Monday, December 4, 2023

የለውጥ ፍኖተ ካርታ አስፈላጊነት የጎላበት መድረክ

- Advertisement -spot_img

በብዛት የተነበቡ

በርካታ ታሪካዊ ዓለም አቀፍ፣ አኅጉራዊና አገር አቀፍ ክንውኖች፣ ውሳኔዎችንና ዝግጅቶችን ሲያስተናግድ የኖረው የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የአፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽን (UNECA) በሳምንቱ መጨረሻ ቅዳሜና እሑድም እንዲሁ፣ ኢትዮጵያ አሁን ላለችበት አጠቃላይ ፖለቲከዊ ሁኔታ ዘላቂ መፍትሔ ለመስጠት ምን መደረግ አለበት በሚል አጀንዳ ላይ የምክክር መደረክ አስተናግዶ ነበር፡፡

መድረኩ የጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድን (ዶ/ር) ጥሪ በመቀበል ከወራት በፊት ወደ አገር ቤት በገባው የኦሮሞ ዴሞክራሲያዊ ግንባር (ኦዴግ) እና መቀመጫውን ጀርመን አገር ካደረገው ከሰላም፣ ከግጭት አፈታትና መረጋጋት ጋር በተያያዙ የተለያዩ ሥራዎችን በሚሠራው ቤርጎፍ ፋውንዴሽን በተባለ መንግሥታዊ ባልሆነ ተቋም አማካይነት ነበር፡፡

ይህ አገር አቀፍ መድረክ ‹‹በኢትዮጵያ ያለው የፖለቲካ ለውጥ›› የሚል ዋነኛ ማጠንጠኛው ሲሆን፣ ከዚህ ጋር በተያያዘ አሁን በኢትዮጵያ ያለው ለውጥ ተግዳሮቶቹ፣ እንዲሁም መልካም ዕድሎች ምንድን ናቸው? መልካም ዕድሎቹ እንዳይጨናገፉ፣ እንዲሁም ተግዳሮቶቹን ደግሞ እንዴት መፍታት ይገባል? የሚሉ ተያያዥ ጉዳዮች ደግሞ የአገር አቀፍ የምክክር መድረኩ ተጨማሪ የትኩረት አቅጣጫዎች ነበሩ፡፡

መድረኩን በንግግር የከፈቱት ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ ሲሆኑ፣ በዕቱም በአገሪቱ የፖለቲካ ምኅዳር ዋነኛ ተዋናዮች የሆኑ የፖለቲካ ፓርቲ አመራሮች፣ ቀድሞ ከፍተኛ ባለሥልጣናት የነበሩ ግለሰቦች፣ ምሁራን፣ እንዲሁም ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ታድመዋል፡፡ አሁን ኢትዮጵያ የያዘችውን የለውጥ ሒደት እንዳይቀለበስ ቢደረግ መልካም ነው የሚሉ የተለያዩ ሐሳቦችም ሰንዝረዋል፡፡

በዚህ መድረክ አንድ ላይ በአንድ አዳራሽ ይገኛሉ ተብሎ ለማሰብ የሚከብዱ የፖሊቲካ ፓርቲ አመራሮች በአንድ ላይ ታድመው፣ ከዚህ ቀደም የነበረ ልዩነታቸውን በማያሳብቅ ሁኔታ ለአገሪቱ ወቅታዊ ሁኔታ መፍትሔ ለመፈለግ ተሰብስበዋል፡፡ ከእነዚህም መካከል ከምርጫ 97 ወዲህ በተፈጠረ የፖለቲካ ልዩነት በተለያየ መንገድ ልዩነታቸውን ሲገልጹ የሰነበቱት አቶ ልደቱ አያሌውና ብርሃኑ ነጋ (ፕሮፌሰር) ተጠቃሽ ናቸው፡፡

ከዚህም በላይ ደግሞ ከጥቂት ወራት በፊት ፈፅሞ ሊታሰብ በማይችል ሁኔታ፣ ባለፈው ሳምንት የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ሰብሳቢ ሆነው የተሾሙት ወ/ሪት ብርቱካን ሚደቅሳም እንዲሁ የመድረኩ ታዳሚ ነበሩ፡፡

የአገሪቱን ፖለቲካ አቅጣጫ ለመምራት የተለያየ ሥራ እያከናወንን ነው የሚሉ የፖለቲካ ፓርቲ አመራሮች፣ እንዲሁም ምሁራን የታደሙበትን ይህንን መድረክ በንግግር የከፈቱት ጠቅላይ ሚኒስትሩ በዋነኛነት አገሪቱ አሁን ያለችበትን ሁኔታ አፅንኦት በመስጠት፣ መድረኩም አገሪቱ ላለችበት ሁኔታ መፍትሔ ሐሳቦችን በሰከነ መንገድ እንዲተልም አሳስበዋል፡፡

‹‹የኢትዮጵያ ፖለቲካ በአሁኑ ጊዜ መስቀለኛ መንገድ ላይ ይገኛል፤›› በማለት፣ አገሪቱ ከመቼውም ጊዜ በበለጠ ይህን መስቀለኛ መንገድ ለመሻገርና የሚታዩትን ተስፋዎች ለማለምለም እጅግ ሥልጡን የሆነ፣ እንዲሁም በሰጥቶ መቀበል መርህ ላይ የተመሠረተ ፖለቲካ ማከናወን እንደሚገባ ለመድረኩ ታዳሚዎች አውስተዋል፡፡

ከዚህ በተጨማሪም በሚደረጉ የፖለቲካ ውድድሮችና ፉክክሮች የሁሉም ተዋናዮች ድርሻ እኔ አሸነፍኩ አሊያም ተሸነፍኩ ወደ ሚል ትርጓሜ ከመግባት ይልቅ፣ ቅድሚያ ለአገር በመስጠት ኢትዮጵያ አሸናፊ እንድትሆን መሥራት እንደሚገባ በመግለጽ፣ ‹‹ዴሞክራሲያዊ፣ ነፃ፣ ገለልተኛ፣ ተዓማኒና ሕጋዊ ምርጫ ማካሄድ የሚያስፈልገው ኢትዮጵያ እንድታሸንፍ ነው፤›› በማለት፣ ሁሉም የፖለቲካ ተዋናዮች በዋነኛነት ኢትዮጵያ አሸናፊ የምትሆንበትን የፖለቲካ ሥራ ማከናወን እንደሚገባቸው አሳስበዋል፡፡

ባለፉት ዓመታት ሲከናወኑ የነበሩ የፖለቲካ እንቅስቃሴዎች ኢትዮጵያ ለዘመናት ከገነባቻቸው የሚያሳሱና የሚያስደስቱ ታሪኮች አንፃር የማይመጥንዋት እንደነበር በማውሳት፣ ‹‹አሁን የተለያየ የፖለቲካ አመለካከት ያላቸው ግለሰቦችና ቡድኖች እርስ በርስ ለመጠፋፋት የሚሻኮቱበት ዘመን አልፎ፣ ለአንድ አገር ዕድገት እንደሚታገሉ ሆነው የሚታዩበት አዲስ ዘመን መጥቷል፤›› ብለዋል፡፡ በፖለቲካ ልዩነቶች ሳቢያ አንዱ አንዱን የሚወቅስበትና የሚጠልፍበት ጊዜ ማክተሙን በመግለጽ፣ ሁሉም ከእነ ልዩነቱ ለኢትዮጵያ ታሪክ የሚመጥን ፖለቲካ እንዲያራምድ ጥሪ አቅርበዋል፡፡

በዚህም መሠረት አሁን አገሪቱ ከደረሰችበት የፖለቲካ ለውጥ አንፃር፣ ‹‹ለውጡን እንደ ወርቃማ ዕድል ተጠቅመን ተስፋውን እያለመለምን እንጓዛልን? ወይስ በለውጡ የተመዘገቡ ውጤቶችን እንቀለብሳለን?›› የሚለውን ጥያቄ የመድረኩ ተወያዮቹ በፅኑ እንዲወያዩበት ጠይቀዋል፡፡

በመጨረሻም ዴሞክራሲ ውጤት ብቻ ሳይሆን ሒደት እንደሆነ በመጥቀስ፣ ከውጤቱ በላይ ግን ሒደቱ በጣም አስፈላጊ መሆኑን አጽንኦት በመስጠት ለዚህ ሒደት ሁሉም የበኩሉን አስተዋጽኦ ሊያበረክት እንደሚገባ አስገንዝበዋል፡፡

ከጠቅላይ ሚኒስትሩ የመክፈቻ ንግግር በመቀጠል ሌተና ጄኔራል ፃድቃን ገብረ ትንሳዔ፣ አቶ ልደቱ አያሌው፣ ወ/ሮ ማክዳ ጌታቸው፣ እንዲሁም አቶ ሃሌሉያ ሉሌ በተወያይነት ለተሰየሙበት መድረክ መነሻ የሚሆን ጽሑፍ ያቀረቡት የኦዴግ ሊቀመንበርና አንጋፋው ፖለቲከኛ አቶ ሌንጮ ለታ ነበሩ፡፡ በጽሑፋቸውም ያሳለፉትን የፖለቲካ ተሞክሮ መሠረት በማድረግ አሁን ላለው የፖለቲካ ሁኔታ ይበጃል ያሉትን ሐሳብ ሰንዝረዋል፡፡   

በዚህም መሠረት ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ለመገንባት ቅድመ ሁኔታው በዋነኛነት ማመቻመች እንደሆነ በመጥቀስ ነው ንግግራቸውን የጀመሩት፡፡ የተካረሩ የፖለቲካ አተያዮችን፣ እንዲሁም አንዱ ወገን ሌላውን እንደ ጠላት ፈርጆ መጓዝ ሊገታ የሚገባው የፖለቲካ ባህል እንደሆነ ካለፉባቸው የደርግ ዘመንም ሆነ ተዋናይ ከነበሩበት የሽግግር መንግሥቱ ምሥረታ ወቅት ያስከተለውን መዘዝ በማስታወስ፣ አሁን አገሪቱ ላለችበት የዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታ እጥረት እንዲህ ዓይነቱ አተያይ እንደሆነ አውስተዋል፡፡

ይህን ሐሳባቸውን ለማስረፅ  የተጠቀሱት ከአገሪቱ የፖለቲካ ጉዞ ውስጥ ታሪካዊ ዳራው ምን ይመስል እንደነበር በመጥቀስ የነበረ ሲሆን፣ በዚህም መሠረት በንጉሡ ጊዜ የተቃውሞ ፖለቲካን ማሰብ እንደ ምድራዊ ስህተት ሳይሆን የሚታየው እንደ ኃጥያት ያህልም እንደነበር በማስታወስ ጭምር ነው፡፡

ለዚህም በዋነኛነት ከሰለሞናዊ ሥርወ መንግሥት ጋር ራሱን ያስተሳሰረውንና ሥዩመ እግዚአብሔር በማለት የሚጠራው የንጉሡ ሥርዓት ለአገዛዝ ያመቸው ዘንድ የተከተለው መለኮታዊ ሽፋን፣ ሕዝቡን በመጋረድ ተቃውሞ እንደ ኃጢያት እንዲቆጠር ተፅዕኖ መፍጠሩን ገልጸዋል፡፡

እንዲህ ያለው አመለካከት ወደ መጠየቅ የገባውና አመለካከቱ ይቀየር ዘንድ ከፍተኛ ድርሻ የተጫወተው የታኅሳስ 1953 ዓ.ም. የንዋይ ወንድማማቾች የመፈንቅለ መንግሥት ሙከራ እንደሆነ አብራርተዋል፡፡ ነገር ግን መፈንቅለ መንግሥቱ ከከሸፈ በኋላ የመፈንቅለ መንግሥት ሞካሪዎቹ በመሳፍንቱ ላይ የወሰዱት የግድያ ዕርምጃ፣ መግደል እንደ አንድ የፖለቲካ አማራጭ ሆኖ ወደ ኢትዮጵያ የፖለቲካ ምኅዳር እንዲገባ እንዳደረገውም ገልጸዋል፡፡

በመቀጠል የንጉሡ ሥርዓትን መወገድ ተከትሎ ወደ ሥልጣን የመጣው ደርግ ደግሞ በወቅቱ ፋሽን በነበረው የማርኪሲስት ሌኒኒስት ርዕዮተ ዓለም በማዘንበሉ፣ እንዲሁ የዴሞክራሲ ሥርዓትን በኢትዮጵያ ምድር የመትከል ጉዞን አዝጋሚና አስቸጋሪ እንዳደረገው አስረድተዋል፡፡

በወቅቱ የማርክሲስት ሌኒኒስትን ርዕዮተ ዓለም ለመከተል በርካታ ገፊ ምክንያቶች እንደነበሩ በመጥቀስ፣ በዚህ ርዕዮተ ዓለም መሠረት አንድ ጠባቂ ፓርቲ (Vanguard Party) የአገሪቱን ሁሉ ችግሮች ለመፍታት መሠረታዊ መፍትሔ ነው የሚለው አተያይም እንዲሁ ከፍተኛ ተግዳሮት መሆኑን ተናግረዋል፡፡

በዚህ የፖለቲካ ዓውድ ሲጓዝ የነበረው የአገሪቱ የፖለቲካ ሁኔታ ከ1983 ዓ.ም. ወዲህም ቢሆን ብዙ የተወራለትን ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት የመገንባት ጉዞ ማሳካት እንዳልቻለና አሁን ለተደረሰበት የፖለቲካ ፈተና እንዳበቃ ገልጸዋል፡፡

በመሆኑም አሁን ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ለመገንባት ከዚህ ቀደም የተሄደበትን ጉዞ መለስ ብሎ በመመልከት አዲስ አተያይ መያዝ እንደሚገባ፣ እንዲሁም የሠለጠነና የሰከነ ውይይት በተለያዩ ጉዳዮች ላይ በተለይም ብዝኃነትን መረዳትና መፍትሔ ማበጀት፣ አወዛጋቢ የሆነው የአገሪቱ ታሪክ ላይ አዳዲስ የአንድነት መሠረቶችን መለየት፣ በሽግግር ወቅት ፍትሕን፣ መንግሥትንና ፖለቲካን መለያየት፣ የመገናኛ ብዙኃንን አስመልክቶ በሰከነ መንገድ መወያየትና እነዚህን ጉዳዮች ደግሞ ለመገንባት ለሚታሰበው ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት አስተዋጽኦቸውን ማበርከት እንዲችሉ ለማድረግ ወደ አማካይ ነጥብ መምጣት ለነገ የማይባል የቤት ሥራ እንደሆነ በመግለጽ፣ መድረኩም ከዚህ አንፃር ሊወያይ እንደሚገባ በማሳሰብ ሐሳባቸውን ቋጭተዋል፡፡

ከተወያዮቹ ይሁንታንና ተቀባይነት ያገኘው የአቶ ሌንጮ ለታ ሐሳብ ከዚህ በተጨማሪ ካለ፣ አሊያም እንዲህ ቢሆን የሚሉ የተለያዩ ሐሳቦች እየጨመሩበት ከመድረኩ ከተሰየሙ ተወያዮችና ተሳታፊዎች ሐሳቦች ተሰንዝረውባቸዋል፡፡  

በዚህም መሠረት የአቶ ሌንጮን ሐሳብ ተከትሎ የተጀመረውን ለውጥ ቀጣይነት ለማረጋገጥ የተሻለ ይሆናል ያሉትን ሐሳብ ያቀረቡት ሌተና ጄኔራል ፃድቃን ገብረ ትንሳዔ ሲሆኑ፣ እሳቸውም አጠር ባለ ንግግራቸው በሦስት ዋነኛ ጉዳዮች ላይ በማተኮር ሐሳባቸውን ሰንዝረዋል፡፡

እሳቸው የተጀመረው የለውጥ ሒደት የታለመለትን ግብ ያሳካ ዘንድ፣ ‹‹በዋነኛነት ከየት ተነስተን የት እንደርሳለን?›› እንዴት እንደርሳለን የሚል ግልጽ የሆነ የፖለቲካ ፍኖተ ካርታ ለውጡን ተፈጻሚ ለማድረግ የመጀመርያው ቅድመ ሁኔታ መሆን እንደሚኖርበት ነው፡፡

የተጀመረውን የለውጥ ሒደት በቅጡ ለመምራት ይቻል ዘንድ ግልጽ የሆነ፣ እንዲሁም ትዕግሥት የተላበሰ የለውጥ አስተዳደር (Reform Management) ሊኖር እንደሚገባ፣ የዚህም መኖር ለውጡን በአግባቡ ለማስተዳደር ዓይነተኛ ሚና የሚጫወት መሆኑን፣ ይህም የፖለቲካው ፍኖተ ካርታ አካል በመሆን ለውጡ የታለመለትን የሕዝቦችን ተጠቃሚነትና የዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታን ማፋጠን፣ እንዲሁም ለውጡን ዘለቄታዊ ለማድረግ ይረዳል የሚል አተያይ እንዳላቸው አመላክተዋል፡፡

ጄኔራሉ በሁለተኛነት ያነሱት ሐሳብ ደግሞ በቅርቡ በተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች እያቆጠቆጡ የሚገኙና የዜጎችን ሕይወትና ንብረት እየነጠቁ ያሉ የማንት ጥያቄዎችን እንዴት መፍታት ይቻላል? የሚለው ነጥብ ላይ በማተኮር፣ ለውጡን ወደ ታለመለት ግብ ማድረስ እንደሚቻል እንደሚያምኑ ገልጸዋል፡፡

ከዚህ አንፃር ከማንነትና ከክልል አስተዳደር ጋር የሚነሱ ጥያቄዎችን በኃይል ለመመለስ መሞከር? ወይስ ሕገ መንግሥቱን መሠረት ባደረገ መንገድ በሰላማዊ መንገድ መፍታት? የሚለው አጽንኦት ተሰጥቶት ሊታይ እንደሚገባው ገልጸዋል፡፡ ለውጡ የታለመለትን ዓላማ እንዲያሳካ የማንነትና የክልል ጥያቄዎች በሕገ መንግሥቱ መሠረት መፍታት ከምንም በላይ ቅድሚያ ሊሰጠው የሚገባ ጉዳይ እንደሆነ አጽንኦት ሰጥተው ተናግረዋል፡፡

በማከልም፣ ‹‹ከማንነትና ከክልል አስተዳደር ጋር የሚነሱ ጥያቄዎችና በኃይል ለመፍታት መሞከር የተጀመረውን የለውጥ ሒደት ብቻ ሳይሆን፣ አገሪቱንም ጭምር አደጋ ላይ ይጥላል፡፡ በኃይል የሚደረግ አማራጭ አደገኛ ነው፤›› በማለት፣ ጉዳዩን በሕገ መንግሥቱ መሠረትና በሰከነ መንገድ በሰላማዊ የውይይት መድረኮች ለመፍታት መሞከር፣ ለአገሪቱም ለተጀመረው ለውጥም ቀጣይነት አስፈላጊ እንደሆነ አስገንዝበዋል፡፡

በሦስተኛነት ለውጡን ተፈጻሚ ለማድረግ አስፈላጊው ነጥብ ደግሞ የሽግግር ፍትሕ (Transitional Justice) ጉዳይ ሲሆን፣ ለውጡን ተከትለው በመጡት ሥራዎችና አካሄዶች እየተወሰዱ ያሉ ዕርምጃዎች የተመረጡ (Selective) እንዳይሆኑ ጥንቃቄ ሊደረግ እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡

በዚህም መሠረት የሚወሰዱ የፍትሕ ዕርምጃዎች በግልጽነት የሚከናወኑ ሊሆኑ እንደሚገባ በማስገንዘብ፣ ተመርጬ ጥቃት ደርሶብኛል የሚል ነገር እንዳይፈጠር ውሳኔዎቹን ማጤን እንደሚገባ ጠቁመዋል፡፡ ይህንን ያሉበትን ምክንያትም ሲገልጹ ጉዳቱ መስመር ከሳተ የሚያዛባው የለውጡን ሒደት ብቻ ሳይሆን፣ የአገሪቱንም ህልውና አደጋ ውስጥ ሊከት የሚችል ነው ብለዋል፡፡

የጄኔራል ፃድቃን ሥጋቶችንና ተስፋዎችን ያዘለ ንግግር ተከትሎ ሐሳባቸውን ያቀረቡት ደግሞ አቶ ልደቱ አያሌው ሲሆኑ፣ እሳቸውም ከአቶ ሌንጮ ሐሳብ ጋር ምንም ልዩነት እንደሌላቸው በመጥቀስ፣ ነገር ግን ለውጡን ከማስቀጥልና ፈተናዎቹን በተመለከተ የሚታያቸውንና ቢሆን የሚመርጡትን አጋርተዋል፡፡   

አቶ ልደቱ በአሁኑ ጊዜ ከለውጡ አንፃር ሊነሳ የሚገባው ጥያቄ፣ አሁን የተጀመረው ለውጥ ሌላ የለውጥ ጥያቄ እንዳያመጣ ማድረግ የሚቻለው እንዴት ነው? የሚለው አጀንዳ መሆን እንደሚገባው ተናግረዋል፡፡

ይህን ጥያቄ ምላሽ መስጠት በጣም አስፈላጊ መሆኑን የሚገልጹት አቶ ልደቱ፣ ‹‹የኢትዮጰያ ሕዝብ ለውጥ ፈላጊ ነው፡፡ በዚያው መጠን ደግሞ ለውጥ አምካኝም ነው፤›› በማለት ከለውጥ ዑደት እንዴት መውጣት እንደሚገባ ማሰቡ፣ ማሰላሰሉ፣ እንዲሁም አቅጣጫ ማስቀመጡ ለውጡ የተነሳበትን ዓላማ ለማሳካት ትልቅ ጉልበት ሊሆነው እንደሚችል ገልጸዋል፡፡

‹‹ለውጥን እየፈጠሩ ማምከን የፖለቲካ ባህላችን መገለጫ ነው፤›› የሚሉት አቶ ልደቱ፣ ይህንም የፖለቲካ ባህል መቀየር አስፈላጊ እንደሆነም አብራርተዋል፡፡ ‹‹ባለፉት 40 ዓመታት በኢትዮጵያ ፖለቲካ ውስጥ ያሉ ተዋናዮች ሳይቀየሩ ባህሉ ይቀየራል ወይ?›› የሚለውን ጥያቄ ለተወያዮቹ በመሰንዘር፣ ይህም ጉዳይ ከተጀመረው የለውጥ ሒደት አንፃር ሊመለስ የሚገባው ጥያቄ እንደሆነ ገልጸዋል፡፡

ከአገሪቱ የፖለቲካ ባህል ባለፈ ደግሞ የዚህ ለውጥ ሥጋት ወይም አደጋ ሊሆን የሚችለው ችግር፣ የአገሪቱ ፖለቲካ ያለ ጠላት መቆም  አለመቻል ነው ብለዋል፡፡ ‹‹በአገሪቱ የፖለቲካ ምኅዳር ብቻውን ሐሳብ ይዞ የሚቆም ኃይል የለም፡፡ ሁሉም ጠላት ይፈልጋል፤›› በማለት፣ ከሌሎች ቡድኖች ወይም ግለሰቦች ጋር ከሚኖር የጠላትነት መፈራረጅ ይልቅ የሐሳብ ልዕልና ላይ በመቆም ፖለቲካውን መዘወር ጠቃሚ መሆኑን አስገንዝበዋል፡፡

በመጨረሻም አቶ ልደቱ ሁሉንም የፖለቲካ ተዋናዮች ያሳተፈ የፖለቲካ ፍኖታ ካርታ ሊኖር እንደሚገባ በመጠቆም፣ በዚህ ወቅት አገሪቱን ወደፊት ለማራመድ ሁሉም የድርሻውን መወጣት እንደሚኖርበት ገልጸዋል፡፡ ‹‹በዚህም መሠረት ለዚህ ለውጥ አሻጋሪና ተሻጋሪ አለ ወይ?›› የሚል ጥያቄ ሰንዝረዋል፡፡ ‹‹ሁላችንም አሻጋሪም ተሻጋሪም መሆን አለብን፤›› ሲሉም ሐሳባቸውን ቋጭተዋል፡፡

ይህ ለሁለት ቀናት በአፍሪካ ኢኮኖሚ ኮሚሽን አዳራሽ የተካሄደው የምክክር መድረክ የተለያዩ የፖለቲካ ኃይሎች የተሳተፉበት በመሆኑ፣ በተለያዩ መንገዶች የሚቀርቡ ጥያቄዎች እንዴት ፈር ይዘው ሊቀርቡ እንደሚችሉ አመላካች ሰነድም በአቶ ሌንጮ ለታ አማካይነት በስብሰባው ማጠናቀቂያ ወቅት ቀርቦ፣ ተሳታፊዎች የቤት ሥራቸውን ለማከናወን በመስመማት ተጠናቋል፡፡   

spot_img
- Advertisement -

ትኩስ ጽሑፎች

ተዛማጅ ጽሑፎች

- Advertisement -
- Advertisement -