይሻላል፡፡

በቅርቡ መንግሥት የጀመረው ተመሳሳይ ባህሪ ያላቸውን ተቋማት አጣምሮ የማደራጀት ጥረት በእጅጉ የሚበረታታ ነው፡፡ ለውጡ ወደ ዴሞክራሲ ተቋማትም መዝለቅ አለበት፡፡ የዚህ ሐሳብ አቅራቢ በአንድ ወቅት (በዘመነ ቢፒአር) ቱባ ባለሥልጣናት በተገኙበት በተካሄደ የውይይት መድረክ ላይ ይኼንን ሐሳብ ፈንጥቆ ነበር፡፡ ሐሳቡ ያኔ ተቀባይነት አላገኘም፡፡ ዛሬ ግን በጉዳዩ ላይ በአደባባይ ወጥቶ በመገናኛ ብዙኃንም ጭምር መከራከርና መተማመን ላይ መድረስ የሚያስችል ዘመን መጥቷል፡፡ መንግሥት ሊታማ፣ ሊነቆር፣ ሊሽሟጠጥ፣ ምን ቸገረኝ ሊባል ሳይሆን ከልብ ሊታገዝ ይገባል፡፡ ሐሳቡም የቀረበው ከዚህ በመነጨ ወኔ ነው፡፡

ውድ አንባብያን! ሐሳቡ የዚህ አስተያየት አቅራቢ የራሱ ነው። ጸሐፊው ካነሳው ርዕሰ ጉዳይ ጋር ሰፊ ትስስር ያለው ሰው ነው፡፡ የብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ተቋማዊ አደረጃጀት ጥናት ግብረ ኃይል ሰብሳቢ በመሆን ሠርቷል፡፡ ከመሥሪያ ቤቱ መሥራቾችም አንዱ ነው፡፡ በኋላም በፓርላማው ተሹሞ በተቋሙ ውስጥ በከፍተኛ አመራር ደረጃ አገልግሏል፡፡ በሕዝብ ዕንባ ጠባቂ ተቋምም በአመራር (በማኔጅመንት) ደረጃ ቁልፍ ከሆኑት የተቋሙ የሥራ ዘርፎች አንደኛውን የመራ ነው፡፡ የተቋሙ ቢፒአር ሲጠናም የጎላ ሚና ነበረው፡፡ አገር አቀፉ የመረጃ ነፃነት አዋጅ ትግበራ ዝግጅት ግብረ ኃይል አባልና ጸሐፊ፣ የፌዴራል የፍትሕ አስተዳደር ማሻሻያ የቴክኒክ ኮሚቴ አባል፣ ወዘተ. ሆኖም ሠርቷል፡፡ በቆይታውም ወቅት ከፍ ብሎ የተጠቀሱት ሦስት ተቋማት እንዲዋሀዱ ሐሳቡን በግልጽ አቅርቧል፡፡ በ1991 ዓ.ም. መጨረሻ በአንድ የፓርላማ ስብሰባ ላይ ቀርቦ በምርጫ ቦርዱ ውስጥ ሙስናና ዝርክርክ አሠራር አለ ብሎ በማጋለጡ፣ በዚሁ ሪፖርተር ጋዜጣ ላይ ‹‹ፓርላማው ፓርላማ ሆኖ ዋለ›› ተብሎ የተጻፈለት ይህ ሰው መሆኑንም ላስታውሳችሁ፡፡

ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እየገለጽን፣ በኢሜይል አድራሻቸው   [email protected] ማግኘት ይቻላል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ሚዲያው በሕዝብ የህሊና ችሎት ከተዳኘ በቂ ነው!

መሰንበቻውን ድንገት ሳይታሰብ ያለ ማስጠንቀቂያ ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ...

የባህር በር ጉዳይ

በታምሩ ወንድም አገኘሁ ድሮ ድሮ ገና ልጅ ሆኜ ፊደል እንደቆጠርኩ...

አገሩ ፖለቲካዊ ስክነትና መደማማጥ ያስፈልገዋል

በንጉሥ ወዳጀነው    ኢትዮጵያ የሁላችንም የጋራ ቤት ነች፡፡ ‹‹ጥያቄዬ ተመለሰልኝ››፣...

የመንግሥት የሰብዓዊ መብት ተቋም ለምን የመንግሥት ሚዲያን ማስተማር አቃተው

በገነት ዓለሙ የአገራችን የ2016 የበጀት ዓመት መሰናበቻና የአዲሱ የ2017 በጀት...