Sunday, September 24, 2023
- Advertisment -
- Advertisment -

የፖለቲካ ምኅዳሩ የሚሰፋው መደማመጥ ሲኖር ነው!

በኢትዮጵያ ፖለቲካ ውስጥ ትልቁ ችግር ለመነጋገርና ለመደማመጥ አለመፈላለግ ነው፡፡ ይህ ለዓመታት የዘለቀ ችግር ከበፊቱ የተሻለ አመቺ ሁኔታ ቢፈጠርለትም፣ አሁንም መተማመን ስለሌለ የጎሪጥ መተያየት ይስተዋላል፡፡ ባለመነጋገርና ባለመደማመጥ ምክንያት የፖለቲካ ምኅዳሩ የጉልበተኞች መጫወቻ ከመሆኑም በላይ፣ ለአገር ጠቃሚ አስተዋፅኦ የነበራቸው በርካታ ልሂቃን ለእስርና ለስደት ተዳርገዋል፡፡ ይህ ሁሉ አልፎ አሁን የመነጋገርና የመደማመጥ ምዕራፍ እየተጀመረ ቢሆንም፣ በሰበብ በአስባቡ ትከሻ መለካካትና በነገር መቋሰል አለ፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) ስደት ላይ የነበሩና የትጥቅ ትግል ያካሂዱ የነበሩ የፖለቲካ ድርጅቶችን ወደ አገር ቤት እንዲመለሱ ከማድረግ በተጨማሪ፣ የፖለቲካ ምኅዳሩ የበለጠ ሰፍቶ መፎካከር የሚቻልበትን ዕድል እንዲመቻች በርካታ ዕርምጃዎችን ወስደዋል፡፡ ለዓመታት የሕዝብ አመኔታ ያጣውን ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ በብዙዎች ዘንድ ተቀባይነት ያላቸውን ሰብሳቢ ሾመውለታል፡፡ ከፖለቲካ ፓርቲዎቹ አመራሮች ጋርም በመጪው ምርጫ ላይ ውይይት አድርገዋል፡፡ ምርጫ ቦርድም ተከታታይ ውይይቶችን እያዘጋጀ በአጀንዳዎች ላይ ለመነጋገር ቀጠሮ ተይዟል፡፡ ካሁን በኋላ ከመነጋገርና ከመደራደር ውጪ ሌላ አማራጭ ሊኖር አይገባም፡፡

ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት የሚገነባው የዴሞክራሲ ጽንሰ ሐሳብ በገባቸው ፖለቲከኞች እንጂ፣ በደመነፍስ በሚመሩ ግለሰቦች ወይም ስብስቦች አይደለም፡፡ የአገሪቱ ፖለቲካ በተለይ ለግማሽ ክፍለ ዘመን ያህል የመጠማመድና እርስ በርስ የመባላት አባዜ ውስጥ በመቆየቱ፣ ለሰላማዊና ለዴሞክራሲያዊ ትግል የተመቸ አልነበረም፡፡ የተሻሉ ሐሳቦችን ለማግኘት የንግግርና የጽሑፍ ነፃነትን ከማበረታታት ይልቅ፣ ለፍረጃና ለማግለል የቀረበ በመሆኑ ብዙዎች ተሸማቀዋል፡፡ ልዩነትን አስታርቆ የጋራ አጀንዳዎች ላይ በማተኮር የሠለጠነ እንቅስቃሴ ለማድረግ ጊዜው አሁን ነው፡፡ ይህ ወቅት እንደ መልካም አጋጣሚ ተወስዶ በጋራ ጥረት የፖለቲካ ምኅዳሩን ለማስፋት መነሳት ይገባል፡፡ እንደተለመደው የመጠላለፍ አባዜ ውስጥ ተገብቶ ሒደቱን ማበላሸት ችግር ውስጥ ይከታል፡፡ ነገሮች አንዴ ከተበላሹ ደግሞ ለመመለስ ያስቸግራል፡፡ የዓመታት ክፉ ልምድም ይኼው ነው፡፡

አሁን እንደሚታየው ከ80 በላይ ፓርቲዎች በምርጫ ለመወዳደር ከሚቀርቡ ይልቅ፣ በተቻለ መጠን የሚመሳሰሉት እየተዋሀዱ ወይም ግንባር እየፈጠሩ ቁጥራቸውን በጣም መቀነስ አለባቸው፡፡ ለምርጫ የሚደረገው ዝግጅት አይበቃም ቢባል እንኳ በጋራ የመወያያ መድረኩ ላይ በሚገባ በመነጋገር ለተወሰነ ጊዜ እንዲራዘም ለማድረግ መሞከር፣ ካልሆነም በተያዘው የጊዜ ሰሌዳ ውስጥ ጣጣን ጨርሶ መገኘት ሊታሰብበት ይገባል፡፡ አሁን ባላቸው ቁመና መቀጠል የሚፈልጉ ካሉም ለሕዝብ ይዘው የሚቀርቡት ሐሳብ ወሳኝ መሆኑን መገንዘብ ይኖርባቸዋል፡፡ ሕዝብ ችግሮቹን ከሥር መሠረታቸው ተረድቶ መፍትሔ የሚሰጠው ፓርቲ የሚፈልግ ሲሆን፣ ፓርቲዎቹም በዚህ ፍላጎት ልክ መገኘታቸውን ማረጋገጥ አለባቸው፡፡ ከዚህ ቀደም ይደረግ እንደነበረው በነበረ ስምና ዝና ሕዝብ ፊት መቅረብ አይቻልም፡፡ ትውልዱ ጠያቂና ሞጋች ስለሆነ የኋላ ታሪክን ጭምር ያያል፡፡ በዚህ መሠረት በመንቀሳቀስ ጠንካራና የሕዝብ አመኔታ ያለው ፓርቲ ሆኖ መገኘት የግድ ነው፡፡ ይህ ካልሆነ ግን ከአጃቢነት ውጪ የትም መድረስ አይቻልም፡፡

በሌላ በኩል የሕዝብ ድምፅ የማግኘት ጥርጣሬ ያላቸው ደግሞ ሰላማዊውን የፖለቲካ ድባብ እንዳያበላሹት ያሠጋል፡፡ ለዚህ ደግሞ ምልክቶች አሉ፡፡ በአገር ውስጥም ሆነ በውጭ በሕዝብ ዘንድ ተቀባይነት የሌላቸው ፓርቲዎች በግለሰቦች ተክለ ሰውነት ላይ የተንጠለጠሉ ወይም የግለሰቦች መጦሪያ ስለሆኑ፣ ለሰላማዊ የፖለቲካ ትግሉ እንቅፋት ናቸው፡፡ የፖለቲካ ምኅዳሩን ለማስፋት በሚደረጉ ጥረቶች ፋይዳ ስለሌላቸው፣ የሌሎች የፖለቲካ መሣሪያ በመሆን ዴሞክራሲያዊ ሒደቱን ያደናቅፋሉ፡፡ እንዲህ ዓይነቶቹን በሕጋዊና በሰላማዊ መንገድ መታገል ይገባል፡፡ ለዚህ ደግሞ አብዛኞቹ የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ኃላፊነት አለባቸው፡፡ መጪው ምርጫ ነፃ፣ ዴሞክራሲያዊና ፍትሐዊ መሆን የሚችለው ለሁሉም ወገኖች የተመቻቸ የመወዳደሪያ ሜዳ ሲኖር ብቻ ነው፡፡ ከአምባገነናዊ አገዛዝ ወደ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታ መሸጋገር የሚቻለው፣ ለሰላማዊ የፖለቲካ ትግል ልዩ ትኩረት ሲሰጥ ነው፡፡ ዴሞክራሲያዊ የፖለቲካ ምኅዳር እንዲፈጠር ሁሉም የፖለቲካ ፓርቲዎች በኃላፊነት መንፈስ በጋራ መሥራት ይጠበቅባቸዋል፡፡

‹‹ብልሆች ከሌሎች ስህተት ይማራሉ፣ ሞኞች ግን ከራሳቸውም አይማሩም፤›› እንደሚባለው፣ ትናንት የተሠሩ ስህተቶችን መድገም ሕዝብና አገርን ለመከራ መዳረግ ነው፡፡ ኢትዮጵያ የሚያስፈልጋት ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ነው፡፡ ይህ ሥርዓት የሚገነባው ሁሉም የፖለቲካ ድርጅቶች ለዴሞክራሲያዊ መርሆች ሲገዙ ነው፡፡ እነዚህ መርሆች ከብጥብጥና ከአመፃ ጋር ግንኙነት የላቸውም፡፡ ለሴራና ለአሻጥር ሥፍራ የላቸውም፡፡ ጉልበትና ሕገወጥነትን ለማስተናገድ አይቻላቸውም፡፡ በኢትዮጵያ ፖለቲካ ውስጥ የሰለቹና የጠነዙ ነገሮች ለመነጋገርና ለመደማመጥ ጀርባ መሰጣጣት ናቸው፡፡ ተፎካካሪን አምርሮ መጥላትና ለማጥፋት መነሳት ኋላቀርነት ነው፡፡ ዴሞክራሲ በሰጥቶ መቀበል መርህ የሚመራ ነው ሲባል፣ ለሐሳብ ልዕልና ክብደት መስጠት ማለት ነው፡፡ የፖለቲካ ምኅዳሩ ሰፍቶ የመወዳደሪያ ሜዳው ምቹ መሆን የሚችለው ከአጉል ድርጊቶች መታቀብ ሲቻል ነው፡፡ ለዚህ ደግሞ ለሕግ የበላይነት መገዛት ተገቢ ነው፡፡ የፖለቲካ ፓርቲዎች በሙሉ ከጥላቻና ከቂም በቀል ፀድተው ለመጪው ምርጫ መዘጋጀት የሚችሉት፣ በመርህ ሲመሩ ነው፡፡ በመርህ መመራት ኢትዮጵያንና ሕዝቧን ማዕከል ያደረገ አጀንዳ ለመሰነቅ ከማስቻሉም በላይ፣ ጠንካራ ተፎካካሪ ያደርጋል፡፡ የፖለቲካ ፓርቲዎች ሆይ እባካችሁ ተነጋገሩ፣ ተደማመጡ፣ ተደራደሩ፡፡ ሥልጡን ፖለቲካ አራምዱ፡፡ የፖለቲካ ምኅዳሩ የሚሰፋው በዚህ መንገድ ብቻ ነው!

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

- Advertisment -

ትኩስ ፅሁፎች

በቀይ ባህር ፖለቲካ ላይ በመከረው የመጀመሪያ ጉባዔ ለዲፕሎማቲክና ለትብብር አማራጮች ትኩረት እንዲሰጥ ጥሪ ቀረበ

ሰሞኑን በአዲስ አበባ ለመጀመርያ ጊዜ በቀይ ባህር ቀጣና የፀጥታ...

የቤት ባለንብረቶች የሚከፍሉትን ዓመታዊ የንብረት ታክስ የሚተምን ረቂቅ አዋጅ ተዘጋጀ

በአዋጁ መሥፈርት መሠረት የክልልና የከተማ አስተዳደሮች የንብረት ታክስ መጠን...

እንደ ንብረት ታክስ ያሉ ወጪን የሚያስከትሉ አዋጆች ከማኅበረሰብ ጋር ምክክርን ይሻሉ!

የመንግሥትን ገቢ በማሳደግ ረገድ አስተዋጽኦ እንዳላቸው የሚታመኑት የተጨማሪ እሴት...

ለዓለምም ለኢትዮጵያም ሰላም እንታገል

በበቀለ ሹሜ ያለፉት ሁለት የዓለም ጦርነቶች በአያሌው የኃያል ነን ባይ...

የመጀመርያ ምዕራፉ የተጠናቀቀው አዲስ አበባ ስታዲየም የሳር ተከላው እንደገና ሊከናወን መሆኑ ተሰማ

እስካሁን የሳር ተከላውን ጨምሮ 43 ሚሊዮን ብር ወጪ ተደርጓል ዕድሳቱ...
spot_img

ተዛማጅ ፅሁፎች

በአገር ጉዳይ የሚያስቆጩ ነገሮች እየበዙ ነው!

በአሁኑም ሆነ በመጪው ትውልድ ዕጣ ፈንታ ላይ እየደረሱ ያሉ ጥፋቶች በፍጥነት ካልታረሙ፣ የአገር ህልውና እጅግ አደገኛ ቅርቃር ውስጥ ይገባና መውጫው ከሚታሰበው በላይ ከባድ መሆኑ...

የትምህርት ጥራት የሚረጋገጠው የፖለቲካ ጣልቃ ገብነት ሲወገድ ነው!

ወጣቶቻችን የክረምቱን ወቅት በእረፍት፣ በማጠናከሪያ ትምህርት፣ በበጎ ፈቃድ ሰብዓዊ አገልግሎትና በልዩ ልዩ ክንውኖች አሳልፈው ወደ ትምህርት ገበታቸው እየተመለሱ ነው፡፡ በአዲስ አበባ ከተማ ሰኞ መስከረም...

ዘመኑን የሚመጥን ሐሳብና ተግባር ላይ ይተኮር!

ኢትዮጵያ በአዲሱ ዓመት ዋዜማ ሁለት ታላላቅ ክስተቶች ተስተናግደውባት ነበር፡፡ አንደኛው የታላቁ ህዳሴ ግድብ አራተኛ የውኃ ሙሌት ሲሆን፣ ሁለተኛው ኢትዮ ቴሌኮም በአዲስ አበባ ከተማ ያስጀመረው...