የጦር ኃይሎች ጠቅላይ አዛዥ ጄኔራሎችን ከሥራ የማሰናበት ሥልጣን እንዲኖረው በረቂቁ ተካቷል
በአገር መከላከያ ሠራዊቱ ውስጥ ከምድርና ከአየር ኃይል በተጨማሪ፣ የባህር ኃይልና የልዩ ዘመቻ ኃይል መደበኛ የሠራዊቱ ኃይሎች ሆነው እንዲደራጁ የሚያስችል ረቂቅ አዋጅ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ቀረበ።
ሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ማክሰኞ ኅዳር 18 ቀን 2011 ዓ.ም. ባካሄደው ስብሰባ የመከላከያ ሠራዊት ማሻሻያ ረቂቅ አዋጅ የቀረበለት ሲሆን፣ ረቂቅ ሰነዱ በሥራ ላይ በሚገኘው የመከላከያ ሠራዊት ማቋቋሚያ አዋጅ ላይ ከ28 በላይ አንቀጾች እንዲሻሻሉ ይጠይቃል።
በዋናነትም በሥራ ላይ በሚገኘው አዋጅ መሠረት ከተደራጁት የምድርና የአየር ኃይሎች በተጨማሪ፣ የባህር ኃይልና የልዩ ዘመቻ ኃይል የመደበኛ ሠራዊት ተጨማሪ አደረጃጀቶች እንዲሆኑ በረቂቅ የሕግ ሰነዱ ተካቶ ቀርቧል።
እንዳስፈላጊነቱም የሕዋና የሳይበር ኃይሎች ሊካተቱ እንደሚችል በረቂቁ የሕግ ሰነድ በማሻሻያነት ቀርቧል።
ከዚህ ቀደም ከሠራዊቱ አባላት ብቻ ይደረግ የነበረው የመኰንኖች ምልመላ፣ ሠራዊቱን ከማዘመን አንፃር እክል ሊፈጥር የሚችል በመሆኑና የተሻለ ዝግጅት ባላቸው ወጣቶች ሠራዊቱን ለመገንባት በቀጥታ ከሲቪል ለመመልመል እንዲቻል በማሻሻያነት ቀርቧል።
በሥራ ላይ የሚገኘው አዋጅ ከጡረታ መውጫ ዕድሜ በፊት በአሠራርና በማሻሻያ ለውጥ ወይም በአቅም ማነስ ምክንያት፣ ጄኔራል መኰንኖችን ከውትድርና አገልግሎት የማሰናበት ሥልጣን የሚሰጠው በጦር ኃይሎች ጠቅላይ ኤታ ማዥር ሹሙ አቅራቢነት ለአዛዦች ካውንስል ሲሆን፣ በቀረበው ማሻሻያ ጄኔራል መኰንኖችን የማሰናበት ሥልጣን የጦር ኃይሎች ጠቅላይ አዛዥ ወይም ጠቅላይ ሚኒስትሩ እንዲሆን ተካቷል።
ከአገልግሎት ዘመን ጋር በተያያዘም ከተራ ወታደር እስከ ከፍተኛ ማዕረግ መሻሻሎች እንዲደረጉ በረቂቁ ተካቷል።
በተጨማሪም ከዚህ ቀደም የሠራዊት አባላት ወደ መንግሥት የልማት ድርጅቶች ብቻ ያደርጉት የነበረው ዝውውር፣ ወደ ማንኛውም የመንግሥት መሥሪያ ቤቶች እንዲያደርጉ የሚያስችል ሊሆን እንደሚችል በማሻሻያነት ቀርቧል።
አንዳንድ የምክር ቤት አባላት የባህር ኃይል አደረጃጀት በማሻሻያ መቅረቡ፣ ከአገሪቱ የባህር በር የሌላት ከመሆኑ ጋር ተያይዞ ሊተገበር የማይችል ስለሆነ አስፈላጊነቱ እንዲመረመር ጠይቀዋል።
የወታደራዊ ፍርድ ቤት ሥልጣን ልቅ መሆኑ፣ ከአገር ደኅንነት ጋር የተያያዙ ከፍተኛ ሚስጥሮችን በተመለከተ፣ እንዲሁም ከመከላከያ ከግዥና ንብረት አስተዳደር ጋር በተያያዘ በሚስተዋሉ ክፍተቶች ላይ ተጨማሪ ምርመራ በቋሚ ኮሚቴ እንዲደረግ ተጠይቋል።
ምክር ቤቱም የቀረበውን የመከላከያ ሠራዊት ረቂቅ አዋጅ ለዝርዝር ዕይታ ለውጭ ግንኙነትና ሰላም ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ መርቶታል።