ባለፈው ሳምንት ወደ ናይጀሪያ አምርቶ በናይጄሪያው ሬንጀርስ 2 ለ0 ተሸንፎ የተመለሰው መከላከያ ቀጣይ የቶታል አፍሪካ ክለቦች ኮንፌዴሬሽን ተሳትፎውን ለመወሰን የሰዓታት ዕድሜ ብቻ ቀርቶታል፡፡ አሠልጣኝ ሥዩም ከበደ በናይጄሪያ ያስመዘገቡት ውጤት ቡድናቸው በዕለቱ ላደረገው እንቅስቃሴ የሚመጥነው እንዳልሆነ፣ ይሁንና በዛሬው ጨዋታም ውጤቱም ለመቀልበስ ወደ ሜዳ እንደሚገቡ ተናግረዋል፡፡
በመድረኩ ልምድ ካላቸው የአገሪቱ ክለቦች አንዱ እንደሆነ የሚነገርለት መከላከያ ሥዩም ከበደን ዋና አሠልጣኝ አድርጎ ከቀጠረ በኋላ፣ በተለይ ደግሞ ቡድኑ አሁን በቅድመ ማጣሪያው በአፍሪካ ክለቦች ኮንፌዴሬሽን ዋንጫ ላይ የሚኖረው ተሳትፎ ጥሩ እንደሚሆን ቅድመ ግምት ተሰጥት ቆይቷል፡፡ ምክንያቱም አሠልጣኙ ቡድኑን በኃላፊነት በተረከቡ ማግሥት የክለቦች ጥሎ ማለፍ ዋንጫ ባለቤት በመሆናቸውና ዘንድሮም በአኅጉራዊው መድረክ የሚኖራቸውን ተሳትፎ የተሻለ ለማድረግ ሲባል ቅድመ ዝግጅታቸውን የጀመሩት ቀደም ብለው መሆኑ ነው፡፡
ይሁንና ለአፍሪካ ክለቦች ኮንፌዴሬሽን ዋንጫ ቅድመ ማጣሪያ ባለፈው ሳምንት ወደ ናይጄሪያ አቅንቶ ከናይጀሪያው ሬንጀርስ ጋር የተጫወተው መከላከያ ያልተጠበቁ ሁለት የፍፁም ቅጣት ምት የሚያሰጡ ስህተቶችን መፈጸሙን ተከትሎ 2 ለ0 በሆነ ውጤት መሸነፉ ይታወሳል፡፡ መከላከያ ያስተናገዳቸውን ሁለት ፍፁም ቅጣት ምት አስመልክቶ የዘርፉ ሙያተኞች እንደሚናገሩት ከሆነ፣ ‹‹ለመከላከያ ተጨዋቾችም ሆነ ለአሠልጣኝ ሥዩም ከበደ ዛሬ ላይ ሆነው ያንን ውጤት ማሰብ ፍፁም ስህተት ነው፡፡ አሁን ማሰብ የሚጠበቅባቸው ውጤቱን መቀልበስ የምንችለው እንዴት ነው? በወቅቱ የተፈጠሩት በመልሱ ጨዋታ እንዳይደገሙ፣ በተቻለ መጠን የሬንጀርስ ተጨዋቾች ወደ መከላከያ ግበ ክልል እንዳይቀርቡ በማድረግና ተደጋጋሚ ጫናዎች በመፍጠር እነሱም ተመሳሳይ ጥፋት እንዲፈፅሙ ማድረግ አንዱ የጨዋታው አካል አድርጎ መውሰድ ይኖርባቸዋል፡፡ መከላከያ ውጤቱን መቀልበስ የሚችለው ይህን ማድረግ ከቻለ ብቻ ነው፤›› የሚሉት ሙያተኞቹ፣ የናይጄሪያው ሬንጀርስ ወደ አዲስ አበባ የሚመጣው ለመጫወት ሳይሆን የጨዋታውን ሰዓት አባክኖ ውጤቱን አስጠብቆ ለመውጣት እንደሚሆንም ያስረዳሉ፡፡
እንደ ሙያተኞቹ ከሆነ መከላከያና የናይጄሪያው ሬንጀርስ ያደረጉትን ሙሉ የጨዋታ እንቅስቃሴ አልተመለከቱትም፡፡ ይሁንና ሜዳ ውስጥ ከሚደረጉ የጨዋታ እንቅስቃሴዎች ልምድ በመነሳት፣ መከላከያ ላይ የተቆጠሩት ሁለት ፍፁም ቅጣት ምቶች ሬንጀርስ በተጋጣሚው ላይ ጫና ፈጥሮ መጫወቱን የሚያሳይ መሆኑን ጭምር ይናገራሉ፡፡ ሽንፈቱንና ለሬንጀርስ የተሰጡትን ሁለት ጎሎች አስመልክቶ አሠልጣኝ ሥዩም ከበደ በበኩላቸው፣ ‹‹ፍፁም እግር ኳሳዊ ባልሆነ አድሎ የተሰጡ ስጦታዎች ናቸው፤›› ብለው ይህን ሲሉ ግን ተጋጣሚያቸው ሬንጀርስን ማጣጣላቸው እንዳልሆነ፣ ቡድኑም ከምዕራብ አፍሪካ በጥንካሬያቸው ከሚጠቀሱ አንዱ ስለመሆኑ ጭምር ለተለያዩ መገናኛ ብዙኃን ሲገልጹ ተደምጠዋል፡፡