ማክሰኞ ኅዳር 18 ቀን 2011 ዓ.ም. ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) ከፖለቲካ ፓርቲዎች አመራሮች ጋር በአገሪቱ ስለተጀመረው ለውጥ፣ እንዲሁም በመጪው ዓመት ስለሚደረገው ምርጫ አስመልክቶ ተወያዩ፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትሩ የተወያዩት ጥሪ ከተደረገላቸው የ80 ፖለቲካ ፓርቲዎች አመራሮች ጋር ነው፡፡
ለውይይት የመነሻ ሐሳብ ያቀረቡት ጠቅላይ ሚኒስትሩ አገሪቱ አሁን ካለችበት የለውጥ ሒደት፣ በመጪው ምርጫ እንዲሁም ድኅረ ምርጫ ወቅት በአገሪቱ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ከመገንባት አንፃር ሊከናወኑ ይገባል ያሏቸውን ዓበይት ነጥቦች በሦስት ምዕራፎች በመክፈል ይፋ አድርገዋል፡፡
የመጀመርያው ምዕራፍ የውይይቱ መክፈቻ መሆኑን በመጥቀስ፣ በዚህ ምዕራፍም በቀጣይ የሚካሄዱ የፖለቲካ ፓርቲዎች ውይይት ምን ዓይነት መልክ ይኑረው በሚለው ሐሳብ ላይ ተወያይቶ ቀጣይ ውይይቶችን የሚመራ መመርያ ማዘጋጀትን እንደሚያካትት ገልጸዋል፡፡
ከዚህ በተጨማሪም ሁሉም የፖለቲካ ፓርቲዎች በውይይቱ ላይ እንዲሳተፉ ማድረግ፣ በአጭር በመካከለኛና በረዥም ጊዜ መፍትሔ ሊበጅላቸው የሚገቡ ችግሮችን መለየት፣ ከዚህ ቀደም ሲደረጉ በነበሩ ውይይቶች ያጋጠሙ ችግሮችን መለየትና መፍትሔ ማስቀመጥ የሚሉት ነጥቦችም ተካተዋል፡፡
ሁለተኛው ምዕራፍ ደግሞ ዋነኛ ትኩረቱን በመጪው ዓመት በሚካሄደው ምርጫ ላይ ትኩረቱን በማድረግ ምርጫው ነፃ፣ ተዓማኒና ፍትሐዊ መሆኑን ለማረጋገጥ የሚከናወኑ ሥራዎችን በተመለከተ አቅጣጫ የሚቀመጥበት እንደሆነ ነው የገለጹት፡፡
በዚህኛው የውይይት ምዕራፍ ደግሞ በዋነኛነት በምርጫ ሕጉ፣ በምርጫ ቦርድ ስያሜና አቅም ላይ የሚያጠነጥን ሲሆን፣ ከእነዚህ ከሕግና ከአሠራር ጉዳዮች በተጨማሪም በቅርቡ ወደ አገር ቤት የተመለሱ የፖለቲካ ቡድኖችን ምዝገባ በተመለከተ በጋራ መሥራት የሚሉ ሐሳቦች መካተታቸውን አስረድተዋል፡፡
ሦስተኛው የውይይት ምዕራፍ ደግሞ ከምርጫ በኋላ የሚከናወኑ ተግባራት ላይ ማተኮሩን ጠቅላይ ሚኒስትሩ አስታውቀዋል፡፡
ከዚህ በተጨማሪም የመገናኛ ብዙኃንን በተመለከተ ውይይት እንደሚደረግ ጠቁመው፣ የመገናኛ ብዙኃኑ በአጠቃላይ ሕጋዊ ሆነው እንዲሠሩ ሁሉም የሚመለከተው አካል ተወያይቶበት የመገናኛ ብዙኃን አዋጁን መለወጥ እንደሚያስፈልግም አስታውቀዋል፡፡
ምንም እንኳን ጠቅላይ ሚኒስትሩ እነዚህን ጉዳዮች በተመለከተ ከተወያዮቹ አስተያየትና ምላሽ የጠበቁ ቢሆንም፣ በመድረኩ የተገኙ አብዛኞዎቹ የፖለቲካ አመራሮች ግን ከእነዚህ መሠረታዊ የመወያያ ነጥቦች በመውጣት በሌሎች አስተዳደራዊ ጉዳዮች ላይ አስተያየት በመስጠት ተጠምደው ነበር፡፡
ለአብነት ያህልም የፖለቲካ አመራሮቹ ምርጫው መራዘም የለበትም፣ ከምርጫ በፊት መደማመጥ አለብን፣ ‹ከምርጫው በፊት ሕገ መንግሥቱ መሻሻል አለበት፣ የፖለቲካ ፓርቲዎች ከመበታተን ወደ ሦስትና አራት በመምጣት መጠንከር ይገባናል› የሚሉ ጥያቄዎችን አቅርበዋል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከፖለቲካ ፓርቲ አመራሮቹ የቀረቡትን የተበታተኑ ጥያቄዎች አድምጠው በመጀመርያ ውይይቱ የሚመራበትን ሥርዓት መዘርጋት አስፈላጊ መሆኑን በመጥቀስ፣ ይኼንን ለማድረግም ምርጫ ቦርድ ኃላፊነቱን ወስዶ ጥያቄዎቹን በማቀናጀት እንዲያቀርብና ቀጣይ የውይይት ሒደቶችም ምርጫ ቦርድ በሚያስቀምጠው የውይይት መመርያ ሥርዓት መሆን እንደሚኖርበት ገልጸዋል፡፡
ከፓርቲዎች ቁጥር መበራከት ጋር ጠቅላይ ሚኒስትሩም ፓርቲዎች ሰብሰብ ቢሉ ለሁሉም ጠቃሚ መሆኑን በማውሳት ‹‹በውሳኔ ሦስት ሁኑ አልልም፡፡ ሦስት አራት ብትሆኑ ግን በግሌም እንደ ድርጅትም ከፍተኛ ድጋፍ ሊደረግላችሁ እንደሚችል አረጋግጥላችኋለሁ፡፡ ሦስት አራት ሆናችሁ ብትጠናከሩ ሐሳብ ለመለዋወጥ ከፍተኛ ጥቅም አለው፤›› በማለት፣ ፓርቲዎች ቢሰባሰቡ ለራሳቸውም ለአገርም የሚጠቅም ሥራ ሊያከናውኑ እንደሚችሉ አሳስበዋል፡፡
የውይይቱን መጠናቀቅ ተከትሎ ለተለያዩ መገናኛ ብዙኃን አስተያየታቸውን የሰጡት የግንቦት 7 ሊቀመንበር ብርሃኑ ነጋ ፕሮፌሰር፣ የፖለቲካ ኃይሎች ተሰባስበው መረዳዳት መፍጠራቸው ለመንግሥት ትልቅ ዕርዳታ ሊሆን እንደሚችል ገልጸዋል፡፡
በተለይም በመጀመርያው ምዕራፍ የቀረበው ሐሳብ መልካም እንደሆነ ጠቁመው፣ ‹‹የምናስበው ዓይነት የፖለቲካ ሥርዓት እንዲቋቋም ከፈለግንና ሐሳቦች በነፃነት እንዲንሸራሸሩ ከተፈለገ፣ መጀመርያ የሰላምና የመረጋጋት ሒደት በደንብ ጠንካራ መሠረት ላይ መቆም አለበት፡፡ ይኼንን ደግሞ መንግሥት ሕግ አስከባሪ ስለሆነና የፀጥታ ኃይሎች ስላሉት የሚያደርገው ብቻ ሳይሆን፣ የፖለቲካ ድርጅቶች ተስማምተው ከአሁን በኋላ ፖለቲካችን የሚቀየረው በዚህ መልኩ ነው ብለው ማድረጋቸው አስፈላጊ የሆነ የመጀመርያ ደረጃ የውይይት ውጤት እንዲሆን እንደሚፈልጉ ያሳዩበት ነው፡፡ እኔም ሙሉ ለሙሉ ነው በዚህ የምስማማው፤›› በማለት፣ ጠቅላይ ሚኒስትሩ በመጀመርያ ምዕራፍ የዘረዘሯቸው ጉዳዮች አስፈላጊና ዋነኛ መሆናቸውን አስረድተዋል፡፡
በተጨማሪም ከዚህ በኋላ ሥራው በዋነኛነት የፖለቲካ ድርጅቶች እንደሆነ በመጥቀስ፣ ‹‹እኔ ምን አገኛለሁ? እኔ ምን እጠቀማለሁ? ከዚህ ምን አተርፋለሁ? ከሚል ነገር ሳይሆን ከዚያ ወጣ ባለ መልኩ እንዴት ነው እውነተኛ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት የምንገነባው? እንዴት ነው የአገር ኃላፊነት ወስደን አገርን እስካሁን ከነበርንበት መዓት አውጥተን ወደ ተረጋጋ ቦታ የምንወስደው የሚለውን በኃላፊነት ስሜት መወያየት ከቻልን ምናልባት ይህች አገር ከመጣባት መዓት ትድናለች ብዬ ተስፋ አደርጋለሁ፤›› በማለት፣ ቀጣይ ውይይት ከፖለቲካና ከግል ጥቅም ይልቅ አገርን የማዳን እንዲሆን ጠይቀዋል፡፡
በመጨረሻም ጠቅላይ ሚኒስትሩ የፖለቲካ ፓርቲ አመራሮቹ አሉን የሚሏቸውን ጥያቄዎች በመዘርዘር ለምርጫ ቦርድ እንዲያስገቡ፣ ምርጫ ቦርድም የቀረቡለትን ጥያቄዎች በፈርጅ በፈርጁ በማዘጋጀት በቀጣይ የውይይት መድረክ በማቅረብ አጀንዳ በመቅረፅ የመወያያ ሥርዓት እንዲያቀርብ የቤት ሥራ በመስጠት የግማሽ ቀኑ ውይይት ተቋጭቷል፡፡