Monday, April 15, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

ሕብረት ኢንሹራንስ ካፒታሉን ወደ ግማሽ ቢሊዮን ብር አሳደገ

ተዛማጅ ፅሁፎች

ሕብረት ኢንሹራንስ የካፒታል መጠኑን ወደ ግማሽ ቢሊዮን ብር ለማሳደግ  ባለአክሲዮኖቹ ወሰኑ፡፡ ኩባንያው በራያ ቢራ ውስጥ ያለውን አክሲዮን መሸጡ የ2010 የሒሳብ ዓመት ትርፉን በ95 በመቶ ማሳደግ እንዳስቻለው ተገለጸ፡፡

ሕብረት ኢንሹራንስ ባለፈው ማክሰኞ ባካሄደው ጠቅላላ ጉባዔ ላይ እንደተመለከተው፣ ካፒታሉን ወደ 500 ሚሊዮን ብር ማሳደግ የሚያስችል ውሳኔ አስተላልፏል፡፡ ይህ የኩባንያው ውሳኔ በአንድ ጊዜ ካፒታሉን በዕጥፍ ማሳደጉን የሚያመለክት ነው፡፡ እ.ኤ.አ. ኦክቶበር 21 ቀን 2015 በተካሄደው አሥረኛ የባለአክሲዮኖች ጠቅላላ ጉባዔ ካፒታሉ ከ175 ሚሊዮን ብር ወደ 250 ሚሊዮን ብር እንዲያድግ ባሳለፈው ውሳኔ መሠረት፣ በ2010 የሒሳብ ዓመት መጨረሻ ላይ የሕብረት ኢንሹራንስ አክሲዮን ማኅበር ጠቅላላ የተከፈለ ካፒታል 250 ሚሊዮን ብር ሊደርስ ችሎ እንደነበር ይታወሳል፡፡ ይህ አዲሱ የካፒታል ማሳደግ ውሳኔ በአንድ ዓመት ልዩነት ያደረገ ነው፡፡

ይህ በእንዲህ እንዳለ በ2010 የሒሳብ ዓመት ኩባንያው 473 ሚሊዮን ብር አጠቃላይ የዓረቦን ገቢ የሰበሰበ ሲሆን፣ ከዚህ ውስጥ 437 ብር ሕይወት ነክ ካልሆነ የኢንሹራንስ ዘርፍ እንዲሁም 35 ሚሊዮን ብር ሕይወት ነክ ከሆነ የመድን ዘርፍ የተሰበሰበ ገቢ ነው፡፡ የቦርድ ሰብሳቢውን አቶ ግርማ ዋቄ እንደገለጹት፣ በተጠናቀቀው ሒሳብ ዓመት የተገኘው ጠቅላላ የዓረቦን ገቢ መጠን ካለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነፃፀር ሕይወት ነክ ያልሆነው ዘርፍ 13 በመቶ ዕድገት የታየበት ሲሆን፣ ከሕይወት ነክ የተገኘው ገቢ ደግሞ የ20 በመቶ ዕድገት ማሳየቱንም ገልጸዋል፡፡ የኩባንያው ሕይወት ነክ ያልሆነው የኢንሹራንስ ዘርፍ ያስመዘገበው የ13 በመቶ ዕድገት በኢንዱስትሪው በአጠቃላይ ከተመዘገበው አማካይ የ11 በመቶ ዓረቦን ገቢ ዕድገት ጋር ሲነፃፀርም መጠነኛ ብልጫ ያለው በመሆኑ፣ በዚህ ረገድ የተመዘገበው ውጤት አርኪ ሊባል የሚችል እንደሆነም ጠቅሰዋል፡፡

ሕብረት ኢንሹራንስ በሒሳብ ዓመቱ ለጉዳት የከፈለው ክፍያ ከቀዳሚው ዓመት ያነሰ ሆኖ መገኘቱንም ለማወቅ ተችሏል፡፡ አቶ ግርማ እንደገለጹትም ‹‹ኩባንያው ያገኘው የዓረቦን ገቢ ከተደረገው የካሳ ክፍያ በንፅፅር ሲሰላ የካሳ ክፍያ ምጣኔ በቀዳሚው ዓመት ከነበረው 7.05 በመቶ ቅናሽ በማስመዝገብ 67.9 በመቶ ሊሆን ችሏል፡፡›› ይህም ለኩባንያው በ2010 የሒሳብ ዓመት ለታየው ትርፍ ዕድገት የራሱን በጎ አስተዋጽኦ እንዳበረከተም ጠቅሰዋል፡፡

ይህ በእንዲህ እንዳለ ኩባንያው በሒሳብ  ዓመቱ አጠቃላይ የትርፍ መጠን 132 ብር ማትረፍ ችሏል፡፡ ይህ የትርፍ መጠን ከቀዳሚው ዓመት የ67 ሚሊዮን ብር ጋር ሲነፃፀር የ95 በመቶ ከፍተኛ ዕድገት ወይም ብልጫ አሳይቷል፡፡ ምንም እንኳ ከዓብይ የመድን ዘርፍ የተገኘው የትርፍ መጠን ካለፈው ዓመት ጋር ሲነፃፀር የ26 በመቶ ብልጫ ያስመዘገበ ቢሆንም፣ በ2010 የሒሳብ ዓመት የተገኘው የትርፍ መጠን ከፍተኛ ሊሆን የቻለው ኩባንያው በራያ ቢራ አክሲዮን ማኅበር የነበረውን የአክሲዮን ድርሻ በመሸጡ ምክንያት ከሽያጩ 54 ሚሊዮን ብር የተጣራ ትርፍ ማግኘት በመቻሉ  መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች