ብዙዎች የፖለቲካ ብስለት የላቸውም ሲሉ የሚተቿቸው የአሜሪካ ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ ‹‹አሜሪካ ፈርስት›› [አሜሪካ ትቅደም] በሚል መፈክራቸው ይታወቃሉ፡፡ የአሜሪካን የሚዲያ ተቋም ደጋፊ (እንደ ፎክስ አውስ ያሉት) እና ተቃዋሚ (ሲኤንኤን የመሳሰሉት) በሚል በሁለት ጎራ እስከ መክፈል ያደረሰ፣ የፖለቲካ አመራሩን ብዙዎች ያልተገባ ሲሉ 24 ሰዓታት በትችት ቢያጣድፉትም፣ አመራሩ አሜሪካ በዓለም ላይ ያላትን ልዕልና ያሳጣታል ቢባልም አሁንም ‹‹አሜሪካ ፈርስት›› እያለ ነው፡፡ ብሪታንያ ከአውሮፓ ኅብረት መፋታትም በሁለቱ አገሮች መካከል ያለውን የንግድ ግንኙነት ይጎዳል ያለውም አሜሪካ ፈርስት በሚል መርሁ ነው፡፡
28 የአውሮፓ አገሮች አባል ከሆኑበት የአውሮፓ የኢኮኖሚና ፖለቲካ ጥምረት ብሪታኒያ ስትወጣ ከሌሎች አባል አገሮች ጋር የሚኖራት የንግድ ትስስር እንደ ቀድሞው እንደማይሆን ነው፡፡ የቢቢሲ ዘገባ እንደሚያሳየውም፣ ፕሬዚዳንት ትራምፕ ብሪታኒያ ከአሜሪካ ጋር ነፃ የንግድ ስምምነት መፈጸም እንዳትችል የሚያደርጋት ይሆናል ማለታቸውን ነው፡፡
የብሪታኒያ ወግ አጥባቂ ፓርቲ አባሉ ዴቪድ ሮይ ፕሬዚዳንት ትራምፕ ለሰጡት አስተያየት አፀፋቸውን ‹‹ያልተጠበቀ አይደለም፡፡ ከአሜሪካ ጋር በንግድ ጉዳይ መደራደር ሁሌም ፈታኝ ነው፤›› በማለት የፕሬዚዳንቱ አስተያየት ከተለመደው የተለየ አለመሆኑን ተናግረዋል፡፡
‹‹አሜሪካ ከባድ ተዳራዳሪነት ነች፡፡ ፕሬዚዳንት ትራምፕ ሁሌም በግልጽ ‹ቅድሚያ የምሰጠው የአሜሪካ ጥቅምን ለማስጠበቅ ነው› ይላሉ፡፡ እኔም የብሪታኒያ ጠቅላይ ሚኒስትር ቅድሚያ ለብሪታኒያ ጥቅም እንደሚሰጡ እጠብቃለሁ፤› ብለዋል፡፡
አስተያየቶቹ የተሰነዘሩት የብሪታኒያ ጠቅላይ ሚኒስትር ቴሬሳ ሜይ በፓርላማቸው ያሰሙትን ንግግር ተከትሎ የምክር ቤት አባላቱ የፍቺ ረቂቁን በሞገቱበት ወቅት ነበር፡፡ ቴሬሳ ሜይ ብሪታኒያ ከአውሮፓ ኅብረት አባልነት ለመውጣት ያዘጋጀችውን የብሪግዚት ውል ረቂቅ ከሳምንታት በፊት ለምክር ቤቱ አቅርበው ነበር፡፡ ይህ ውል ብሪታኒያ ከኅብረቱ ከመውጣቷ በፊት መፅደቅ ይኖርበታል፡፡ ከካቢኔ አባላት ጋር ሰዓታት ከፈጀ ውይይት በኋላ ከቀናት በፊት ድጋፍ አግኝተዋል፡፡ ይሁን እንጂ አራት የብሪታኒያ ሚኒስትሮች ጠቅላይ ሚኒስትሯ ያቀረቡትን ረቂቅ በመቃወም በፈቃዳቸው ከሥልጣናቸው መልቀቃቸውም ውጥረት ውስጥ ላሉት ቴሬሳ ሜይ ተጨማሪ ጫና ፈጥሯል፡፡ የብሪታኒያ ሚኒስትር የነበሩት ዶሚኒ ራብ ሥራቸውን ከለቀቁት መካከል አንዱ ናቸው፡፡
ብሪታኒያ ከአውሮፓ ኅብረት ለመውጣት ያቀረበችው ሐሳብ ጁን 23 ቀን 2016 በተካሄደው ውሳኔ ሕዝብ 51.9 በመቶ ለ48.1 በመቶ በሆነ ድምፅ ነበር ተቀባይነትን ያገኘው፡፡ በዚህ ውሳኔ ሕዝብ ላይ 30 ሚሊዮን ዜጎች ድምፅ ሰጥተዋል፡፡ ብሪታኒያ የአውሮፓ ኅብረትን የምትለቀው የሊዝቦን ቃል ኪዳን አንቀጽ 50 ላይ የተቀመጠው ሕግ መሠረት አድርጋ ነው፡፡ አንቀጹ ሁለት ወገኖች ማለትም የአውሮፓ ኅብረትና እንግሊዝ ፍቺውን በሁለት ዓመታት ጊዜ ውስጥ እንደፈቱት በተቀመጠው መሠረት ነው፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትር ሜይም የብሬግዚትን ሒደት የጀመሩት ማርች 29 ቀን 2017 ሲሆን፣ ፍቺው ተፈጻሚነት የሚያገኘው ማርች 29 ቀን 2019 ላይ ነው ተብሏል፡፡
ፍቺው ከሌበር ፓርቲ ከባድ ተቃውሞ ገጥሞት እንደነበር የሚታወስ ሲሆን፣ ውሳኔ ሕዝብ ዳግመኛ እንዲካሄድም ጠይቆ እንደነበር አይረሳም፡፡ ይህ ያልተጠበቀ የብሪታኒያ ፍላጎት ግን ከውስጥና ከውጭ ያለው ተቃውሞ ሊገታው አልቻለም፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትር ሜይም ትኩረት አድርገው እየሠሩ በሚገኙት 585 ገጽ ያሉት የመልቀቅ ስምምነት የተዘጋጀ ሲሆን፣ ስምምነቱ ሕጋዊ ተፈጻሚነት ያለውና ብሪታንያን ከአውሮፓ ሕግጋት የምትፋታበትን ሁኔታዎች የሚዳስስ ነው፡፡
እንግሊዝ ለኅብረቱ 39 ቢሊዮን ዶላር መክፈል እንዳለባት፣ ከብሪታንያ ውጪ በተለያዩ የአውሮፓ አገሮች የሚገኙ የእንግሊዝ ዜጎችን ዕጣ ፈንታ እንዲሁም በእንግሊዝ የሚኖሩ የአውሮፓ ዜጎችን የተመለከተም ነው፡፡ በሁለቱ ወገኖች መካከል ስለሚኖረው የወደፊት ግንኙነት በተመለከተም ባለ 26 ገጽ የአቋም መግለጫ ተዘጋጅቷል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር ቴሬስ ወደ ሥልጣን የወጡት የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር ዴቪድ ካሜሮን በፈቃዳቸው ከሥልጣን መልቀቃቸውን ተከትሎ ነው፡፡ ብሪታኒያን ለስድስት ዓመታት የመሩት ካሜሮን ከሥልጣናቸው የለቀቁት ብሪታኒያ ከኅብረቱ ለመልቀቅ ያላትን ፍላጎት ተከትሎ ነው፡፡
‹‹የብሪታንያ ዜጎች ፈቃድ ተፈጻሚነት ያለው መመርያ ነው›› በሚል ንግግር በፈቃዳቸው እንደሚለቁ ያሳወቁት በተለያዩ መድረኮች ላይ እየተገኙ እንግሊዝ ከኅብረቱ መውጣት እንደሌለባት በምክንያት አስደግፈው ቢወተውቱም የቆሙለት ዓላማ በድምፅ ብልጫ ከታጠፈ በኋላ ነው፡፡
ከተቀራራቢው ውሳኔ ሕዝብ ውጤት በኋላ ብሪታኒያ ብዙ ክስተቶችን አስተናግዳለች፡፡ አገሪቱ ከኅብረቱ መውጣቷ ለኪሳራ ይዳርጋል በሚል ውጤቱን እንደማይቀበል በማሳወቅ ሌላ ውሳኔ ሕዝብ እንዲካሄድ እስከ መጠየቅ ተደርሶ ነበር፡፡
ካሜሮንን የተኩት ሜይ ሥልጣን ከጨበጡ በኋላ፣ ወደ ኋላ አንመለስም ብሬግዚት ብሬግዚት ነው ውሳኔ ሕዝቡን እንተገብራለን ብለው መነሳታቸው ይታወሳል፡፡
መሰንበቻውን በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫቸውም ይህንኑ አቋማቸውን ዳግም አንፀባርቀዋል፡፡ ‹‹ሥራዬ እንደ ጠቅላይ ሚኒስትርነቴ የብሪታኒያ ሕዝብ ይሁንታ የሰጠበትን ወሳኔ በማክበር ለሕዝብና ለአገር የሚበጅ ውል ተዋውያለሁ፡፡››