Thursday, June 1, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ማኅበራዊየስዊድኑ ‹‹ራዕይ ዜሮ›› በኢትዮጵያ የትራፊክ ደኅንነትን ለማስጠበቅ እንደሚረዳ ተገለጸ

የስዊድኑ ‹‹ራዕይ ዜሮ›› በኢትዮጵያ የትራፊክ ደኅንነትን ለማስጠበቅ እንደሚረዳ ተገለጸ

ቀን:

የትራፊክ ደኅንነትን በማስጠበቅና የሞት ቁጥርን በመቀነስ ከቀዳሚ አገሮች ተርታ የተሠለፈችው ስዊድን፣ የትራፊክ አደጋን ለመቀነስ የተጠቀመችበት ‹‹ራይዕ ዜሮ›› ዕቅድ ለኢትዮጵያም እንደሚረዳ ተገለጸ፡፡

በኢትዮጵያ የትራፊክ ደኅንነትና ቀጣይነት ያለው የትራንስፖርት አገልግሎት ያሉበት ፈተናና መፍትሔዎች በሚል በኢትዮጵያ የስዊድን ኤምባሲና ትራንስፖርት ሚኒስቴር ኅዳር 19 ቀን 2011 ዓ.ም. ባዘጋጁት መድረክ እንደተገለጸው፣ በኢትዮጵያ በተለይም እያደጉ ባሉት የአገሪቱ ከተሞች አሳሳቢ እየሆነ የመጣውን የትራፊክ አደጋ ለመቀነስ ስዊድን የተከተለቻቸው አሠራሮች ለኢትዮጵያ መልካም ተሞክሮ ሊሆኑ ይችላሉ ተብሏል፡፡

ከስዊድን ኤሪክሰን፣ ስካኒያ፣ እንዲሁም ከአማካሪ ድርጅቱ ስዊሮድ ባለሙያዎች በተገኙበትና ልምዳቸውን ባካፈሉበት መድረክ የተገኙት በኢትዮጵያ የስዊድን አምባሳደር ቶርቢያን ፔተርሾን እንዳሉት፣ የስዊድንን የትራንስፖርት፣ የመንገድ ደኅንነትና አቅርቦት ከዚህ ቀደም የጎበኙ የመንግሥት የሚመለከታቸው አካላት አገር ቤት ከተመለሱ በኋላ ከስዊድን ‹‹ራዕይ ዜሮ››ን ያካተተውን የትራፊክ ደኅንነት መመርያ የተወሰኑትን መተግበር መጀመራቸውን ተናግረዋል፡፡

የ‹‹ራዕይ ዜሮ›› ዓላማ የመኪና አደጋን በመቀነስ በአደጋው የሚደርስ ሞትን ዜሮ ማድረግ መሆኑን፣ ስዊድንም ይህንን ዓላማ በ2020 ከግብ ለማድረስ እየሠራች እንደምትገኝ ገልጸው፣ ዓላማው በዓለም አቀፍ ደረጃ ተቀባይነት እያገኘ መምጣቱን አመልክተዋል፡፡

አዲስ አበባም ሆነች ሌሎች አካባቢዎች እያደጉ መምጣታቸውን፣ ከዚህ ዕድገት ጋር ተያይዞ ሊመጡ የሚችሉ የመኪና አደጋዎችን ለመቀነስና ቀጣይነት ያለው የትራንስፖርት አገልግሎት ለማቅረብ በስዊድንና በኢትዮጵያ በኩል የተጀመረው ትብብር ለውጥ እንደሚያመጣና የትራንስፖርት ዘርፍ ችግሮችን ለመፍታት እንደሚያስችል ተናግረዋል፡፡

የመንገድ ደኅንነትን፣ የትራፊክ ሥርዓትን፣ ሥነ ምግባርን፣ መንጃ ፈቃድ አሰጣጥንና በአጠቃላይም ከትራንስፖርት አገልግሎት ጋር ተያይዞ የሚከሰት ሞትንና የአካል ጉዳትን ዜሮ የማድረግ ዓላማ ያለው ‹‹ራዕይ ዜሮ›› በስዊድን ተግባራዊ መደረጉ ለስዊድን ለውጥ እንዳመጣው ሁሉ፣ በኢትዮጵያም በትራፊክ አደጋ የሚደርስ ሞትን ለመቀነስ እንደሚያግዝ፣ ይህንንም ራዕይ ኢትዮጵያ በሕጎቿ ማዕቀፍ በተስማሚ መልኩ አካታ እንድትሠራ የስዊድን ኤምባሲ እየተባበረ እንደሚገኝ በኤምባሲው የንግድና ፕሮሞሽን ክፍል ከፍተኛ ኦፊሰር አቶ ሙራድ አብድራህማን ኢሳ ተናግረዋል፡፡

የትራንስፖርት ሚኒስቴር ሚኒስትር ዴኤታ ወ/ሮ ሕይወት ሞሲሳ በበኩላቸው፣ የስዊድን መንግሥት ባደረገው ጥረት የተሳካ ሥራ አከናውኖ ሕዝባቡ በመኪና አደጋ እንዳይሞት ማድረግ መቻሉን፣ የመኪና ኩባንያዎቹም ዓለም አቀፍ ደኅንነትን የሚያስጠብቅ ምርት በማውጣት ተወዳዳሪ መሆናቸውንና ይህንን ለማድረግ በርካታ ዓመታት እንደፈጀ በማስታወስ፣ የትራፊክ ፍሰቱ ዝቅተኛ በሆነበት፣ የመንገድ ግንባታ እየተካሄደ ባለበትና ኢኮኖሚው እያደገ በሚገኝበት በአሁኑ ወቅት በኢትዮጵያም የስዊድን ተሞክሮ  በሚያመች መልኩ ተወስዶ ይሠራል ብለዋል፡፡

በኢትዮጵያ አደግ ባሉና በማደግ ላይ ባሉ ከተሞች የሚደርሰው አደጋ ተለያይነትን በማውሳትም፣ ይህንን ችግር ለመፍታት በጥናት የተደገፈ ሥራ እየተሠራ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

በአዲስ አበባ ከትራንስፖት አቅርቦት፣ ከመንገድ ተጠቃሚና ከተያያዥ ጉዳዮች ጋር ተያይዞ ከስምንት በላይ ጉዳዮች በጥናት ተደግፈው መሰራታቸውን፣ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር እየሠራባቸው ያሉ ጉዳዮች እንዳሉ ሆነው ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ አዲስ አበባ ላይ የሚታየው ችግር ሌሎች ከተሞች ላይ እንዳይደገም የኢትዮጵያ የከተማ የትራንስፖርት እንቅስቃሴ ምን ዓይነት አቅጣጫ ይያዝ በሚለው ዙሪያ ጥናት ተደርጎ በፖሊሲ እንዲደገፍ ወደ መንግሥት የማቅረብ ሒደት ላይ መሆኑንም ተናግረዋል፡፡

የሕግ፣ የአሠራርና የደረጃ ማሻሻያዎች እንዲደረጉ ጥናት እየተደረገ መሆኑንና ከስዊድን ልምድ ተቀስሞም ለጥናቱ ግብዓት እንደሚሆን ወ/ሮ ሕይወት አክለዋል፡፡

የአዲስ አበባ ተገልጋይን የሚመጥን የትራንስፖርት አገልግሎት አለመኖሩን በተመለከተም፣ የከተማዋን የትራንስፖርት ችግር ለመፍታት በርካታ አማራጮች መጠቀም እንደሚገባና፣ የብዙኃን ትራንስፖርት በዋነኝነት ችግሩን ይፈታል ተብሎ እንደተገመተ ተናግረዋል፡፡ በዚህ ውስጥ በኤሌክትሪክ የሚሠሩ አውቶብሶችንና ባቡሮችን ማስገባት፣ ይህ ሲሆን ደግሞ ከዲዛይን ጀምሮ ከተማ ውስጥ ብዙ መፈታት ያለባቸው የግንዛቤና በአገልግሎቶች ዙሪያ ያሉ ችግሮችን እየተፈቱ መሄድ ቀጣይ ስራ ነው ብለዋል፡፡

የአዲስ አበባን የትራንስፖርት ችግር የመፍታት ሥራው ሚኒስትር መሥሪያ ቤቶች በ100 ቀናት እንዲፈጸሙ ባቀረቡት ዕቅድ የተካተተ ሲሆን፣ በዚህም የባቡር ትራንስፖርት ችግርን መፍታት፣ የትራፊክ ማኔጅመንትን ማሻሻል፣ የሕዝብ ትራንስፖርትን መጨመር፣ ሕግን ማስከበር፣ በሥነ ምግባር በኩል ያሉ ችግሮችን መፍታትና የታክሲ ትራንስፖርት ሥምሪትን ማሻሻል ከ100 ቀን ዕቅድ ውስጥ ገብቶ እየሠራንበት ነው ብለዋል፡፡    

ከፌዴራል ትራንስፖርት ባለሥልጣን የመንገድ ደኅንነት ትምህርትና ግንዛቤ ዳይሬክቶሬት ክፍል የተገኘ መረጃ እንደሚያሳየው፣ በኢትዮጵያ 2005 .. እስከ 2009 .. ድረስ 215,531 አደጋዎች የደረሱ ሲሆን፣ ከዚህም ውስጥ 149,918 አደጋዎች የደረሱት በአሽከርካሪዎች ነው፡፡ አደጋውን ያደረሱትም 2009 .. ብቻ ከደረሱት 38,450 አደጋዎች ውስጥ 18,000 በላይ የደረሰው ዕድሜያቸው 18 እስከ 30 ዓመት በሆኑ ወጣት አሽከርካሪዎች ነው፡፡

አደጋ ያደረሱ አሽከርካሪዎች በትምህርት ደረጃ ሲታዩ 2009 .. ከተከሰቱት መካከል ወደ 21,311 የሚሆነው አደጋ ያደረሱት ከአንደኛ እስከ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት የተማሩ ናቸው፡፡

2005 .. እስከ 2010 .. ድረስ በትራፊክ አደጋ የደረሰው የሞት መጠን 33.22 በመቶ፣ ከባድ የአካል ጉዳት 48.47 በመቶ ጨምሯል፡፡ አምስት ቢሊዮን ብር የሚገመት ንብረት ወድሟል፡፡ ይህም ለሰው የሚከፈለውንና ኢንሹራንሶች ለቶታል ዳሜጅ እያሉ የሚከፍሉት ሳይቆጠር ነው፡፡   

2009 .ምን በማሽከርከር የዕድሜ ገደብ አኳያ ሲታይ ከደረሱ አደጋዎች ውስጥ ከፍተኛውን ደረጃ ይዘው የሚገኙት መንጃ ፈቃድ ካወጡ እስከ አምስት ዓመት ድረስ ያሽከረከሩ ናቸው፡፡ ይህም ማለት ወደ 18,652 የሚሆኑ አደጋዎች የተመዘገቡት በእነዚህ አሽከርካሪዎች ነው፡፡ ከአንድ እስከ ሁለት ዓመት ያገለገሉም እጅግ በጣም ከፍተኛውን ቦታ ይዘው ይገኛሉ፡፡

የትራፊክ አደጋ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ ለመምጣቱ እንደ መንስዔ ከሚጠቅሱት ውስጥ የመንጃ ፈቃድ አሰጣጥ ሥርዓት አንዱ ነው፡፡ ይህንና ተያያዥ ችግሮችን ለመፍታት ስዊድን ከኢትዮጵያ ጋር የጀመረችው ትብብር ተስፋ ተጥሎበታል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የአዛርባጃንን ብሄራዊ ቀን በአዲስ አበባ በድምቀት ተከበረ

የአዛርባጃን ኤምባሲ  የአዛርባጃንን ብሄራዊ ቀን በትላንትናው ዕለት አከበረ። ሰኞ...

የመንግሥትና የሃይማኖት ልዩነት መርህ በኢትዮጵያ

እንደ ኢትዮጵያ ባሉ አገሮች የሃይማኖት ተቋማት አዎንታዊ ሚና የጎላ...

ሐበሻ ቢራ ባለፈው በጀት ዓመት 310 ሚሊዮን ብር የተጣራ ትርፍ ማግኘቱን አስታወቀ

የአንድ አክሲዮን ሽያጭ ዋጋ 2,900 ብር እንዲሆን ተወስኗል የሐበሻ ቢራ...