የአፍሪካ ቀንዷ ጅቡቲ እያስተናገደችው ባለው ሁለተኛው ዓለም አቀፍ የንግድ ትርዒት በርካታ አገሮች የተሳተፉበት ሲሆን በትርዒቱን የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቴአትር የባህል ቡድን ባህላዊ ሙዚቃና ውዝዋዜውን አቅርቦ አድናቆትን አግኝቷል፡፡
በጂቡቲ ንግድ ምክር ቤት አዘጋጅነት ኅዳር 24 ቀን 2011 ዓ.ም. የተጀመረውን ዓለም አቀፍ የንግድ ትርዒት የጂቡቲው ፕሬዚዳንት እስማኤል ኦማር ጉሌህ የከፈቱት ሲሆን፣ ኢትዮጵያና ጂቡቲን ጨምሮ የሶማሊያና የግብፅ ባህላዊ የጥበብ ቡድኖች የየራሳቸውን ውዝዋዜና ዜማ አቅርበው ነበር፡፡ በዝግጅቱም ላይ የብሔራዊ ቴአትር አባላት የተለያዩ ብሔረሰቦችን ሙዚቃና ውዝዋዜ ባቀረበበት ወቅት ከተሳታፊዎች ከፍተኛ ጭብጨባና አድናቆት ከመቸሩም በላይ ተሳታፊዎች ቁጭ ብድግ ሲያደርግ ማርፈዱን ሪፖርተር በሥፍራው አስተውሏል፡፡ በጂቡቲ የኢትዮጵያ አምባሳደር አቶ ሻሎም ፊሞ በውዝዋዜው በመሳተፍ ተጨማሪ ድምቀት ሰጥተውታል፡፡