Friday, March 24, 2023
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

የዘመን ባንክ ትርፍ በ26 ሚሊዮን ብር ቀነሰ

- ማስታወቂያ -

ተዛማጅ ፅሁፎች

የባንክ ኢንዱስትሪውን ከተቀላቀለ አሥረኛ ዓመቱን ያከበረው ዘመን ባንክ በ2010 የሒሳብ ዓመት ያስመዘገበው ትርፍ ካለፈው ዓመት ጋር ሲነፃፀር የ26 ሚሊዮን ብር ቅናሽ አሳየ፡፡ ባንኩ አሥረኛ ዓመቱን ክብረ በዓል በዘከረበትና ዓመታዊ ጠቅላላ ጉባዔውን ባለፈው ቅዳሜ ኅዳር 15 ቀን 2011 ዓ.ም. ባካሄደበት ወቅት እንደገለጸው፣ ከታክስ በኋላ ያገኘው ትርፍ ከቀዳሚው ዓመት መጠነኛ ዕድገት ያሳየ ቢሆንም፣ ያልተጣራ የትርፍ መጠኑ ግን ከቀዳሚው ዓመት ቅናሽ የታየበት ስለመሆኑ ከባንኩ ዓመታዊ ሪፖርት መረዳት ተችሏል፡፡

ባንኩ በ2010 የሒሳብ ዓመት ከታክስ በፊት ያገኘው ትርፍ 342.3 ሚሊዮን ብር ሲሆን፣ በ2009 የሒሳብ ዓመት ደግሞ ከታክስ በፊት አግኝቶት የነበረው ትርፍ 368.4 ሚሊዮን ብር ነበር፡፡

በሁለቱ ዓመታት ከታክስ በፊት የተገኘው ትርፍ ወደ 26 ሚሊዮን ብር ቅናሽ እንዳለው ያሳያል፡፡ በ2009 ከታክስ በኋላ ያገኘው ትርፍ 266 ሚሊዮን ብር በመሆኑ በ2010 ከታክስ በኋላ ያገኘው ትርፍ ግን አራት ሚሊዮን ብር ብልጫ አሳይቷል፡፡ የባንኩ ዳይሬክተሮች ቦርድ ሰብሳቢ አቶ አበበ ድንቁ (ኢንጂነር፣ ዶክተር፣ ፕሮፌሰር) ባቀረቡት ሪፖርት ላይም ባንኩ ያገኘውን የትርፍ መጠን በተመለከተ እንደገለጹትም፣ ባንኩ ከታክስ በኃላ ያገኘው የተጣራ 270.3 ሚሊዮን ብር የትርፍ ምጣኔ ከፍተኛ መሻሻል ያልታየበት እንደሆነ ጠቅሰዋል፡፡

በሒሳብ ዓመቱ ውስጥ የተገኘው ትርፍ ከፍተኛ መሻሻል ካልታየባቸው ምክንያቶች ውስጥ ለባንኩ ተቀምጦለት የነበረው የብድር ጣሪያ በIFRS ትግበራ ምክንያት የተደረገው ተጨማሪ ማስተካከያ 21.8 ሚሊዮን ብር ልዩነት ስላመጣ መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡ ከዚህም ሌላ ለተቀማጭ ገንዘቦች የተከፈለው ወለድ፣ ለሠራተኞች ደመወዝና ጥቅማ ጥቅም፣ እንዲሁም ልዩ ልዩ ወጪዎች በከፍተኛ ሁኔታ በመጨመራቸው መሆኑንም አስታውሰዋል፡፡

ከዚህ ባሻገር ግን በሌሎች የባንክ አገልግሎት ዕድገት የታየበት አፈጻጸም ያሳየ ስለመሆኑ በሪፖርቱ የተመለከተ ሲሆን፣ ከባንኩ የአሥር ዓመታት ጉዞ ጋር በተያያዘ እንዳመለከቱትና ባንኩ በጥሩ ደረጃ ላይ የሚገኝ ስለመሆኑ አቶ አበበ ተናግረዋል፡፡ እንደ እሳቸው ገለጻ፣ እ.ኤ.አ. በ2009 ከነበረው 228 ሚሊዮን ብር ተቀማጭ ገንዘብ በአማካይ 58 በመቶ ዓመታዊ ዕድገት በማስመዝገብ መቀጠሉ ተነግሯል፡፡

ለተለያዩ የኢኮኖሚ ዘርፎ የተሰጠው የብድር መጠንም የዛሬ አሥር ዓመት  ከነበረበት 187 ሚሊዮን ብር 47 በመቶ ዓመታዊ አማካይ ዕድገት በማስመዝገብ 5.2 ቢሊዮን ብር መድረሱ፣ ባንኩ በአሥር ዓመታት ውስጥ ዕድገት እያሳየ ስለመምጣቱ አመላካች መሆኑን ጠቁመዋል፡፡

ከምሥረታው ዓመት በኋላ ላለፉት ዘጠኝ ዓመታት በተከታታይ አትራፊ ስለመሆኑ ያስታወሱት አቶ አበበ፣ የአሥር ዓመቱ አማካይ በአንድ አክሲዮን የተገኘ ገቢ 40.4 በመቶ ሲሆን፣ አማካይ የትርፍ ክፍያ ደግሞ 28.9 በመቶ በመሆን በኢንዱስትሪ ውስጥ ከፍተኛ ከሚባሉት አንዱ መሆኑን ያሳያልም ብለዋል፡፡

ባንኩ በ2010 የሒሳብ ዓመት አፈጻጸም ከቀዳሚ ዓመት አንፃር ሲታይም በጠቅላላ ገቢ የ15.3 በመቶ በማደግ 1.1 ቢሊዮን ብር መድረሱ የባንኩን ውጤት ያሳያል ተብሏል፡፡ በተቀማጭ ገንዘብ ረገድም በቀዳሚው ዓመት ስምንት ቢሊዮን ብር የነበረ ሲሆን፣ በ2010 የሒሳብ ዓመት በ2.2 ቢሊዮን ብር ወይም በ27.5 በመቶ ጨምሮ 10.2 ቢሊዮን ብር መድረሱ ተመልክቷል፡፡ ባንኩ በሒሳብ ዓመቱ የሰጠው የብድር መጠን 5.2 ቢሊዮን ብር እንደደረሰ የሚያመለክተው የባንኩ መረጃ፣ ከቀዳሚው ዓመት በ25 በመቶ ዕድገት ያሳየ ነው፡፡ ከፍተኛውን ብድር የሰጠው ለአምራች ዘርፍ ሲሆን፣ 25.6 በመቶ ድርሻ ነበረው፡፡

አቶ አበበ ባንኩ እስካሁን ያለው ሒደት አመርቂ ስለመሆኑ የገለጹ ቢሆንም፣ የ2010 የሒሳብ ዓመት በርካታ ተግዳሮቶች የነበሩበት ስለመሆኑ ሳይገልጹ አላለፉም፡፡ ምንም እንኳን 2010 ዓ.ም. የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ዕድገት የተቀዛቀዘና በባንኮች መካከል ያለ የእርስ በርስ ውድድር ከፍተኛና በተለይም እንደኛ ላለ በውስን ቅርንጫፎች አገልግሎት ለሚሰጥ ባንክ ከፍተኛ ፈተና ነበርም ብለዋል፡፡ ሆኖም በደንበኞቻቸው፣  በባለአክሲዮኖቻቸውና በሠራተኞቻቸው ባንኩ የተቀናጀ ጥረት የገጠሙትን ፈተናዎች በመቋቋም በሁሉም ረገድ ሊባል በሚችል መልኩ መልካም ውጤቶችን አስመዝግቧል ይላሉ፡፡

አያይዘውም በአጠቃላይ በሒሳብ ዓመቱ የተገኘው ትርፍ በአንድ አክሲዮን በአማካይ ሲሰላ 28.6 በመቶ ሲሆን፣ ባንኩ አጠቃላይ የአምስት ዓመት የትርፍ ክፍፍል ከአቻ ባንኮችና ከባንክ ኢንዱስትሪው ከፍ ብሎ መቀጠሉን አመልክተዋል፡፡  ከዚህ ጋር ተያይዞ በዓመቱ የተገኘው ውጤት በተቀማጭ ገንዘብ ረገድ የተሠራውን ያህል ሥራ በብድር ረገድ ትኩረት ተሰጥቶት ቢሆን ኖሮ ግኝቱ ከዚህ የበለጠ ሊሆን እንደሚችልም ጠቅሰዋል፡፡ አቶ አበበ ስለባንካቸው ከጠቀሱት ሪፖርት ባሻገር የዓለም ወቅታዊ ሁኔታን ከወቅቱ የአገሪቱ ኢኮኖሚ ጋር በማስተሳሰርና  የዓለም ባንክ ሪፖርትን በመጥቀስ የዓለም ኢኮኖሚ ምልከታ ሰነድ መሠረት በማድረግ ያቀረቡት ማብራሪያ የሪፖርታቸው አካል ነበር፡፡ እ.ኤ.አ. በ2017 የዓለም ኢኮኖሚ በሦስት በመቶ ዕድገት ያስመዘገበ ሲሆን፣ በ2018 ደግሞ ይህው አኃዝ ወደ 3.1 በመቶ እንደሚያድግ በመግለጽ የዓለም ኢኮኖሚ በዚህ መልኩ መሻሻል ለግብርና ምርቶች ገበያ በመፍጠር ረገድ የጎላ አስተዋፅኦ እንደሚኖረው ጠቁመዋል፡፡ ይኼም እንደ ኢትዮጵያ ላሉ በግብርና ምርቶች ላይ የውጭ ንግዳቸውን መሠረት ላደረጉ አገሮች ጠቀሜታው የጎላ እንደሚሆን ይታመናል፡፡ የኢኮኖሚ ዕድገቱ መነቃቃትን የፈጠረ ሲሆን፣ እ.ኤ.አ. ከ2015/16 አጋማሽ በኋላ የዓለም የነዳጅና ዘይት ዋጋ እያደገ መምጣት በአንፃሩ እንደ ኢትዮጵያ ላሉ ምርት ከውጭ ለሚያስገቡ አገሮች ደግሞ ከፍተኛ የውጭ ምንዛሪ እንዲያወጡ በማድረግና የክፍያ ሚዛን ጉድለቱን በማባባስ ኢኮኖሚውን ከሚፈታተኑት መካከል በቀደምትነት የሚሠለፍ ነው ብለዋል፡፡ ባሳለፍነው ዓመት የዓለም የውጭ ምንዛሪ እጥረትና አሁንም እጥረቱ አለመሻሻሉ ኢኮኖሚውን እየተፈታተነው ስለመሆናቸውም አስታውሰው፣ በዚህም ምክንያት በብድር ፍላጎትና አመላለስ ላይ የጎላ ተፅዕኖ ከማሳደሩም በላይ በባንክ ኢንዱስትሪ ውስጥ የተበላሹ ብድሮች መጠን እንዲያደግ ምክንያት ስለመሆኑ ተናግረዋል፡፡ መንግሥት የተቀማጭ ገንዘብ ወለድ ከፍ ማድረጉና የ30 በመቶ የውጭ ምንዛሪ መግዣ ዋጋ ለኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ እንዲሰጥ መደረጉም ባንኮች ገቢ ላይ ቀጥተኛ ተፅዕኖ ማሳረፉንም ገልጸዋል፡፡ ይህንንም ሲያብራሩ የዝቅተኛ ወለድ ጭማሪው ባንኮች ተቀማጭ ገንዘብ ላይ የሚከፍሉት ወለድ ከፍ እንዲል ያደረገ ብቻ ሳይሆን፣ በተበዳሪዎችም ላይ በተደረገው የብድር ወለድ ማስተካከያ ምክንያት ጫናው እንደበረታባቸውና ዋጋውን ወደ ሸማቹ እንዲተላለፍ ምክንያት ሆኗል፡፡

እንደ ባንኩ መረጃ በቀጣይ ዓመታት ለመተግበር ያሰባቸውን ወሳኝ ሥራዎች ለባለአክሲዮኖች የተገለጸ ሲሆን፣ ከዚህ ውጪ በ2011 ዓ.ም. 22 አዳዲስ ቅርንጫፎች ለመክፈት መዘጋጀቱ የተለያዩ አሠራሮችን ለማዘመን እየሠራ መሆኑ ተጠቅሷል፡፡ ይህ በእንዲህ እንዳለ ባንኩ አሥር ዓመቱን በማስመልከት ለበጎ አድራጎት ድርጅቶች የአንድ ሚሊዮን ብር ድጋፍ ያደረገ ሲሆን፣ ማኅበራዊ ኃላፊነቱን ለማውሳት ቋሚ የሆነ ዕቅድ መንደፉንም አስታውቋል፡፡

ዘመን ባንክ ከአሥር ዓመት በፊት ሲቋቋም 87 ሚሊዮን ብር የነበረውን የተከፈለ ካፒታል፣ በአሁኑ ወቅት 1.1 ቢሊዮን ብር በማድረስ አጠቃላይ የካፒታል መጠኑን ሕጋዊ መጠባበቂያን ጨምሮ 1.5 ቢሊዮን ብር ለማድረስ ችሏል፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች