Friday, June 14, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

ትራንሽን ማኑፋክቸሪንግ ከ100 ሚሊዮን ዶላር በላይ ያስገኙ የቴክኖ ሞባይል ስልኮችን ለውጭ ገበያ አቀረበ

spot_img

ተዛማጅ ፅሁፎች

በሆቴል ንግድ ሥራ ለመሠማራት እንቅስቃሴ ጀምሯል

በትራንሽን ማኑፋክቸሪንግ ኩባንያ ሥር የሚተዳደረው የቴክኖ ሞባይል፣ በኢትዮጵያ በገነባቸው ሁለት ፋብሪካዎች አማካይነት በወር ከአንድ ሚሊዮን በላይ ስልኮችን በመገጣጠም ለውጭ ገበያ በማቅረብ በአሁኑ ወቅት ከ100 ሚሊዮን ዶላር በላይ የውጭ ምንዛሪ ማስገኘቱን አስታውቋል፡፡ ካቻምና 60 ሚሊዮን ዶላር የውጭ ምንዛሪ ገቢ አስገኝቶ ነበር፡፡ እ.ኤ.አ. በ2018 መጨረሻ ሥራ እንደሚጀምር የሚጠበቀው ፋብሪካ፣ እስከ 300 ሚሊዮን ዶላር የሚገመት የውጭ ምንዛሪ ገቢ ለማስገኘት እንደሚያስቸለው መግለጹ አይዘነጋም፡፡

በኢትዮጵያ ሁለት ፋብሪካዎችን የገነባው ትራንሽን ማኑፋክቸሪንግ፣ በአሁኑ ወቅት ቴክኖ ሞባይልን ጨምሮ አይቴልና ኢነፊኒክስ የተሰኙ የሞባይል ብራንዶችን በኢትዮጵያ እየገጣጠመ ለአገር ውስጥም ለውጭ ገበያም በማቅረብ ላይ ይገኛል፡፡

ኩባንያው በሳምንቱ መጀመሪያ ባካሄደው ሥነ ሥርዓት፣ በኢትዮጵያ ትልቁን ፋብሪካ ለመትከል እየተንቀሳቀሰ ይገኛል፡፡ ይህ ፋብሪካ አይሲቲ ፓርክ በተሰኘውና ቦሌ ለሚ አካባቢ ከመሃል አዲስ አበባ 15 ኪሎ ሜትር ገደማ በሚርቀው የአይሲቲ መንደር በወር እስከ ሁለት ሚሊዮን ስልኮችን ለመገጣጠም የሚያስችለውን ማምረቻ እየገነባ ይገኛል፡፡ ከዚህ በተጨማሪም ሲኒክስ የተሰኘ የኤሌክትሮኒክስና ልዩ ልዩ የቤት ውስጥ መገልገያዎች አምራች ኩባንያም ቴክኖ ሞባይልን የተቀላቀሉ በመሆናቸው የኩባንያውን የገበያ ድርሻ ሰፊ አድርገውታል፡፡

ምንም እንኳ ቴክኖ ሞባይል በአፍሪካ ብሎም እያደጉ በሚገኙ የዓለም አገሮች ውስጥ ተፈላጊነቱ እየጨመረ ቢመጣም፣ በተለይ ባለፉት ስድስት ዓመታት ውስጥ በኢትዮጵያ ቆይታው ያሰበውን ያህል መጓዝ እንዳልቻለ የኩባንያው ኃላፊዎች ሲገልጹ ቆይተዋል፡፡ ዋነኛው ችግራቸው ደግሞ የውጭ ምንዛሪ እጦት ነው፡፡ በዚህ ሳቢያ ለበርካታ ጊዜያት ምርት ለማምረት ሲቸገር መቆየቱንም ሲገልጹ ከርመዋል፡፡ ይህንን ችግር ለመቅረፍ ይረዳው ዘንድ በሆቴል ንግድ ሥራ ውስጥ ለመሠማራት እንቅስቃሴ ስለመጀመሩም ታውቋል፡፡ የባለ አራት ኮከብ ሆቴሎችን በመገንባት በመጪዎቹ አምስት ዓመታት ውስጥ በርካታ ሆቴሎችን የመክፈት ዕቅድ ይዟል፡፡

ይሁንና በአፍሪካ ለገበያ ከሚቀርቡ አሥር ስልኮች ውስጥ ሦስቱ የትራንሽን ወይም የቴክኖ ሞባይል ሥሪቶች ስለመሆናቸው መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡ ኩባንያው የመካከኛው ምሥራቅ ገበያውን ጨምሮ ከ90 ሚሊዮን በላይ ስልኮችን በመሸጥ በአፍሪካም ከፍተኛውን የሽያጭ መጠን በማስመዝገብ ሦስተኛው ከፍተኛ የሽያጭ ባለድርሻ ሆኗል፡፡

 በአዲስ አበባ በ28 ሺሕ ካሬ ሜትር ቦታ ላይ በተገነባው ፋብሪካው በየወሩ ሁለት ሚሊዮን የተለያዩ ሞዴል ያላቸውን የሞባይል ስልኮች በመገጣጠም ለገበያ የማቅረብ አቅም አለው፡፡ በዓለም ከ240 ሚሊዮን በላይ የተለያዩ ስማርትና መደበኛ የስልክ ቀፎዎችን እንዲሁም ታብሌቶችን በማምረትና በመሸጥ የሚታወቀው ቴክኖ ሞባይል፣ እ.ኤ.አ. በ2017 ብቻ ከ120 ሚሊዮን በላይ ምርቶችን ለገበያ በማቅረብ መሸጡን አስታውቋል፡፡

በቻይና ሼንዜን ከተማ እ.ኤ.አ. በ2006 የተመሠረተውና በ2007 ማምረት የጀመረው  ቴክኖ ሞባይል፣ በአፍሪካ ኢትዮጵያን በማስቀደም ሁለት ፋብሪካዎችን በመክፈትና የሞባይል ስልኮችን በመገጣጠም ለአገር ውስጥና ለውጭ ገበያዎች ሲያቀርብ ቆይቷል፡፡

በወር በአንድ ፈረቃ ከአንድ ሚሊዮን በላይ ስልኮችን የመገጣጠም አቅም ባላቸው፣ በጎፋ አካባቢና በዓለም ገና ከተማ በገነባቸው ሁለት ፋብሪካዎች አማካይነት ለገበያ እያቀረበ እንደሚገኝ የኩባንያው ኃላፊዎች ለሪፖርተር መግለጻቸው ይታወሳል፡፡ በዓለም ገና እንዲሁም በጎፋ ካምፕ አካባቢ የተገነቡት ሁለቱ ፋብሪካዎች ከ2,000 በላይ የሥራ ዕድል በመፍጠር አስተዋጽኦ እንዳበረከቱም የኩባንያው ኃላፊዎች ይናገራሉ፡፡ በ2010 ዓ.ም. አፈጻጸሙ ገቢው ከ100 ሚሊዮን ዶላር ማደግ እንደቻለ ተጠቅሷል፡፡

ቴክኖ ሞባይል እስካሁን በኢትዮጵያ ከነበረው እንቅስቃሴ ይበልጥ በመስፋፋት በቦሌ ለሚ በሚገኘው የኢትዮ አይሲቲ ፓርክ ውስጥ ትልቅ ፋብሪካ በመገንባት ላይ ይገኛል፡፡ ይህ ፋብሪካ በወር ከሁለት ሚሊዮን በላይ ስልኮችን ለገበያ ማውጣት እንደሚችል ኩባንያው ይገልጻል፡፡ ከዚህም በተጨማሪ ለ4,000 ሠራተኞች የሥራ ዕድል ያስገኛል የተባለው አዲሱ ፋብሪካ፣ ወደ ጋና፣ ኮትዲቯር፣ ናይጄሪያ፣ ኬንያ፣ ኡጋንዳና ሌሎችም አገሮች ሲደረግ የቆየውን የ60 ሚሊዮን ዶላር የወጪ ንግድ ገቢ ወደ 300 ሚሊዮን ዶላር በማሳደግ ትልቅ ሚና እንደሚጫወት ተጠቅሷል፡፡

በኢትዮ አይሲቲ መንደር የሚገነባው የቴክኖ ሞባይል ፋብሪካ፣ በቻይና ከሚገኘው ፋብሪካ አኳያ ግዙፉ እንደሚሆን ሲጠበቅ፣ የቻይናው የማምረት አቅሙ ሦስት ሚሊዮን ስልኮችን እንደሚያመርት የኩባንያው መረጃ ያሳያል፡፡ በጎፋ ካምፕ አካባቢ የተገነባው የቴክኖ ሞባይል ፋብሪካ ከሰባት ዓመታት በፊት ሥራ የጀመረ ሲሆን፣ በወር 425 ሺሕ ስልኮችን ገጣጥሞ የማምረት አቅም ያለው ነው፡፡ ከሦስት ዓመት በፊት የተገነባው የዓለም ገናው ፋብሪካ በበኩሉ በወር 580 ሺሕ ስልኮችን የማምረት አቅም እንዳለው ለማወቅ ተችሏል፡፡

በኢትዮጵያ ከመገጣጠም ባሻገር በድኅረ ሽያጭ የጥገና አገልግሎት የሚሰጡ መደብሮችን የሚያንቀሳቅሰው ቴክኖ ሞባይል፣ በተለይ የሽያጭ መደብሮችን ከነጋዴዎች ጋር በሚደረግ ስምምነት መሠረት በሚሰጣቸው የችርቻሮ መሸጫ ዋጋ አማካይነት ለመደብሮች ምርቶቹን ያቀርባል፡፡

በኢትዮጵያ ከ100 በላይ የሽያጭ መደብሮች በፍራንቻይዝ መልክ የሚንቀሳቀሰው ስልክ አምራቹ ስታንዳርድ፣ ስታንዳርድ ኤክስክሉሲቭ፣ ሜጋ ኤክስክሉሲቭ እንዲሁም ፍላግሺፕ የሚባሉ ደረጃዎች ያሏቸውን መደብሮች ለመክፈት የሚስማሙ ነጋዴዎችን ሲያገኝ፣ የምርት ዓይነቶቹም እንደ መደብሮቹ ደረጃና አቅም የተለያየ መጠን እንደሚያቀርብ ይታወቃል፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች