Thursday, May 30, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

የተመድ ሪፖርት ያላደጉ አገሮች ለሥራ ፈጠራ እንደማይመቹ አስፍሯል

spot_img

ተዛማጅ ፅሁፎች

የዓለም ንግድ ድርጅት የድጋፍ ፎረም ለአፍሪካ ተስፋ ተደርጓል

ኢትዮጵያ አዲሱን ተደራዳሪዋን ትጠብቃለች

ሰሞኑን ይፋ የተደረገው የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት አካል የሆነው የንግድና የልማት ጉባዔ ሪፖርት፣ አብዛኞቹ ያላደጉ ወይም በልማት ወደ ኋላ የቀሩ አገሮች ለሥራ ፈጠሪዎች የሚያበረታታ ምቹና ድጋፍ የመስጠት ችግር እንደሚታይባቸው አስፍሯል፡፡

‹‹ሥራ ፈጣሪነት ለመዋቅራዊ ለውጥ›› ወይም ‹‹ኢንተርፕርነርሺፕ ፎር ስራክቸራል ትራንስፎርሜሽን›› በሚል ርዕስ ይፋ የተደረገው ሪፖርት፣ ኢትዮጵያን ጨምሮ በዓለም ካሉ አገሮች ውስጥ 47 በልማት ወደ ኋላ የቀሩ የሚላቸውን አገሮች ጠቅሶ እንዳሰፈረው፣ እነዚህ አገሮች ውስጥ በራሳቸው መንገድ ሥራ በመፍጠር ራሳቸውን ቀጥረው የሚሠሩ ሰዎች ብዛት ከ70 በመቶ በላይ ሥራ ፈጣሪዎች እንዳሏቸው ይጠቅሳል፡፡ ይሁን እንጂ ሰፊው የእነዚህ ድሃ አገሮች ሥራ ፈጣሪዎች እንቅስቃሴና ደፋ ቀና ድጋፍ ባለማግኘቱ እንደበለፀጉትና እያደጉ ካሉ አገሮች ሥራ ፈጣሪዎች አኳያ መዋቅራዊ ለውጥ ለማምጣት የሚያስችል ቁመና አልተላበሱም፡፡

የፋይናንስ አቅም ውሱንነት ሲኖርም ለአነስተኛ ሥራ ፈጣሪዎች አለማቅረብ፣ የመሠረተ ልማት አለመሟላት በተለይም መብራት በየጊዜው የሚቋረጥበት፣ ውኃ፣ ስልክ ኢንተርኔትና ሌሎችም ለንግድና አገልግሎት ሥራዎች ወሳኝነት ያላቸው መሠረተ ልማቶች መጓደል፣ አስፈላጊውን ድጋፍና ዕገዛ የሚሰጡ ተቋማት አለመኖር፣ ድህነት፣ ሴቶችን የሚያገሉ ልማዳዊ አሠራሮች መንሰራፋት፣ ሥራ ለመጀመር ሲነሱም የንግድ ምዝገባና መሰል ወጪዎች ከፍተኛ መሆን፣ የፖለቲካ፣ የኢኮኖሚና የአካባቢ ነክ ሥጋቶች ከፍተኛ መሆን ኢትዮጵያን ጨምሮ የበርካታ በልማት ወደ ኋላ የቀሩ ያላደጉ አገሮች ውስጥ የሚፍጨረጨሩ ሥራ ፈጣሪዎችን እንቅስቃሴ ከባድ በማድረግ የማይመቹ አገሮች ተብለዋል፡፡

በእነዚህ አገሮች ውስጥ የሚገኙ ጥቃቅንና አነስተኛ ኢንተርፕራይዞች ቢያንስ እስከ 20 ሠራተኞች የመቅጠር አቅም ያላቸው ሆነው ቢገኙም፣ ከ70 በመቶው ያላነሱት በአብዛኛው ራሳቸውን በመቅጠር የሚተዳደሩ ናቸው፡፡ አብዛኞቹም ለሥራ ምቹ አጋጣሚዎችን በመመልከትና ለፈጠራ በመነሳት ሳይሆን የጎደላቸውን መሠረታዊ ጉዳይ ለማሟላት በማሰብ የሚመሠረቱ ስለመሆናቸው የተመድ ሪፖርት ይተነትናል፡፡

በእነዚህ አገሮች ውስጥ የሚገኙ ሥራ ፈጣሪዎችን ለመደገፍ መንግሥታት ሊከተሏቸውና ሊያከናውኑ ከሚገቧቸው ድጋፎች በተጨማሪ ‹‹የልማታዊ መንግሥት›› ሥርዓትን አጠንክረው እንዲከተሉ፣ የኢንዱስትሪ ፖሊሲዎችን በማውጣትና በመተግበር እንዲያግዙ የሚጠይቀው ሪፖርት፣ የእነዚህ አገሮች ሥራ ፈጣሪዎች በመንግሥታቸው ፖሊሲ፣ በገበያ ሥርዓት፣ በገበያ ውድድር፣ በዓለም አቀፍና አኅጉራዊ የኢኮኖሚ ሁኔታዎች ሳቢያ ጫና ውስጥ የሚገኙ ስለመሆናቸው ያትታል፡፡

በእንዲህ ያሉት ጫና ውስጥ እንዲያልፉና ከተሳካላቸውም አብዛኛውን ውጣ ውረድ ማለፍ ግድ የሚላቸው ሥራ ፈጣሪዎች፣ ብዙውን ጊዜ ሥራ በጀመሩ በአምስት ዓመት ውስጥ ከገበያ የመውጣት አደጋ ያንዣበባቸው ናቸው፡፡ አብዛኞቹም ኢመደበኛ በሆነው የኢኮኖሚ መስመር ውስጥ ለመቆየት ይገደዳሉ፡፡ በመሆኑም የፋይናንስ ችግራቸው ቢቀረፍላቸው፣ የመፍጠር አቅማቸውን የሚያበረታታ ድጋፍ ቢደርግላቸው፣ የሕግ፣ የትምህርትና የግንዛቤ ማስጨበጫ ድጋፎች ቢያገኙ፣ የድሆቹ አገሮች ሥራ ፈጣሪዎች ከራሳቸው አልፈው ለሌሎች በርካታ ዜጎች የህልውና መሠረት መሆን የሚችሉበት አቅም እንዳላቸው ሪፖርቱ ይጠቅሳል፡፡

ባለፈው ሳምንት በመላው ዓለም ይፋ የተደረገው ይህ ሪፖርት፣ በኢትዮጵያም በተመድ የንግድና የልማት ጉባዔ የአፍሪካ ጽሕፈት ቤት አማካይነት በአዲስ አበባ ይፋ ተደርጎ ነበር፡፡ የጽሕፈት ቤቱ ተጠሪዋ ጆይ ካቴጌካዋ (ዶ/ር) ሪፖርቱን ባቀረበቡት ወቅት ተጋባዥ ከነበሩት እንግዶች መካከል ወ/ሪት ሰምሃል ጉዕሽ አንዷ ነበረች፡፡ ሰምሃል ካባና የተሰኘ የቆዳ ውጤቶች አምራች ድርጅት ከፍታ ምርቶቿን ወደ ውጭ በተለይም ወደ አውሮፓና ሰሜን አሜሪካ በመላክ እየሠራች ትገኛለች፡፡

በትምህርቷ በአርክቴክቸር ሙያ ተመርቃ፣ በአማካሪነት ተቀጥራ ስትሠራ መቆየቷን ሆኖም፣ በራሷ ሥራ ፈጥራ፣ የራሷን ዲዛይኖች እያወጣች በማምረት ለገበያ ማቅረብ የምትችላቸውን ምርቶች በመፍጠር በአሁኑ ወቅት 31 ያህል ሠራተኞችን ያቀፈውን ካባና የተሰኘ ድርጅት ለመጠንሰስ ሥራዋን ትታ ወደ ራሷ ሥራ እንደገባች ትናገራለች፡፡

በዘንድሮው የተባበሩት መንግሥታት የልማት ፕሮግራም ድጋፍ የሚከበረውን የሥራ ፈጠራ ውድድር፣ በወጣት ሥራ ፈጣሪ ዘርፍ አሸንፋ ተሸልማች፡፡ ይሁን እንጂ አሁን ለደረሰችበት ከመብቃቷ በፊት የጀመረችውን ሥራ ለማቋረጥና መልሳ ተቀጣሪ ለመሆን ጫፍ ደርሳ የነበረችበት ጊዜ እንደነበረም ታስታውሳለች፡፡ እንደ አዲስ ከዜሮ በመነሳት አሁን ላይ በጥሩ ደረጃ እያደገ የሚገኝ ኩባንያ ለመመሥረት መብቃቷንም ገልጻለች፡፡ በተለይም የዓለም አቀፍ ገበያ ውስጥ ለመሳተፍ ያለው ዕድልና ፈታኝነቱ፣ የፋይናንስ ችግር፣ የግብዓት እጥረት፣ የአቅም ግንባታ ድጋፍ ማጣት፣ የጥናትና ምርምር ድጋፍ አለማግኘት ብሎም የመንግሥት ፖሊሲ ወሳኝ የሚባሉ ችግሮች እንደሆኑ ትጠቅሳለች፡፡

ይሁን እንጂ በኢትዮጵያ እንደ እሷ ላሉ ወጣት ሥራ ፈጣሪዎች የማይመቹ፣ ከማደግና ከማሳደግ ይልቅ ቁልቁል እየጎተቱ፣ ተስፋ አስቆርጠው ለውድቀት የሚያበቁ በርካታ ፈተናዎች እንዳሉም አብራርታለች፡፡ ሥራ ከመፍጠርና ለሌሎች የሥራ በሮችን ከመክፈት ባሻገር ልክ እንደ እሷ ሁሉ ለሌሎችም ለራሳቸውም ሥራ በመፍጠር አለኝታ መሆን የቻሉ፣ ለእሷ ተቀጥረው ይሠሩ የነበሩ ሦስት ሴቶችን ሥራ ፈጣሪ እንዲሆኑ አግዛለች፡፡

እንደ ሰምሃል ያሉ ወጣት ሥራና ፈጠራ አመንጪዎችን ለመደገፍ በማሰብ የተቋቋመው የኢትዮጵያ ሥራ ፈጠራ ልማት ማዕከል፣ በአምስት ዓመታት ቆይታው 70 ሺሕ ሠልጣኞችን ለስድስት ቀናት በሚቆይ ፕሮግራም ከመስጠት ባሻገር፣ 6,000 የሥራ ዕድሎችን ማስገኘት ያስቻሉ ድርጅቶች እንዲቋቋሙ ማገዙን የማዕከሉ የቴክኒክ አማካሪ ወ/ሪት ሃና ፈለቀ ገልጻለች፡፡ ማዕከሉ ከአዲስ አበባ ባሻገር በባህር ዳር፣ መቀሌ፣ አዳማ እንዲሁም በሐዋሳ የሥልጠና ማዕከላትን በመክፈት የራሳቸውን ድርጅት ለመክፈት የሥራ ሐሳብ ያላቸውን፣ ከፍተውም የቴክኒክ፣ የንግድ ሥራ አመራርና ሌሎችም ጉዳዮች ላይ የሥልጠና ድጋፍ የሚሹትን እየተቀበለ በነፃ እያሠለጠነ እንደሚገኝም ተጠቅሷል፡፡

እንዲህ ያሉትን ችግሮች በማቃለል ሥራ ፈጣሪነት ቢስፋፋ በኢትዮጵያና በሌሎቹም ያላደጉ አገሮች ውስጥ የሚታየውን መጠነ ሰፊ ድህነት ከማቃለል ባሻገር በየአገሮቹ ውስጥ መሠረታዊ የመዋቅራዊ ለውጥ ለማምጣት ሚና እንዳለው ጆይ (ዶ/ር) አሳርገዋል፡፡

በሌላ በኩል ከማክሰኞ ኅዳር 18 ቀን 2011 ዓ.ም. ጀምሮ እስካለፈው ሐሙስ ድረስ በአዲስ አበባ ቆይታ በማድረግ በዓለም ንግድ ጉዳይ ላይ ለውይይት የሚመጡት የተመድ የንግድና የልማት ጉባዔ ዋና ጸሐፊ ሙኪሳ ኪቱዬ (ዶ/ር)፣ ለመጀመርያ ጊዜ መላው አፍሪካን ያሳተፈ ፎረም ላይ ታድመው፣ ባለሥልጣናትንም አነጋግረዋል፡፡ ፎረሙ በዓለም የንግድ ድርጅት በኩል ለድሃ አገሮች በተቋሙ በኩል ለዓለም አቀፍ ንግድና መሰል ጉዳዮች ላይ ድጋፍ የሚያገኙበትን ስምምነት በተመለከተ እንዲሁም በአፍሪካ አገሮች የተፈጠረው የአኅጉራዊው ነፃ የንግድ ቀጣና ስምምነትና ትግበራውን የተመለከቱ ጉዳዮች ላይ በፎረሙ ውይይት ተካሔዷል፡፡ ዋና ጸሐፊው ከፎረሙ ባሻገር በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በመገኘት ለዩኒቨርሲቲው ማኅበረሰብ በዓለም የንግድ ስምምነቶችና በአፍሪካ ነፃ የንግድ ቀጣና ስምምነት ላይ ገለጻ ማቅረባቸውም ታውቋል፡፡

ኢትዮጵያ ላለፉት 16 ዓመታት የዓለም የንግድ ድርጅት አባል ለመሆን ሙከራ ስታደርግ ቆይታለች፡፡ ይሁንና የድርድሩ ሒደት ሲጓተት ቆይቷል፡፡ ለዓመታትም ተቋርጦ ነበር፡፡ የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ መለስ ዜናዊ ሕልፈት ምክንያት ተቋርጦ የቆየው የኢትዮጵያ የአባልነት ድርድር ሒደት አሁን በአዲስ መልኩ እንደሚጀመር በጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት የሚደረጉ እንቅስቃሴዎች ይጠቁማሉ፡፡ በዓለም ባንክ የዓለም አቀፉ የፋይናንስ ኮርፖሬሽን (አይኤፍሲ) ባልደረባ የሆኑት አቶ ማሞ ምሕረቱ የጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አሕመድ (ዶ/ር) አማካሪ በመሆን መመደባቸው ይታወቃል፡፡ ኢትዮጵያን በመወከል ዋና ተደራዳሪ ሆነው በዓለም የንግድ ድርጅት አባልነት ሒደት እንደሚሳተፉም መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡

እስካሁን በነበረው ሒደት ኢትዮጵያ ‹‹ጉድስ ኦፈር›› የተባለውን የድርድር ሒደት አላለፈችም፡፡ በዚህ ሒደት፣ የሌሎች አገሮች ምርቶች ከኢትዮጵያ ምርቶች አኳያ በምን አግባብ፣ በእኩልነትና በተወዳዳሪነት እንደሚስተናገዱ የሚጠይቁ እንደ ጉምሩክ ያሉ አሠራሮችን የሚመለከቱ የድርድር ሒደቶች የሚታለፍበት ሥርዓት ነው፡፡ ከዚህ የሚከተለው ‹‹ሰርቪስ ኦፈር›› የሚባለውና በአገልግሎት መስክ በተለይም እንደ ባንክ፣ ቴሌኮም፣ ኢነርጂ፣ ትራንስፖርት ወዘተ. የመሳሰሉትን የሚመለከት የታሪፍ፣ የውጭና የአገር ውስጥ የግል ኩባንያዎች የሚሳተፉበትን ዕደል የሚሰጥ፣ በመንግሥት እጅ የተያዙ የአገልግሎት ዘርፎችን ክፍት የማድረግ ድርድር የሚደረግበት ምዕራፍ ነው፡፡ ይሁንና በአዲሱ አስተዳደር እንዲህ ያሉት የድርድር ሒደቶች በቶሎ ተጠናቀው በሁለት ወይም በሦስት ዓመታት ውስጥ ኢትዮጵያ የዓለም የንግድ ድርጅት አባል የምትሆንበት ጊዜ እንደሚመጣ እየተነገረ ነው፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች