Saturday, September 30, 2023
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

አገር በቀል ባለ ኢንዱስትሪዎች መብታችንን ተነፍገናል አሉ

ተዛማጅ ፅሁፎች

የገቢ ዕቃዎችን በአገር ውስጥ ምርት በመተካት ላይ የሚገኙ የፋብሪካ ባለቤቶች ኢትዮጵያዊ በመሆናቸው ብቻ መብታቸው በመነፈጉ፣ ለጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት አቤቱታ አቀረቡ፡፡

ከውጭ ጥሬ ዕቃ በማስገባት ያለቀላቸው ገቢ ዕቃዎችን በአገር ውስጥ የሚያመርቱ አገር በቀል ፋብሪካዎች የዱቤ ሽያጭ አሠራር ለውጭ አገር ኢንቨስተሮች ተፈቅዶ፣ ለአገር ውስጥ ኢንቨስተሮች መከልከሉ በገዛ አገራቸው የባይተዋርነትና የሁለተኛ ዜግነት ስሜት እንዲሰማቸው ማድረጉን አመልክተዋል፡፡

ለጠቅላይ ሚኒስትሩ የቀረበው አቤቱታ ማጠንጠኛ በአቶ ተክለ ወልድ አጥናፉ ይመራ የነበረው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ባለፈው ዓመት ጥቅምት 2010 ዓ.ም. ያወጣው የውጭ አቅራቢዎች ዱቤ ሽያጭ መመርያ፣ አገር በቀል ኢንዱስትሪያሊስቶችን በማግለሉ ነው፡፡ ዋነኛ የኢንዱስትሪው ተዋናዮች ይህንን የብሔራዊ ባንክ መመርያ ‹‹የአፓርታይድ መመርያ›› እያሉ ይጠሩታል፡፡

ባለፈው አንድ ዓመት የውጭ ኢንቨስተሮች በመመርያው መሠረት በውጭ አቅራቢዎች ዱቤ ሽያጭ (ሰፕላየርስ ክሬዲት) ከብሔራዊ ባንክ ልዩ ደብዳቤ በማጻፍ ጥሬ ዕቃ ከውጭ በማስገባት ማምረት መቻላቸውን፣ አገር በቀል ፋብሪካዎች ግን መመርያው ስላልፈቀደላቸው ከማምረት መስተጓጎላቸውን ገልጸዋል፡፡ የውጭ አቅራቢዎች ዱቤ ሽያጭ አሠራር ለአገር ውስጥ ባለሀብቶች እንዲፈቀድ ካስፈለገ ኤክስፖርት አድርገው ምንዛሪውን ካመጡ ብቻ ሲሆን እንጂ፣ እንደ ውጭ ባለሀብቶች በአገሪቱ ግምጃ ቤት ምንዛሪ ስለማይፈቀድላቸው ከምርት እየወጡና የተበደሩትን መክፈል ባለመቻላቸው ያስያዙት ንብረት የመወረስ ሥጋት አንዣብቦበታል ብለዋል፡፡

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ገዥ ሆነው በቅርቡ የተሾሙት ይናገር ደሴ (ዶ/ር) የአገር ውስጥ ኢንዱስትሪያሊስቶች በጥሬ ዕቃ ዕጦት ምክንያት ማምረት ባለመቻላቸው ለብድር ያስያዙት ንብረት እንዳይወረስ ለባንኮች ደብዳቤ የጻፉ ቢሆንም፣ አገር በቀል ፋብሪካዎች ከአቅማቸው በታች በማምረት በመገደዳቸው መንግሥት ዘላቂ መፍትሔ እንዲሰጣቸው ጠይቀዋል፡፡

የብሔራዊ ባንክ መመርያ ኩባንያው አገር በቀል ከሆነ የውጭ ምንዛሪ ወደ ውጭ ልኮ ባመጣው መጠን የውጭ አቅራቢዎች ዱቤ ሽያጭ ይፈቀድለታል፡፡ ነገር ግን በተገላቢጦሽ የውጭ ዜጋ ኩባንያ ከሆነ ግን በቀጥታ ከብሔራዊ ባንክ በማጻፍ በቀጥታ ሌተር ኦፍ ክሬዲት ወይም በውጭ አቅራቢዎች ዱቤ ሽያጭ አሠራር የውጭ ምንዛሪ ይፈቀድለታል፡፡

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ባወጣው የውጭ አቅራቢዎች ዱቤ ሽያጭ መመርያ FXD/47/2017 ከፍተኛ ጉዳት ካደረሰባቸው አገር በቀል ባለ ኢንዱስትሪዎች መካከል፣ የብረታ ብረት ፋብሪካ ባለቤቶች ተጠቃሾች ናቸው፡፡

ሰባ አራት አባላት ያሉት የኢትዮጵያ መሠረታዊ ብረታ ብረትና ኢንጂነሪንግ ኢንዱስትሪዎች ማኅበር ኅዳር 13 ቀን 2011 ዓ.ም. ለጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤትና ለሚመለከታቸው መንግሥታዊ ተቋማት በጻፈው ደብዳቤ፣ የብሔራዊ ባንክ መመርያ ከፍተኛ ኢፍትሐዊ የንግድ ውድድር እንዲፈጠር ያደረገ በመሆኑ መንግሥት አፋጣኝ ምላሽ እንዲሰጥ ጠይቋል፡፡

ማኅበሩ በጻፈው ደብዳቤ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ካለፈው ጥቅምት 2010 ዓ.ም. ጀምሮ ተግባራዊ እንዲሆን ባወጣው የውጭ አገር ብድርና የዱቤ ሽያጭ አቅርቦት መመርያ አንቀጽ አራት ላይ በግልጽ እንደተቀመጠው፣ ኤክስፖርት አድራጊዎችንና የውጭ አገር አልሚዎችን ብቻ በተናጠል ተጠቃሚ የሚያደርግ ሥርዓት ዘርግቷል፡፡

ይህ መመርያ እነዚህ አካላት ውስን የሆነውን የውጭ ምንዛሪ በወረፋም ሆነ በብሔራዊ ባንክ በሚጻፍ ልዩ ትዕዛዝ ያዘለ ደብዳቤ ያለ ወረፋ በቅድሚያና በፈለጉት ጊዜ ሊከፍቱ የሚችሉት የዱቤ ሽያጭ ወይም ሌተር ኦፍ ክሬዲት መውሰድ የሚችሉበት፣ በአንፃሩ በኢትዮጵያውያን የተቋቋሙ አገር በቀል ፋብሪካዎች የውጭ ምንዛሪ ሊያገኙ የማይችሉበት ሁኔታ መፈጠሩን ማኅበሩ ገልጿል፡፡

ይህ የብሔራዊ ባንክ መመርያ የኢንቨስትመንት አዋጁን የጣሰ ነው በማለት የገለጸው ማኅበሩ፣ በመስከረም 2005 ዓ.ም. ተሻሽሎ የወጣው የኢንቨስትመንት አዋጅ ቁጥር 769/2005 ላይ በግልጽ እንደተመለከተው፣ ‹‹ባለሀብት›› ማለት በኢትዮጵያ ውስጥ ኢንቨስት ያደረገ የአገር ውስጥ ወይም የውጭ ባለሀብት እንደሆነ በአንቀጽ ሁለት ንዑስ አንቀጽ አራት ላይ ተመልክቷል፡፡

በተጨማሪም በዚሁ አዋጅ አንቀጽ 36 ንዑስ አንቀጽ አንድ ላይ ማንኛውም ባለሀብት ከውጭ የተበደረውን የውጭ ምንዛሪ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ በሚያወጣው መመርያ መሠረት እንዲያስመዘግብ ከማዘዝ ውጪ፣ የአገር ውስጥና የውጭ ባለሀብት በሚል የከፈለበት አሠራር እንደሌለም ማኅበሩ አስታውሷል፡፡

‹‹በአንቀጽ 36 ንዑስ አንቀጽ 2 ላይም የሚደነግገው የውጭ ባለሀብት ሥራውን ለማንቀሳቀስ የውጭ ምንዛሪ ሒሳብ መክፈት እንደሚችል ከመግለጽ ያለፈ፣ የአገር ውስጥ ባለሀብት ከውጭ መበደርን የሚከለክል ነገር የለውም፡፡ በመሆኑም በእኛ እምነት የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ መመርያ ተቃርኖ አለው፤›› በማለት፣ ማኅበሩ የብሔራዊ ባንክ መመርያ የኢንቨስትመንት አዋጁን እንደጣሰ አመልክቷል፡፡

ኤክስፖርት ከምንም በላይ ሊበረታታ የሚገባው መሆኑ ይታመናል ያለው ማኅበሩ፣ ለዘለቄታው የውጭ ምንዛሪ ችግር የሚፈታው የኤክስፖርት አቅም ሲገነባ መሆኑ ግልጽ ነው ብሏል፡፡ ከዚህ ጎን ለጎን ግን ኢትዮጵያ በከፍተኛ መጠን የውጭ ምንዛሪ የምታወጣባቸው ስትራቴጂካዊ ገቢ ምርቶችን በአገር ውስጥ የመተካት ጉዳይ ልዩ ትኩረት ተሰጥቶት እየተሠራ መሆኑን፣ በዚህ ረገድ የብረታ ብረትና ኢንጂነሪንግ ምርቶችን በመተካት ከፍተኛ የውጭ ምንዛሪ የማዳን ፋይዳው ከፍተኛ ነው ብሏል፡፡

ይሁን እንጂ ማኅበሩ እንደሚለው፣ ኤክስፖርትና ገቢ ምርቶችን የመተካት ጥረት በተገቢው መጠን አመጣጥኖ ማስተናገድ የተሳነው የብሔራዊ ባንክ መመርያ፣ ለአገር ውስጥ ገበያ የሚያመርቱ የውጭ አገር ኢንቨስተሮችን ጭምር በልዩ ሁኔታ በመደገፍ፣ በሌላ በኩል ደግሞ በተመሳሳይ ሥራ የተሰማሩና ገቢ ምርት የሚተኩ በኢትዮጵያውያን የተቋቋሙ ኢንዱስትሪዎችን ከጨዋታ ውጪ ሊያደርግ የሚችል አሠራር ተዘርግቷል፡፡

‹‹የአገር ውስጥ የብረት አምራች ኢንዱስትሪዎች በቢሊዮኖች በሚቆጠር ገንዘብ የተገነቡ ከመሆናቸው በላይ፣ ከፍተኛ የሕዝብና የመንግሥት ገንዘብ ከባንኮች ተበድረው የሚሠሩ እንደሆነ ይታወቃል፡፡ ፋብሪካዎቹ ለአሥር ሺዎች የሥራ ዕድል በመፍጠር ለበርካታ ዜጎች የኑሮ ዋስትና የሰጡ ናቸው፡፡ የብረት ምርቶች በአገር ውስጥ በቀጥታ ለፍጆታ የሚውሉ፣ ተጨማሪ እሴት ለሚፈጥሩ፣ ለቀጣይ የሥራ ዘርፎች ግብዓት ስለሆኑ እንደ ምርት ወስዶ ማየቱ ብቻ አግባብ አይደለም፡፡ ስለሆነም የሚፈጥሩትን ተጨማሪ እሴትና አቅፈው የያዟቸውን ዜጎች ግምት ውስጥ በማስገባት፣ የውጭ ምንዛሪ አቅርቦት ትኩረት ሊሰጠው ይገባል፤›› ሲል ማኅበሩ ጠይቋል፡፡

ከዚህ በተጨማሪ መንግሥት በሁለተኛው የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅዱ የአገሪቱ የኢንዱስትሪ ልማት ምሰሶ የአገር ውስጥ ባለሀብቱ መሆኑን እንደሚገልጽ፣ የብሔራዊ ባንክ መመርያ ግን በተቃራኒው የቆመ ነው ማኅበሩ ያለው፣ ለውጭ አገር አልሚዎች ይህ ዕድል መፈቀዱን አልቃወምም ብሏል፡፡ ነገር ግን በኢትዮጵያውያን ባለሀብቶች ለተቋቋሙ ኢንዱስትሪዎች ፍትሐዊ ድጋፍ መነሳት አግባብ አይደለም ሲልም አክሏል፡፡

ለአብነት በብሔራዊ ባንክ ትዕዛዝ በፍጥነት በሚከፈት ሌተር ኦፍ ክሬዲትና የውጭ አቅራቢዎች ዱቤ ሽያጭ አንድ የውጭ ኩባንያ ለተለያዩ ባንኮች የተጻፈለት ሲሆን፣ ከአንድ ባንክ ብቻ ከ20 ሚሊዮን ዶላር በላይ ሲያገኝ ከፍተኛ የማምረት አቅም ያላቸው አገር በቀል ብረት ፋብሪካዎች ከጨዋታ እየወጡ መሆኑ ተነግሯል፡፡

ማኅበሩ ለጠቅላይ ሚኒስትሩ በጻፈው ደብዳቤ፣ አገር በቀል ፋብሪካዎች ከአቅም በታች እያመረቱ በመሆኑ የማምረቻ ወጪያቸው በመናሩ ምርታቸውን በተመጣጣኝ ዋጋ ለማቅረብ አልቻሉም፡፡ የተወሰኑት ደግሞ ምርት ማቆማቸውን ገልጿል፡፡

‹‹በሙሉ አቅማቸው በማያመርቱ ኢንዱስትሪዎች ውስጥ የሚሠሩ በሺዎች የሚቆጠሩ ሠራተኞች፣ በውጭ አገር ባለሀብቶች በተቋቋሙ ፋብሪካዎች ውስጥ የሚሠሩ ሠራተኞች የተለያየ ጥቅማ ጥቅም እያገኙ እንደሆነ በማየት የኢንዱስትሪ ሰላም እየተናጋ ይገኛል፤›› በማለት ማኅበሩ ገልጾ፣ ‹‹ብሔራዊ ባንክ ቅሬታ ለሚያቀርቡ ኢንዱስትሪያሊስቶች ‹ኢትዮጵያውያን ስለሆናችሁ ዕድሉን ለማግኘት መመርያው አይፈቅድም› የሚል መሆኑ፣ ኢትዮጵያውያን ባለሀብቶች በአገራቸው ባይተዋርነትና ተስፋ ቢስነት እንዲሰማቸው አድርጓል፤›› በማለት ማኅበሩ ለጠቅላይ ሚኒስትሩ አቤቱታውን አሰምቷል፡፡

በዚህ ምክንያት ኢትዮጵያውያን ባለሀብቶች ያቋቋሟቸውን ፋብሪካዎች ዕድሜ ለማራዘም፣ ለውጭ አገር ዜጎች በወደቀ ዋጋ ሸጠው ለመውጣት እንቅስቃሴ መጀመራቸውንም ማኅበሩና የብረታ ብረት ኢንስቲትዩት ገልጸዋል፡፡ 

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች