Wednesday, May 22, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

ስፖርትየመጀመሪያው የግንባታ ምዕራፍ በመጠናቀቅ ላይ የሚገኘው ብሔራዊ ስታዲየም

የመጀመሪያው የግንባታ ምዕራፍ በመጠናቀቅ ላይ የሚገኘው ብሔራዊ ስታዲየም

ቀን:

ለግንባታው ከተያዘው 2.47 ቢሊዮን ብር እስከ አሁን 1.4 ቢሊዮን ብር ክፍያ ተፈጽሟል

በቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ዘመነ መንግሥት (1923-1967) ተገንብቶ እስካሁን ከእግር ኳሳዊ እንቅስቃሴዎች እስከ ኮንሰርት ዝግጅቶች እያስተናገደ ይገኛል፡፡ የኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን የአፍሪካ መዲና ተብላ ዓመታት ላስቆጠረችው አዲስ አበባ በብዙዎች ዘንድ ‹‹አንድ ለእናቱ›› በሚል መጠሪያ የሚታወቀውን የአዲስ አበባ ስታዲየምን በውስጧ ይዛ እስከ ቅርብ ዘልቃለች፡፡ የታላቁን ኦሊምፒያን ሻምበል አበበ ቢቂላ ስያሜ የያዘው ስታዲየም ለብቸኛው የአዲስ አበባ ስታዲየም አጋዥ ይሆናል ተብሎ የተገነባው የአበበ ቢቂላ ስታዲየም በተለያዩ ውጣ ውረዶች ግንባታው በመጓተቱ  ዕድሜ ከማስቆጠር ያለፈ ፋይዳ ሳይኖረው ዛሬም በግንባታ ላይ ይገኛል፡፡

በአዲስ አበባ ቦሌ ክፍለ ከተማ በአሁኑ ወቅት የመጀመርያውን የግንባታ ሒደቱ በመጠናቀቅ ላይ መሆኑ የሚነገርለትና ‹‹አደይ አበባ›› በሚል መጠሪያ በግንባታ ላይ የሚገኘው ብሔራዊ ስታዲየም መሠረቱን የጣለው የዛሬ ሦስት ዓመት ነው፡፡ ቃልና ተግባር ባይገኛኙም የዚህ ብሔራዊ ስታዲየም የግንባታ ጥንስስ በቃል ደረጃ የታቀደው ከሦስት አሠርታት በፊት ኢትዮጵያ የምሥራቅና መካከለኛው አፍሪካ አገሮች (ሴካፋ) ዋንጫ በአዲስ አበባ አስተናግዳ ዋንጫውን ባነሳችበት ወቅት የቀድሞ የአገሪቱ ርዕሰ ብሔር ሌተና ኮሎኔል መንግሥቱ ኃይለማርያም ለብሔራዊ ቡድኑ በብሔራዊ ቤተ መንግሥት የራት ግብዣ ሲያደርጉ በዚሁ ሥፍራ መቶ ሺሕ ተመልካች ማስተናገድ የሚችል ብሔራዊ ስታዲየም እንደሚያስገነቡ መናገራቸው አይዘነጋም፡፡

- Advertisement -

ከኢትዮጵያ ወጣቶች ስፖርት አካዴሚ ፊት ለፊት በምዕራብ አቅጣጫ ባለው 48.8 ሔክታር መሬት ላይ በ2008 ዓ.ም. የተጀመረው ብሔራዊ ስታዲየም የዓለም አቀፉን እግር ኳስ ማኅበር (ፊፋ) እና የዓለም አቀፉን ኦሊምፒክ ኮሚቴ (አይኦሲ) መሥፈርት ጠብቆ ግንባታው በመከናወን ላይ እንደሚገኝ በቀድሞ የወጣቶችና ስፖርት ሚኒስቴር በአዲሱ አደረጃጀት ስፖርት ኮሚሽን በድረ ገጹ ይፋ አድርጓል፡፡ እንደ ድረ ገጹ ከሆነ፣ የብሔራዊ ስታድየሙ የመጀመርያው የግንባታ ምዕራፍ 95 በመቶ ደርሷል፡፡

በወንበር 62,000 ተመልካቾችን እንደሚያስተናግድ የሚነገርለት የአደይ አበባ ብሔራዊ ስታዲየም፣ ጣሪያው ሙሉ በሙሉ በብረት ውቅሮች ሆኖ ቲኤፍኢ በተባለ ፋይበር ፕላስቲክ እንደሚለብስ ይጠበቃል፡፡ በቻይናው ስቴት ኮንስትራክሽን ኮርፖሬሽንና በአማካሪ ድርጅቱ ኤምኤች ኢንጂነሪንግ አማካይነት ግንባታው እየተከናወነ የሚገኘው ብሔራዊ ስታዲየም፣ ከዋናው ስታዲየም ውጪ 3,231 ተመልካቾችን ማስተናገድ የሚችሉ መለስተኛ የእግር ኳስና የመሮጪያ ትራክ (መም) ሲኖረው፣ በአንድ ጊዜ 3,500 ተሽከርካሪዎችን ማስተናገድ እንደሚችል ድረ ገጹ ያስረዳል፡፡

የብሔራዊ ስታዲየሙ ግንባታ ተጠናቆ አገልግሎት ላይ ሲውል፣ አኅጉራዊና ዓለም አቀፋዊ ዝግጅቶችን በሚያስተናግድበት ወቅት ከፍተኛ የመንግሥት ባለሥልጣናትም ይሁን ተያያዥ አገልግሎቶችን በፍጥነት ማከናወን ይቻል ዘንድ የሔሊኮፕተር ማረፍያን ጨምሮ፣ የመረብ ኳስ፣ የቅርጫት ኳስ፣ የባድሜንተን፣ የሜዳ ቴኒስ፣ ሰው ሠራሽ ሱቆችን፣ አምፊቲያትር፣ አዳራሾችን፣ እንዲሁም ፓርኮችንና ዓለም አቀፍ ደረጃቸውን የጠበቁ መፀዳጃ ቤቶችን አሟልቶ የያዘ እንደሚሆንም ተመልክቷል፡፡

በተጨማሪም ርዕሳነ ብሔርና ርዕሳነ መንግሥታት በመጡበት አግባብ ያለአንዳች ውጣ ውረድ የሚስተናገዱበት፣ ለሚዲያና ለክብር እንግዶች፣ ለስፖርተኞችና የሚመለከታቸው ሙያተኞች የሚቀመጡበት 2,000 ደረጃቸውን የጠበቁ መቀመጫዎች ይኖሩታል፡፡ የፊፋ ወይም የኦሊምፒክ ዝግጅቶች በሚኖሩበት ወቅት በሁሉም አቅጣጫ መቆጣጠር የሚችሉ ሦስት ቦታ ላይ የደኅንነት መፈተሻ መሣሪያዎች የሚገጠሙለት ስለመሆኑ ጭምር መረጃው ያመለክታል፡፡

በእነዚህ የደኅንነት መፈተሻ መሣሪያዎች አማካይነት አደጋ በሚያጋጥምበት ወቅት በአንድ ጊዜ ስድስት ሺሕ ተመልካቾችን በ9.8 ደቂቃ ውስጥ ከስታዲየሙ ማስወጣት እንደሚቻል፣ ለዚህም ሲባል 69 ሜትር ስፋት ያላቸው ደረጃዎች ይኖሩታልም ተብሏል፡፡ በስታዲየሙ ጨዋታ በሚኖርበት ወቅት  ታዳሚ ተመልካቾች አንዱ ሌላውን ዕይታ እንዳይከለክል ከ210 እስከ 340 ዲግሪ ወንበሮቹ እንደሚቀመጡና መቀመጫዎቹም በአንድ ረድፍ 30፣ 35፣ 45፣ 52፣ እና 54 ሴንቲ ሜትር ላይ በቅደም ተከተል የሚቀመጡ ይሆናል፡፡

በአዲስ አበባ ስታዲየም እንደሚደረጉት የበዓላት ዝግጅቶችና ኮንሰርቶች ዓይነት የባለቤትነት ስሜት በሌለው መልኩ ሳይሆን፣ በስታዲየሙ ዓለም አቀፍ ዝግጅቶችና ውድድሮች በማይኖሩበት ወቅት በባዶ ቦታዎች ላይ ኃላፊነት በተመላበት አግባብ ለተለያዩ ፌስቲቫሎች፣ ለሜዳ ላይ ሱቆች፣ ኤግዚቢሽኖችና ለሃይማኖታዊ በዓላት አገልግሎት እንደሚውልም በድረ ገጹ ተካቷል፡፡

ብሔራዊ ስታዲየሙ በውስጡ የሚያካትታቸው ለጨዋታ አገልግሎት የሚውለው ሜዳ ዓለም አቀፍ ደረጃውን የጠበቀ ሆኖ፣ 105 በ69 ሜትር የሆነ የእግር ኳስ ሜዳ፣ ባለስምንት ረድፍ መም ያለው የመሮጫ ትራክ ይኖረዋል፡፡ ከመሬት በታች ለተለያዩ አገልግሎት የሚውል እንዲሁም በአንድ ጊዜ ለአራት የእግር ኳስ ቡድኖች መታጠቢያና ልብስ መቀየሪያ ክፍሎች፣ ማሳጅና ማሟሟቂያ፣ የዳኞችና የአሠልጣኞች እንዲሁም ደረጃቸውን የጠበቁ የመሰብሰቢያ አዳራሾች፣ የሕክምናና የአበረታች ቅመሞች መመርመሪያ ክፍሎች፣ ቢሮዎችና የጋራ ክፍሎች እንዲሁም ካፌና ሬስቶራንቶችን አሟልቶ የያዘ መሆኑ ጭምር ተነግሯል፡፡

በተጨማሪም ከ200 በላይ አትሌቶችን መያዝ የሚችል የመታጠቢያና የልብስ መቀየሪያ ክፍል፣ የሳውና ማሳጅና የማሟሟቂያ ቦታ ያለው የስፖርት ዞን እንዲሁም አራት የመኪናና የእግረኞች መተላለፊያ ቦዮች ሲኖሩት እነዚህም ለአደጋ ጊዜ ማለትም ለእሳት አደጋ ተሸከርካሪዎች፣ ለአምቡላንስና ፀጥታና ቴክኒክ አገልግሎት እንደሚሰጥም ይታመናል፡፡

በስታዲየሙ የተለያዩ ቦታዎች አገልግሎት የሚሰጡ አሳንሰሮች፣ ደረጃቸውን የጠበቁ ጅምናዚየሞችና በአጠቃላይ ወደ 20 የሚጠጉ የመወጣጫ ደረጃዎች ያሉት መሆኑም ተመልክቷል፡፡ ለመገኛኛ ብዙኃን ባለሙያዎች በአጠቃላይ እስከ 216 ለሚደርሱ ሪፖርተሮች የሚያገለግሉ 30 ሳትኖችም ይገጠሙለታል ተብሏል፡፡ የፕሮጀክቱ ባለቤት ስፖርት ኮሚሽን በአሁኑ ወቅት ብሔራዊ ስታድየሙ የደረሰበትን የግንባታ ሒደትና ደረጃ አስመልክቶ ፕሮጀክቱን የተለያዩ ሙያተኞች ኅዳር 21 ቀን 2011 ዓ.ም. እንዲጎበኙት አድርጓል፡፡ በኮሚሽኑ መሐንዲስና የስፖርት ፋሲሊቲ ዳይሬክተር አቶ አስመራ ግዛው ስለፕሮጀክቱ ተጨማሪ ማብራሪያ ሰጥተዋል፡፡

እንደ ባለሙያው ከሆነ፣ ይህ ፕሮጀክት ለግንባታው በአጠቃላይ 2.47 ቢሊዮን ብር በጀት የተያዘለት ሲሆን፣ እስካሁን 1.4 ቢሊዮን ብር ክፍያ ተፈጽሟል፡፡ ከመጀመርያው የግንባታ ምዕራፍ የቀሩት አንዳንድ ሥራዎች በሁለት ወር ጊዜ ውስጥ ለማጠናቀቅ ዕቅድ የተያዘ መሆኑና ለመጀመርያው ምዕራፍ ግንባታ በአጠቃላይ 1.9 ቢሊዮን ብር በጀት መያዙ ጭምር ተነግሯል፡፡

እንደ ባለሙያው ገለጻ ከሆነ፣ ግንባታውን በበላይነት የሚመራው የቻይናው ስቴት ኮንስትራክሽን ኮርፖሬሽን ቢሆንም ከተቋራጩ 45 በመቶ የሚሆነው ደግሞ በአገር ውስጥ ተቋራጮች የተያዘ ነው፡፡ ሁለተኛው የግንባታ ምዕራፍ ከሁለት ወር በኋላ እንደሚጀመር የተገለጸ ሲሆን፣ የብሔራዊ ስታድየሙ ኤሌክትሮ ሜካኒካል ሥራዎች ማለትም የካሜራ፣ የወንበር፣ ሳውንድ ሲስተምና ለሌሎችም ግንባታዎች ጨረታ መውጣቱና አሸናፊዎችን የመለየት ሥራዎች እየተከናወኑ ስለመሆኑ ጭምር ተነግሯል፡፡ ለእነዚህ ግንባታዎች የሚፈርሱ ተጨማሪ መንደሮች እንደሚኖሩም ተጠቁሟል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የማዳበሪያ አቅርቦትና ውጣ ውረዱ

በቅፅል ስሙ “The Father of Chemical Warfare” እየተባለ የሚጠራው...

የኢትዮጵያ ልማት ባንክ የትርፍ ምጣኔውን ከ70 በመቶ በላይ አሳደገ

ከሁለቱ መንግሥታዊ ባንኮች መካከል አንዱ የሆነው የኢትዮጵያ ልማት ባንክ...