Monday, May 29, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ዓለምጆርጅ ኸርበርት ዎከር ቡሽ (1924-2018)

ጆርጅ ኸርበርት ዎከር ቡሽ (1924-2018)

ቀን:

በአሜሪካ ማሳቹሰትስ እ.ኤ.አ. ሰኔ 12 ቀን 1924 የተወለዱትና የአሜሪካ 41ኛ ፕሬዚዳንት በመሆን ያገለገሉት ጆርጅ ኸርበርት ዎከር ቡሽ (ጆርጅ ደብሊው ቡሽ ትልቁ) ዜና ዕረፍታቸው የተሰማው ባለፈው ሳምንት ነበር፡፡

የአሜሪካ 43ኛ ፕሬዚዳንት ጆርጅ ዎከር ቡሽ አባት ጆርክ ደብሊ ቡሽ ትልቁ በ94 ዓመታቸው ከዚህ ዓለም በሞት የተለዩት ኅዳር 2018 መሆኑን የተለያዩ ዓለም አቀፍ መገናኛ ብዙኃን የቡሽን ቃል አቀባይ በመጥቀስ አስፍረዋል፡፡

ጆርጅ ኸርበርት ዎከር ቡሽ ማን ናቸው?

በአሜሪካ ሚልቶን ማሳቹሰትስ የተወለዱት ጆርጅ ቡሽ ትልቁ በሁለተኛው ዓለም ጦርነት በጦር ጄት አብራሪነት ተሠልፈዋል፡፡ በ1966 በአሜሪካ ተወካዮች ምክር ቤት በመመረጥ ያገለገሉ ሲሆን፣ በሮናልድ ሬገን የፕሬዚዳንትነት ዘመንም ለሁለት ጊዜ ያህል ምክትል ፕሬዚዳንት ሆነው አገልግለዋል፡፡ በ1988 የአሜሪካ ፕሬዚዳንት ሆነው ቢመረጡም ከአንድ የሥራ ዘመን በላይ መምራት አልቻሉም፡፡ የአሜሪካ 42ኛ ፕሬዚዳንት ለሆኑት ቢል ክሊንተን ፕሬዚዳንትነቱን ቢያስተላልፉም በልጃቸው 43ኛው የአሜሪካ ፕሬዚዳንትና የቡሽ ክሊንተን ካተሪና ፈንድ ተባባሪ መሥራች ጆርጅ ዎከር ቡሽ መታወሳቸው አልቀረም፡፡

የኮንግረስ አባልና ምክትል ፕሬዚዳንትነት

በ1963 የሃሪስ ግዛት ሪፐብሊካን ፓርቲ ሰብሳቢ የነበሩት ቡሽ በ1964 በአሜሪካ ሴኔት የቴክሳስ ግዛትን መቀመጫ ለማግኘት ቢወዳደሩም አልተሳካላቸውም ነበር፡፡ ሆኖም ከሁለት ዓመታት በኋላ የአሜሪካ ተወካዮች ምክር ቤት ተመርጠው ለሁለት የሥራ ዘመን አገልግለዋል፡፡ ከዚህ በተጨማሪም በተለያዩ የኃላፊነት ሥራዎች ያገለገሉ ሲሆን፣ በ1971 በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የአሜሪካ አምባሳደር ሆነዋል፡፡ በዋተር ጌት ቅሌት ጊዜ የሪፐብሊካን ናሽናል ኮሚቴ ኃላፊም ነበሩ፡፡ በቻይና የአሜሪካ መልዕክተኛና በማዕከላዊ ኢንተለጀንስ ኤጀንሲም (ሲአይኤ) ዳይሬክተር ሆነው አገልግለዋል፡፡

ፕሬዚዳንትነት

ጆርጅ ኸርበርት ዎከር ቡሽ የአሜሪካን ፕሬዚዳንትነት የያዙት እ.ኤ.አ. በ1988 ነው፡፡ ቡሽ እንዲታወሱ ካደረጋቸው አንዱ ለፕሬዚዳንትነት ከተመረጡ በኋላ በሪፐብሊካን ናሽናል ኮንቬንሽን ባደረጉት የመጀመርያ ንግግር ‹‹ሪድ ማይ ሊፕስ ኖው ታክስስ›› አዲስ ታክስ አይኖርም ማለታቸው ነው፡፡ አዲስ ታክስ አይኖርም በማለታቸውም በታክስ ከፋዩ ዘንድ ይሁንታን አስችሯቸው ነበር፡፡

በፕሬዚዳንትነት ካከናወኗቸው ተግባራት ጥቂቶቹ

ጆርጅ ቡሽ ትልቁ ፕሬዚዳንትነቱን የተቆናጠጡት የአሜሪካ የውጭ ግንኙነት ውጥረት ውስጥ በነበረበት ጊዜ ነው፡፡ ሥልጣን በያዙ የመጀመርያዎቹ ወራት ከቀድሞዋ ሶቭዬት ኅብረት ጋር የነበረው ቀዝቃዛ ጦርነት እንዲያከትም አድርገዋል፡፡ ምሥራቅና ምዕራብ በሚል ተከፍላ የነበረችው ጀርመን ውህደቷ እንዲሰምር በግንባር ቀደምትነት ከተሰለፉት መሪዎች አንዱ ነበሩ፡፡

 በ1990 በዘይት ሀብቷ የበለፀገችውን ኩዌት የወረረችውን ኢራቅ ለማስወጣት ብሔራዊ ጥምረት ፈጥረው በወሰዱት ወታደራዊ ዕርምጃም ተሳክቶላቸዋል፡፡ ይህም በፕሬዚዳንትነት ዘመናቸው ከፈጸሟቸው ሥራዎች ውጤታማ አስብሏቸዋል፡፡

ሥልጣናቸውን ከለቀቁ በኋላ

በአንድ የሥራ ዘመን ሥልጣናቸው የለቀቁት ጆርጅ ቡሽ ትልቁ በልጃቸው ደብሊው ጆርጅ ቡሽ ሳቢያ ወደ መድረክ ብቅ ማለታቸው አልቀረም፡፡ እ.ኤ.አ. በ2000 43ኛው የአሜሪካ ፕሬዚዳንት ሆነው ለተመረጡ ልጃቸው ድጋፍ ለመስጠት በበርካታ ሕዝባዊ መድረኮች ላይ በመገኘት ንግግር አድርገዋል፡፡ ልጃቸውን በፖለቲካው ዓለም ከመደገፍ ጎን ለጎንም በአገሪቱ ባጋጠሙ ጉዳዮች ላይ ያገባኛል በማለት ተባባሪም ነበሩ፡፡  በ2005 በሃሪኬን ካትሪን ለተጎዱ ሰዎች ለመድረስ በቀድሞ የአገሪቱ ፕሬዚዳንት ቢል ክሊንተን በተቋቋመ ግብረ ኃይል ውስጥም አገልግለዋል፡፡ አደጋው በተከሰተ በጥቂት ወራት ውስጥም የቡሽ ክሊንተን ካትሪና ፈንድ ከ100 ሚሊዮን ዶላር በላይ ዕርዳታ ማሰባሰብ ችሎ ነበር፡፡ በነበራቸው የተባባሪነት መንፈስም በ2011 የፕሬዚዳንት የፍሪደም ሜዳሊያን ከባራክ ኦባማ ተሸልመዋል፡፡

የጤና እክል

ጆርጅ ኸርበርት ዎከር ቡሽ ጤናቸው መቃወስ የጀመረው ከስድስት ዓመት በፊት በ88 ዓመታቸው ነው፡፡ ብሮንካይተስ (የመተንፈሻ አካል በሽታ)፣ ፓሪኪንሰን (ራስን ችሎ የመንቀሳቀስ ችግር) በኋላም በኪንቡንከፖርት በሚገኘው ቤታቸው በመውደቃቸው የደረሰባቸው ስብራት በሕይወት ዘመናቸው የፈተኗቸው በሽታዎች ነበሩ፡፡

ባለፈው ሚያዝያ ባለቤታቸው ባርባራ ፔይርስ ቡሽ ከ73 ዓመታት የጋብቻ ሕይወት በኋላ በሞት የተለዩዋቸውን ተከትለውም ከሰባት ወራት በኋላ ማረፋቸው ተሰምቷል፡፡ ጆርጅ ዎከር ቡሽና ባለቤታቸው ባርባራ ቡሽ ስድስት ልጆችን ያፈሩ ሲሆን፣ የበኩር ልጃቸው የአሜሪካ 43ኛ ፕሬዚዳንት የነበሩት ጆርጅ ደብሊ ቡሽ ናቸው፡፡

የትልቁ ቡሽ አስከሬን ቴክሳስ ከሚገኘው መኖሪያቸው ወደ ዋሽንግተን ከመጣ በኋላ በካፒቶል ሕንፃ በመቀመጥ ለቅሶ ደራሾች ተሰናብተውታል፡፡ ከተሰናባቾቹም መካከል ፕሬዚዳንት ዶናልድና ባለቤታቸው ሜላኒያ ትራምፕ ይገኙባቸዋል፡፡ የቡሽ ሥርዓተ ቀብር ኅዳር 26 ቀን 2011 ዓ.ም. እንደሚፈጸም ታውቋል፡፡

ጥንቅር በምሕረት ሞገስ

*******

ኳታር ከነዳጅ አምራች አገሮች አባልነቷ ልትወጣ ነው

ኳታር ከነዳጅ አምራችና ላኪ አገሮች (ኦፔክ) አባልነቷ እ.ኤ.አ. ከ2019 መጀመርያ ጀምሮ እንደምትወጣ ሮይተርስ የገልፍ ኔሽን የኢነርጂ ሚኒስትር ሰኢድ ሸሪዳ አል ካቢን ጠቅሶ ዘግቧል፡፡

ለዓለም 40 በመቶ የሚሆነውን የነዳጅ ምርት ከሚያቀርቡ 15 የነዳጅ ዘይት አምራች አገሮች (ኦፔክ) አባልነት ኳታር ራሷን የምታገል መሆኑንም የአገሪቱ የነዳጅ ዘይት ኩባንያ ኳታር ፔትሮሊየም አረጋግጧል፡፡

ሚኒስትሩ አል ካቢ በዶሃ በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ ኳታር ከኦፔክ አባልነቷ ለመውጣት የወሰነችው አገሪቷ በአሁኑ ወቅት በዓመት የምታመርተውን 77 ሚሊዮን ቶን የነዳጅ ምርት በቀጣዮቹ ዓመታት ወደ 110 ሚሊዮን ቶን ለማሳደግ በማቀድ ነው ማለታቸውን አልጀዚራ ዘግቧል፡፡

ኳታር ከኦፔክ አባል አገሮች አባልነቷ ራሷን ለማግለል የወሰነች የመጀመርያዋ የገልፍ አገር ናት፡፡

የቻይናና አሜሪካ የንግድ ጦርነት ለጊዜው እፎይታ ያገኘበት የቡድን 20 አገሮች ጉባዔ

ከ19 አባል አገሮችና ከአውሮፓ ኅብረት የተሰባሰቡት የቡድን 20 አገሮች መሪዎች ባለፈው ዓርብ ነበር ጉባዔያቸውን በአርጀንቲና ቦነስ አይረስ ያደረጉት፡፡ በአካባቢያዊ የፖለቲካ ጉዳዮች ላይ በመከረው በዚህ ጉባዔ የአሜሪካው ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ፣ የቻይናው ፕሬዚዳንት ዢ ጃፒንግ የሩሲያው ፕሬዚዳንት ቭላድሚር ፑቲን፣ የጀርመኗ መራሒተ መንግሥት አንጌላ መርከልና ሌሎችም ተገኝተዋል፡፡

በዚህ ጉባዔ ነጥረው ከወጡ የኢኮኖሚ ጉዳዮች አንዱ የአሜሪካው ፕሬዚዳንት ወደ ሥልጣን ከመጡ በወዲህ በአሜሪካና በቻይና መካከል የተፈጠረውን የንግድ ጦርነት ለተወሰነ ጊዜ ረገብ የሚያደርግ ውሳኔ መተላለፉ ነው፡፡ ሁለቱም ፕሬዚዳንቶች ለቀጣዮቹ 90 ቀናት በየትኞቹም የየአገሮቹ ምርቶች ላይ የታክስ ታሪፍ ላለመጨመር ተስማምተዋል፡፡

ቢቢሲ እንደዘገበው ፕሬዚዳንት ትራምፕ 200 ቢሊዮን ዶላር በሚያወጡት የቻይና ምርቶች ላይ ለቀጣዮቹ ሦስት ወራት ታሪፍ ላለመጨመር ማለትም ከነበረው የአሥር በመቶ ታሪፍ 25 በመቶ ላለማድረግ ተስማምተዋል፡፡ በቻይና በኩልም የሁለቱን አገሮች ገበያ ክፍት ለማድረግ መስማማታቸው ተነግሯል፡፡

ዓለም አቀፉ የንግድ ድርጅት አንዱ የውይይት አጀንዳ የነበረ ሲሆን፣ የፈረንሣዩ ፕሬዚዳንት ኢማኑኤል ማክሮን የንግድ ግጭቶች እንዳይኖሩ የሚቆጣጠረው ዓለም አቀፍ የንግድ ድርጅት ዘመናዊ መሆን ይገባዋል ብለዋል፡፡

ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ዓለም አቀፍ የንግድ ድርጅት ዓላማውን እየሳተ እንደነበር ቢነገርም ይህ በቡድን 20 አባል አገሮች በኩል ተቀባይነት አላገኘም ነበር፡፡ ሰሞኑን በአርጀንቲና በተደረገው ጉባዔ ግን ድርጅቱ ግቡን ለመምታት እየተነሳ መሆኑን ቡድኑ ያመነ ሲሆን፣ መልሶ መዋቀር ይገባዋል መባሉንም ሮይተርስ የአሜሪካ ከፍተኛ ባለሥልጣንን ጠቅሶ አስፍሯል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የመስቀል አደባባይ የመግቢያ ክፍያ ለምን?

ወጣቶች፣ ሕፃናትና አረጋውያን ሳይቀሩ መንፈሳቸውን የሚያድሱበት እንዲሁም ሐሳባቸውን በነፃነት...

በሕገ መንግሥቱ የተዋቀረው ‹‹የብሔር ፖለቲካ›› እና ‹‹ሥርዓቱ›› ያስከተለው መዘዝና መፍትሔው

(ክፍል አራት) በዓቢዩ ብርሌ (ጌራ) ባለፈው ጽሑፌ (በክፍል ሦስት) አሁን ያለው...

የኢትዮጵያ ኅብረተሰብና የመንግሥት መሪ ምሥል

በበቀለ ሹሜ በ2015 ዓ.ም. መጋቢት ወር ውስጥ ይመስለኛል በ‹ሸገር ካፌ›...

ዩኒቨርሲቲዎችን ራስ ገዝ ያደረገው አዋጅ የፍትሐዊነት ጥያቄ አስነሳ

በቀጣዮቹ ሁለት ዓመታት ስምንት ዩኒቨርሲቲዎችን ራስ ገዝ በማድረግ ተቋማዊና...