Tuesday, January 31, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ዜናግጭቶችን የሚያቀነባብሩት በኮንትሮባንድና በሕገወጥ ንግድ ገንዘብ ያከማቹ መሆናቸው ተገለጸ

ግጭቶችን የሚያቀነባብሩት በኮንትሮባንድና በሕገወጥ ንግድ ገንዘብ ያከማቹ መሆናቸው ተገለጸ

ቀን:

በሦስት ዓመታት 14.3 ቢሊዮን ብር የግለሰቦች ኪስ ማድለቢያ መሆኑ ተጠቆመ

በኢትዮጵያ የተጀመረውን የዴሞክራሲ፣ የሰላም፣ የልማትና የዕድገት ለውጥ ለማደናቀፍና በተለያዩ አካባቢዎች በወንድማማች ሕዝቦች መካከል ግጭቶችን በማቀነባበር ሁከትና ብጥብጥ በመፍጠር ላይ ያሉት፣ በኮንትሮባንድና በሕገወጥ ንግድ ኪሳቸውን ያደለቡ ጥቂት ግለሰቦች መሆናቸውን የገቢዎች ሚኒስቴር አስታወቀ፡፡

‹‹ኮንትሮባንድና ሕገወጥ ንግድን መከላከል፤›› በሚል መሪ ቃል ኅዳር 23 ቀን 2011 ዓ.ም. በሐዋሳ ከተማ ከባለድርሻ አካላት ጋር ለአንድ ቀን ባዘጋጀው የምክክር መድረክ፣ ‹‹የለውጡን እንቅስቃሴ እያተራመሰው ያለው ጥቅሙ የተነካበት ኃይል ነው፡፡ የፀጥታ ኃይሉ የለውጡ አጋር ሆኖ በማገዝ ለውጡ እንዳይፋጠን እዚያም እዚህም እሳት በመለኮስና የሰው ሕይወት በማጥፋት ጊዜውን በዚያ ላይ እንዲያጠፋ እየተደረገ ነው፤›› ተብሏል፡፡

የገቢዎች ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ዘመዴ ተፈራ ባቀረቡት አጭር የዳሰሳ ጥናት እንዳስታወቁት፣ ገንዘብ ያከማቹ አካላት ለውጡን ለማደናቀፍ ጎንበስ ቀና እያሉ ነው፡፡ ሕዝቡ ኢትዮጵያ ስትፈጠር ጀምሮ አብሮ ያለ፣ ተዋዶና ተዋልዶ የኖረ መሆኑ ቢታወቅም፣ ጥቅማቸው የተነካባቸው ኮንትሮባንዲስቶች ግን እርስ በርስ በማጋጨትና የፖለቲካ አለመረጋጋት በመፍጠር አደገኛ ድርጊት እየፈጸሙ መሆኑን አስረድተዋል፡፡ ፈጥኖ ማስቆም ካልተቻለም ወዳልተፈለገ አቅጣጫ ሊሄድ እንደሚችልና የሚያስከትለውም ውጤት አደገኛ መሆኑን አክለዋል፡፡

በአገሪቱ ባሉ ዋና ዋና የጉምሩክ መፈተሻና መቆጣጠሪያ ጣቢያዎች ላይ ኮንትሮባንዲስቶች ሲያዙ የእኔን አካባቢ ሰው አትንካ የሚል አስተሳሰብ ፈተና እየሆነ መምጣቱን የጠቆሙት አቶ ዘመዴ፣ በተለይ ወጣቱ ለኮንትሮባንዲስቶችና ለሕገወጦች ኃይል እንዲሆን እየተገፋፋና ሌላ አቅጣጫ እንዲይዝ እየተደረገ መሆኑን ገልጸዋል፡፡ ኮንትሮባንድና ሕገወጥ ንግድ ከኢኮኖሚያዊና ከማኅበራዊ ጉዳቱ ባለፈ፣ የደኅንነት ወይም የጤና ጉዳይም እየሆነ መምጣቱን የገለጹት ሚኒስትር ዴኤታው፣ የመጠቀሚያ ጊዜያቸው ያለፈባቸው የምግብና የመጠጥ ምርቶች በገፍ እየገቡ በመሆኑ ልዩ ትኩረትና ጥንቃቄ እንደሚያስፈልግ አስረድተዋል፡፡ በምክክር መድረኩ ላይ የአዲስ አበባና የድሬዳዋ ከተማ አስተዳደሮችን ጨምሮ የሁሉም ክልሎች፣ ወረዳና ዞኖች የንግድ መምርያ ኃላፊዎች፣ የቢሮ ኃላፊዎች፣ የፌዴራል ፖሊስ ከፍተኛ ኃላፊዎችና የአገር ሽማግሌዎች ተሳትፈዋል፡፡

አይነኬዎች እነማን እንደነበሩና እንደሆኑ እንደሚታወቁ ተሳታፊዎቹ ጠቁመው፣ ‹‹ለምን አይጠየቁም?›› የሚል ጥያቄም አቅርበዋል፡፡ ኮንትሮባንድ ወደ መሀል አገር ሲገባ በልዩ ተሽከርካሪዎች ታጅቦ ከመግባቱም በተጨማሪ፣ በአንዳንድ ኬላዎች አካባቢ መብራት እንዲጠፋ ተደርጎ ያለ ምንም ችግር ሲገባ እንደነበር ተናግረዋል፡፡ አሁን አሁን ኬላዎችን ብቻ ሳይሆን መሀል ከተማዎችን በማለፍ፣ የጦር መሣሪያ ሳይቀር ወደተፈለገበት ከተማ እየተዘዋወረ መሆኑን፣ ደብረ ብርሃን ከተማ ላይ ተያዙ የተባለውን ክላሽንኮቭ ጠብመንጃዎች በምሳሌነት አንስተዋል፡፡ ቀንደኛ ኮንትሮባንዲስቶች ከሞያሌ በቀጥታ መርካቶ ድረስ እጃቸውን መዘርጋታቸው እየታየና እነማን እንደሆኑ እየታወቁ፣ አለባብሶ ማለፍ ጉዳቱ የከፋ እንደሚሆን ተሳታፊዎቹ ተናግረዋል፡፡

የኮንትሮባንድ ችግር ከላይ ከአመራሩ እስከ ታች ኬላ ሠራተኛ ድረስ ባሉ አካላት የሚፈጸም መሆኑን የጠቆሙት ተሳታፊዎቹ፣ የገቢዎች ሚኒስቴር አመራር ራሱ ምን ያህል ከደሙ ንፁህ ነው? ወይም ራሱን ለመለወጥ ቆርጦ ተነስቷል? በማለትም ጠይቀዋል፡፡ ችግሩ ከአመራሩና ከበታች ሠራተኞች ጋር ብቻ ተወስኖ የሚቀር ሳይሆን፣ እስከ ፍትሕ ተቋማቱ ድረስ የተዘረጋ አሠራር ስላለው ሊፈተሽ እንደሚገባም አሳስበዋል፡፡

ቀደም ሲል ለይምሰል ሆነ ወይም በነበረ አሠራር የኮንትሮባንድ ዕቃ እንጂ ያስጫነው ወይም ባለቤቱ እንደማይያዝ ጠቁመው፣ አሁን ግን ግለሰቦቹ ስለሚታወቁ አብረው መያዝና ተጠያቂ መሆን እንዳለባቸው ተሳታፊዎቹ ጠይቀዋል፡፡ ሚኒስትሩም ሆነ ሌላው ባለሥልጣን ደውሎ የእኛው ነው ይለፍ የሚባልበት ጊዜ ማብቃት እንዳለበት፣ ለአገር ዕድገትና ሕጋዊ ነጋዴዎችን ለማበረታታት ሁሉም በቅንጅት ተባብሮ መሥራትና ሕገወጦችን ማስወገድ ተገቢ መሆኑን አውስተዋል፡፡

ሌብነት ከሃይማኖት ከዘርና ከማንነት ጋር የሚያገናኘው እንደሌለ፣ ማንም ይሁን ማን ሌባ መባል አለበት በማለት ሕገወጥነትን ማስወገድ፣ ወደኋላ የማይባልበት መሆኑን አስምረውበታል፡፡ አንድ አስተያየት ሰጪ፣ ‹‹ፍትሕ ሚኒስቴር ኮንትሮባንድ ወንጀል አይደለም ብሎ ደብዳቤ ጽፎልኛል፡፡ ደብዳቤውን ማሳየት እችላለሁ፤›› ካሉ በኋላ፣ የሕገወጥ ድርጊት ተባባሪዎች የት እንዳሉ ከዚህ በላይ ማስረጃ የለም ብለዋል፡፡ ሕጉን አስፈጽሞ የሚመጣውን ጉዳት መቀበል እንደሚሻል፣ ራስን ነፃ አድርጎና ለሕግ ታዛዥ በመሆን የአገርንና የዜጎችን ደኅንነት መጠበቅ ተቀዳሚ ተግባር መሆን እንዳለበት አስገንዝበዋል፡፡

በኮንትሮባንድ የጦር መሣሪያ ሲገባ ዝም ብሎ ማየት ሽብርተኝነት ነው ያሉት የውይይቱ ተሳታፊዎች፣ ከሞያሌ እስከ ደብረ ብርሃን እስከሚደርስ ድረስ ካልተደረሰበት ቀጣዩ ምን ሊሆን እንደሚችል መናገር ጉንጭ ማልፋት ነው ብለዋል፡፡ በመሆኑም ጥቅማቸው ስለተነካባቸው እየተቅበዘበዙ የሕዝብን ሰላም እየነሱ ያሉ ኮንትሮባንዲስቶችን መቆጣጠር ጊዜ የማይሰጠው ጉዳይ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

በአገሪቱ በከፍተኛ መጠን በኮንትሮባንድ ወደ አገር ውስጥ እየገቡ ያሉ ሞተር ብስክሌቶችና ሺሻ መሆናቸውን፣ አልፎ አልፎ ሀሺሽም እንደሚገባ ተሳታፊዎቹ ተናግረዋል፡፡ ነገር ግን ሕጉ በራሱ ክፍተት ስላለበት ሺሻ ሲያጨስ የተገኘን ሰው ማጨሻውን ከማቃጠል ባለፈ፣ በወንጀል መጠየቅ እንደማይቻል ተናግረዋል፡፡ ምክንያቱም በኢትዮጵያ ሕግ ሺሻ ወንጀል ስለመሆኑ የተደነገገ ሕግ ስለሌለ መሆኑን ገልጸዋል፡፡ በተለይ በደቡብ ክልል በታክስ ሥርዓት ውስጥ ያላለፉና ታርጋ የሌላቸው ሞተር ብስክሌቶች በአሥር ሺዎች እንደሚቆጠሩ ጠቁመው፣ አብዛኛዎቹን የሚጠቀሙት አርሶ አደሮች መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡ በአንድ የገጠር ቀብር ላይ ከፈረሶች ይልቅ በመቶዎች የሚቆጠሩ ሞተር ብስክሌቶች እንደሚገኙ ገልጸው፣ ወደ ታክስ ሥርዓቱ ካለመግባታቸውም በላይ እየደረሰ ያለው አደጋ አሳሳቢ ደረጃ ላይ በመድረሱ ሊታሰብበትና ሥርዓት ሊበጅለት እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡ ያለችው አንድ አገር በመሆኗ በሰላምና በሕግ ሥርዓት ውስጥ መኖር እንደሚገባ፣ ኪሳቸው እንዳይጎልባቸው እየተሯሯጡ ሰላምን የሚያደፈርሱትም ስለሚታወቁ መንግሥት የማያዳግም ዕርምጃ መውሰድ እንዳለበት ጠቁመዋል፡፡ ይኼ ካልሆነ ግን ሕዝብ ገንፍሎ ከወጣ መመለሻ ስለሌለው መንግሥት ቁርጠኛ መሆን አለበት ብለዋል፡፡

ኮንትሮባንድ፣ ሕገወጥ ንግድ፣ ታክስ ሥወራና ማጭበርበር የኅብረተሰቡን ሚዛናዊ ሀብት ክፍፍል ከማዛባቱም ባለፈ አገር አፍራሽ በመሆኑ፣ ሁሉም የኅብረተሰብ ክፍል አምርሮ ሊታገለው የሚገባ አፀያፊ ተግባር መሆኑን የገቢዎች ሚኒስትሯ ወ/ሮ አዳነች አበቤ አስታውቀዋል፡፡

ኮንትሮባንድ ኢኮኖሚያዊ ውንብድና መሆኑንና ወጣቶችን ከማጥፋቱ በፊት በመከላከልና እስከ መጨረሻው በማጥፋት፣ ሁሉም አገራዊ ግዴታውን መወጣት እንዳለበት አሳስበዋል፡፡ ‹‹ድርጊቱ ሌብነት በመሆኑ ሁላችንም ለፍተንና ተግተን ያገኘነውን ፈጣሪ ይባርክልን ብለን፤›› ለመልካም ተግባርና አገራዊ ዕድገት መሠለፍ እንደሚገባ መክረዋል፡፡

ሚኒስትር ዴኤታው አቶ ዘመዴ፣ የኮንትሮባንድ ጉዳትን ለማሳየት፣ በአምስት ዓመታት ውስጥ ወደ አገር ውስጥ የገቡ የኮንትሮባንድ ዕቃዎችና በሕገወጥ መንገድ ወደ ውጭ የወጡ ዕቃዎችን ብዛትና የዋጋ ግምት አሳይተዋል፡፡ በአምስት ዓመታት ውስጥ ከ3.2 ቢሊዮን ብር በላይ ግምት ያላቸው ዕቃዎች ወደ አገር ውስጥ መግባታቸውንና መያዛቸውን ገልጸዋል፡፡ ወደ ውጭ በሕገወጥ መንገድ ሲወጡ የተያዙ ዕቃዎች ግምት ደግሞ 537 ሚሊዮን ብር መሆኑንም ጠቁመዋል፡፡ ይኼ የሚያሳየው ወደ አገር ውስጥ ምን ያህል ይገባል የሚለው ባይታወቅም፣ በአምስት ዓመታት ውስጥ ከተያዘው አኳያ እየጨመረ መሆኑን የሚያሳይ እንደሆነ አስረድተዋል፡፡

ሌላው ከኮንትሮባንድ ባልተናነሰ ከፍተኛ ችግር እየፈጠረ ያለው ፍራንኮ ቫሉታ መሆኑን የጠቆሙት አቶ ዘመዴ፣ በጠረፍ አካባቢ ለሚኖሩ ዜጎች ተብሎ የተፈቀደን የንግድ ሥርዓት ላልተገባ ጥቅም በማዋል የግለሰቦች ኪስ ማድለቢያ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡ ወደ ጠረፋማ አካባቢዎች መድረስ የነበረበት ሸቀጣ ሸቀጥና የንግድ ዕቃ አዳማ፣ ድሬዳዋና አዲስ አበባ እየተራገፈ ሕገወጥ ንግዱን በማባባስ ላይ እንዳለም አክለዋል፡፡ በጠረፍ አካባቢ ያሉ ዜጎች ባህላዊ አልባሳትና ቀለብ እንዲያገኙ ታቅዶ ቢፈቀድም፣ ዓላማውን ስቶ ኮንትሮባንድን በማባባስ ላይ በመሆኑ ሊቆም እንደሚገባም አሳስበዋል፡፡ ፍራንኮ ቫሉታ ከቀረጥ ነፃ በራሳቸው የውጭ ምንዛሪ እያስገቡ እንዲነግዱ መፍቀዱ በራሱ ጥቁር ገበያውን በማስፋፋትና ሌሎች ሕጋዊ ነጋዴዎች ከባንክ የሚያገኙትን የውጭ ምንዛሪ እንዲያጡ በማድረጉ፣ የተፈቀደበት አግባብ በራሱ ሕገወጥ እንደነበረም ገልጸዋል፡፡ ከ2007 ዓ.ም. እስከ 2010 ዓ.ም. አጋማሽ ድረስ 24.7 ቢሊዮን ብር ግምት ያላቸው ዕቃዎች በፍራንኮ ቫሉታ ንግድ የገቡ መሆናቸውን መንግሥት 14.3 ቢሊዮን ብር ማግኘት ሲገባው የግለሰቦች ኪስ ማድለቢያ መሆኑን በምሳሌነት ጠቅሰዋል፡፡ ይኼ ለአገር ልማት መዋል ሲችል አገር ለሚያተራምሱና ሕይወት ለሚቀጥፉ ኮንትሮባንዲስቶች መዋሉን አክለዋል፡፡ በእዚህ ላይ በተጨባጭ የሚታወቁ የአመራሮች እጅም እንዳለበት አስታውቀዋል፡፡ ለዚህ ማሳያ አንድ የኮንትሮባንድ ዕቃ መያዙ ሲሰማ ለማስለቀቅ የሚረባረበው አመራሩ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡ ‹‹የእኔን አካባቢ ሰው ይዘኸዋል›› እየተባለም ፖለቲካዊ ገጽታ እንዲኖረውም መደረጉን ገልጸዋል፡፡ ኢንቨስትመንትን በማዳከምና የሀብት ልዩነት በማምጣት አገርን ሰላም እየነሳ በመሆኑ በዚህ ሁኔታ መቀጠል እንደሌለበት ተናግረዋል፡፡

በ2006 ዓ.ም. ወደ ውጭ ከተላከ ምርት 3.2 ቢሊዮን ዶላር የተገኘ መሆኑን፣ በ2010 ዓ.ም. የተገኘው የውጭ ምንዛሪ 2.7 ቢሊዮን ዶላር መሆን ጠቁመው፣ የውጭ ምንዛሪ ግኝቱ በየዓመቱ በአማካይ 3.8 በመቶ መቀነሱን አስረድተዋል፡፡ ይኼ በልማት ላይ ያለውን እንቅፋት የሚያሳይ መሆኑንና ባንክ ወደ ውጭ ምርቶችን ለሚልኩ ፋይናንስ ማድረግ እየተሳነው እንደመጣ ተናግረዋል፡፡ ይኼም የሆነው ከፍተኛ ገቢ የሚያስገኙ ምርቶች በኮንትሮባንድ እየተንቀሳቀሱ በመሆኑ ነው ብለዋል አቶ ዘመዴ፡፡ ‹‹እንስሳትና ወርቅ ከፍተኛ የውጭ ምንዛሪ የሚገኝባቸው ምርቶች ሆኑም፣ በሕገወጦች ወደ ጎረቤት አገሮች እየተሸጋገሩ ይሸጣሉ፣ በቀንድ ከብት አንደኛ ብንሆንም በገቢ መጨረሻ ነን፤›› በማለት አስረድተዋል፡፡ እንስሳት በሕገወጥ መንገድ ተሸጠው የሚገዛው የጦር መሣሪያ በመሆኑ፣ በጣም አሳዛኝ እንደሚያደርገው ተናግረዋል፡፡

በርካታ የግብርና ምርቶች በሞያሌ በኩል እየወጡ መሆኑን፣ በቢሾፍቱ ፋብሪካው የተዘጋበት ኢንቨስተር ኬንያ ሄዶ በመክፈቱ፣ በየቀኑ በርካታ አህዮች በሞያሌ በኩል እየወጡ ስለሆነ፣ ምናልባትም በቀጣይ ዝርያቸው እንዳይጠፋ አሳሳቢ መሆኑን ተሳታፊዎቹም ጠቁመዋል፡፡ በአጠቃላይ ኮንትሮባንድ፣ ሕገወጥ ንግድንና ሕገወጦችን መንግሥትና ኅብረተሰቡ ተባብረው መቆጣጠር እንደሚገባቸው ሚኒስትሯ ወ/ሮ አዳነች አሳስበዋል፡፡            

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የገጠር መሬት ማሻሻያና የመሬት ባለቤትነት ጥያቄ በኢትዮጵያ

በኢትዮጵያ ከቅርብ ወራት ወዲህ መሬትን በተመለከተ ጠንከር ያሉ የለውጥ...

በፖለቲከኞች እጅ ያለው ቁልፍ

ኢትዮጵያ በተለይ ካለፉት አምስት ዓመታት ወዲህ ሰላሟ መረጋጋት አቅቶታል፡፡...

የኤክሳይስ ታክስ ረቂቅ አዋጅ ፓርላማው ያፀደቀውን አዋጅ የሚጥሱ ድንጋጌዎችን በማካተቱ እንዳይፀድቅ ተጠየቀ

ሰሞኑን ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የቀረበው የኤክሳይስ ታክስ ማሻሻያ...

በፀጥታ ችግር ሳቢያ ከተለያዩ አካባቢዎች ተፈናቅለው አማራ ክልል የገቡ ዜጎች ቁጥር 800 ሺሕ መድረሱ ተነገረ

በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል 112 ሺሕ ተማሪዎች ከትምህርት ገበታ ውጪ...