- አቤት ክቡር ሚኒስትር?
- ሪፖርቱን ከምን አደረስከው?
- የቱን ሪፖርት ክቡር ሚኒስትር?
- ሳምንታዊ የሥራ ሪፖርት አቅርብልኝ ብዬህ አልነበር?
- ብለውኝ ነበር ክቡር ሚኒስትር?
- ሥራውን እርግፍ አድርገህ ትተኸዋል ልበል?
- ኧረ በፍፁም ክቡር ሚኒስትር፡፡
- ታዲያ ምን እያልከኝ ነው?
- ትንሽ ሥራ ስለሚበዛብኝ ነው፡፡
- የለውጥ ጊዜ ላይ መሆናችንን ረሳኸው?
- እሱማ እንዴት ይረሳል?
- ስለዚህ 24 ሰዓት መሥራት ነው ያለብን፡፡
- ለዛ እኮ ነው ሌት ተቀን የምሠራው፡፡
- እንደዛማ ቢሆን ሪፖርቱን በሠራኸው ነበር፡፡
- ኃላፊነት ተደራርቦብኝ ነው እኮ፡፡
- የምን ኃላፊነት ነው?
- ክቡር ሚኒስትር እርስዎን ከማማከር በተጨማሪ ሌሎች ኃላፊነቶችን ወስጃለሁ፡፡
- ምን ዓይነት የተለያዩ ኃላፊነቶች?
- ለምሳሌ የሕዝብ ክንፉን የምመራው እኔ ነኝ፡፡
- እሱ አደረጃጀት አልቀረም እንዴ?
- ክቡር ሚኒስትር እንደውም ተጠናክሮ እኔን የሕዝብ ክንፉ መሪ አድርገውኛል፡፡
- እንደዛም ቢሆን ይኼን ኃላፊነት ያገኘኸው እኮ የእኔ አማካሪ በመሆንህ ነው፡፡
- ልክ ነው ሌላም ተጨማሪ ኃላፊነት አለብኝ፡፡
- ምን ዓይነት ኃላፊነት?
- የመሥሪያ ቤታችን ዕድር ዋና ሰብሳቢ ሆኛለሁ፡፡
- እሱ እኮ የማኅበራዊ ሕይወትህ ኃላፊነት መስሎኝ?
- ቢሆንም ክቡር ሚኒስትር ወደፊት ሹመት ሲመጣ የማኅበራዊ ሕይወቴ ስለሚታይ እሱንም ወደ ጎን መተው የምችለው ኃላፊነት አይደለም፡፡
- ሰውዬ ሥራ ሌላ ነው ማኅበራዊ ሕይወት ሌላ ነው፡፡
- ግን ሌላም ኃላፊነት አለብኝ፡፡
- የምን ኃላፊነት?
- እንደሚያውቁት ከለውጡ በፊት የመሥሪያ ቤታችን ሠራተኞች እርስ በርሳቸው ሊባሉ ነበር፡፡
- ይኼ እኮ በመላ አገሪቷ የነበረ ችግር ነው፡፡
- ልክ ነው ግን አገራዊ ችግሩን ለመፍታት ከራሳችን ቢሮ መጀመር አለብን፡፡
- ምን እያልክ ነው?
- በሠራተኞች መካከል የተፈጠረውን መቃቃር ለመፍታት የተቋቋመው የእርቅ ኮሚቴም ሰብሳቢ ነኝ፡፡
- እ. . .
- ስለዚህ ይህ ኮሚቴ ስኬታማ እንዲሆን ለሠራተኞቹ መቃቃር ችግር የሆነው አመለካከታቸው ይቀየር ዘንድ ፀሎት አደርጋለሁ፡፡
- እየቀለድክ ነው ሰውዬው?
- ክቡር ሚኒስትር እንደውም ፀሎት የሚደረገው እንደየእምነቱ ስለሆነ ሁሉንም የማስተባበር ኃላፊነት አለብኝ፡፡
- ጤነኛ አልመሰልከኝም?
- ክቡር ሚኒስትር ከዚህም ውጪ የመሥሪያ ቤታችን ልሳን የኤዲቶሪያል ቦርድ ሰብሳቢ ሆኛለሁ፡፡
- እኔ ጠፋሁ?
- ክቡር ሚኒስትር ሚዲያውን ካልተቆጣጠርነው አካሄዳችን ከባድ ይሆናል ብዬ ነው፡፡
- ስማ አንተ የተመደብክበትን የማማከር ኃላፊነት ትተህ ከአቅም በላይ የሆኑ ኃላፊነቶችን እየወሰድክ እኮ ነው፡፡
- ክቡር ሚኒስትር ለውጡን ለማሳለጥ ብዬ ነው እኮ?
- ታዲያ ያለንተ ሰው የለም እንዴ?
- እ. . .
- ለማንኛውም መዋጥ ከምትችለው በላይ እየጎረስክ መሆኑን ተረድተኸዋል?
- ምን አሉኝ ክቡር ሚኒስትር?
- የጎረስከው ኃላፊነት እንዳያንቅህ እፈራለሁ፡፡
- እ. . .
- ከአቅሙ በላይ የሚጎርስ ምን እንደሚባል ታውቃለህ?
- ምንድነው የሚባለው?
- ሜቴክ!
[ክቡር ሚኒስትሩ ከልጃቸው ጋር እያወሩ ነው]
- በዚህ ሰዓት ቤት ምን ታደርጋለህ?
- ምነው ዳዲ?
- ትምህርት የለም እንዴ?
- አልሄድም ዳዲ፡፡
- ለምን?
- በጣም ደብሮኛል ዳዲ፡፡
- ምኑ ነው የደበረህ?
- የተሠራውን ስለማታውቅ ነው ዳዲ፡፡
- ምን ተሠራ?
- ትምህርት ቤት አንድ አሪፍ አስተማሪ ነበር አባረሩብን፡፡
- ለምን?
- ቅናት ነዋ ዳዲ፡፡
- የምን ቅናት ነው?
- ተማሪ ሁሉ ስለሚወደው ነዋ፡፡
- ተማሪ ስለወደደው ለምን ይባረራል?
- በቃ ሁሉም ተማሪ ሲወደው አስተዳዳሪዎቹ ቀኑ መሰለኝ አባረሩት፡፡
- እንዴት እንደዚህ ይደረጋል?
- የሚገርምህ ዳዲ እኔ ትምህርት ቤታችንን ራሱ እንድወደው ያደረገኝ አስተማሪ እሱ ነው፡፡
- ምን አድርጎ ነው እንድትወደው ያደረገህ?
- ፈታ አድርጎ ነዋ የሚያስተምረን፡፡
- ምን ማለት ነው?
- በቃ በጣም እያዝናና ነው የሚያስተምረን፡፡
- የሚያስተምረው ግን ይገባህ ነበር?
- ከእሱ ውጪ እንደውም የሌሎቹ ምንም አይገባኝም፡፡
- ታዲያ እንዴት ያባርሩታል?
- የሚገርምህ ደግሞ በኅብረት ሥራ በጣም ነው የሚያምነው፡፡
- እንዴት ማለት?
- ፈተና እንኳን ተጋግዛችሁ ሥሩ ነው የሚለን፡፡
- በጣም የሚገርም አስተማሪ ነው፡፡
- ታዲያ ዳዲ እንደዚህ ዓይነት አስተማሪ መባረር ነበረበት?
- ኧረ በፍፁም፡፡
- ለእሱ እንደውም የሚገባው ዕድገት ነበር፡፡
- ልክ ብለሃል፡፡
- የትምህትርት ቤታችንን አስተዳዳሪ ብታወራቸው ደስ ይለኛል፡፡
- አሁን ነው የምደውልላቸው፡፡
- እስከዚያ ግን እኔ እቀጥላለሁ፡፡
- ምኑን?
- እምቢተኝነቴን!
[ክቡር ሚኒስትሩ የትምህርት ቤት አስተዳዳሪ ጋር ደወሉ]
- ጤና ይስጥልኝ?
- እንዴት ነህ?
- ማን ልበል?
- ክቡር ሚኒስትር ነኝ፡፡
- እንዴት ነዎት ክቡር ሚኒስትር? ምን ልርዳዎት?
- ምንድነው የምሰማው?
- ምን ሰሙ ክቡር ሚኒስትር?
- ልጄ ትምህርት ቤት አልሄድም እያለኝ ነው፡፡
- ክቡር ሚኒስትር ከትምህርት ለሚቀሩ ልጆች ወላጆች ደብዳቤ ለመጻፍ እየተዘጋጀን ነው፡፡
- ለመሆኑ ለምንድነው ተማሪ የሚወደውን መምህር የምታባርሩት?
- ይቅርታ አድርጉልኝና ክቡር ሚኒስትር መምህር የሚለው መጠሪያ ለእሱ አይገባውም፡፡
- እንዴት?
- ይኼ ሰውዬ ላለፉት አምስት ዓመታት ትምህርት ቤቱ የለየላቸው ዱርዬዎች እንዲያፈራ ዋናውን ሚና ሲጫወት የነበረ ነው፡፡
- ምን ማለት ነው?
- ክቡር ሚኒስትር ተማሪዎቹን ማስተር ሳይሆን ማበላሸት ነበር የያዘው፡፡
- ምን እያልከኝ ነው?
- በርካታ ተማሪዎች ጫት ቃሚዎችና ሱሰኞች እንዲሆኑ ከማድረጉም ባሻገር በትምህርታቸው ግድ የለሽ እንዲሆኑ አድርጓቸዋል፡፡
- ታዲያ ይኼን ሁሉ ዓመት ለምን ዝም አላችሁት?
- ክቡር ሚኒስትር ትምህርት ቤት ውስጥ የማፊያ ቡድን አደራጅቶ በጣም ይፈራ ነበር፡፡
- አሁን ምን ተገኘ?
- አሁንማ ለትምህርት ቤቱ አዲስ አስተዳደር ሆኜ ስለተሾምኩ ለውጥ እያደረግኩ ነው፡፡
- ለማንኛውም ተማሪ የሚወደውን አስተማሪ ማባረር አትችልም፡፡
- ለትምህርት ቤቱ የሚሻለውን የማውቀው እኔ ነኝ፡፡
- ስማ ያለበለዚያ እኔም ከልጆቹ ጋር መውጣቴ አይቀርም፡፡
- ምንድነው የሚወጡት?
- ሠልፍ!
[ክቡር ሚኒስትሩ ከአንድ ታዋቂ ፓርቲ ኃላፊ ጋር ተገናኝተው እያወሩ ነው]
- ክቡር ሚኒስትር አሁን ትክክለኛ ለውጥ እያረጋችሁ እንደሆነ አውቄያለሁ፡፡
- እንዴት አወቅክ?
- በቃ የምርጫ ቦርድ ላይ ያመጣችሁት ለውጥ ተቀባይነት ያለው ነው፡፡
- ዋናው እናንተ ዝግጁ ናችሁ ወይ የሚለው ነው?
- ለምኑ ነው ዝግጅቱ?
- ለምርጫው ውድድር ነዋ፡፡
- በቃ አለቀላችሁ እኮ ክቡር ሚኒስትር፡፡
- ምኑ ነው ያለቀልን?
- ምርጫ ቦርድን ነፃ ካደረጋችሁት በራሳችሁ ላይ ነው የፈረዳችሁት፡፡
- ኪኪኪ. . .
- ምን ያስቆታል?
- ፖለቲካ ወኔ ብቻ ቢሆን ኖሮ ሥልጣን ላይ ትወጡ ነበር፡፡
- ክቡር ሚኒስትር እስከ ዛሬ የመጫወቻ ሕጉ ይዞን እንጂ በዝረራ እንደምናሸንፋችሁ መቼም ያውቁታል፡፡
- እናንተ እኮ በጣም ትንሽ ፓርቲ ናችሁ፡፡
- ክቡር ሚኒስትር ትልቅ ቦታ የሚደረሰው ከትንሽ ተነስቶ ነው፡፡
- አባባሉ ለጊዜው ይቅርብህና ለምርጫው ምን ዓይነት ዝግጅት እያደረጋችሁ ነው?
- ክቡር ሚኒስትር እናንተን ያለዝግጅት ነው የምንዘርራችሁ፡፡
- የምትወዳደሩት በፕሮግራማችሁ ብቃት ነው ወይስ በጉራችሁ ብዛት?
- ክቡር ሚኒስትር እኛ ሁሌም የሕዝቡ ልብ ውስጥ ነን፡፡
- ይቅርታ አድርግልኝና እናንተ እንኳን የሕዝቡ ልብ ውስጥ ልትሆኑ ቀርቶ የራሳችሁ ልብ ራሱ ያለው ሌላ ቦታ ነው፡፡
- ምን እያሉ ነው?
- ፖለቲካውን እንደ ቢዝነስ ነው እንጂ የምታስቡት ሕዝብን ለማገልገል ቁርጠኝነቱ ያላችሁ አይመስለኝም፡፡
- ክቡር ሚኒስትር በጣም በቁርጠኝነት ነው የተነሳው፡፡
- እንደዚያ ከሆነ ለምን ተደራጅታችሁ ከእኛ ጋር በደንብ ለመፎካከር አትጥሩም?
- መደራጀት ሳይሆን መበታተን ነው የሚያዋጣው፡፡
- እ. . .
- ከተደራጀንማ ለጥቃት እንመቻለን፣ ከተበታተንን ግን ለመያዝ ስለምናስቸግር ለእናንተም ፈተና ነው የምንሆነው፡፡
- ይኼ አካሄዳችሁ ግን የትም አያደርሳሁችም?
- ይኸው እናንተ አገር እየከፋፈላችሁ አይደል እንዴ ይኼን ያህል የገዛችሁት?
- የመከርኩህን ግን ብትቀበል ጥሩ ነው፡፡
- ፈጽሞ አልቀበለውም፡፡
- እንግዲያው ዕጣ ፈንታችሁ አንድ ነው ነው የሚሆነው፡፡
- ምንድነው?
- መዋጥ!
[ክቡር ሚኒስትሩ ከሚስታቸው ጋር እያወሩ ነው]
- በጣም ደስ የሚል ዜና ልንገርህ?
- የምን ዜና?
- ለመንግሥት ልማት ድርጅት የቦርድ አባል እንድሆን ተጠየኩ፡፡
- ምን?
- ለቦርድ አባልነት ተጠየኩ፡፡
- ፈጽመሽ ጥያቄውን እንዳትቀበይ፡፡
- ለምን?
- የያዝሽው ፓስፖርት የውጭ አገር መሆኑን ረሳሽው?
- ታዲያ ምን ችግር አለው?
- ሚዲያዎቹ ወሬውን ካገኙት በኋላ ችግር ነው፡፡
- ገና ለገና ትፎካከረኛለች ብለህ ነው አይደል?
- ወሬው ከተሰማ ለእኔም ሳይቀር ችግር ነው፡፡
- እኔ ግን ሳስበው በእኔ መሾም የቀናህ መሰለኝ፡፡
- ሴትዮ መሾም ከፈለግሽ ያለሽ ምርጫ አንድ ነው፡፡
- ምንድነው?
- የውጭውን ፓስፖርት መቅደድ፡፡
- እሱንማ ከምቀድ ሌላ ነገር ብቀድ ይሻለኛለ፡፡
- ሌላ ምን?
- ሰማኒያዬን!