Thursday, June 13, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

የአውሮፓ ኢንቨስትመንት ባንክ የ960 ሚሊዮን ብር ብድር ፈቀደ

spot_img

ተዛማጅ ፅሁፎች

ዴንማርክ ለአራት ዓመታት የሚውል የ4.2 ቢሊዮን ብር ዕርዳታ አቅርባለች

የአውሮፓ ኢንቨስትመንት ባንክ በረዥም ጊዜ ክፍያ የሚጠናቀቅና ዝቅተኛ ወለድ የሚታሰብበት የ960 ሚሊዮን ብር ወይም የ30 ሚሊዮን ዩሮ ብድር ለኢትዮጵያ ፈቅዷል፡፡

ሐሙስ ኅዳር 13 ቀን 2011 ዓ.ም. በተካሄደ ሥነ ሥርዓት የአውሮፓ ኢንቨስትመንት ባንክ ፕሬዚዳንት ቬርነር ሆየር (ዶ/ር)፣ ከገንዘብ ሚኒስትሩ አቶ አህመድ ሺዴ ጋር ተፈራርመዋል፡፡ ብድሩ ለሴቶች የሥራ ፈጠራ ልማት ፕሮግራም የሚውል ሲሆን፣ በሴቶች ለሚመሩና ለተመሠረቱ የግል ድርጅቶች ድጋፍ እንዲውል የሚታሰብ ነው፡፡

ባንኩ የሰጠው ብድር በከተማና በገጠር አካባቢ የሚኖሩ ሴቶች በጥቃቅንና አነስተኛ የንግድ ሥራ ዘርፎች ለመሰማራት ሲነሱ የሚገጥማቸውን የፋይናንስ ችግር ለመቀነስ ብሎም ገቢያቸውን ለማሳደግ የሚረዱ እንቅስቃሴዎችን ማከናወን ይቻላቸው ዘንድ ድጋፍ ማድረጉን ፕሬዚዳንቱ አስታውቀዋል፡፡ ከዚህ በተጨማሪም አዳዲስ ተበዳሪዎችም የፋይናንስ አቅርቦቱ ተቋዳሽ እንዲሆኑ ለማገዝም ብድሩ መለቀቁን፣ የገንዘብ ሚኒስቴር አስታውቋል፡፡

በዓለም ባንክ በኩል የሚተገበረው የሴቶች የሥራ ፈጣሪዎች ድጋፍ የሚሰጠው ፕሮግራም ይፋ ከተደረገ አምስት ዓመታት አስቆጥሯል፡፡ በዚህ ጊዜ ውስጥም ከአሥር ሺሕ በላይ ሴቶች በመንግሥትና በዓለም ባንክ ፋይናንስ ድጋፍ አማካይነት ተጠቃሚ መሆናቸውን የዓለም ባንክ መረጃ ይጠቁማል፡፡

ፕሮግራሙ ይፋ ከተደረገ ወዲህ በየወሩ የሁለት ሚሊዮን ዶላር አነስተኛ ብድር ለበርካታ የፕሮግራሙ ተጠቃሚዎች በማቅረብ ላይ እንደሚገኝ ሲገለጽ፣ ከሦስት ዓመታት በፊትም በፕሮግራሙ አማካይነት ከሦስት ሺሕ በላይ ሴቶች የብድር አገልግሎት ሲያገኙ፣ ከ4,500 ያላነሱት የንግድ ሥራ ሥልጠናዎችን ተከታትለዋል፡፡ እስካለፈው ዓመትም ሴቶች በወሰዱት ብድር አማካይነት ስድስት ሺሕ ያህል አዳዲስ የሥራ ዕድሎችን ስለመፍጠራቸውም ይነገራል፡፡

የአውሮፓ ኢንቨስትመንት የ30 ሚሊዮን ዩሮ ብድርን ሳይጨምር፣ የሴቶች የሥራ ፈጠራ ልማት ፕሮግራም ከዓለም አቀፉ የልማት ማኅበር በተገኘ 50 ሚሊዮን ዶላር ብድር፣ ከእንግሊዝና ከካናዳ በተገኘ የ13 ሚሊዮን ዶላር፣ ከአውሮፓ ኅብረት አገሮች በተገኘ ተጨማሪ 15 ሚሊዮን ዶላር እንዲሁም ከጃፓን መንግሥት ቃል በተገባ የ50 ሚሊዮን ዶላር ብድር የሚተገበር የሥራ ዕድል ልማት ፕሮግራም ነው፡፡

በተያያዘ የዴንማርክ መንግሥት የ995 ሚሊዮን ዳኒሽ ክሮን ወይም የ4.26 ቢሊዮን ብር የዕርዳታ ድጋፍ ማዕቀፍ ስምምነት ከመንግሥት ጋር ተፈራርሟል፡፡ ሐሙስ፣ ኅዳር 13 ቀን 2011 ዓ.ም. በገንዘብ ሚኒስቴር በተካሔደው የፊርማ ሥነ ሥርዓት አምባሳደር ካሪን ፖውልሰን ከሚኒስትር ዴኤታው አቶ አድማሱ ነበበ ጋር ስምምነቱን ተፈራርመዋል፡፡

እ.ኤ.አ. ከ2018 እስከ 2022 ለሚዘልቀው አገር አቀፍ የፕሮግራም ስምምነት ማስተግበሪያ ይውል ዘንድ ዴንማርክ የለገሰችው ይህ ዕርዳታ፣ በአብዛኛው በወጣቶችና በሴቶች ተሳትፎ ላይ በሚያተኩሩ የልማት ሥራዎች ላይ እንዲውል ስምምነት የተደረገበት የልማት ትብብር እንደሆነ ከዴንማርክ ኤምባሲ የተገኘው መረጃ ይጠቁማል፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች