Sunday, September 25, 2022
ሌሎች ዓምዶች
  - Advertisement -
  - Advertisement -
  ማኅበራዊአነጋጋሪው ጉዲፈቻ

  አነጋጋሪው ጉዲፈቻ

  ቀን:

  ከሰውነት ተራ ያወጣት ሕመሟ ደጋግሞ ሲደቁሳት ቆይቷል፡፡ አንዴ በወጉ እንዳትራመድ እግሯን ሲሸመቅቅ፣ ሲለው ደግሞ ውስጥ አፏን እያቆሰለው እንዳትናገር እንዳትጋገር ሲያደርጋት አትደናገጥም፡፡ ምች ይሆናል ሲሏት በአፍንጫዋ ዳማከሴ ትወሽቃለች፣ ቀላል ራስ ምታት ሲመስላት አናቷን በሻሽ ሸብ ከማድረግ ባለፈ በትክክል በሽታዋ ምን እንደሆነ ታክማ ለማወቅ ሙከራ አታደርግም፡፡ የምትተኛውም ከአቅም በላይ ሆኖ ለመንቀሳቀስ ያስቸገራት እንደሆነ ነው፡፡

  ይህ ነው የሚባል ቋሚ ገቢ የላትም፡፡ የተለያዩ ሰዎች ቤት ተቀጥራ የምትሠራ ሲሆን፣ ‹‹ሚሚ›› እያለ የሚጠራትን የአራት ዓመት ልጇንና የእሷን ጉሮሮ ለመሸፈን እንኳ በወር የምታገኘው በቂዋ አይደለም፡፡ የሚፈራረቅባት ሕመም እንደ ልብ ከመሥራት ስለሚያግዳት ብዙዎች ሚሚን ቀጥሮ ለማሠራት ፍላጎቱ የላቸውምና ባላት አቅም ያገኘችውን ከመሥራት ወደ ኋላ አትልም፡፡ ስለዚህም ሕመሟን ለማስታመም ጊዜ የላትም፡፡

  የልጇ አባት ሌላ አግብቶ የሚኖር ሲሆን፣ አባትነቱንም ክዷል፡፡ አጋጣሚው ቢያሳዝናትም ከመበሳጨት ባለፈ ምንም አላደረገችም፡፡ ልጇ ባይኖር ወጥታና ወርዳ ኑሮዋን ማቅናት እንደምትችል ይሰማት ነበር፡፡ ለልጇ ፍፁም የሆነ ፍቅር ቢኖራትም በአንድ መልኩ ደግሞ የድህነታቸው ምክንያት እሱ ይመስላታል፡፡ የእናትና ልጅ ትስስር ግን እንኳንስ ድህነት ምጥን የመሰለ ስቃይ የማይበግረው ነውና አትጨክንበትም፡፡ እንቅፋት ብለ ብታባርረውም ተመልሶ እሷ ሥር ነው፣ ለውድቀቴ ምክንያት ነው ብትለውም እናሳድግልሽ ለሚሏት ጨክና አትሰጠውም፡፡ ችግሯን ያዩ ልጅሽን ውጭ አገር እንውሰደው ሲሏት ልጇ ውጭ ሲኖር እንዴት ሊደላው እንደሚችል ታስብና ደስ ቢላትም ውሰዱት ግን ለማለት ድፍረቱ የላትም፡፡ እንዲያውም ትምህርት ቤት ሲሄዱ መንገድ ላይ አግኝተው ይወስዱት ይሆን የሚል ጭንቀት ስለሚያድርባት ከእይታዋ እንዲርቅ አትፈልግም፡፡ ውጭ ቢወጣላት ለእሷም እረፍት ለእሱም የተሻለ እንደሆነ እየተሰማት ለመወሰን ስታወላውል ነው ድንገት ሁሉንም ጣጥላ የሚያስጨንቃትን የልጇን ሕይወት መስመር ሳታስይዝ የሞተችው፡፡

  ወላጅ በተለይም እናት ለልጇ ያላት ፍቅር በቀመር የማይገለጽ፣ በምክንያት የማይተማመኑበት፣ ድህነት የማይበጥሰው ጠንካራ ትስስር ነው፡፡ ልጅ ከነገሮች ቁጥብ፣ ፈሪ፣ የሚያደርግ ከፈሱ የተጣለ የሚባለውን ሳይቀር ወኔ ቢስ ያደርጋል፡፡ ጨካኙን ሩህሩህ፣ ጨዋውን ሌባም ሊያደርግ ይችላል፡፡ ልጅ ዓይንን በዓይን ከማየት ባለፈ ብዙ ነገር ማለት ነው፡፡ የልጅ ፍቅር የወለዱ ብቻ የሚያውቁት የመውደድ ጥግ ነው፡፡ በአስከፊ ድህነት ውስጥ ሆነው እኔ ለልጄ አላንስም ብሎ ራስን መሸወድም ሊሆን ይችላል፡፡ ወይም ደግሞ ልክ እንደ ‹‹ሚሚ›› ቀላል ውሳኔ ለመወሰን መቸገር ነው፡፡ ይኼንን የመሰለው ትስስር መኖር ስንክሳሩ ለበዛበት ዓለም ተስፋ፣ መላላቱ ደግሞ በተቃራኒው ጨለማ ሊሆን ይችላል፡፡

  ድህነታቸው በልጃቸው ላይ ድል የነሳቸው በብጣሽ ወረቀት ላይ ፈርመው ልጃጀውን ለሌላ አሳልፈው ሲሰጡ ሞታቸውን እየተመኙ ይሆናል፡፡ በመታቀፊያ ውስጥ ሆኖ የሚያለቅስ ልጇን ሆስፒታል በር ላይ ጥላው ስትሄድ ራሷን ማጥፋት ከጅሏትም ይሆናል፡፡ ምክንያቱም የራስን ልጅ አሳልፎ መስጠት ከተፈጥሮ ጋር የመጋጨት ያህል ከባድ ነው፡፡ ብዙዎቹ ድህነት የተጫናቸው ወላጆች ልጃቸውን ለሀብታም ሰጥተው የተሻለ ነገ ሊሰጡት እንደሚችሉ ቢያውቁም ወደ ኋላ የሚጎትታቸው በቀላሉ የማይበገረው የልጅ ፍቅር ነው፡፡

  በተቃራኒው ደግሞ ችግራቸው ከምንም በላይ የሆነባቸው ግን በአጋጣሚዎች ተገደው ልጃቸውን አሳልፈው ሲሰጡ፣ አስፋልት ዳር ጥለውት ሲጠፉ ይታያል፡፡ ልጆች በቆሻሻ ገንዳ አካባቢ፣ ቱቦ ውስጥ፣ ሆስፒታል፣ ቤተ ክርስቲያን በር ላይ ተጥለው ይገኛሉ፡፡ ‹‹እኛ ልጅ ከእናት አንቀበልም ድጋፍ እንዲደረግለት ነው የምናደርገው፡፡ ለልጅ ምቹ ቦታ እናት ነች፤›› የሚሉት በአዲስ አበባ ሴቶችና ሕፃናት ቢሮ የሕፃናት ድጋፍ አገልግሎት ኢንስፔክሽን ዳይሬክተር ወ/ሮ ገነት ጴጥሮስ ያጋጠማቸውን እንዲህ አስታውሰዋል፡፡ ‹‹የካቲት 12 ሆስፒታል ወልዳ ቀጥታ እኛ ጋር ነው የመጣችው፡፡ ውሰዱልኝ ስትል ያለውን አሠራር ነገርናትና አይሆንም አልናት፡፡ ከዚያ ግቢ ውስጥ የሚገኝ ፒክአፕ መኪና ላይ ጥላው ሄደች፤››

  አብዛኞቹ እናቶች ልጃቸውን የሚጥሉት ድህነት አስገድዷቸው ነው፡፡ ከገጠር ሰው ቤት ተቀጥሮ ለመሥራት ወደ አዲስ አበባ የሚመጡ ሴቶች በደላላ፣ በአሠሪዎቻቸውና በሌሎች ተገደው ይደፈሩና ያረግዛሉ፡፡ ብዙዎቹ ተደፍረው ሲያረግዙ ምን ማድረግ እንዳለባቸው እንኳ አያውቁም፡፡ ጽንስ ማቋረጥ ቀርቶ ማርገዛቸውን እንኳ በውል የማያውቁም ያጋጥማሉ፡፡ እነዚህ ወልደው የማሳደግ አቅሙ የላቸውም፡፡ ከዚህ ባለፈ ደግሞ ልጅ ስላላቸው ብቻ ቀጥሮ ለማሠራት ወገቤን የሚሉ ብዙ ናቸው፡፡

  ‹‹ልጅ ያላትን ሴት ሠራተኛ አድርጎ የመቅጠር ፍላጎት ያለው የለም፡፡ አዝዬው ልብስ ልጠብ ብትል እንኳ የማያሳጥባት ብዙ ሰው አለ፡፡ ተከራይቶ ለመኖር የቤት ኪራይ ይቸግራታል፡፡ ልጇንስ ምን ታብላው ምን ታጠጣው? ይህቺ ሴት ምን ማድረግ አለባት?›› የሚሉት ወይዘሮ ገነት ልጅን ለመጣል ተቀባይነት ያለው ምክንያት ባይኖርም የሚገቡበት አጣብቂኝ ለማንም ከባድ እንደሆነ የታዘቡትን ገልጸዋል፡፡

  ሕፃናትን የማሳደግ ቀዳሚ ኃላፊነት በሕግ የሚጣለው በወላጆች ላይ ነው፡፡ ስለዚህም ልጆቻቸውን አውጥተው የሚጥሉ ወላጆች የሕግ ተጠያቂነት አለባቸው፡፡ ‹‹እስካሁን እናቶች ናቸው ልጆቻቸውን ሲጥሉ ያየነው፡፡ ይህ ማለት ግን አባቶች ልጆች አይጥሉም ማለት አይደለም፡፡ ልጆቻቸውን ክደው የሚጠፉ፣ ቀለብ የማይቆርጡ አባቶች ብዙ ናቸው፤›› የሚሉት የአዲስ አበባ ሴቶችና ሕፃናት ቢሮ ምክትል ዳይሬክተር ወይዘሪት ሜሮን አራጋው፣ እናቶች ልጆቻቸውን እንዲጥሉ የአባቶችም እጅ እንዳለበት ይናገራሉ፡፡ ልጆቻቸውን ጥለው የተገኙ ወላጆች በፖሊስ ተገቢው ምርመራ ተደርጎባቸው በሕግ እንዲጠየቁ ይደረጋል፡፡

  ‹‹የሚጥሏቸው ሳይፈልጉ የሚወልዷቸውን ሕፃናትን ነው፡፡ ልክናቸው እያልኩ አይደለም ነገር ግን ተደፍረው የሚወልዱ ልጆቻቸውን ነው በብዛት ሲጥሉ የሚታዩት፡፡ የአዕምሮ ሕመም ያለባቸው እናቶችም እንዲሁ ልጆቻቸውን ጥለው ሊሄዱ ይችላሉ፡፡ በድህነት ምክንያት የሚያደርጉትን ሲያጡ ለመጣል ይወስናሉ፤›› ሲሉ የታዘቡትን ያስረዳሉ፡፡

  አብዛኞቹ ሴቶች በኢኮኖሚ ራሳቸውን ያልቻሉ የባሎቻቸው ጥገኛ መሆናቸው ይህም በራሳቸው እንዳይወስኑ ነፃነታቸውን የሚነፍግ ነው፡፡ አባት ልጁን ሲክድ ልጅ የማሳደግ ኃላፊነት በደሃዋ እናት ጫንቃ ላይ ሲያርፍ ልጅ የማሳደግ ፈተናው ከባድ ይሆናል፡፡ በዚህ ላይ ተንቀሳቅሶ ለመሥራት ልጅ እንቅፋት ሲሆን፣ አውጥቶ ለመጣል የመጀመሪያው ምክንያት ይሆናቸዋል፡፡ ከዚህም ባሻገር ሳታገባ ወለደች በሚል ማኅበረሰቡ እንዳያሽሟጥጣቸው ወልደው መጣልን የሚመርጡም አሉ፡፡

   በዚህ መልኩ ተጥለው የተገኙ ልጆች እንዴት መያዝ እንዳለባቸው የሚያሳየው ጋይድ ላይን አምስት ዓይነት አማራጮችን አዘጋጅቷል፡፡ አንደኛው የማኅበረሰብ አቀፍ ድጋፍና እንክብካቤ ነው፡፡ ሕፃናት በደብተር ዕጦት፣ በልብስ ዕጦት፣ በምግብ ዕጦት ከማኅበረሰቡ አፈንግጠው እንዳይወጡ ባሉበት ከችግራቸው የሚላቀቁበት ድጋፍ ይደረግላቸዋል፡፡ በዚህ መስክ የትምህርት ቤት ምገባና የትምህርት ድጋፍን ማንሳት ይቻላል፡፡ ፕሮግራሙ ምን ያህል ልጆችን መድረስ ችሏል የሚለው አጠያያቂ ቢሆንም እንደ አማራጭ ከተቀመጡት ውስጥ ነው፡፡ ‹‹በስፋት እንዲሠራ የምናደርገው ይህንን ፕሮግራም ነው፡፡ በዚህ ምክንያት ከማኅበረሰቡ የወጡ ሕፃናትን መልሰን ወደ ማኅበረሰቡ እናቀላቅላለን፤›› ብለዋል ዳይሬክተሯ፡፡     

  ልጆች በተቋም እንዲኖሩ የሚደረገው ከጎዳና ሕይወት ስለሚሻል ነው፡፡ ልጆችን በተቋም እንዲኖሩ ማድረግ የመጨረሻው አማራጭ ሲሆን፣ ወደ ማኅበረሰቡ መልሶ መቀላቀል ቅድሚያ የሚሰጠው ተግባር ነው፡፡ ስለዚህም እነኚህ ሕፃናት በቤተሰብ ውስጥ እንዲያድጉ ወደ ማኅበረሰቡ መመለስ ዓይነት አማራጭ ነው፡፡

  ልጆች በአደራና በጉዲፈቻ መልክ በቤተሰብ ውስጥ እንዲያድጉ ማድረግ  አንደኛው አማራጭ ነው፡፡ እንዲሁም ፍላጎቱ ኖሯቸው ግን ልጅ ለማሳደግ አቅሙ የሌላቸው በሴቶችና ሕፃናት ቢሮ በሚደረግላቸው ድጎማ ልጁ በአደራ ቤተሰብ ውስጥ ገብቶ እንዲኖር የሚደረግበት ነው፡፡ የሚደረገው ድጎማ ምን ያህል ይሁን የሚለው ገና ያልተወሰነ ቢሆንም ቢሮው ለአንድ ልጅ 2,000 ብር እንዲከፈል የሚል ነጥብ በምክረ ሐሳብ ደረጃ አቅርቧል፡፡ አጋጣሚው ከማህበረሰቡ የተገለሉ ሕፃናት ቤተሰብ ውስጥ ገብተው እንዲያድጉ ከማድረግ ባለፈ ቤት ለሚውሉ እናቶችም የሥራ ዕድል መፍጠር ነው፡፡

  እንደ ዳይሬክተሯ ገለፃ፣ አሠራሩ የሚተዳደርበት መመርያ የፀደቀ ሲሆን፣  አስፈላጊው በጀትም በካፒታል በጀት ተይዟል፡፡ በዚህ ዘርፍ እንዲሳተፉ ከተመለመሉ እናቶች መካከል ከ20 በላይ የሚሆኑት የተለያዩ ቅድመ ሁኔታዎችን አጠናቅቀው ፕሮግራሙ እስኪጀመር በመጠባበቅ ላይ ይገኛሉ፡፡ ‹‹የፀደቀ በጀት አለን፡፡ ነገር ግን አፈጻጸሙ እንዴት ይሁን? እንዴት ይውጣ እንዴት ይግባ የሚለው ነው ያቆየን፤›› የሚሉት ወ/ሮ ገነት ለዚሁ ተግባር ለአንድ ዓመት አንድ ሚሊዮን ብር በጀት እንደተያዘ፣ ገንዘቡ የቻለውን ያህል ሕፃናቱ በቤተሰብ ውስጥ እንዲያድጉ የማድረግ ሥራ እንደሚሠሩ ገልጸዋል፡፡

  ከዚህ አምልጠው ወደ ተቋም የሚገቡ ሕፃናትን ደግሞ በአደራና በጉዲፈቻ በቤተሰብ ውስጥ እንዲገቡ ይደረጋል፡፡ በእነዚህ አማራጮች ውስጥ መካተት ያልቻሉ ደግሞ በተቋም ውስጥ እንዲያድጉ ይደረጋል፡፡ በተቋም እንዲያድጉ ሲደረግ ግን የሕግ፣ የጤና፣ የትምህርትና ሌሎችም መሠረታዊ ድጋፎች ተሟልተውላቸው ነው፡፡ በአሁኑ ወቅት በአዲስ አበባ ውስጥ በመንግሥት የሚተዳደሩ ሦስት የሕፃናት ማሳደጊያና አንድ የማገገሚያ (ሪሀብሊቴሽን) ማዕከል፣ 30 የሚሆኑ የግል የሕፃናት ማሳደጊያ ተቋማት ይገኛሉ፡፡

  በመንግሥት ሥር የሚገኙ የሕፃናት ማሳደጊያ ተቋማት መካከል አንዱ በሆነው በክበበ ፀሐይ የሕፃናት ማሳደጊያ ተቋም ከዜሮ እስከ ስምንት ዓመት ድረስ ባለው የዕድሜ ክልል ውስጥ የሚገኙ ሕፃናት እንዲቆዩ ይደረጋል፡፡ በአሁኑ ወቅት በተቋሙ 174 ህፃናት መኖራቸውን የሚናገሩት የማዕከሉ ተወካይ አቶ ይድነቃቸው ንጉሤ ናቸው፡፡

  ስምንት ዓመት ሲሞላቸው ወንዶች ወደ ኮልፌ የወንዶች ሕፃናት ማሳደጊያ ይገባሉ፡፡ ሴቶቹ ደግሞ ወደ ቀጨኔ ሴት ሕፃናት ማሳደጊያ ይዛወራሉ፡፡ በቀጨኔ 200 ሴቶች፣ በኮልፌ 200 ወንዶች ይገኛሉ፡፡ ወደ ሪሀብሊቴሽን ማዕከል እንዲገቡ የሚደረጉት ከዘጠኝ እስከ 15 ዓመት የዕድሜ ክልል ውስጥ የሚገኙ በወንጀል ነክ ጉዳዮች ውስጥ ተሳትፈው የተገኙና በሕግ ሒደት ውስጥ የሚገኙ ታዳጊዎች ናቸው፡፡ በአሁኑ ወቅት ከ80 በላይ የሚሆኑ ታዳጊዎች በሪሀብሊቴሽን ማዕከሉ ይገኛሉ፡፡

  አሳዳጊ የሌላቸውና ከማኅበረሰቡ የወጡ ሕፃናትን በአደራና በጉዲፈቻ መልክ ተመልሰው ወደ ማኅበረሰቡ እንዲቀላቀሉ ማድረግ ቅድሚያ የሚሰጠው ቢሆንም ወላጅ ሲገኝ ለወላጅ መመለስ ዋናው ጉዳይ ነው፡፡ ‹‹ወላጅ ልጁን የሚጥለው በአጋጣሚዎች ተገፍቶ ነው፡፡ እናት ልጇን ለምን ጠላች ብለን አንወቅሳትም፡፡ እናት ወዳ ልጇን አትጥልም፡፡ በቦታው ስላልነበርን መውቀስ የለብንም፡፡ በድርጊቷ ተጸጽታ ከመጣች ለእናት ነው አሳልፈን የምንሰጠው፤›› የሚሉት ወይዘሮ ገነት የቱንም ያህል ደሀ ብትሆን እናት ለልጇ ውድድር ውስጥ የማትገባ አማራጭ እንደሆነች ይናገራሉ፡፡  

  ተጸጽተው ልጃቸውን ፍለጋ ወደ ተቋማት በፈቃዳቸው ከሚሄዱ እናቶች ባሻገር በፖሊስ ምርመራ የሚያዙም ይኖራሉ፡፡ ነገር ግን ልጅነቱን ካላመኑ በስተቀር ፍርድ ቤት ልጅ እንዲረከቡ አያስገድዳቸውም፡፡ ልጃቸውን በአጋጣሚዎች ተገደው የሚጥሉ እናቶች ለፍርድ ቤት በሚሰጡት የእምነት ቃል እናት መሆናቸው ሲረጋገጥ ልጃቸውን እንዲወስዱ ይደራጋል፡፡ በዓመት በአማካይ እስከ ሦስት ልጆች በዚህ መልኩ ወደ ቤተሰቦቻቸው እንዲቀላቀሉ ይሆናል፡፡

   ሕፃናትን ከወላጆቻቸው መልሶ ማገናኘት ካልተቻለ አይነተኛው መፍትሄ ፍላጎቱና አቅሙ ላላቸው ሰዎች በጉዲፈቻ መስጠት ነው፡፡ ሕፃኑ በጉዲፈቻ ቤተሰቦቹ ላይ ሙሉ የልጅ መብትና ግዴታ ኖሮት የሚያድግበት ይህ ሥርዓት የውጭና የአገር ውስጥ በሚል ለሁለት ይከፈላል፡፡ ጉዲፈቻ በኢትዮጵያ የረዥም ጊዜ ታሪክ ያለው ቢሆንም ያንን ያህል ግን የዳበረ አይደለም፡፡ የአገር ውስጥ ጉዲፈቻ በተለያዩ ምክንያቶች ከውጭ ጉዲፈቻ የሚመረጥ ቢሆንም በርካታ ሕፃናት ወደ ውጭ ይላኩ ነበር፡፡ ይህም የሆነው አብዛኞቹን በተቋም ውስጥ የሚገኙ ሕፃናትን በማደጎ የሚወስዱት ምዕራባውያን ስለሆኑ ነው፡፡ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የውጭ ጉዲፈቻ በመዘጋቱ በተቋም ውስጥ የሚኖሩ ህፃናት ቁጥር አለወትሮው ጨምሯል፡፡ 

  የውጭ ጉዲፈቻን የሚከለክለው አዋጅ ሲወጣ ‹‹ትውልድ ኢትዮጵያዊ የሆኑ ልጆችን በጉዲፈቻ መውሰድ አልቻሉም፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ የሚኖሩ ነገር ግን የሌላ አገር ፓስፖርት ያላቸው ሰዎችም ልጅ ማሳደግ እንፈልጋለን ብለው የሚመጡንም ማስተናገድ አልተቻለም፡፡ የአፈጻጸም መመርያው እስካሁን አልመጣም፡፡ ስለዚህ የውጭ ጉዲፈቻ ስለተዘጋ እነዚህንም ሰዎች ማስተናገድ አልቻልንም፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ የሚኖሩ ትውልደ ኢትዮጵያውያንን እንኳ አናስተናግድም፡፡ አቅም ያለው ባህላቸውን፣ ቆዳ ቀለማቸውን የሚጋራ ኢትዮጵያዊ የሌላ አገር ፓስፖርት ስለያዘ ብቻ ጉዲፈቻ መከልከል የለበትም፡፡ ዳያስፖራው በአገሩ ልማት ቀጥተኛ ተሳታፊ ነው እያሉን በዚህ በኩል ደግሞ ዞር ብለን ልጅ ማሳደግ አትችልም ማለት ተገቢ አይደለም፡፡ እስካሁን በመቶዎች የሚቆጠሩ ዳያስፖራዎች የጉዲፈቻ ጥያቄ ቢያቀርቡም ማስተናገድ አልቻለም ብዙ ሮሮ አለ፤›› የሚሉት ወይዘሮ ገነት አዋጁ መፈተሽ አለበት ይላሉ፡፡

  ከአዲስ አበባ ብቻ በዓመት እስከ 500 የሚሆኑ ሕፃናት በጉዲፈቻ ወደ ውጭ ይወጣሉ፡፡ ለምሳሌ በ2007 ዓ.ም. በአዲስ አበባ ከሚገኙ ሕፃናት ማሳደጊያ ተቋማት በአገር ውስጥ ጉዲፈቻ የተወሰዱ ሕፃናት ቁጥር ዘጠኝ ብቻ ነበር፡፡ በተሠሩ የማንቃት ሥራዎች በ2010 ዓ.ም. በአገር ውስጥ ጉዲፈቻ 178 ልጆች እንዲወሰዱ ሲደረግ 160 ሕፃናት ደግሞ በአደራ እንዲወሰዱ ማድረግ ተችሏል፡፡ ይህ ትልቅ መሻሻል ቢሆንም አሁንም ድረስ ሊቀረፉ ያልቻሉ ችግሮች በአገር ውስጥ ጉዲፈቻ ወሳጆች ዘንድ እንደሚታይ ይገለጻሉ፡፡

  ልጅን ከልጅ የመለየት ነገር በስፋት ይታያል፡፡ ‹‹እንደ ውጭ ጉዲፈቻ ልጅ ልጅ ነው ብለው የተሰጣቸውን አይደለም የሚወስዱት፡፡ ባለቤቴን የሚመስል ቀይ፣ ሴት ትሁን እያሉ መሥፈርቶች ያስቀምጣሉ፤›› የሚሉት ወ/ሮ ገነት ናቸው፡፡ በጉዲፈቻ የሚወስዱ በብዛት እስከ ስድስት ወር ድረስ ያሉ ሕፃናት ናቸው፡፡ ዕድሜያቸው ከዚያ በላይ የሆነ በማደጎ ልጅነት የመወሰድ ዕድላቸው በጣም ጠባብ ነው፡፡ ልጆችን በጉዲፈቻ ለመውሰድ ወደ ኢትዮጵያ ብቅ ይሉ የነበሩ ምዕራባውያን ታክመው መዳን የሚችል የጤና ችግር ያለባቸውን መርጠው በመውሰድ በሕይወታቸው ሁለተኛ ዕድል ይሰጧቸዋል፡፡ የአገር ውስጥ ጉዲፈቻ አሳዳጊዎች ግን ኒሞኒያ ያለባቸውን ሕፃናት እንኳ መውሰድ አይፈልጉም፡፡ በደማቸው ውስጥ ኤችአይቪ የሚገኝባቸው፣ ከአካል ጉዳት ጋር የሚኖሩና የመሳሰሉትን ከምርጫ የሚያስገባም የለም፡፡

  ለዚህም በክበበ ፀሐይ የሕፃናት ማሳደጊያ ማዕከል ያለውን ሁኔታ መመልከት በቂ ነው፡፡ በማዕከላችን የሴቶች ቁጥር አነስተኛ ነው የሚሉት ተወካዩ አቶ ይድነቃቸው ከ174ቱ መካከል ሴቶች 50 ብቻ እንደሆኑ ይናገራሉ፡፡ በማዕከሉ ውስጥ ከሚገኙ ሕፃናት መካከል 12ቱ ልዩ ፍላጎት ያላቸው የአካል ጉዳትና ሕመም ያለባቸው እንደሆኑ ገልጸዋል፡፡ እስካሁን ድረስ እነዚህን ልጆች ለመውሰድ ጥያቄ ያቀረበም የለም፡፡

  የእነዚህ ሕፃናት ዕጣ ፋንታ የመጨረሻ አማራጭ በሆነው በማሳደጊያ ተቋማት ውስጥ መኖር፣ ወጪና ገቢው መቁጠር ነው፡፡ ይህ የሚፈጥርባቸው የሥነ ልቦና ተፅዕኖ ሌላው ልብ የሚሰብር አጋጣሚ ነው፡፡ ‹‹ከቤተሰብ ጋር ተቀላቅለው በሚኖሩና በተቋም ውስጥ ያሉን ሕፃናት ሁኔታና በራስ መተማመን ትልቅ ልዩነት አለው፡፡ አዲስ አበባ ላይ ብዙ ሀብታም አለ፡፡ እነዚህ ሰዎች ልጆችን ከተቋም ኑሮ አውጥተው እንዲያሳድጓቸው ብዙ መሠራት አለበት፤›› በማለት የውጭ ጉዲፈቻ በመቅረቱ የተፈጠረውን ከፍተት የሚናገሩት ወይዘሮ ገነት ናቸው፡፡

  በአሁኑ ወቅት በአዲስ አበባ በሚገኙ የሕፃናት ማቆያዎች ውስጥ ከአራስ እስከ 15 ዓመት የዕድሜ ክልል ውስጥ የሚገኙ ከ1,800 በላይ ሕፃናት ይገኛሉ፡፡ አብዛኞቹ ሕፃናት የሚገኙትም በመንግሥት ማሳደጊያ ማዕከላት ነው፡፡ የውጭ ጉዲፈቻ ከመዘጋት በፊት ግን የግል ማሳደጊያ ተቋማት በአንዴ በርካታ ልጆችን ይይዙ ነበር፡፡ ድጋፍ የሚያደርጉላቸው የነበሩትም በውጭ አገር የሚገኙ የአዶፕሽን ኤጀንሲዎች ናቸው፡፡ ሲዘጋ ግን ድጋፉም አብሮ በመቆሙ ማዕከላቱን የሚደግፍ ባለመኖሩ ከምግብ ጀምሮ የተለያዩ ወጪዎችን ለመሸፈን እየተቸገሩ ነው፡፡ የሚይዟቸው ሕፃናት ቁጥርም እንደ ድሮው አይደለም፡፡ አንዳንድ ተቋማት ሦስትና አራት ልጆች ይዘው ነው ያሉት፡፡ እስካሁን ጥቂት የማይባሉ ተቋማትም ልጆቻቸው እያስረከቡ ከሥራው እየወጡ ነው፡፡

  የውጭ ጉዲፈቻ መዘጋቱን የሚቃወሙት ወይዘሮዋ፣ ጉዳዩን በተመለከተ ክትትል የሚያደርገው ሚኒስቴሩ ቢሆንም የነበረውን ክፍተት ግን እንዲህ አብራርተዋል፡፡ ‹‹በተለያዩ ጊዜያት ክትትል እንዲያደርጉ ከመሥሪያ ቤቱ የተላኩ ሰዎች ክትትል ማድረጉን ትተው ይጠፋሉ፡፡ በቅርቡም ጉዳዩ የሚመለከተው የመምርያው ኃላፊ ውጭ ሄዶ ቀርቷል፡፡ ባለሙያዎችም እንደዚሁ ተራቸው ሲደርስ ወጥተው ይቀራሉ፡፡ የሕፃናትን መረጃ አጥርቶ ሪፖርት የሚያቀርብ ማነው? ብዙዎቹ አሜሪካ ሄደው ነው የቀሩት፡፡ ይህንን አሠራር እንጂ ማስተካከል ጨርሶ መዝጋት መልስ አይሆንም፤›› በማለት በየአገሩ ያሉ የኢትዮጵያ ኤምባሲዎች የጉዲፈቻ ነገሮችን እየተከታተሉ መሥራት የሚችሉበት አሠራር ቢዘረጋ ጥሩ አማራጭ እንደሆነ ይናገራሉ፡፡

  - Advertisement -

  ይመዝገቡ

  spot_img
  spot_img

  ተዛማጅ ጽሑፎች
  ተዛማጅ

  በኢትዮጵያ ላይ የቀጠለው የምዕራባውያን ጣልቃ ገብነት

  ምዕራባውያን አገሮች በኢትዮጵያ ላይ ጠንካራ ጫና ማሳደራቸውን ቀጥለዋል፡፡ በዲፕሎማሲም...

  የመንግሥት ዩኒቨርሲቲዎች የድጎማ በጀት ለፖለቲካ ሥራ ማስፈጸሚያ እንደሚውል የሚያሳይ ሪፖርት ቀረበ

  ለመንግሥት ዩኒቨርሲቲዎች የሚደረግ የበጀት ድጎማ ከመደበኛው ሥራ ይልቅ ከዋናው...

  መንግሥት የሥራ ግብር ምጣኔን እንዲቀንስ ተጠየቀ

  የኢትዮጵያ ሠራተኛ ማኅበራት ኮንፌዴሬሽን (ኢሠማኮ) መንግሥት የሠራተኛውን የኑሮ ጫና...

  የአዲስ አበባ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት የአመራሮች ምርጫና ቀጣይ ዕቅዶቹ

  የአዲስ አበባ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት ሲጠበቅ የነበረውን...