የኢትዮጵያ ሕክምና ማኅበር በ2.4 ቢሊዮን ዶላር ለ7,000 የሕክምና ባለሙያዎች በአዲስ አበባ ቤት፣ ባለአምስት ኮከብ ሆቴል፣ ሪዞርትና መናፈሻ ያካተተ መንደር እንደሚያሠራ አስታወቀ፡፡
የማኅበሩ ፕሬዚዳንት ዶ/ር ገሚቺስ ማሞ እንደገለጹት፣ የግንባታው ሥራ የሚከናወነው በሁለት ዕርከን ሲሆን፣ በመጀመርያው ዕርከን የሚከናወነው የመኖሪያ ቤቶች ግንባታ ነው፡፡
የቤቶቹ ግንባታ ከተጠናቀቀ በኃላ በሁለተኛ ዕርከን የሆቴል፣ የሪዞርትና የመናፈሻ ግንባታ እንደሚቀጥል አስረድተዋል፡፡
የመኖሪያ ቤቶቹ ግንባታ ለ30,000 ሰዎች የሥራ ዕድል እንደሚፈጥርና ግንባታውም በሁለት ዓመት ውስጥ እንደሚጠናቀቅ ዶ/ር ገመቺስ ተናግረዋል፡፡ ግንባታውንም የሚያካሂደው ቱርክ የሚገኘው ‹‹አክናሊ›› የተባለ ኮንስትራክሽን ኩባንያ ሲሆን፣ ለሕክምና ባለሙያዎችም የሚከፋፈለው በግዥ ነው፡፡ ግዥውም የሚፈጸመው በረዥም ጊዜ በሚከፈል ብድር መሆኑን አስታውቀዋል፡፡
የአዲስ አበባው የመንደር ግንባታ ከተጠናቀቀ በኋላ በእያንዳንዱ ክልል ርዕስ ከተማ ቢያንስ ለ500 የሕክምና ባለሙያዎች የሚውል መኖሪያ ቤት የመገንባት ዕቅድ መኖሩንም ዶ/ር ገመቺስ ተናግረዋል፡፡
ለአዲስ አበባ ግንባታ የሚውለው ቦታ የካ ተራራ አካባቢ እንደሚገኝ፣ ይህን ሐሳብ የጤና ጥበቃ ሚኒስትር ዶ/ር አሚር አማንና የአዲስ አበባ ከተማ ምክትል ከንቲባ ኢንጂነር ታከለ ኡማ በደስታ እንደተቀበሉትና በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የሳይት ጥናት የሚያደርግ ባለሙያ፣ በጤና ጥበቃ ሚኒስቴር ደግሞ የፕሮጀክት ቢሮ እንደተቋቋመ ዶ/ር ገመችስ ተናግረዋል፡፡
የማኅበሩ ምክትል ፕሬዚዳንት ዶ/ር ብርሃኑ ነጋ የማኅበሩ የሕግ አማካሪና የጤና ጥበቃ ሚኒስቴር የሕግ ባለሙያ ከአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የሕግ ክፍል ጋር በመተባበር የቤቶቹ ግንባታ የሕግ አካሄድ ምን መሆን አለበት የሚል የመግባቢያ ሰነድ ስምምነት በማርቀቅ ላይ መሆናቸውንም ገልጸዋል፡፡
ድርጅቱ ይህን መሰል የመኖሪያ ቤት ግንባታ የማካሄድ የቆየ ልምድ እንዳለው፣ ቀደም ሲል በዴሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎና በኡጋንዳ ለሕክምና ባለሙያዎች የመኖሪያ ቤቶችን ሠርቶ እንዳስረከበና በቅርቡም ሱዳን ውስጥ ስምንት ሆስፒታሎችን በ1.4 ቢሊዮን ዶላር ለመሥራት የሚያስችል ስምምነት መፈራረሙን ምክትል ፕሬዚዳንቱ ተናግረዋል፡፡
ኅብረተሰቡን በተለያዩ የሙያ ዘርፎች በማገልገል ላይ ያሉ 3,000 ኢትዮጵያውያን ሐኪሞችን ያቀፈው የኢትዮጵያ ሐኪሞች ማኅበር የተቋቋመው ከ55 ዓመት በፊት በ1956 ዓ.ም. ነው፡፡
ማኅበሩ ‹‹ሁሉን አቀፍ የጤና ሽፋንን ማዳረስ የኢትዮጵያ ተሞክሮ›› የሚል መሪ ቃል የሚኖረው ከየካቲት 16 ቀን እስከ የካቲት 17 ቀን 2011 ዓ.ም. ድረስ የሚቆይ ኮንፈረንስና ዓለም አቀፍ የጤና ኤግዚቢሽን ያካሂዳል፡፡
ገርጂ በሚገኘው የወጣቶች ስፖርት አካዴሚ አዳራሽ በሚከናወነው በዚሁ ዝግጅት ላይ ወደ 50 የሚጠጉ የምርምር ጽሑፎች ይቀርባሉ ተብሎ ይጠበቃል፡፡