Saturday, May 25, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

ማኅበራዊሙዚቃና ዳንኪራ ያጀበው የባንግላዴሽ ገጽታ

ሙዚቃና ዳንኪራ ያጀበው የባንግላዴሽ ገጽታ

ቀን:

ባንግላዴሽ ሁሉን ያቀፈች አገር ናት ይሏታል፡፡ ከሃይማኖት አንፃር እስልምና፣ ቡድሂዝም፣ ሂንዱዝምና ክርስትና በአንድነት የሚኖሩበት በርካታ ነገዶችና ጎሳዎችንም በጉያዋ ያቀፈች ናት፡፡ ከተለያዩ ነገዶቿና ሃይማኖቶቿ ጋር ተያይዘው የሚፈልቁ ባህሎች ትውፊቶችና ልማዶችም ባለፀጋ ናት፡፡

ከዚህ አንፃር ባንግላዴሾች ሰብል ወደ ጎተራ የሚሰበስቡበት አዝመራውም የሚካተትበት በዓላቸው ናባና ይባላል፡፡ ክብረ በዓሉም በሙዚቃና በዳንኪራ የሚታጀብ ነው፡፡ ናባና በቁም ሲፈታ አዲስ ምግብ ማለት ሲሆን፣ ከየመስኩ የሚሰበሰቡትን ያመለክታል፤ ይህም በባንግላ ካላንደር መሠረት በስምንተኛው አግራሃያን ወር በመጀመሪያው ቀን ይውላል፡፡

የመኸር በዓሉ በቤንጋሊ ትውፊት ሁነኛ ሥፍራ ያለውና የኅብረተሰቡ ትስስር የሚገለጥበት ከመቶዎች ዓመታት በላይ በየመንደሩ ሲከበር የኖረ፣ ከበርካታ ዓመታት ወዲህም በከተማዎችም እየተከበረ ያለ ነው፡፡ ዘንድሮም በዓሉ መሰንበቻውን በዋና ከተማዋ ሲከበር፣ አዲስ አበባ የሚገኘው የባንግላዴሽ ኤምባሲም ‹‹የባንግላዴሽ ገጽታዎች›› በሚል መሪ ቃል የአገሪቱን ባህልና ትውፊት የሚያስተዋውቅ በባህላዊና ዘመናዊ ሙዚቃ የታጀበ መሰናዶውን ባለፈው ሳምንት መገባደጃ በጌት ፋም ሆቴል አዘጋጅቶ ነበር፡፡ ባህር ተሻግረው የብስ አቋርጠው ከአገራቸው የመጡ የባህል ሙዚቃ ጓዶችና ታዋቂ ድምፃውያን የዝግጅቱ አካል ነበሩ፡፡

- Advertisement -

በኢትዮጵያ የባንግላዴሽ አምባሳደር ሚስተር ሞኒሩል ኢዝላም፣ በክብረ በዓሉ መክፈቻ የተለያዩ ሃይማኖቶች ላይ ቡድሂዝምና ሂንዱዚም፣ እስልምናና ክርስትና ተከባብረው የሚገኙባት የተለያዩ ጎሳዎችና ነገዶች በፍቅር የሚኖሩባት አገር ባንግላዴሽ ናት ብለዋል፡፡ የአገሪቷን ገጽታ በባህላዊ ትርዒት ለማስተዋወቅ ትዕይንቱ መቅረቡንም አክለዋል፡፡

የሙዚቃ ትዕይንት ጥበቡ መገለጫ በዋናነት ዳንስ (ዳንኪራ) ሲሆን በቀዳሚነት የቀረበው የባንግላዴሽን ውበት የአገር ፍቅር መገለጫ በሆኑ የአርበኝነት ዝማሬዎችን በማሰማት ነው፡፡

‹‹ቢሆ ዳንስ›› የተሰኘውና በተለያዩ የባንግላዴሽ አካባቢዎች የሚኖሩ ጎሳዎች አኗኗርና የኑሮ ሥልት የሚያንፀባርቀው የጎሳ ዳንስ፣ በፈጣን እንቅስቃሴ የታጀበው ዳንኪራ፣ በኅብረ ቀለማት የተዋቡ አልባሳትን ከተለያዩ ባህላዊ ቁሶች ጋር ተቀናጅቶ የቀረበበት ነው፡፡

ክላሲካል (ብሉይ) እና ያሁን ዘመን (ኮንቴምፖራሪ) ዳንስን ያዋሀደው ትርዒትም የታዳሚውን ቀልብ የገዛ ነበር፡፡ ባንጊሎች የዕለት ተዕለት ኑሮአቸው ከእርሻ፣ ዓሳን ከማስገር ጋር የተያያዘበትን ገጽታ በባህላዊ ዳንኪራ ከተስማሚው ሙዚቃ ጋር ተሰናስሎ የቀረበበት መድረክ ወንዱ ሲያርስ፣ ሲያጭድ፤ ሴቷ በሰፌድ ስታበጥር፣ ውኃ በማድጋ (እንስራ) ስትቀዳ፣ ሰብሉ በመንሸ ሲዘረዝር፣ ዓሳ ሲሰገር፣ ጀልባ ሲቀዘፍ የሚያሳየው ትዕይንት በታዳሚው ይበልታን አግኝቷል፡፡

ከትዕይንት ዳንኪራው በተጓዳኝ የአገሪቱ ኮከብ ድምፃውያን ታፓን ቾውድሁሪና ፋህሚዳ ነቢ ሲያቀነቅኑ የታዳሚውን በተለይም የባንግላዴሽ ማኅበረሰብን አነቃንቀውት ነበር፡፡ በተንጣለለው አዳራሽ እየተሽከረከሩ አብረው ተጫውተዋል፡፡

ቾውድሁሪ በባንግላዴሽ የሙዚቃ ታሪክ ከባንድ ሙዚቃ ፈር ቀዳጆች አንዱ እንደሆነ ይነገርለታል፡፡ ባህላዊውም ዘመናዊውንም የሚያቀነቅን በብዙዎች ልብ ውስጥ እንደነገሠም በመድረኩ ተወስቷል፡፡ የአገሪቱ ሙዚቃ ፊታውራሪ ማህሙዱን ነቢ ልጅ የሆነችው ፋህሚዳ ነቢም ከስመጥር ድምፃውያን አንዷ ነች፡፡ ዘመናዊን ከክላሲካሉ ጋር አቆራኝታ በማቀንቀን ትወሳለች፡፡

በባንግላዴሽ ያሉ በርካታ ማኅበራዊ ቡድኖች የባህል ስብጥርን ብዝኃ ባህልን በማስተዋወቅ ረገድ ዳንሳቸው ዓይነተኛ ሆኖ ለሺሕ ዓመታት ዘልቋል፡፡ ኪናዊና ባህላዊ መገለጫዎች እያንዳንዱን የሕይወት ገጽታ ይንፀባረቅበታል፡፡ ይህም ሥነ ጥበብ፣ ዕደ ጥበብ፣ ፎክሎርን (ትውፊት)፣ ቋንቋና ሥነ ጽሑፍ፣ ፍልስፍና፣ ሃይማኖት፣ ክብረ በዓልንና ሥነ ምግቡን ያካተተ ነው፡፡

የአዲስ አበባው የዳንስ ትዕይንቱ መካተቻ የሆነው የቡድን ዳንስ ክዋኔ በአርበኝነት መዝሙር ላይ የተመሠረተ ነው፡፡ ባንግላዴሽ ከግማሽ ምዕት ዓመት በፊት ለነፃነቷ ያደረገችውን ተጋድሎና ሰማዕትነት እንዲሁም ሕዝቡ ለአገሪቱ ብልፅግናና ዕድገት የሚያደርገውን ጥረት ‹‹ተደሰቺ ባንግላ›› በሚል መንፈስ የቀረበ ነበር፡፡

የቤንጋሊ ክብረ በዓል ያለ ጥሩ ምግብ ከነተከታዮቹ ምሉዕ አይሆንም፡፡ የእስያ የዓሳ ዘር የሆነው ኢሊሽ ዓሳ፣ ሩዝ፣ አትክልትና ፍራፍሬ፣ ጣፋጮች ሌሎችም ባህላዊ ምግቦች የበዓል ፈርጦች ናቸው፡፡

በአዲስ አበባው ክብረ በዓልም እነዚሁ ምግቦች ለታዳሚው ቀርበው ተቋድሰውታል፡፡ በባህላዊ መስተንግዶው የባንግላዴሽ ማኅበረሰብ፣ ዲፕሎማቶች የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ከፍተኛ ባለሥልጣኖች ተገኝተዋል፡፡

“ፖሄላ ቦይሻክህ” የቤንጋሊ አዲስ ዓመት መጠሪያ ሲሆን የተገኘውም ከመጀመሪያው ወር (ቦይሻክህ) መባቻ ነው፡፡ ቀመሩም በፀሐይና ጨረቃ ጥምር አቆጣጠር የተመሠረተ ነው፡፡ የፀደይ ወቅታቸው ሲመጣ የጠራ ሰማይ፣ አረንጓዴ መስክ፣ መከሩም አምሮ ይታያል፡፡ የወቅቱ ክስተት ደራስያንና ገጣሚያንን ለሥራ ያነቃቃቸዋል፡፡ የወቅቱ መለወጥ ተከትሎም በሚቶሎጂ (ሥነ ተረት) የምትታወቀው የሒንዱ የመሬት አምላክ ዱርጋ ትታሰባለች፡፡ ምድሪቱንም የሰውንም ዘር ትባርካለች ተብሎም ይታሰባል፡፡ ፀደያዊው ክብረ በዓል በዓመታዊው የመኸር በዓል ናባና ዑትሻብም በመቀጠል እስከ ክረምት መግቢያ እንደሚቀጥል ሜህሪን ሙብዲ ቾውድሁሪ ‹‹Of Qutumn & Bengal›› ብሎ በጻፈው ድርሳኑ ገልጾታል፡፡

የቤንጋሊ ሥነ ጽሑፍ ሙዚቃን መልክ ያስያዘው የኖቤል ተሻለሚው ታዋቂው ባለቅኔ ታጎር ግጥማዊ ምናቡን የቀሰመው የፀደይ ወቅት ከፈጠረበት የጋለ ስሜትና ከወቅቱ አዝመራ መሆኑም ይጠቀሳል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የማዳበሪያ አቅርቦትና ውጣ ውረዱ

በቅፅል ስሙ “The Father of Chemical Warfare” እየተባለ የሚጠራው...

የኢትዮጵያ ልማት ባንክ የትርፍ ምጣኔውን ከ70 በመቶ በላይ አሳደገ

ከሁለቱ መንግሥታዊ ባንኮች መካከል አንዱ የሆነው የኢትዮጵያ ልማት ባንክ...