Saturday, July 13, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

የመሠረተ ልማት ተቋማት በቅንጅት ባለመሥራታቸው የአገሪቱ ሀብት መባከኑ አሳስቧል

ተዛማጅ ፅሁፎች

በአገር አቀፍ ደረጃ የሚገኙ የመሠረት ልማት ተቋማት ተቀናጅተው እየሠሩ ባለመሆኑ የአገሪቱ ሀብት እየባከነ መሆኑ አሳሳቢ ሆኗል፡፡

የፌዴራል የተቀናጀ የመሠረተ ልማት ማስተባበሪያ ኤጀንሲ ዓርብ ኅዳር 13 ቀን 2011 ዓ.ም. የከተማ ልማትና ኮንስትራክሽን ሚኒስትሩ አቶ ጃንጥራር ዓባይ በተገኙበት በጉዳዩ ላይ ከመሠረተ ልማት ተቋማት ጋር መክሯል፡፡

አቶ ጃንጥራር በወቅቱ እንደተናገሩት፣ የመሠረተ ልማት አስፈጻሚ ተቋማት በፌዴራልም ሆነ በክልል ደረጃ የሚካሂዱ ቅንጅት የጎደላቸው ግንባታዎች የአገሪቱን ሀብት እየባከኑ ነው፡፡

በውይይቱ ወቅት እንደተገለጸው፣ አገራዊ የመሠረተ ልማት ማስተር ፕላን አለመኖር፣ ወጥነት ያለው የካሳ አከፋፈል ሥርዓት አለመኖር፣ አገራዊ የመሠረተ ልማት መረጃዎችን አደራጅቶ አለመያዝና ሲጠየቁም ለሚመለከታቸው አካላት ያለመስጠት፣ ሁሉም የመሠረተ ልማት ተቋማት ተቀናጅተው የሚገነቡ ባለመሆናቸው የአገሪቱን ሀብት፣ ጉልበትና ጊዜ ያላግባብ እየወደመ መሆኑ ተገልጿል፡፡

አዲስ አበባን ጨምሮ በመላ አገሪቱ የመንገድ፣ የባቡር፣ የቴሌኮም፣ የኃይል ማመንጫ፣ የውኃ ልማትና የአየር ትራንስፖርት አውታሮች ግንባታ እየተካሄደ ይገኛል፡፡

በግንባታ ሒደት አንዱ ተቋም ከሌለው ጋር ተቀናጅቶና ተናቦ እየሠራ ባለመሆኑ፣ አንዱ የገነባውን ሌላው እያፈረሰ አገሪቱ ብዙ ሀብት እያጣች መሆኑ ተመልክቷል፡፡

ከዚህም በተጨማሪም የመሠረተ ልማት ተቋማቱ ተናበው ባለመሥራታቸው የጥራት መጓደል፣ የአገልግሎት አሰጣጥ መጓተት፣ የሕዝብና የመንግሥት ሀብት ውድመት ምክንያት መሆናቸው፣ በተመሳሳይም በግንባታ ወቅት ከይዞታ መፈናቀልና ንብረት ጉዳት ተገቢ ካሳ የሚከፈልበት ወጥነት ያለው የአገማመት ቀመር አለመኖር፣ በመሠረተ ልማት ግንባታ አፈጻጸም ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ ከመፈጠሩ ባሻገር የመልካም አስተዳደር ችግር መፈጠሩ ተገልጿል፡፡

ሚኒስትሩ እንዳሉት፣ የካሳ ቀመር አዋጅ በፌዴራል ደረጃ ተግባራዊ እንዲሆን ለማድረግ ወደ ተግባር ተገብቷል፡፡

ባልተቀናጀ አሠራር እየባከነ ያለውን የአገር ሀብት ከብክነት ለማዳን ሁሉም አስፈጻሚ አካል በትኩረት ሊሠራ እንደሚገባ ሚኒስትሩ ማሳሰቢያ ሰጥተዋል፡፡

በኢትዮጵያ ሳይቆራረጡ በመካሄድ ላይ የሚገኙ የመሠረተ ልማት ግንባታዎች ተቀባይነት ቢያገኙም፣ በተያዘላቸው የጊዜ ገደብ የማይጠናቀቁ በመሆናቸው በኅብረተሰብ ቅሬታ ይቀርብላቸዋል፡፡ ከዚህ ባሻገርም የመንገድ፣ የኤሌክትሪክና የቴሌኮም አውታሮች ግንባታ እርስ በርሳቸው ስለማይናበቡ በተለይ በከተሞች ከፍተኛ ችግር እየፈጠሩ መሆናቸው በስፋት የሚታወቅ ነው፡፡

በዚህ ምክንያት ከፍተኛ የሀብት ብክነት እየደረሰ ከመሆኑም በተጨማሪ ማኅበራዊ ቀውስ እየተፈጠረ መሆኑ ይነገራል፡፡

በአዲስ አበባ ከተማ መንገዶች ግንባታ ላይ በተካሄደ ጥናት መሠረት በቅንጅት አለመኖር ብቻ በዓመት 300 ሚሊዮን ብር ይታጣል፡፡ በአጠቃላይ በአገሪቱ የመሠረተ ልማት ተቋማት ባለመናበባቸው ብቻ በዓመት ሦስት ቢሊዮን ብር እየባከነ መሆኑ በጥናት መታወቁ ተነግሯል፡፡

ይህን ችግር ለመፍታት መንግሥት የፌዴራል የተቀናጀ የመሠረተ ልማቶች ማስተባበሪያ ኤጀንሲ የተሰኘ ተቋም አቃቁሟል፡፡

ይህ ተቋም ከተመሠረተ በኋላ የመሠረተ ልማት ተቋማት ተቀናጅተው እንዲሠሩ ለማድረግ በ2009 ዓ.ም. የመናበቢያ ስምምነት የተፈራረመ ቢሆንም፣ ለውጥ አለመታየቱ አሁንም እየተገለጸ ነው፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች