የፌዴራል ሥርዓትን የሚከተሉ ሁሉም በመላው ዓለም የሚገኙ መንግሥታት የተለያየ ቅርፅና አደረጃጀት ይኑራቸው እንጂ፣ በሁለት መሠረታዊ ባህርያት ያመሳስላቸዋል። እነዚህም በሚመሩበት ሕገ መንግሥት ተደንግጎ የተለየ የሥልጣን ክፍፍል ማድረጋቸው፣ በዚህ ማዕቀፍ ውስጥ ሆነው በአንድ አገር ውስጥ የሚኖሩ ሕዝቦችን የሚያገለግሉ ከአንድ በላይ የሆኑ ነገር ግን የሚተባበሩና የሚደጋገፉ መንግሥታት መሆናቸው ነው። ኢትዮጵያ ብሔርን መሠረት ያደረገ የፌዴራል ሥርዓት መከተል ከጀመረች ከሁለት አሥርት ዓመታት በላይ ያስቆጠረችና በዚህም የብሔረሰቦችን ተፈጥሯዊ መብቶች በማስከበርና ራስን በራስ በማስተዳደር ረገድ አዎንታዊ ዕርምጃ ብትራመድም፣ በተለይ ከቅርብ ዓመታት ወዲህ በፌዴሬሽኑ ውስጥ የሚገኙ መንግሥታትና የሕዝቦች ግንኙነት ከመተባበር ይልቅ መገዳደር ውስጥ መግባቱ ላለመረጋጋት መንስዔ እየሆነ ይገኛል። ከማንነትና ከአስተዳደር ወሰን፣ እንዲሁም ከፍትሐዊ የኢኮኖሚ ተጠቃሚነት ጋር በተያያዘ የበርካቶችን ሕይወት እየቀጠፉ በሚገኙ ደም አፋሳሽና አሰቃቂ የእርስ በርስ ግጭቶች በመላጋት፣ በሕዝቦችና በፌዴሬሽኑ ህልውና ላይ የፈጠጠ ሥጋት ተደቅኖ ይገኛል።
በመጋቢት 2010 ዓ.ም. ወደ ሥልጣን የመጣው የጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) መንግሥት አንፃራዊ መረጋጋትን በመፍጠር ተስፋን ቢፈነጥቅም፣ ግጭቶች በተለያዩ አካባቢዎች አሁንም መታየት መቀጠላቸው ሥጋቱ ከእነ ሙሉ ባህሪው አለመወገዱ ለማንም የተሰወረ አይደለም።
የግጭቶቹ መልክና ባህሪ ተመሳሳይ ቢመስልም ራሳቸውን የቻሉ ፖለቲካዊና ማኅበራዊ ልዩነቶች የወለዷቸው መንስዔዎችን የተላበሱ ናቸው። አፋጣኝ መፍትሔን ካላገኙ ደግሞ በሕዝቦች ላይ ብሎም በፌዴሬሽኑ ላይ የሚያደርሱት ጉዳት ሥጋት ይፈጥራሉ።
ይኼንን የተረዱ የሚመስሉት ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ ከፌዴራል ሥርዓቱ የተገኘውን ጥቅምና ጉዳቶች ለማጥናትና መደረግ የሚገባቸውን እርማቶች ለመለየት፣ ኮሚሽን እንደሚያቋቁሙ በተለያዩ ሕዝባዊ መድረኮች ላይ በተደጋጋሚ ሲናገሩ ተደምጠዋል።
ኮሚሽኑን ዕውን ለማድረግም እሳቸው የሚመሩት የሚኒስትሮች ምክር ቤት ኅዳር 5 ቀን 2011 ዓ.ም. ባካሄደው ስብሰባው ሁለት ኮሚሽኖችን ለማቋቋም በተረቀቁ የሕግ ሰነዶች ላይ ተወያይቶ በማፅደቅ፣ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ረቂቅ አዋጆቹን እንዲያፀድቃቸው በላከው መሠረት ኅዳር 20 ቀን 2011 ዓ.ም. ረቂቆቹ ለምክር ቤቱ ቀርበዋል።
የሕግ ሰነዶቹ እንዲያቋቁሟቸው ከሚፈለጉት ሁለት ተቋማት አንዱ የብሔራዊ ዕርቀ ሰላም ኮሚሽን ሲሆን፣ ሌላው ደግሞ የማንነትና የአስተዳደር ወሰን ጉዳዮች ኮሚሸን ነው።
የብሔራዊ ዕርቀ ሰላም ኮሚሽንን ለማቋቋም የቀረበው ረቂቅ አዋጅ እንደሚያስረዳው፣ ኮሚሽኑ የሚቋቋምበት መሠረታዊ ዓላማ በኢትዮጵያ ለበርካታ ዓመታት በተለያዩ ማኅበራዊና ፖለቲካዊ ግጭቶች ምክንያት በሕዝቦች መካከል የተደራረቡ የቁርሾ ስሜቶችን እውነትና ፍትሕ ላይ በመመሥረት ለማከም፣ በእነዚህ የታሪክ አጋጣሚዎች የሰብዓዊ መብት ጥሰትና ሌላ በደል ተጠቂዎች ወይም ተጠቂ ነን ብለው የሚያምኑ ዜጎች ስለበደላቸው የሚናገሩበት፣ እንዲሁም በደል ያደረሱ ያደረሱትን በደል በግልጽ በማውጣት የሚፀፀቱበትና ይቅርታ የሚጠይቁበትን መንገድ ለማበጀት ነው።
በውጤቱም በኢትዮጵያ ሕዝቦች መካከል ሰላም፣ ፍትሕ፣ ብሔራዊ አንድነት፣ መግባባትና ዕርቅ እንዲሰፍን በማድረግ እየፈረሰ የሚሠራ ሳይሆን፣ እየተገነባ የሚሄድ ሥርዓት እንዲፈጠር ማስቻል መሆኑን የረቂቅ አዋጁ አንቀጾች ያመለክታሉ።
የኮሚሽኑ አባላት በመንግሥት እንደሚሰየምና የኮሚሽኑ ሰብሳቢ፣ ምክትል ሰብሳቢና ሌሎች አባላት በጠቅላይ ሚኒስትሩ አቅራቢነት በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እንደሚሰየሙ፣ እንዲሁም ኮሚሽኑ ኃላፊነቱን ለመወጣት እንዲያስችለው ራሱን የቻለ ጽሕፈት ቤት እንደሚኖረው ረቂቅ ሰነዱ ይገልጻል።
የኮሚሽኑ ጽሕፈት ቤት በጠቅላይ ሚኒስትሩ የሚሾም ኃላፊና ሌሎች አስፈላጊ ሠራተኞች እንደሚኖሩትም ረቂቁ ይገልጻል። በተጨማሪም ኮሚሽኑ ሥራውን በነፃነትና በገለልተኝነት እንደሚያከናውን በረቂቁ አንቀጽ 12 ላይ የተመለከተ ሲሆን፣ የኮሚሽኑ ተጠሪነትም ለጠቅላይ ሚኒስትሩ እንደሚሆን፣ በረቂቁ አንቀጽ 2(12) ላይ ተደንግጓል። የኮሚሽኑ የሥራ ዘመን ሦስት ዓመት እንደሚሆን ነገር ግን እንደ ሁኔታው ሊራዘም እንደሚችል ተገልጿል።
በርካታ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት የኮሚሽኑን መቋቋም እንደሚቀበሉት የገለጹ ቢሆንም፣ በረቂቁ የተገለጹ አንዳንድ ቃላት ለምሳሌ ‹‹በደል›› የሚለው ቃል ትርጓሜ ሊሰጠው እንደሚገባ፣ ለበርካታ ዓመታት በተለያዩ ፖለቲካዊና ማኅበራዊ ግጭቶች ምክንያት በሕዝቦች መካከል የተፈጠረውን ቁርሾ ማከም ተገቢ ቢሆንም፣ ‹‹ለበርካታ ዓመታት›› ማለት የተለጠጠ የጊዜ ወሰን በመሆኑ ለኮሚሽኑ አዳጋች ከመሆኑ ባለፈ፣ የተረሱ በደሎችን በማስታወስ ማለቂያ ወደ ሌለው ግጭት ሊከት እንደሚችል ሥጋታቸውን ገልጸዋል።
የኮሚሽኑ አባላት በጠቅላይ ሚኒስትሩ እንደሚቀርቡ፣ የኮሚሽኑ ተጠሪነትም ለጠቅላይ ሚኒስትሩ እንደሚሆን፣ በሌላ በኩል ደግሞ ኮሚሽኑ ኃላፊነቱን በነፃነትና በገለልተኝነት ያከናውናል የሚሉት ድንጋጌዎች የኮሚሽኑን ገለልተኝነት ለማረጋገጥ እንደማያስችሉ፣ የተለያዩ የምክር ቤቱ አባላት በመግለጽ እንዲሻሻል ጠይቀዋል።
በቀጣይ የቀረበው ረቂቅ አዋጅ የአስተዳደር ወሰንና የማንነት ጉዳዮች ኮሚሸንን የሚያቋቁም ነው።
ይኼንን ኮሚሽን ማቋቋም ያስፈለገበት ምክንያት በተለያዩ ክልሎች ከአስተዳደር ወሰን፣ ራስን በራስ ከማስተዳደርና በማንነት ጥያቄዎች ዙሪያ በተደጋጋሚ የሚታዩ ግጭቶች ከፍተኛ አለመረጋጋት መንስዔ በመሆናቸው፣ ከፍተኛ ሙያዊ ብቃት ባለውና ሰላማዊ በሆነ መንገድ በአገር አቀፍ ደረጃ በማያዳግም መንገድ ለመፍታት መሆኑን የረቂቅ ሰነዱ ድንጋጌዎች ያስረዳሉ።
የዚህ ኮሚሽን ሰብሳቢ፣ ምክትል ሰብሳቢና ሌሎች አባላት በጠቅላይ ሚኒስትሩ አቅራቢነት በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እንደሚሰየሙ፣ የኮሚሽኑ ተጠሪነትም ለጠቅላይ ሚኒስትሩ እንደሚሆን በረቂቁ ተደንግጓል።
የኮሚሽኑ ሥልጣንና ተግባር በረቂቁ ተዘርዝሮ የቀረበ ሲሆን፣ ከእነዚህም መካከል ከአስተዳደራዊ ወሰኖች አከላለል፣ ራስን በራስ ከማስተዳደርና ከማንነት ጥያቄ ጋር የተገናኙ ማናቸውንም ችግሮችና ግጭቶች በጥናት በመለየት፣ አማራጭ የመፍትሔ ሐሳቦችን ለጠቅላይ ሚኒስትሩና ለፌዴሬሽን ምክር ቤት ማቅረብ አንዱ ነው።
ከአስተዳደራዊ ወሰኖች ጋር በተያያዘ የተነሱ ግጭቶች ተፈተው፣ በአጎራባች ክልሎች መካከል ያለው መልካም ግንኙነት የሚታደስበትና የሚጠናከርበትን መንገድ ማመቻቸት፣ በሕዝቦች እኩልነትና ፈቃድ ላይ የተመሠረተ አንድነት ሥር እንዲሰድና እንዲዳብር ለማድረግ ሊወሰዱ ስለሚገባቸው ዕርምጃዎች፣ ለጠቅላይ ሚኒስትሩና ለፌዴሬሽን ምክር ቤት ምክረ ሕሳቦችን ማቅረብ ሌላው የኮሚሽኑ ሥልጣን ሆኖ በረቂቁ ተደንግጓል።
ኮሚሽኑ ሥራውን በነፃነትና በገለልተኝነት እንደሚያከናውን፣ የሥራ ዘመኑ ለሦስት ዓመት ሆኖ እንዳስፈላጊነቱ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ሊራዘም እንደሚችልም በረቂቁ ተደንግጓል።
በርካታ የምክር ቤት አባላት የዚህን ረቂቅ አዋጅ ሕጋዊነት የተመለከተ ጥያቄዎችን ያነሱ ሲሆን፣ ምክንያታቸው ደግሞ ለኮሚሽኑ የሚሰጠው ተልዕኮ በሕገ መንግሥቱ በግልጽ ለፌዴሬሽን ምክር ቤት የተሰጠ መሆኑ ነው።
ሁለቱንም ኮሚሽኖች ለማቋቋም የቀረቡት ረቂቅ አዋጆች በዝርዝር እንዲታዩ ምክር ቤቱ ለሚመለከታቸው ቋሚ ኮሚቴዎች መርቷል።
ይሁን እንጂ ሪፖርተር ሁለቱንም ኮሚሽኖች ለማቋቋም በቀረቡት ረቂቅ አዋጆች ዙሪያ ያነጋገራቸው የሕግ ባለሙያዎች፣ የሚኒስትሮች ምክር ቤት በተጠቀሱት የዕርቅና ከአስተዳደር ወሰን ጋር በሚያያዙ ጉዳዮች ዙሪያ ረቂቅ ሕጎችን የማመንጨትም ሆነ ተቋማቱ እንዲቋቋሙ የማድረግ ሕገ መንግሥታዊ ሥልጣን እንደሌለው፣ ተግባሩም በፍጥነት ካልታረመም ደካማ በሆነው የተቋማት ግንባታ ሒደት ላይ ሌላ አሉታዊ ተፅዕኖ ሊያስቀጥል እንደሚችል አስጠንቅቀዋል።
የሚኒስትሮች ምክር ቤት ውሳኔ የሚፈጥረው እክል ምንድነው?
የአገሪቱ ሕገ መንግሥት ለጠቅላይ ሚኒስትሩና እሳቸው ለሚመሩት የሚኒስትሮች ምክር ቤት በዋነኝነት የሚሰጠው ሥልጣንና ተግባር የፌደራል መንግሥቱ ርዕሰ መስተዳድርነት ወይም ሥራ አስፈጻሚነት ሲሆን፣ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ደግሞ ሕግ የማውጣትና አስፈጻሚውን የመቆጣጠር፣ ለፌደሬሽን ምክር ቤትም በዋናነት ሕገ መንግሥቱን የመተርጎምና የፌዴሬሽኑ መንግሥታትን ግንኙነት በማስተባበር አገራዊ የፖለቲካ፣ የኢኮኖሚና የማኅበራዊ አንድነት እንዲጎለብት የማድረግ ኃላፊነትን በመስጠት ሕገ መንግሥቱ የሥልጣን ክፍፍልን፣ እንዲሁም የእርስ በርስ ክትትልና ቁጥጥርን ማበጀቱን በጉዳዩ ላይ ሪፖርተር ያነጋገራቸው የፌዴራሊዝምና የመንግሥታት ግንኙነት (Inter Governmental Relation) ተመራማሪ የሆኑ ስማቸውን መጥቀስ ያልፈለጉ ባለሙያ ይገልጻሉ።
ሕገ መንግሥቱ ለፌዴሬሽን ምክር ቤት በዝርዝር ከሰጠው ሥልጣንና ተግባር መካከል የሕዝቦች እኩልነትና በመፈቃቀድ ላይ የተመሠረተ አንድነት ሥር እንዲሰድና እንዲዳብር ማድረግ፣ በክልሎች መካከል ለሚነሱ አለመግባባቶች መፍትሔ ማፈላለግና የብሔር ብሔረቦችና ሕዝቦች የራስን ዕድል በራስ የመወሰን እስከ መገንጠል መብት ጋር ተያይዞ ለሚነሱ ጥያቄዎች ሕገ መንግሥቱን መሠረት በማድረግ መወሰን ዋነኞቹ መሆናቸውን ያስረዳሉ።
በተጨማሪም ይኼንን የፌዴሬሽን ምክር ቤትን ኃላፊነት ለማጠናከርና ሥልጣንና ተግባሮቹን ለመዘርዘር አዋጅ ቁጥር 251/1993 በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት መደንገጉን ያስታወሱት እኚሁ ባለሙያ፣ የፌዴሬሽን ምክር ቤት በሕገ መንግሥቱ የተጣሉበትን ኃላፊነቶች ለመወጣት የሚያስችለውን ተቋማዊ አሠራር መፍጠር እንደሚችል የዚህን አዋጅ ድንጋጌ ለአብነት ይጠቅሳሉ።
‹‹የሚነሱ አለመግባባቶችን ለማስወገድ የሚረዱ ባህላዊም ሆነ ዘመናዊ የግጭት መከላከያና ማስወገጃ ሥልቶችን በማጥናት የአሠራር ሥርዓትና ሥልት እንደሚዘረጋና ተቋማዊ ይዘትና አደረጃጀትም እንዲኖራቸው ያደርጋል፤›› በማለት በግልጽ እንደሚደነግግና ይህም የተጠቀሱት ኮሚሽኖችን የማቋቋም ኃላፊነት የፌዴሬሽን ምክር ቤት መሆኑን ያስረዳሉ።
ለሕዝቦች እኩልነትና አንድነት መጠናከር እንቅፋት የሆኑ አመለካከቶችንና አዝማሚያዎችን በማጥናትና በመለየት የመፍትሔ አቅጣጫ ቀይሶ የሚመለከታቸው እንዲያስፈጽሟቸው፣ የፌዴሬሽን ምክር ቤት ማድረግ እንደሚችል በዚሁ አዋጅ መደንገጉንም ይጠቅሳሉ።
በተለይ በዚህ አዋጅ አንቀጽ 57 ላይ የፌዴሬሽን ምክር ቤት በሥልጣን ክልሉ ውስጥ በሆኑ ጉዳዮች ላይ የሕግ ረቂቅ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የማቅረብ ሥልጣን፣ እንዲሁም የተሰጡትን ኃላፊነትና ተግባራት ለማከናወን ተገቢ ሆኖ ሲያገኘው ደንብ ማውጣት እንደሚችል መደንገጉ፣ የሚኒስትሮች ምክር ቤት ሁለቱን ኮሚሽኖች ለማቋቋም ያረቀቃቸው አዋጆች ሕግን የጣሱ ስለመሆናቸው ግልጽ ማሳያ መሆኑን ያስረዳሉ።
የሚኒስትሮች ምክር ቤትን ሥልጣንና ተግባር በሚዘረዝረው የሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 77 ሥር ሁለቱ ኮሚሽኖች እንደሚያከናውኗቸው የተገለጹ ኃላፊነቶች አንድም ቦታ አለመጠቀሱን፣ ሕገ መንግሥቱ ለጠቅላይ ሚኒስትሩና እሳቸው ለሚመሩት የሚኒስትሮች ምክር ቤት የሚሰጠው ሥልጣን የፌዴራል መንግሥት ርዕሰ መስተዳድርነትን ወይም አስፈጻሚነትን እንደሆነ ያስረዳሉ።
ይሁን እንጂ በአንቀጽ 77 ሥር የሚኒስትሮች ምክር ቤት የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅን ጨምሮ በማናቸውም አስፈላጊ ነው ብሎ ባመነባቸው ጉዳዮች ላይ ሕግ በማመንጨት፣ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ማፀደቅ እንደሚችል የሚደነግግ መሆኑን ባለሙያው ይጠቅሳሉ። ነገር ግን ይህ ድንጋጌ መታየት ወይም መተርጎም ያለበት ሕገ መንግሥቱ ለሚኒስትሮች ምክር ቤት ከሰጠው መሠረታዊ የሥራ አስፈጻሚነት ሥልጣን አንፃር ብቻ ሊሆን እንደሚገባ ባለቤታቸው ይከራከራሉ።
ማናቸውንም ሕግ የማመንጨት ሥልጣን ለሚኒስትሮች ምክር ቤት ተሰጥቷል ተብሎ ኮሚሽኖቹ እንዲቋቋሙ የሕግ ረቂቅ ማፅደቁ የፌዴሬሽን ምክር ቤት የሥልጣን ክልልን የሚጥስ የሕግ ስህተት ብቻ ሳይሆን፣ ተቋሙን በድጋሚ የማዳከም ተግባር እንደሚሆን ወይም ይኼንን ውጤት እንደሚያስከትልም አስጠንቅቀዋል።
አገሪቱ ከወሰንና ከማንነት ጋር በተያያዙ ግጭቶች ለዓመታት ስትናወጥ በከረመችበት ወቅት የፌዴሬሽን ምክር ቤት ይህ ሥልጣን የት ነበረ የሚል ጥያቄ መነሳቱ ተገቢ ቢሆንም፣ መልሱ የሚያጠነጥነው ሥራ አስፈጻሚው መንግሥት ላለፋት ሁለት አሥርት ዓመታት የፌዴሬሽን ምክር ቤትን ሥልጣንና ተግባር ነጥቆ በመውሰዱ መሆኑን ባለሙያው ይሞግታሉ።
ላለፋት ሁለት አሥርት ዓመታት የነበረው ሥራ አስፈጻሚ መንግሥት ባቋቋመው የፌዴራል ጉዳዮች ሚኒስቴር አማካይነት የፌዴሬሽን ምክር ቤትን ሥልጣንና ኃላፊነት ነጥቆ በመጠቅለሉ ምክር ቤቱ ደካማ ተቋም ሆኗል፡፡ ነጣቂ የነበረውም የፌዴሬሽን ምክር ቤት ፋይዳ አልባ ሆኖ በአሁኑ ወቅት መፍረሱን ይጠቅሳሉ። በመሆኑም አሁን ሥልጣን ላይ ያለው ሥራ አስፈጻሚ መንግሥት ኮሚሽኖቹን ለማቋቋም የሚያደርገው ጥረት ከተመሳሳይ ጣልቃ ገብነት የዘለለ ፋይዳ እንደማይኖረው ይከራከራሉ።
ለዚህ የሚያቀርቡት ምክንያት ደግሞ በፌዴራሊዝም ሥርዓት ወስጥ በተለይም ቋንቋንና አሰፋፈርን መሠረት ባደረገ ፌዴሬሽን ውስጥ ግጭት ተፈጥሯዊ በመሆኑ፣ ግጭቶችን የሚፈታ ጠንካራ ተቋም መገንባት ዘላቂ መፍትሔ ሊሆን እንደሚገባ ያሳስባሉ።
በጉዳዩ ላይ ሪፖርተር ያነጋገራቸው በፌዴራል ጉዳዮች ሚኒስቴር በግጭት ጉዳዮች ላይ ከፍተኛ አማካሪ የነበሩትና በአሁኑ ወቅት በአንድ የውጭ ተቋም የፖለቲካ ጉዳዮች አማካሪ ሆነው በማገልገል ላይ የሚገኙት አቶ ምሥጋናው ሙሉጌታ፣ የፌዴሬሽን ምክር ቤትን ደካማ ተቋም ያደረገው በፌዴራል ጉዳዮች ሚኒስቴር በኩል የተደረገው የፖለቲካ ጣልቃ ገብነት መሆኑን ይስማማሉ።
በአሁኑ ወቅት ጊዜያዊ ኮሚሽኖችን ለማቋቋም የተፈለገበት ምክንያት ትርጉም ይኖረዋል ብለው አንደማያምኑም ለሪፖርተር ገልጸዋል።
በሰጡት ማብራሪያም ጊዜያዊ (Ad hoc) ኮሚሽኖች ወይም ተቋማት እንዲቋቋሙ የሚደረገው በሁለት ምክንያት እንደሆነ ያስረዳሉ።
‹‹አንደኛው ምክንያት ኃላፊነቱን መወጣት የሚችል ተቋም ሳይኖር ሲቀር ወይም ያለው ተቋም ሽባ ሲሆን፣ አልያም በሕዝብ ዘንድ ተዓማኒነቱን ያጣ ከሆነ ነው፤›› የሚሉት አቶ ምሥጋናው፣ ‹‹ሌላው አዲስ ኮሚሽን ለማቋቋም ምክንያት የሚሆነው ተቋሙ የሚሠራበት መርህ (ፎርሙላ) የተቀየረ እንደሆነ ነው፤›› ብለዋል።
አሁን ባለው ሁኔታ የሚቋቋሙት ሁለት ኮሚሽኖች እንዲያከናውኑ የሚፈለገውን ተግባር ለመወጣት እንዲያስችለው የተነደፈ አዲስ መተግበሪያ ‹ፎርሙላ› አለመኖሩን፣ የሚሰጣቸውን ተልዕኮ ለመወጣት የሚከተሉት ማንነትን፣ ቋንቋንና አሰፋፈርን መሠረት ያደረገ የከረመ ‹ፎርሙላ› መሆኑን ይገልጻሉ። ይህ ፎርሙላ ሕገ መንግሥታዊ ከመሆኑ የተነሳ ለመቀየር እንደማይቻል የጠቀሱት አቶ ምሥጋናው፣ በተመሳሳይ የችግሮቹ መፍቻ መንገድ እንዲሠሩ ኮሚሽኖቹን ማቋቋም ከጊዜ መግዣነት ያለፈ ትርጉም ይኖረዋል ብለው እንደማያምኑ ገልጸዋል።
ይህ ከሆነ ደግሞ ያለውን የፌዴሬሽን ምክር ቤት ድክመቶች የሚቀርፍ ጥገና በማካሄድ፣ በማጠናከርና ገጽታውን በመመለስ የተባሉትን ኃላፊነቶች ይዞ እንዲቀጥል በማድረግ ዘላቂና ጠንካራ ተቋም መገንባት የተሻለ መሆኑን ያሳስባሉ።
ምርጫ ቦርድ ምርጫ ለመምራት ተዓማኒነት እንዳልነበረው፣ ነገር ግን ይኼንኑ ተቋም በመጠገንና ገጽታውን በማሻሻል እንዲቀጥል በአሁኑ ወቅት በመካሄድ ላይ የሚገኙትን ተግባራት በማሳያነት በመጥቀስ፣ ይኼንኑ ተሞክሮ በመድገም የፌዴሬሽን ምክር ቤትን ማጠናከሩ ተገቢና ዘላቂ ፋይዳ እንደሚኖረው አስተያየታቸውን ሰጥተዋል። የፌዴሬሽን ምክር ቤት ምን ይላል?
የፌዴሬሽን ምክር ቤት በሚያዚያ ወር 2010 ዓ.ም. ባካሄደው ስብሰባ አንድ ፖሊሲ አፅድቋል። ይህ ፖሊሲ በክልል መንግሥታት መካከል፣ እንዲሁም በክልሎችና በፌዴራል መንግሥት መካከል የሚኖረው ግንኙነት በሕግ የሚመራና ዘላቂ የሆነ ተቋማዊ መሠረት እንዲኖረው የሚያስችል የመንግሥታት ግንኙነት ፖሊሲ የተሰኘ ነው።
የኢትዮጵያ ፌዴራሊዝም ሥርዓት ከተመሠረተ ከሁለት አሥርት ዓመታት በላይ ቢያስቆጥርም፣ የፌዴሬሽኑ መንግሥታት ሕጋዊ ማዕቀፍን የተከተለ ተቋማዊ ግንኙነት ከማድረግ ይልቅ በገዥው ፓርቲ ላይ የተንጠለጠለ እንደሆነ፣ ይህ የፓርቲ መስመር በመንግሥታት ግንኙነት ላይ የበላይነትን በመያዝ የመንግሥታት ግንኙነት ሥርዓቱ ተቋማዊ እንዳይሆን እክል መፍጠሩን ፖሊሲውን ለማፅደቅ በወቅቱ የቀረበው የውሳኔ ሐሳብ ይገልጻል።
የፓርቲ ግንኙነት መስመሩ ለጊዜው ጠቃሚ ቢመስልም የኢሕአዴግ አውራ ፓርቲነት ቀስ በቀስ ተቀይሮ የተለያዩ ፓርቲዎች በተለያዩ እርከን ሥልጣን የሚይዙበት ዕድል ቢፈጠር፣ በፓርቲዎቹ ብሎም በፌዴሬሽኑ መንግሥታት መካከል የሚኖረው ግንኙነት ሰላማዊና የሰመረ ላይሆን እንደሚችልና የፌዴራል ሥርዓቱን ህልውና አደጋ ላይ ሊጥል እንደሚችል ይገልጻል።
በመሆኑም የመንግሥታቱን ግንኙነት ተቋማዊ ለማድረግና ግንኙነቱን ሙያዊና ቴክኒካዊ በሆነ መንገድ የሚያስተባብርና ተፈጻሚነቱንም የሚከታተል አንድ አገር አቀፍ ተቋም፣ በፌዴራልና በክልል መንግሥታት በጋራ እንዲመሠረት የሚያስችል ፖሊሲ በማፅደቅ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤትም ሕግ እንዲወጣለት ወስኗል።
በዚህ ፖሊሲ አማካኝነት እንዲመሠረት የታቀደው ተቋም በፌዴራል መንግሥትና በክልሎች መካከል፣ እንዲሁም በክልሎች መካከል አለመግባባቶችና ግጭቶች የሚፈቱበት የግንኙነት ተቋም እንደሚሆንም የውሳኔ ሐሳቡ ያመለክታል።
ይህ ፖሊሲ በፌዴሬሽን ምክር ቤት በሚያዚያ ወር ቢፀድቅም፣ እስካሁን ፖሊሲው በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ቀርቦ አልፀደቀም። ፖሊሲው በዚህ የተጓተተ ሁኔታ ውስጥ እያለ ነው፣ የሚኒስትሮች ምክር ቤት ሁለቱ ኮሚሽኖች እንዲቋቋሙ ረቂቅ አዋጆቹን ለፓርላማ ያቀረበው።
ሪፖርተር ሁለቱን ኮሚሽኖች የሚያቋቁሙ አዋጆችን የማፅደቅ ሒደት መጀመሩን ተከትሎ የፌዴሬሽን ምክር ቤትን አቋም ጠይቋል።
በጉዳዩ ላይ አስተያየት የሰጡት የፌዴሬሽን ምክር ቤት የሕዝብ ግንኙነት ዳይሬክተር አቶ ገብሩ ገብረ ሥላሴ ምክር ቤቱ ኮሚሽኖቹን ለማቋቋም የተጀመረውን ጥረት እንደሰማ፣ የባለሙያዎች ቡድን መሥርቶ ከፌዴሬሽን ምክር ቤት ሥልጣንና ከሕገ መንግሥቱ ጋር የሚጣረስ መሆን ወይም አለመሆኑን ማጥናት እንደ ጀመረ ተናግረዋል። በመሆኑም ጥናቱን እንደጨረሰ የፌዴሬሽን ምክር ቤት አቋሙን እንደሚገልጽ አስታውቀዋል።