Monday, October 2, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ስፖርትብሔራዊ የዳኞች ኮሚቴ ፌዴራል ዳኛ ጌቱ ተፈራን ለአንድ ዓመት ተኩል አገደ

ብሔራዊ የዳኞች ኮሚቴ ፌዴራል ዳኛ ጌቱ ተፈራን ለአንድ ዓመት ተኩል አገደ

ቀን:

የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ብሔራዊ የዳኞች ኮሚቴ ፌዴራል ዳኛ ጌቱ ተፈራን አገደ፡፡ በፕሪሚየር ሊጉ የሁለተኛ ሳምንት ጨዋታ ፋሲል ከተማንና ሐዋሳ ከተማን በጎንደር ስታዲየም ጨዋታውን በዋና ዳኝነት የመሩት ፌዴራል ዳኛ ጌቱ ስህተት መፈጸማቸውን ያመኑ ስለመሆኑ ጭምር ብሔራዊ የዳኞች ኮሚቴ በመግለጫው አብራርቷል፡፡

በኢትዮጵያ እግር ኳስ በተለይም ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ከስፖርታዊ ጨዋነት ጋር ተያይዞ ለሚነሱ አለመግባባቶችና ሁከቶች የእግር ኳስ ዳኝነት በዋናነት ይጠቀሳል፡፡ ቡድኖች የእግር ኳስ ዳኞች በሜዳ ውስጥ በሚፈጽሙት ያልተገባ ውሳኔ ውጤት ማጣታቸው ብቻ ሳይሆን፣ ችግሩ በሚከሰትበት ወቅት ደጋፊዎቻቸው ወዳልተገባ አቅጣጫ እንዲያመሩ ምክንያት ተደርጎ ሲጠቀስ መቆየቱም አይዘነጋም፡፡

ጥቅምት 17 ቀን 2011 ዓ.ም. በይፋ የተጀመረው የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ መደበኛ ዓመታዊ የውድድር መርሐ ግብር በታሰበውና በተጠበቀው ልክ ቡድኖች በወጣላቸው ፕሮግራም መሠረት እየተከናወነ አለመሆኑ ይታወቃል፡፡ በወጣው መርሐ ግብር መሠረት ጨዋታቸውን እያከናወኑ ከሚገኙት ክለቦች መካከል ጥቅምት 25 ቀን ጎንደር ላይ የፋሲል ከተማ ሐዋሳ ከተማን 3 ለ1 ያሸነፈበት ጨዋታ ተጠቃሽ ነው፡፡ በዕለቱ ጨዋታው የተጠናቀቀው በሰላም ሳይሆን የጨዋታው የመሀል ዳኛ ሠሩት በተባለው ስህተት በከፍተኛ ውጥረት እንደነበርም ሲነገር መቆየቱ ይታወሳል፡፡

ይህንኑ ጉዳይ ሲከታተል የሰነበተው የፌዴሬሽኑ ብሔራዊ የዳኞች ኮሚቴ፣ የጨዋታውን ታዛቢ ዳኛ ሪፖርት እንዲሁም ጨዋታውን በዋና ዳኝነት የመሩት ፌዴራል ዳኛ ጌቱ የሠሩትን ስህተት አምነው ይቅርታ በመጠየቃቸው ኮሚቴው፣ በእግር ኳስ ዳኞች፣ ኢንስትራክተሮችና ታዛቢዎች የሥነ ሥርዓት ዕርምጃ ደንብ ክፍል ሦስት አንቀፅ ስድስት ተራ ቁጥር 6.8.2 እና 6.9 መሠረት ዋና ዳኛው አንድ ዓመት ከስድስት ወር ያህል ከማናቸውም የእግር ኳስ ዳኝነት እንዲታገዱ መወሰኑን አስታውቋል፡፡

ብሔራዊ የዳኞች ኮሚቴ ጥቅምት 27 ቀን ባደረገው ስብሰባ፣ ፌዴራል ዋና ዳኛ ጌቴ የፈጸሙት ከፍተኛ የቴክኒክ ስህተት ከአንድ ልምድ ካለው ፌዴራል ዳኛ የማይጠበቅ ጥፋት መሆኑን በማስታወስ፣ ዳኛው በፌዴራል ዳኝነት ማገልገል ከጀመሩበት ጊዜ አንስቶ እንዲህ ዓይነት ስህተት ፈጽመው የማያውቁና ባሳዩት የአፈጻጸም መሻሻል እንዲሁም እስከዚህ ጨዋታ ድረስ የነበራቸው መልካም ተግባር ግምት ውስጥ ገብቶ ቅጣቱ ተሻሽሎ የተላለፈ መሆኑም ተነግሯል፡፡

እንደ ብሔራዊ ዳኞች ኮሚቴ መግለጫ ከሆነ፣ በፕሪሚየር ሊጉ የሁለተኛ ሳምንት መርሐ ግብር፣ የጨዋታው የመሀል ዳኛ የሠሩት ቴክኒካል ስህተት በሕጉ መሠረት ጨዋታው እንደገና እንዲደገም የሚያደርግ መሆኑ፣ ይህ ደግሞ ፌዴሬሽኑንም ሆነ ቡድኖቹን ለተጨማሪ ኪሳራ የሚዳርግ ስህተት በመሆኑ በሕጉ መሠረት ዳኛው ሦስት ዓመት የሚደርስ ቅጣት እንዲተላለፍባቸው የሚያደርግ የነበረ መሆኑን የብሔራዊ ዳኞች ኮሚቴ ሰብሳቢ አቶ ዮሴፍ ተስፋዬ ተናግረዋል፡፡ እገዳው የተላለፈባቸው ፌዴራል ዳኛ ጌቱ ተፈራን ለማግኘት ያደረግነው ጥረት አልተሳክም፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ተመድንና ዓለም አቀፋዊ ሕግን ከእነ አሜሪካ አድራጊ ፈጣሪነት እናድን!

በገነት ዓለሙ በእኔ የተማሪነት፣ የመጀመርያ ደረጃ ተማሪነት ጊዜ፣ የመዝሙር ትምህርት...

የሰላም ዕጦትና የኢኮኖሚው መንገራገጭ አንድምታ

በንጉሥ ወዳጅነው ፍራንክ ቲስትልዌይት የተባሉ አሜሪካዊ ጸሐፊ ‹‹The Great Experiment...

ድህነት የሀብት ዕጦት ሳይሆን ያለውን በአግባቡ ለመጠቀም አለመቻል ነው

በአንድነት ኃይሉ ድህነት ላይ አልተግባባንም፡፡ ብንግባባ ኖሮ ትናንትም ምክንያት ዛሬም...