- Advertisement -

ለመተማመንም እንፈራረም እንዴ?

ሰላም! ሰላም! አንዱ በቀደም ሰተት ብሎ በጠዋቱ ቤቴ መምጣቱ፣ ስንተዋወቅ እኮ ገና ሰባት ቀናችን ነው። ማንጠግቦሽ፣ ‹‹እንኳን ሰባት ቀን ሰባት ደቂቃ ቆሞ የሚያወራህ በጠፋበት በዚህ ጊዜ እንዲህ አትበል. . . ›› እያለች ለምሳ የቆጠበችውን ለእንግዳው ጨምራ ቁርስ ታቀርባለች። ምናለበት አንድ ጉርሻ ብጎርስ? ምናለበት አንድ ጊዜ ቡናዬን ፉት ብል? ‹‹አንበርብር ዛሬ ሰባ ሺሕ ብር ካላበደርከኝ መታነቄ ነው፤›› አይለኝ መሰላችሁ? ማንጠግቦሽም ይህን ስትሰማ የምሳ ፍጆታችንን ማባከኗ ሳይነዳት አይቀርም። ምን እኮ በቃ ሳንወድ በግድ ጋቭሮባውያንን ሆንን እናንተ። አጅሬ ዋ ብዬ መቅረቴን አላየ፣ እጄ ላይ በቀመር የጠቀለልኩት አጓጊ ጉርሻ መፍረሱን አላየ ብቻ፣ ‹‹እነዚህ ሰዎች በዚህ ወር አንድ ነገር ከላደረግኩ ልጅቷን ይገሏታል፤›› ይለኛል። ‹‹ኧረ ማን ነው ገዳይ? ማን ነው ተገዳይ? አንተስ የማን ገላጋይ ነህ?›› ብዬ ሳልጨርስ፣ ‹‹አንበርብር ስንቴ ነው የምነግርህ? የሚስቴ ቤተሰቦች ናቸዋ። እሷ (ሚስቱ) እርጉዝ ናት ብዬሃለሁ። ቤተሰቦቿ ይኼን ሲያውቁ ጠቅልል ብለዋል። እኔም እሷም የምንፈልገው ይኼንኑ ነው። ግን እነሱ ተደግሶ ተሠርጎ ነው ብለው ደረቁ። ቢያንስ አንድ ሁለት በሬ መግዛት የለብኝም?›› ብሎ ዓይን ዓይኔን ያየኛል።

ወይ ዘንድሮ። ሰው እንዲህ የሩቁን ማየት እየተሳነው በየሜትሩ ጉድጓድ የሚገባበት ዘመን ይሁን? እሺ የሆነውስ ይሁን። ግን እንዴት ያለ ኃፍረተ ቢስነት ቢጠናወተን ነው እንዲህ ገመና ከመሸፈን በአንዴ በገመና ወደ መሸቀል የኮበለልነው? የምሬን እኮ ነው። እንዴት ተስፋ አድርጎኝ እንደመጣ ሳስብ ደግሞ ልቤ አልችል አለ። ‹‹ቆይ እስኪ ጊዜ ስጠኝ፤›› ብዬ ከሸኘሁት በኋላ እግሩ ከመውጣቱ ማንጠግቦሽ ትኩር ብላ እያየችኝ፣ ‹‹የእኛ ጊዜ እንኳን በሬ በግ እንዳልታረደ አስታውስ፤›› ብላ ወደ ጓዳዋ ገባች። ዘንድሮስ እኔም ባለጓዳ በሆንኩ አያሰኝም አሁን ይኼ?

አረፋፍጄ የወጣቱን ታሪክ ካስተዋወቀኝ ሰው ስሰማ ይህች አሁን ቤተሰቦቿ ድል ባለ ድግስ በወግ ውሰዳት የሚሉት ገና የሃያ ዓመት ወጣት ናት። ‹‹ቆይ አልተማረም?›› ብዬ ስጠይቅ፣ ‹‹ኧረ በሕግ የመጀመርያ ዲግሪ አለው፡፡ ምነው ስንት ጊዜ አላጫወትኩህም እንዴ?›› ተባልኩ። ምንድነው ይኼ አሥር ጊዜ ‘አጫውቼህ የለም ወይ’ እያሉ መደጋገም ብዬ በስጨት አልኩ። ጨዋታ የሰማንያ ሕግ ሆነ እንዴ? የምር። ‹‹አጫውቼሀለሁና ሰምተሃልና የገባህበት ገብተህ ሸክሜን ተሸከም ብሎ ነገር አለ እንዴ?›› እያልኩ ስነጫነጭ ባሻዬ ሰምተው፣ ‹‹ብሎ ብሎ ደግሞ ሰው በዚህ መጣብህ?›› አሉኝ። ‹‹በየቱ?›› ስላቸው፣ ‹‹ኧረግ አንተስ እውነትም ልብህ ጠፍቷል፤›› ብለው ፈገግ እያሉ፣ ‹‹ክርስቶስ ቃሌን አንዴ ሰምቶ እንዳልሰማ የሆነ የተመለሰ፣ ያፈገፈገ ሰው ፍርዱ በራሱ ላይ ነው ብሎ ነበር። ይኼ መቼም መንፈሳዊ ነገር ስለሆነ አግባብነቱ ያመዝናል። እኔን የሚገርመኝ ግን ይኼኛው ነገር ነው። የዘመኑ ሰው ቃል ምን እንደሆነ በቅጡ ሳያውቅ የትም እየማለ፣ የትም እየተገዘተ ይቆይና የታሪኬ ባለዕዳ ካልሆንክ፣ የሕመሜ ተጋሪ ካልሆንክ ይል ይዟል። እንኳንም የመንግሥተ ሰማይ መዝጊያ በአንድ ፈጣሪ እጅ ሆነ፤›› እያሉ አበስኩ ገበርኳቸውን ቀጠሉ። አንዳንዴ ባሻዬ እንዲህ ሲያወሩ ቃል በቃል መከታተል ያቅተኛል በተለይ ብድር ተጠይቄ፡፡ ‹‹ማን ጠየቀህ?›› አሉኝ ባሻዬ። ለካስ እሳቸው እየሰሙኝ ኖሯል በልቤ ያወራሁ እየመሰለኝ። ታሪኩን ሳጫውታቸው ዝም ብለው ሲያደምጡ ቆይተው፣ ‹‹ምን ያስጨንቅሃል ታዲያ? የሚቻልህ ከሆነ አበድረው። ካበደርከውም መልስ የማትለው ከሆነ ጭምር ማለቴ ነው፤›› ሲሉኝ ጥያቸው ጠፋሁ። እንዲያማ ብለን መስሎን መሰላል ሆነን ስንቱ መወጣጫ አድርጎን አናታችን ላይ የተቀመጠው!

ለነገሩ በባሻዬ አልፈርድም። እሳቸውም በደህናው ጊዜ ልባቸው መንግሥተ ሰማይን ናፋቂ ስለሆነ የዚህ ዓለም ነገር በፊታቸው የተናቀ ነው። ለእኛ ደግሞ ሌላ ነው። ‘እያለህ ካልሆነ ከሌለህ የለህም’ የተዘፈነው ለምሳሌ ለእኛ ለእኛ ዓይነቱ በሁለት ልብ ለሚያነክስ ለፍቶ አዳሪ ነው። ማስጠንቂያውን ብሰማና የለኝም ብል ደግሞ ንፉግ፣ ቆጥቋጣ፣ ገብጋባ፣ ራስ ወዳድ. . . ’ ብዙ ብዙ መሰል ስሞች ጀርባዬ ላይ ሲለጠፉ ይታዩኛል። እኛ ደግሞ እንደምታውቁት የመለጣጠፍ ችግር የለብንም። አንስቼ ብሰጥ የማንጠግቦሽ ጉምጉምታና የእኔ ላብ መና መቅረት ብቻ ስቀመጥ ስነሳ ሰላሜን ሊነሱት ነው። ይኼን እያሰብኩ አንድ ሥራ መጣ። ያበደ ዘመናዊ ባለ አምስት ፎቅ ሕንፃ ይሸጣል ተባልኩ። ወዲያው አካባቢውን አጣርቼ ሳበቃ ለአራት ቤት ፈላጊ ደንበኞቼ ደወልኩ። ሁለቱ አላነሱም፣ አንዱ ስልኩ አይሠራም። ሰዎቹ ታስረዋል ወይም ተደብቀዋል ማለት ነው፡፡ ምን ልበል ታዲያ፡፡ አንደኛው ግን ወዲያው ‘ሃሎ?’ አለ። የነገርኩትን ሰማ። ጊዜ ሳያጠፋ አገኘኝና ሕንፃውን ሄዶ አየ።

ብታምኑም ባታምኑም የዕለቱ ዕለት ሚሊዮኖችን በባንክ ወደ ባለቤቶቹ ከአካውንቱ እንዲዛወሩ አደረገ። ያንተስ ሲለኝ ሰባ ሺሕ ብር በእጄ ስጠኝ ብዬው ሌላውን ወደ አካውንቴ እንዲያስገባው ነገርኩት። ወዲያው ያንን ብር ወስጄ ለሰውየው ሰጥቼ ተገላገልኩ። ግን እንዲያው ሲያስበው ራሷን ያልቻለች፣ በቤተሰብ ጥገኝነት ሥር ያለች ታዳጊ አባብሎ ለጥብስ ሲያደርስ እንዴት ሰው ዝም ይባላል? ነገን ማሰብ ማንን ገደለ? ምን አለኝ የለኝም ማለት?’ ምሁሩን የባሻዬ ልጅ ይኼን ጥያቄ ብጠይቀው፣ ‹‹ይኼ ሁሉ ሰው እንዲህ ማሰብ ቢችል እንኳን በግለሰብ ደረጃ እንደ አገር የብድር ድር ላያችን ላይ ያደራብን ነበር?›› ብሎ ልክ አስገባኝ። ለካ እንደ ግለሰብ በአበዳሪነቴ ስታበይ እንደ ማኅበረሰብ ተረጂነቴን ረስቼው ነበር። አይገርምም!

እናላችሁ ሰሞኑን የማስበው በገንዘብ አቅም ራስን ከመቻል በፊት በአስተሳሰብ ራስን ስለመቻል ሆኗል። የእናንተን ባላውቅም የብዙ ሰዎችን ውድቀትና ስኬት ስታዘብ ሚስጥሩ በአስተሳሰብ ራሳቸውን የቻሉና ያልቻሉ መሆናቸው ይከሰትልኛል። እኛ ደግሞ እንደምታውቁት በአለባበስ፣ በሜክአፕ፣ በምንነዳው መኪና፣ በውፍረትና በክሳታችን ነው ስንመዛዘን የምንውለው። ይኼን ትታችሁት በቀደም አንድ ቅጥቅጥ ላሻሽጥ ደንበኛዬን እየጠበቅኩ ካፌ ተቀምጬ ሁለት ወንድማማቾች ሲነጋገሩ የሰማሁትን ላጫውታችሁ። አንደኛው አክራሪ ሃይማኖተኛ ነው። አንደኛው ልዝብ መሆኑ ነው። በማን ዓይን? በአክራሪው ዓይን። እናም ይመክረዋል። ‹‹አንተ እስከ መቼ ነው ዕድሜህን፣ ገንዘብህን፣ ዕውቀትህን አልባሌ ቦታ የምትጨርሰው? መቼ ነው ሰው የምትሆነው? መቼ ነው ወደ ፈጣሪ ፀጋ የምትመጣው? እስካሁን እኮ የኖርከው ሁሉ ከንቱ ነው፤›› ይለዋል።

- Advertisement -

ተተቺው በትህትናና በየዋህነት፣ ‹‹ለእኔ ስለምታስብ እንዲህ እንደምትለኝ አውቃለሁ። ግን እኔ የራሴ የሆነ ከፈጣሪ ጋር የምገናኝበት መንገድ አለኝ። የግድ የአንተን መምሰል የለበትም። እኔንም አንተንም ፈጣሪ እኩል ነው የሚያየን። ምናልባት አንተ ጠንካራ እምነት ሊኖርህ ይችላል። እኔ ደግሞ ደካማ ልመስል እችላለሁ። ነገር ግን ሁሉንም የሚያውቀው ፈጣሪ ነው። የአንተን ምክርና ሐሳብ እረዳለሁ፣ እቀበለዋለሁ። ግን በሕይወቴ ዘመን የማደርገውን ሁሉ ማድረግ የምፈልገው በራሴ ጊዜና ውሳኔ እንዲሆን ስለምፈልግ ታገሰኝ፤›› ይለዋል። ያኛው አይሰማውም። ‹‹አልገባህም። ዛሬ ወደ ትክክለኛው መንገድ ካልተመለስክ ከዚህ ካፌ ተነስተህ ስትሄድ ሰይጣን በመኪና አደጋ ሊወስድህ ይችላል፤›› ሲለው ተተቺው በዝምታ ተነስቶ መኪናውን አስነስቶ ተፈተለከ። እኔ አልኩኝ፣ ‘እስከ መቼ ይሆን በቡድን ፍረጃ፣ በቡድን አስተሳሰብ፣ በቡድን ብያኔ ሕይወታችን እየተቃኘ ስንራብ አንድ ላይ ስንጠግብ አንድ ላይ፣ ስንፀድቅ አንድ ላይ ስንኮነን አንድ ላይ መሆኑ የሚያከትመው?’ የዴሞክራሲያችንም ማነቆ ዋነኛ እንከኑ የሚጀምረው በቤተሰብ መሀል መሰለኝ። ከተሳሳትኩ አርሙኝ ብያለሁ!

በሉ እንሰነባበት። እናውራው ብንል የእኛ ነገር አያልቅም። ብቻ እኔን የሚገባኝ ብዙ ብዙ መከርከም ያለበት ነገር እንዳለ ነው። ከባሻዬ ልጅ ጋር ትናንት አመሻሽ ላይ አንድ አንዳንድ ልንል ወደ ግሮሰሪያችን እያመራን ሳለን አንድ ከሰውነት ደረጃ የወረደ ወጣት መጥቶ ፊታችን ወደቀ። ‹‹እናንሳው?›› ስለው የባሻዬ ልጅ፣ ‹‹ኧረ አርፈህ ተቀመጥ። የት ታውቀዋለህ?›› አለኝ። ትተነው ወደ ግሮሰሪያችን ገባን። የግሮሰሪያችን ታዳሚ የዚያን ምስኪን መጨረሻ እርስ በርሱ ትከሻ ለትከሻ እየተንጠራራ ይከታተላል። አንዱ፣ ‹‹ይኼ ጫት ምናምኑ እኮ ነው እንዲህ የሚያደርገው፤›› ይላል። ‹‹የለም ይኼማ የአዕምሮ በሽታ ነው። ቢታከም እኮ ይድናል። አካሚው ሳይጠፋ አሳካሚው ነው የጠፋው፤›› ይላል።

‹‹የምን የአዕምሮ በሽታ ነው ደግሞ እሱ። ገና ለገና ዘመናዊ ነን ለማለት ሲሉ የሰሙትን መደጋገም አይደብራችሁም እንዴ? ይኼ አንድ ሁለት የሌለው የሰይጣን ሥራ ነው። ፀበል ቢሄድ በቃው፣ ተገላገለ፤›› ይላል ወዲያ ማዶ በባሻዬ ልጅ ጀርባ። እኔና የባሻዬ ልጅ ተያይተን ተሳሳቅን። አንዱ የየዕምሮ በሽታ ነው ሲል፣ አንዱ ‘ሱሴ’ ነው ሲል፣ አንዱ ሰይጣን ነው ሲል የጋለ ንትርክ ተነስቶ አረፈው። የባሻዬ ልጅ፣ ‹‹ተመልከት የአስተሳሰብ ልዩነትና የግንዛቤ እጥረት። እንግዲህ ይኼ ሁሉ ሰው በየፊናው ትክክል ነኝ ካለ አይመለስም። ታዲያ እንዴት ሆኖ ነው አገር የጋራ በሆነ ፖሊሲና ሥርዓት የሚለወጠው? በተጨባጭ ማስረጃ መተማመን ዘበት በሆነበት ጎዳና ድክ ድክ ብለው የሚያድጉትንስ እንዴት ብለህ ተስፋ ትጥልባቸዋለህ?›› ሲለኝ ቆም ብዬ አሰብኩ። እስኪ እናንተም ቆም በሉማ። አዕምሮ ካልተለወጠ እኮ ሌላው ዘበት ነው ጎበዝ። የስንቱ መወጣጫ እንዳልሆንን ደንዘን እንቅር እንዴ? ከቤተሰብ እስከ አገር መተማመን ከሌለ የትም መድረስ አይቻልም፡፡ ሕይወታችን በመተማመን ላይ ካልተገነባ መኖራችን ትርጉም የለውም፡፡ ለዘመናት መተማመን አቅቶን የባከኑ ወርቃማ ዕድሎች ሊቆጩን ይገባል፡፡ በዚህ ዘመን ከመተማመን ውጪ አማራጭ የለንም፡፡ ለመተማመን ደግሞ የግድ መፈራረም አይኖርብንም መሰለኝ፡፡  ጨርሻለሁ። መልካም ሰንበት!

- Advertisement -

በማህበራዊ ሚዲያዎች ይከታተሉን

ከ ተመሳሳይ አምዶች

ላይ ላዩን መውረግረግ!

ሰላም! ሰላም! ‹ከእንጨት መርጦ ለታቦት፣ ከሰው መርጦ ለሹመት› እንዲል ነባሩ ብሂል፣ እኔም ወጉ ደርሶኝ በድምፄ ተወካዬን ልመርጥ ተዘጋጅቻለሁ፡፡ እናንተስ እንዳልል ውሳኔው በእጃችሁ ነው፡፡ ‹ተቀመጥ...

ለጤናችን!

ሰላም! ሰላም! በቀደም ዕለት እንዲያው ግራ ግብት ብሎኝ የሆድ የሆዴን የማጫውተው ሰው ብፈልግ አጣሁ። ምሁሩ የባሻዬ ልጅ ሥራ ሥራ እያለ ቀልቡ ከእሱ ጋር የለም።...

ተንከራታች ሕይወት!

ሰላም! ሰላም! ክቡራትና ክብራን ወገኖቼ እንደምን ሰነበታችሁ? እንዲያው ዝም ብላችሁ ሕይወትን ታዝባችሁ ታውቃላችሁ? የእኔ ትዝብት የሚያሳየኝ ከይዘቷ ይልቅ የቅርጿን ብዛት ነው። በአሜሪካ እንኳ ባይደን...

አደራ በልነት!

ሰላም! ሰላም! ሁላችሁም ሰላማችሁ ይብዛ፡፡ የዘመኑ ኮበሌዎችና ጉብሎች ‹ሎሚ ጣልባት በደረቷ…› አስታዋሽ የሆነውን የጥቅምት በዓል በሰላም አሳልፋችሁ ለሦስት ጉልቻ ተመቻችሁ? ወይስ ‹ሕይወት በነበረበት ይቀጥላል…›...

በጎደለ ሙላ!

ሰላም! ሰላም! እንዴት ነው ወገን? ያለፈው ሳምንት አልፎ ይኼኛው ሲተካ መገናኘት ግድ በመሆኑ እንኳን በሰላም ተገናኘን፡፡ ድሮ ነው አሉ ተለያይተው የከረሙ ሰዎች ሲገናኙ ከቤተሰብ...

ከፈንጠዝያው ባሻገር!

ሰላም! ሰላም! በዓል በሰላም አልፎ መገናኘት ደስ ይላል፡፡ በተለይ ደግሞ ከተጎሳቆሉ ወገኖች ጋር በዓል ያከበራችሁም ሆናችሁ ከሩቅ ሆናችሁ የቸገራቸውን ወገኖች የደገፋችሁ ውስጣችሁ በሐሴት እንደሚረሰርስ...

አዳዲስ ጽሁፎች

የጤናው ዘርፍ ባለፉት ስድሥት ወራት

የወባ በሽታ ከሰሃራ በታች በሚገኙ የአፍሪካ አገሮች ዋነኛ የጤናና የማኅበራዊ ቀውስ መንስዔ ነው፡፡ የዓለም ጤና ድርጅት እ.ኤ.አ. በ2024 ያወጣው መረጃም 263 ሚሊዮን ሰዎች የወባ...

የአዲስ አበባ የኮሪደር ልማት በባለሙያ ዓይን

(በጎ ጎኖችና እርምት የሚፈልጉ ጉዳዮች) በዮሐንስ መኮንን በጥር ወር 2016 ዓ.ም. የአዲስ አበባ ዋና ዋና ኮሪደሮችን በማዘመን ከተማዋን ለነዋሪዎቿና ለጎብኚዎቿ ምቹ ያደርጋታል የተባለ ፕሮጀክት በ43 ቢሊዮን...

በልዩነት ውስጥ ሆነንም እስኪ እንነጋገር

በገነት ዓለሙ ዴሞክራሲ መብቶችና ነፃነቶች የሚሠሩበት የሕዝብ አስተዳደር ነው፡፡ ሰብዓዊ መብቶችንና ነፃነቶችን መኗኗሪ ያደረገ ሥርዓት ነው፡፡ እነዚህ መሠረታዊ መብቶችና ነፃነቶች በተፈጥሮ የተገኙ፣ ሰው በመሆናችን ብቻ...

ለጤናማ የትራፊክ ፍሰትና ለመንገድ ደኅንነት ቅጣት መጣል ብቻውን መፍትሔ አይሆንም!

በአዲስ አበባ ከተማ ለተሽከርካሪዎች ምቹ የሆኑ መንገዶችን እየተመለከትን ነው፡፡ ከአዳዲሶቹ መንገዶች ባሻገር አንዳንድ ነባር መንገዶች የማስፋፊያ ሥራ ታክሎባቸው አገልግሎት ላይ ውለዋል፡፡ ከኮሪደር ልማቱ ጋር...

የግጭት አዙሪት ውስጥ ሆኖ የአፍሪካ ማዕከል መሆን ያዳግታል!

የአፍሪካ ኅብረት 38ኛው የመሪዎች ጉባዔ በአዲስ አበባ ሲካሄድ ብዙ ትዝ የሚሉ ጉዳዮች አሉ፡፡ እጅግ በጣም አሰልቺ፣ ውጣ ውረድ የበዛበትና ታላቅ ተጋድሎ ተደርጎበት ከከፍተኛ ዲፕሎማሲያዊ...

አገሬ ምንተባልሽ – ልብ ያለው ልብ ይበል

በቶማስ በቀለ ይቺ አገራችን ብዙ ተብሎላታልም፣ ብዙ ተወርቶባታልም፣ አገሪቱ በቅኝ ያልተገዛች ብቸኛ አገር (ላይቤሪያን ጨምሮ) ከመሆኗ አኳያ የሚነገርላት ብዙ ጥሩና የሚገርሙ ነገሮች ያሉትን ያህል፣ ከረሃብ...
[the_ad id="124766"]

በማህበራዊ ሚዲያዎች ይከታተሉን