ወደ ውጭ የሚላከው የማር ምርት በከፍተኛ ሁኔታ እያሽቆለቆለ መምጣቱ ተገለጸ፡፡ ማርን ለውጭ ገበያ ማቅረብ ብዙም ያልተሠራበት በጅምር ላይ የሚገኝ የኢኮኖሚ ክፍል ቢሆንም፣ ጅምሩ ግን ወደ ኋላ እየተቀለበሰ እንደሆነ የዘርፉ ተዋናዮች ገለጹ፡፡
እ.ኤ.አ. በ2013 884 ቶን ማር ወደ ውጭ እንደተላከ፣ እንዲሁም እ.ኤ.አ. በ2017 ደግሞ ወደ ውጭ የተላከው የማር መጠን በግማሽ መቀነሱ ታውቋል፡፡ ባለፈው ዓመት በዘጠኝ ወራት ውስጥ ወደ ውጭ የተላከውም 260 ቶን ብቻ እንደነበር ተገልጿል፡፡
ኢትዮጵያ በየዓመቱ 550 ሺሕ ቶን ማር የማምረት አቅም ቢኖራትም የሚመረተው ግን ከ70 ሺሕ ቶን ያነሰ ነው፡፡ ለዚህም 95 በመቶ የሚሆነው የማር ምርት የሚመረተው በባህላዊ መንገድ መሆኑ በምክንያትነት ይገለጻል፡፡
በየዓመቱ ከሚመረተው 60 ሺሕ ቶን የማር ምርት ውስጥ ለውጭ ገበያ እየቀረበ ያለው ከሦስት በመቶ ያነሰ እንደሆነ የሚናገሩት የግብርና ሚኒስትሩ አቶ ዑመር ሁሴን፣ ይኼንን አኃዝ ለመጨመር ጥራት፣ የምርት መጠን ላይ መሠራት አለበት ይላሉ፡፡ አያይዘውም ኢትዮጵያ በቡና ምርት ከምታገኘው ጥቅም ያልተናነሰ ከማር ልታገኝ እንደምትችል፣ በዚህ ዘርፍ ትኩረት አድርጎ መሥራትም ብዙ ሳይለፉ ማትረፍ የሚያስችል መሆኑን ገልጸዋል፡፡
ከግብርና ትራንስፎርሜሽን ኤጀንሲ ጋር በመሆን ከማምረቻው ጀምሮ ገበያ እስኪደርስ ያለውን የምርት ሰንሰለት በማጥናት፣ በመካከል ያሉ ማነቆዎችን ለይቶ በማውጣትና እንዲፈቱ ማድረግ፣ ከዚያ ባለፈም የውጭ ባለሀብቶች ገብተው የሚያለሙባቸው ሁኔታዎች ተለይተው እየተሠራባቸው መሆኑንም ሚኒስትሩ ገልጸዋል፡፡
‹‹ዘርፉ አዲስ እንደ መሆኑ መጠን አለው የሚባለው መልካም አጋጣሚ ትንሽ ነው፡፡ ችግሮቹ ግን ብዙ ናቸው፡፡ ዋናው ችግራችን ግን የጥራትና የብዛት ነው፤›› የሚሉት የኢትዮጵያ ንብ ሀብት ቦርድ ፕሬዚዳንትና የቤዛ ማር አግሮ ኢንዱስትሪ ባለቤትና ሥራ አስኪያጅ አቶ ኃይለ ጊዮርጊስ ናቸው፡፡ ማርን በዘመናዊ ዘዴ ማምረት ገና በጅምር ላይ ያለ ቢሆንም፣ እስካሁን ጥቂት የማይባሉ ድርጅቶች ማር ወደ ውጭ እየላኩ ይገኛሉ ብለዋል፡፡ ላኪዎቹ ከሚያጋጥማቸው የጥራትና የብዛት ችግር ባሻገር የማሸጊያ ግብዓቶች ተደራሽ ያለመሆን በሥራቸው ላይ እንቅፋት መሆኑን የቦርዱ ፕሬዚዳንት ገልጸዋል፡፡
በዚህ መስክ የተሰማሩ ኩባንያዎች አቅማቸውን አጎልብተው በሚጠበቅባቸው መጠን ተንቀሳቅሰው እንዳይሠሩ፣ መሠረታዊ የሆነ የፋይናንስ ችግር እንዳለባቸው አቶ ኃይለ ጊዮርጊስ ገልጸዋል፡፡ ‹‹ችግሩ ብድር ማጣት አይደለም፡፡ ነገር ግን ይህ ዘርፍ በኢትዮጵያ ገና በጅምር ላይ በመሆኑ ኩባንያዎች ተበድረው ቢሠሩም፣ ያንን ያህል ተጠቃሚ የሚያደርጋቸው ገበያ አይደለም ያለው፡፡ ስለዚህም የተበደሩትን ገንዘብ ለመመለስ ጊዜ ያስፈልጋቸዋል፤›› ብለዋል፡፡
ንቦች ማርን ከማዘጋጀት ባለፈ ከአንዱ ተክል ወደ ሌላው እየበረሩ የሚፈልጉትን ሲቀስሙ ዕፅዋትን በማዳቀል ረገድ ከፍተኛ ሚና እንዳላቸው፣ ያደጉት አገሮች በብዛት የንብን ድርብ ሚና ተረድተው ከንብ ማግኘት የሚችሉትን ጥቅም እስከ መጨረሻው በመጠቀም ላይ መሆናቸውን፣ በኢትዮጵያ ግን ይኼንን ካለመረዳት ባለፈ በሚቀስሟቸው ዕፅዋት ላይ በሚረጨው ፀረ ተባይና ፀረ አረም ኬሚካሎች ምክንያት ዕልቂት እየደረሰባቸው እንደሆነ፣ እንደ ፈረንሣይ ያሉ አንዳንድ አገሮች ንቦችን የሚገድሉ ኬሚካሎች ወደ አገራቸው እንዳይገቡ ያገዱ መሆናቸውን፣ በኢትዮጵያም አምራቾችና ገበሬዎች የኬሚካሎቹን አደገኛነት ተረድተው አስፈላጊውን ጥንቃቄ እንዲያደርጉ አቶ ኃይለ ጊዮርጊስ ጥሪ አቅርበዋል፡፡