Thursday, June 8, 2023
- Advertisment -
- Advertisment -

ከግጭት ወደ ግጭት የሚደረገው ሽግግር ይብቃ!

በአገሪቱ የተለያዩ አካባቢዎች አሁንም ግጭቶች አሉ፡፡ ከግጭት ወደ ግጭት የሚደረገው ሽግግር መቋጫ ባለማግኘቱ፣ በተለያዩ ሥፍራዎች ግጭቶች እየተቀሰቀሱ የንፁኃን ደም እየፈሰሰ ነው፡፡ በሰላም ወጥቶ መግባት ከባድ በሆነባቸው ቦታዎች ንፁኃን ሕይወታቸውን በከንቱ እየገበሩ ነው፡፡ ሕፃናት፣ አረጋውያንና አቅመ ደካሞች ጭምር የጥቃት ሰለባ እየሆኑ ነው፡፡ በቅርቡ በኦሮሚያ ክልልና በቤኒሻንጉል ጉሙዝ አካባቢዎች በተፈጸሙ ጥቃቶች ንፁኃንና የፀጥታ አስከባሪዎች ተገድለዋል፣ በሺዎች የሚቆጠሩ ወገኖች ተፈናቅለዋል፡፡ ሰሞኑን በአማራ ክልል በማዕከላዊ ጎንደር ዞን በጭልጋ በተፈጸመ ጥቃት በንፁኃን ሕይወትና ንብረት ላይ ከፍተኛ ጉዳት ደርሷል፡፡ ቀደም ሲል በተለያዩ አካባቢዎች በተፈጸሙ ጥቃቶች ከደረሰው ጉዳት ማገገም ሳይቻል፣ በተለያዩ አካባቢዎች እየደረሱ ያሉ ጥቃቶች የንፁኃንን ሕይወት እየቀጠፉ ነው፡፡ ሰላምና መረጋጋት እየደፈረሰ የዜጎች ደኅንነት ለአደጋ ተጋልጧል፡፡ ከዚህ ዓይነቱ አደገኛ አዙሪት ውስጥ በፍጥነት መውጣት ይገባል፡፡

መንግሥት የሕዝብን ደኅንነትና ሰላም የማስከበር ኃላፊነት ብቻ ሳይሆን፣ የአገር ሉዓላዊነት የመጠበቅ ግዴታም አለበት፡፡ በሌላ በኩል የአገር ጉዳይ ያገባናል የሚሉ ወገኖችም የበኩላቸውን ኃላፊነት መወጣት ይኖርባቸዋል፡፡ በተለይ ሕግ የማስከበር ኃላፊነት ያለባቸው አካላት ሕገወጦችን ለሕግ የማቅረብ ኃላፊነት ሲኖርባቸው፣ ዜጎችን ከአጥቂዎች የመከላከል ግዴታም አለባቸው፡፡ መንግሥት በየደረጃው ያሉ መዋቅሮቹን ፈትሾና አጥርቶ በአግባቡ ሥራቸውን ማከናወናቸውን ወይም አለማከናወናቸውን ማረጋገጥ አለበት፡፡ በተለይ የታችኛው መዋቅር ሥራውን ማከናወን የሚችልበት ደረጃ ላይ ስለማይገኝ፣ ሕገወጦች እንዳሻቸው እየፈነጩ የሕዝብና የአገር ሰላም እያደፈረሱ ነው፡፡ ከዚህ ቀደም ታይተው የማይታወቁ ግጭቶች በየቦታው እየተከሰቱ የንፁኃን ደም ሲፈስ፣ የየአካባቢዎቹ የአስተዳደር መዋቅሮችና የፀጥታ አካላት ምን እየሠሩ እንደሆነ በግልጽ መታወቅ አለበት፡፡ አንፃራዊ የነበረው ሰላም ደፍርሶ ንፁኃን ሰለባ እየሆኑ ነው፡፡ ይህ ችግር በፍጥነት ካልተገታ አደጋ አለው፡፡

መንግሥት መግለጫ ከማውጣትና ጥቃቶችን ከማውገዝ በዘለለ፣ ሕገወጥነትንና ሥርዓተ አልበኝነትን በሕጋዊ መንገድ አደብ የማስገዛት ኃላፊነት አለበት፡፡ የሕዝብ ደኅንነትና የአገር ህልውና ለመንግሥት የተሰጠ ኃላፊነት በመሆኑ፣ አጥፊዎችን ሕግ ፊት አቅርቦ ተገቢውን ቅጣት እንዲያገኙ ማድረግ ጊዜ ሊሰጠው የማይገባ ተግባር መሆን አለበት፡፡ ሰሞኑን በኦሮሚያ ክልል በተደረጉ ሰላማዊ ሠልፎች ሕዝብ እየጠየቀ ያለው ይኼንን ነው፡፡ በሌሎች አካባቢዎችም ግጭቶች ከመቀስቀሳቸውና ጥፋት ከማድረሳቸው በፊት፣ መንግሥት የሕዝቡን ደኅንነት የማስጠበቅ ኃላፊነት እንዳለበት ግልጽ ነው፡፡ ይኼንን ኃላፊነት ሌሎች የኅብረተሰብ ክፍሎችም ሊጋሩት ይገባል፡፡ በተለይ የሃይማኖት ተቋማት፣ የፖለቲካ ፓርቲዎች፣ የትምህርት ተቋማት፣ የሲቪክና የሙያ ማኅበራት፣ የአገር ሽማግሌዎች፣ ወጣቶች፣ ሴቶችና የመሳሰሉት የኅብረተሰብ ክፍሎች የግጭት መቀስቀሻ መሠረታዊ ምክንያቶችን አብጠርጥረው ይፋ ማድረግ ይገባቸዋል፡፡ በተለያዩ ሥፍራዎች ግጭቶች ለምን ይቀሰቀሳሉ? ከግጭቶቹ ጀርባስ እንማን አሉ? ፍላጎታቸውስ ምንድነው? ወዘተ ለሚሉት ጥያቄዎች ጥርት ያለ ምላሽ መገኘት አለበት፡፡ ይኼንን ማድረግ ካልተቻለ ፈተናው ከባድ ነው፡፡ ማድረግ እየተቻለ ግን ፈተናውን ማክበድ ተገቢ አይደለም፡፡

ሰሞኑን በሐዋሳ ከተማ ገቢዎች ሚኒስቴር ባዘጋጀውና ኮንትሮባንድን አስመልክቶ በተካሄደው ውይይት ላይ የተሰማው አስደንጋጭ ነው፡፡ በመላ አገሪቱ ከሚቀሰቀሱ ግጭቶች በስተጀርባ የኮንትሮባንድ ንግድ ጥቅማቸው የተነካባቸው ቡድኖች እንዳሉበት፣ በተለያዩ ተሳታፊዎች አንደበት ተነግሯል፡፡ በኮንትሮባንድ ንግድ የደለቡ ግለሰቦች ጥቅማቸው ሲነካባቸው በየቦታው ግጭት እየቀሰቀሱ መንግሥትንና የፀጥታ ኃይሎችን ውጥረት ውስጥ ከመክተት አልፈው፣ ሕዝብ በመንግሥት ላይ ያለው አመኔታ እንዲቀንስ እያደረጉ መሆናቸው ተወስቷል፡፡ በዋና ዋና ኬላዎች ላይ እንዳሻቸው ያዙ የነበሩ ኮንትሮባንዲስቶች በግልጽ እየታወቁ፣ ለምን ተገቢው ሕጋዊ ዕርምጃ አይወሰድም ተብሏል፡፡ በውይይቱ ላይ የነበሩት ተሳታፊዎች በየደረጃው የሚገኙ አካላት ኃላፊነታቸውን በአግባቡ መወጣት ከቻሉ፣ ኮንትሮባንዲስቶችን በቁጥጥር ሥር በማዋል ግጭቶችን ማስቆም እንደሚቻል አስረድተዋል፡፡ መንግሥት ይኼንን የመሰለ ግብዓት እየቀረበለት ምን እየሠራ ነው ተብሎ መጠየቅ አለበት፡፡ በንፁኃን ሕይወት ላይ አደጋ የደቀኑ ኃይሎች በሕግ የበላይነት አደብ እንዲገዙ ማድረግ የወቅቱ ዕርምጃ መሆን አለበት፡፡ ለዚህ ዓይነቱ ዕርምጃ ደግሞ ሕዝብ ከመንግሥት ጎን ነው፡፡ የፌዴራል ጠቅላይ ዓቃቤ ሕግም ባወጣው መግለጫ የግጭት ተዋናዮችን ለሕግ አቀርባለሁ ብሏል፡፡ መፍጠን አለበት፡፡ የግድ ነውና፡፡

ምንም እንኳን በሽግግር ውስጥ በምትገኝ አገር በርካታ ውስብስብ ችግሮች ቢኖሩም፣ ሕዝብን ከጎን ማሠለፍ ከተቻለ የማይፈታ አንዳችም ችግር አይኖርም፡፡ መንግሥት ከላይ የተጠቀሱትን የኅብረተሰብ ክፍሎች በሚገባ በማሳተፍና በየመስኩ ያሉ ባለሙያዎችንና ባለድርሻ አካላትን በመጠቀም፣ ከጊዜ ወደ ጊዜ መጠናቸው እየጨመሩ ያሉ ግጭቶችን ማስቆም ይቻላል፡፡ ከሕዝብ ፍላጎት በተፃራሪ ቆመው አገሪቱን የጦርነት አውድማ ለማድረግ የሚቋምጡ ኃይሎችን ጠንከር ያለ ማሳሰቢያ ወይም ማስጠንቀቂያ ከመስጠት ባለፈ፣ የሕግ ተጠያቂነት ስላለባቸው በፍጥነት ለፍትሕ ማቅረብ ተገቢ ነው፡፡ በተጨማሪም በመንግሥት መዋቅር ውስጥ ሆነው አሁንም ከሕዝብ ፍላጎት ጋር የሚጋጭ አጀንዳ ያላቸውን ወገኖች አደብ ማስገዛት ይገባል፡፡ በፀጥታ አካላት ውስጥም የሚታዩ ደንታ ቢስነቶችን መግራት ተገቢ ነው፡፡ የሕዝብንና የአገርን ደኅንነት የሚፈታተኑ ግጭቶች እያንከባለሉ አገር ማስተዳደር ስለማይቻል፣ እንዲሁም የሕዝብን አመኔታ ስለሚያሳጣ በፍጥነት መወሰን ይገባል፡፡ የሚወሰደው ዕርምጃም በሕግ የበላይነት አማካይነት የሚከናወን መሆን አለበት፡፡ የኢትዮጵያ ሕዝብ የሚፈልገው ሰላም፣ ዴሞክራሲና ልማት ነው፡፡ ከዚህ ውጪ ሌላ ዓላማ ያላቸው ኃይሎች ፀባቸው ከሕዝብ ጋር መሆኑን ማወቅ አለባቸው፡፡ መንግሥት ደግሞ የሕዝብ ተጠያቂነትና ኃላፊነት ስላለበት ሕግ የማስከበር ኃላፊነት የእሱ ብቻ ነው፡፡ በዚህ መንፈስ ከግጭት ወደ ግጭት የሚደረገውን ሽግግር በፍጥነት ማስቆም አለበት!

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

በኦሮሚያ ክልል በስድስት ከተሞች የተዋቀረውን ሸገር ከተማን የማደራጀት ሥራ ተጀመረ

በአዲስ አበባ ዙሪያ በሚገኙ ስድስት ከተሞች የተዋቀረው ሸገር ከተማን...

የኦሮሞን ሕዝብ ታሪክ አልባ በማድረግ ታሪክ አይሠራም

በኢተፋ ቀጀላ​​  ከዛሬ ሃምሳ ዓመት ወዲህ ከተፈጠሩት የኦሮሞ ድርጅቶች መካከል ከኢጭአት በስተቀር፣...

የኢትዮጵያ ምርት ገበያ ከተለመደው አሠራር ወጣ ያለውን ‹‹የወደፊት ግብይት›› ሥርዓት በይፋ አስጀመረ

የኢትዮጵያ ምርት ገበያ ከተለመደው የማገበያየት ተግባሩ ወጣ ያለና በኢትዮጵያ...
- Advertisment -

ትኩስ ፅሁፎች

ከቀጣዩ ዓመት በጀት ውስጥ 281 ቢሊዮን ብሩ የበጀት ጉደለት ነው ተባለ

ለቀጣዩ በጀት ዓመት ከቀረበው 801.65 ቢሊዮን ብር አጠቃላይ በጀት...

የኢትዮጵያ ምርት ገበያ ከተለመደው አሠራር ወጣ ያለውን ‹‹የወደፊት ግብይት›› ሥርዓት በይፋ አስጀመረ

የኢትዮጵያ ምርት ገበያ ከተለመደው የማገበያየት ተግባሩ ወጣ ያለና በኢትዮጵያ...

የባንክ ማቋቋሚያ መሥፈርት እንደሚጠነክር ሚኒስትሩ ተናገሩ

 ባንኮች ስለውህደት እንዲያስቡም መክረዋል በኢትዮጵያ ውስጥ ባንክ ለማቋቋም የሚያስፈልገው መሥፈርት...

ማን ይቻለን?

በጠዋት የተሳፈርንበት ታክሲ ውስጥ በተከፈተው ሬዲዮ፣ ‹‹ይኼኛው ተራራ ያን...
spot_img

ተዛማጅ ፅሁፎች

አገር አጥፊ ድርጊቶች በአገር ገንቢ ተግባራት ይተኩ!

ኢትዮጵያ ውስጥ በስፋት የሚስተዋሉ ችግሮችን ለመፍታት በመንስዔዎች ላይ መግባባት ያስፈልጋል፡፡ መግባባት ሊኖር የሚችለው ደግሞ በሠለጠነ መንገድ ለመነጋገር የሚያስችል ዓውድ ሲፈጠር ነው፡፡ ለዚህ ስኬት ዕውን...

ሕገ መንግሥት ለማሻሻል ባህሪን መግራት ያስፈልጋል!

በሥራ ላይ ያለው አወዛጋቢ ሕገ መንግሥት ከፀደቀበት ከ1987 ዓ.ም. ጀምሮ እስካሁን ድረስ ከተለያዩ አቅጣጫዎች ወቀሳዎችና ተቃውሞዎች ይቀርቡበታል፡፡ ከተቃውሞዎቹ መካከል በሕገ መንግሥቱ መግቢያ ላይ ኢትዮጵያዊነትን...

የፖለቲካ ምኅዳሩ መላሸቅ ለአገር ህልውና ጠንቅ እየሆነ ነው!

የኢትዮጵያ ፖለቲካ ምኅዳር ከዕለት ወደ ዕለት የቁልቁለት ጉዞውን አባብሶ እየቀጠለ ነው፡፡ በፖለቲካ ፓርቲዎች የእርስ በርስ ግንኙነትም ሆነ በውስጠ ፓርቲ ዴሞክራሲ የሚታየው መስተጋብር፣ ውል አልባና...